Tuesday, February 7, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

አገር የጥፋት ቤተ ሙከራ አትሁን!

መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ከወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የሚለዋወጡ ስትራቴጂዎች እንደሚኖሩት ዕውን ቢሆንም፣ በየጊዜው መዋቅሮችንና ፖሊሲዎችን መለዋወጥ ግን አይችልም፡፡ ‹‹ሁሉን መርምሩ የተሻለውን ያዙ›› የሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክር ለሰማይ ቤት ብቻ ሳይሆን፣ ለምድርም እንደሚሠራ ከበቂ በላይ ማሳያዎች አሉ፡፡ መንግሥት ለፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ሌሎች ጉዳዮቹ ፖሊሲ ሲቀርፅ በጥናት ላይ ተመሥርቶ መሆን ያለበት፣ ከብዙ አማራጮች መካከል የተሻለውን በመምረጥ ውጤታማ ሥራ ለማከናወን ነው፡፡ በኢትዮጵያ የመንግሥት አስተዳደር ታሪክ ግን የሚታወቀው፣ ካሉት አማራጮች በጥናት ላይ ተመርኩዞ መርጦና አማርጦ በሥርዓት መምራት እንደሚቸግር ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ጀምሮ በተለዋወጡ መንግሥታት ያሉትን ዓመታት ሒደቶች ስንቃኝ የፊውዳሊዝም፣ የሶሻሊዝም፣ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ የልማታዊ መንግሥት፣ የመደመርና የመሳሰሉት ዕሳቤዎች ተራ በተራ ተግባራዊ ቢደረጉም፣ ኢትዮጵያ ግን ቤተ ሙከራ ከመሆን አልዘለለችም፡፡ ፖለቲካው ዕድገቱ ተጨናግፎ ጨለምተኛ የሆነበትና ኢኮኖሚው እያደር የሚቀነጭርበት ምክንያት፣ አገር ማስተዳደርን ከጥፋት ቤተ ሙከራ መውጣት ባለመቻሉ ነው፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጣም የተባባሰበት አንድ ችግር ደግሞ የተቋማትና የተሿሚዎች  ጉዳይ ነው፡፡ ተቋማት በየጊዜው አደረጃጀታቸው፣ የሥራ ስምሪታቸው፣ ተጠሪ የሚሆኑለት የበላይ ተቋምና ስያሜያቸው ይለዋወጣል፡፡ ጉዳይ ያላቸው አገልግሎት ፈላጊዎች ተቋማቱ በተለዋወጡ ቁጥር ለእንግልት ይዳረጋሉ፡፡ የተቋማቱ ተልዕኮና ራዕይ እንደ አየሩ ሁኔታ ሲለዋወጥ ከአመራሮች ጀምሮ ባለሙያዎችና ሠራተኞች፣ ከማያውቁት አዲስ አሠራርና ከባቢ ጋር ሲቀላቀሉ ግራ መጋባትና መጨናነቅ ይፈጠራል፡፡ ትናንት በአዲስ አደረጃጀትና ስያሜ ራሱን ያስተዋወቀ ተቋም፣ ድንገት ሌላ አደረጃጀትና ስያሜ ይሰጠውና ሌላ ትርምስ ውስጥ ይገባል፡፡ የመንግሥት ተቋማት ሚና መደበላለቅም ሌላው ችግር ነው፡፡ ትናንት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተብሎ ብዙ ሥራዎችን በውስጡ ያቀፈ ተቋም፣ ሁለት ቦታ ተከፍሎ በሌሎች ስያሜዎች ሲደራጅ ወሳኝ የሚባሉ ሥራዎቹ ለሌላ ሦስተኛ ተቋም ተላልፎ በሲሚንቶ ገበያ ውስጥ የታየው ውዝግብ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተሿሚዎችን መለዋወጥ ደግሞ ሌላው የራስ ምታት ነው፡፡ ሹመቱ ከቤተ ሙከራ አሠራር አለመውጣቱ ለቀውስ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡

የምርቶች አቅርቦት ጉዳይ ሌላው ራስ ምታት ነው፡፡ ገበያው ውስጥ የዋጋ ጭማሪም ሆነ የምርት እጥረት ሲፈጠር ጣቶች የሚቀሰሩት ነጋዴዎች ላይ ነው፡፡ ነገር ግን የግብይት ሥርዓቱ በቀጥታ የሚመለከተው መንግሥት የሚፈጥረው ችግር በለሆሳስ ይታለፋል፡፡ መንግሥት የግብይት ሥርዓቱ የተረጋጋ፣ ጤናማና ተወዳዳሪ እንዲሆን ቁጥጥር የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ዋጋ መወሰን፣ ንግዱ ውስጥ በቀጥታ ተሳታፊ መሆንና ለግብይት እንቅፋት የሚፈጥሩ መመርያዎችንም ሆነ ደንቦችን ማውጣት የለበትም፡፡ የመንግሥት ሚና እንደ ትራፊክ ፖሊስ መሀል ላይ ሆኖ ፍሰቱን ማስተናበር ነው፡፡ መንግሥት ገበያ ውስጥ ዘው ብሎ ሲገባ ከዋጋ ግሽበት በተጨማሪ፣ የምርት እጥረት እንደሚፈጠር በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ከመሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች በተጨማሪ በቅርቡ በሲሚንቶ ላይ የታየው መረን የለቀቀ ድርጊት አይረሳም፡፡ አሁን ደግሞ በስንዴ ምርት ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ለመፈጸምና የሲሚንቶውን ታሪክ ለመድገም እየተሞከረ ነው፡፡ በስንዴ ምርት የዓለም ካርታ ላይ ስሟ የሰፈረው ኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ የስንዴ እጥረት እየተፈጠረ፣ ዳቦ መብላትም ቅንጦት እንዳይሆን ሥጋት አለ፡፡

የምርት አቅርቦት ችግርን ከሚያባብሱ ነገሮች መካከል አንደኛው መንግሥት ለመረጃ ዝግ መሆኑ ነው፡፡ ላለፉት ሦስት ወራት ያህል መንግሥት የውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥ እንደሚያደርግ በስፋት ሲወራ ነበር፡፡ የአንድ ዶላር ምንዛሪ በጥቁር ገበያ ውስጥ ካለው ዋጋ ጋር ተቀራራቢ እንደሚሆን፣ እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰውም መንግሥት ከአይኤምኤፍ ባደረገው ስምምነት መሆኑም በተለያዩ መንገዶች ሲነገር ነበር የሰነበተው፡፡ በዚህ ምክንያት ገበያው ለግመታ ተጋልጦ የምርቶች እጥረት ሲፈጠር፣ ባንኮች አካባቢ በነበረ ውዥንብር ብድር ሲቀዛቀዝና የዋጋ ግሽበቱ እንደ ሰደድ እሳት ዜጎችን ሲለበልብ ነው የከረመው፡፡ ይህ ሁሉ ጉዳትና ትርምስ ከተፈጠረ በኋላ መንግሥት እንደ ዘበት፣ ‹‹የሚወራው ሁሉ አሉባልታ ነው›› ሲል፣ በብዙዎች ላይ የተፈጠረው ብስጭት ብዙ ይናገራል፡፡ የአገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ አቅም አልባ ሆኖ የሰዎች የመግዛት አቅም ሲዘቅጥ በግልጽ እየታየ፣ የግብይት ሥርዓቱ ምስቅልቅሉ ወጥቶ ምርቶች ዋጋቸው አልቀመስ እያለ ሕይወት እየከበደ እንደ ዘበት ‹‹ተረጋጉ›› ሲባል ያስደነግጣል፡፡ አገር ከቤተ ሙከራነት ካልተላቀቀች መጪው ጊዜ ከባድ ነው፡፡

በየትኛውም የመንግሥት ሥራ ውስጥ ስህተት ማጋጠሙ ያንን ያህል ሊያስገርም አይገባም፡፡ ነገር ግን ተመሳሳይ ስህተቶች በአጭር የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ ሲደጋገሙ ግን ምንድነው ነገሩ ያሰኛል፡፡ መንግሥት እጁን ከሲሚንቶ ገበያ ማስወጣቱን አስታውቆ ግብይቱ በተለመደው መንገድ ሲከናወን የታየው አንፃራዊ ለውጥ እየታወቀ፣ አሁን ደግሞ የስንዴ ግብይት በተመሳሳይ ስህተት ውስጥ እንዲያልፍ እንዳይደረግ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ በስንዴ ግብይት ጥቂቶች ተደራጅተው ያላግባብ እንዲበለፅጉ የሚያደርግ ብልሹ አሠራር መኖር የለበትም፡፡ ከፍተኛ መጠን ያለው ስንዴ ተመርቶ ወደ ገበያ በአግባቡ ካልወጣ ሸማቾች ይቸገራሉ፣ የዱቄት ፋብሪካዎች ምርት ያቆማሉ፣ ዳቦ ጋጋሪዎች ሥራ ይፈታሉ፡፡ የአቅርቦት ሰንሰለቱ ከታነቀ የስንዴ ኮንትሮባንድ ተጀምሮ ዋጋው ወደ ላይ ሲሰቀል፣ የሚጎዳው ማን እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ የስንዴ ምርት የሕገወጦች መጫወቻ እንዳይሆን ይታሰብበት፡፡ የምግብ ምርቶች አቅርቦት የደላሎች ሰለባ የሚሆነው የዘፈቀደ አሠራሮች ሲበዙ ነው፡፡ 

በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት፣ መንግሥትና ሃይማኖት መለያየታቸውን በይፋ ይደነግጋል፡፡ ለአገር ልማት፣ ዕድገትና ሰላም ከመደጋገፍ ውጪ አንዳቸው በሌላቸው ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ አይገቡም፡፡ ይህ ማለት ማንኛውም ተሿሚ በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ መግባት የማይችል ሲሆን፣ ማንኛውም የእምነት መሪ በየትኛውም የመንግሥት ሥራ ላይ ተፅዕኖ ማሳደር አይችልም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን በተለይ የመንግሥት ተሿሚዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሕጉን ሲጥሱ ይታያሉ፡፡ በክርስትናም ሆነ በእስልምና ወይም በሌሎች እምነቶችና አስተሳሰቦች ዙሪያ ያሉ ጉዳዮችን ለባለቤቶቹ መተው የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡ ይህ ግን እየተጣሰ ምዕመናንን የሚያደናግሩና የሚያጋጩ ድርጊቶች ይስተዋላሉ፡፡ ከእንዲህ ዓይነቶቹ አላስፈላጊ ድርጊቶች መታቀብ የግድ መሆን አለበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በፍርድ ቤቶች ጉዳይ ጣልቃ መግባትና ነፃነታቸውን ማሳጣት፣ ፖሊስና ዓቃቢያነ ሕግም ሕጉን ብቻ ተከትለው እንዲሠሩ አለመከታተል መዘዙ ከባድ ነው፡፡ አገር የሕገወጥ ድርጊቶች መናኸሪያ ስትሆን ከሰላም ይልቅ ሁከት ይበዛል፡፡ ስለዚህ አገር የጥፋት ቤተ ሙከራ አትሁን!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...

አዲስ ሲኖዶስ አቋቁመዋል በተባሉና በኦሮሚያ መንግሥት ላይ ክስ ለመመሥረት ዕግድ ተጠየቀ

የፌዴራል ፖሊስና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽኖችም ተካተዋል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ቤተክህነት ባቀረበችው የይግባኝ አቤቱታ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለዕሮብ ተቀጠረ

የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሀገወጥ ነው በተባለው አዲሱ ሲኖዶስና...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ከገባችበት አረንቋ ውስጥ በፍጥነት ትውጣ!

የአገር ህልውና ከሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ አገር ሰላም ውላ ማደር የምትችለው ደግሞ የሕዝብ ደኅንነት አስተማማኝ ሲሆን ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥት በአገር ህልውና...

የፈተናው ውጤት የፖለቲካው ዝቅጠት ማሳያ ነው!

በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከአጠቃላይ ተፈታኞች ውስጥ 3.3 በመቶ ያህሉ ብቻ ማለፋቸው፣ የአገሪቱን የትምህርት ጥራት ደረጃ በሚገባ ያመላከተ መስተዋት እንደሆነ አድርጎ መቀበል ተገቢ ነው፡፡...

የምግብ ችግር አገራዊ ሥጋት ስለደቀነ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆችን አቅም በብርቱ እየፈተኑ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለማስቀደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የምግብና የሰላም...