Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፓርላማ የገቡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሚያቀርቧቸው አገራዊ አጀንዳዎች ወርኃዊ ክርክር ሊጀመር ነው

ፓርላማ የገቡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሚያቀርቧቸው አገራዊ አጀንዳዎች ወርኃዊ ክርክር ሊጀመር ነው

ቀን:

በምርጫ አሸንፈው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተለያዩ አገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ቀርፀው በሚያቀርቧቸው አጀንዳዎች ላይ፣ በፓርላማ ወርኃዊ የውይይትና የክርክር መድረክ ሊዘጋጅ ነው፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውይይት ጊዜ አመዳደብና የተናጋሪ አመራረጥ የሚመራበትን አሠራር ለመወሰን በወጣው መመርያ ቁጥር 6/2000 አንቀጽ 10፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሚያቀርቡት አጀንዳ ላይ በየወሩ ለአንድ ሰዓት ውይይት እንደሚደረግ ይደነግጋል፡፡

በመመርያው ወርኃዊ ውይይት እንደሚደረግ ቢደነግግም እስካሁን በነበሩት የፓርላማ አሠራሮች ሳይተገበር ቆይቷል፡፡ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ አሸንፈው ፓርላማ የገቡ አራት ፓርቲዎች ተሰባስበው እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን፣ የፓርቲዎቹ የጋራ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አባል አወቀ አምዛየ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ከተወዳደሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ የጌዴኦ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅትና የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በፓርላማው መቀመጫ ያገኙ ናቸው፡፡

ምክትል ሰብሳቢው እንደተናሩት መመርያውን መሠረት በማድረግ ፓርላማው የክርክርና መወያያ ጊዜ እንዲይዝ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ የጋራ የሆነ አገራዊ የውይይት አጀንዳ ቀርፀው ለማቅረብ ሥራ ላይ ናቸው፡፡

የመወያያ አጀንዳዎቹ በዋነኝነት መንግሥት የሚተገብራቸው ፖሊሲዎችን፣ በተለይም የመሬትና የቋንቋ የመሳሰሉና አጨቃጫቂ የሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ጨምሮ በርካታ ሐሳቦች፣ ክፍት በሆነ የፓርላማ መድረክ ለውይይት እንደሚቀርቡ ምክትል ሰብሳቢው ተናግረዋል፡፡

ሊካሄድ የታሰበው ውይይት የዴሞክራሲ ባህልን ለማዳበር፣ እርስ በርስ እንደ ጠላት ከመተያየት በምክንያትና በውይይት የሚያምን ማኅበረሰብ በመፍጠር ገዥ ሐሳብ ላይ ለመድረስ፣ እንዳስፈላጊነቱ በወር አንድ ጊዜ ወይም በሁለት ወራት ‹‹የተፎካካሪ ፓርቲዎች ቀን›› በሚል የሚከበር በመሆኑ ከፓርላማው አበረታች ምላሽ ማግኘታቸውን አወቀ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ፓርቲዎቹ የውስጥ ደንብ እያዘጋጁ መሆኑን፣ በቀጣይ ፓርቲዎቹ በጋራ የሚስማሙባቸውን አጀንዳዎች መርጠው ለአፈ ጉባዔው እንደሚያቀርቡ አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አባል አቶ ባርጡማ ፈቃዱ እንደገለጹት፣ ፓርቲዎች የሚመሠርቱት ቡድን ከአስፈጻሚው አካል በኩል የሚታዩና ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ የተገናኙ ጥያቄዎች ይስተናገዱበታል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ አባልና የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጂጌ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ይህ ‹‹የተፎካካሪ ፓርቲዎች ቀን›› በሚል ሊካሄድ የታሰበው ዕቅድ ባለፈው ዓመት በነበረው አገራዊ ሁኔታ ከጊዜ እጥረት የተነሳ ባለመካሄዱ በተያዘው ዓመት ሁኔታዎች ተመቻችተው ውይይትና ክርክሩ ይጀመራል፡፡

በፓርላማው ውስጥ የሐሳብ ብዝኃነትና የተሻለ የውይይት ባህልን እንደሚፈጥርና የዴሞክራሲ ባህል እንደሚያዳብር የገለጹት አቶ ተስፋዬ፣ በዚህ ዓመት በሚጀመረው ፕሮግራምና በሚቀርቡ አጀንዳዎች ላይ ‹‹እንወያይባቸዋለን፣ እንከራከርባቸዋለን፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...