ከአዲስ አበባ 104 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የሉና አትክልትና ፍራፍሬ እርሻ በሸኔ ታጣቂዎች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት፣ በአካባቢው የሚገኙ የአበባ የአትክልትና ፍራፍሬ አምራቾችም ሥጋት እንዳደረባቸው ተገለጸ፡፡
የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት ሰኞ ጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. የሸኔ ታጣቂዎች፣ በምሥራቅ ሸዋ ዞን ሊበን ጭቋላ ወረዳ ውስጥ የሚገኘውን የሉና እርሻ ለተለያዩ አገልግሎቶች ይጠቀምባቸው የነበሩ መሠረተ ልማቶችን አውድመዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የድርጅቱ ሥራ የተስተጓጎለ ሲሆን፣ በጥቃቱ የተደናገጡ በአካባቢው የሚገኙ ሌሎች ትልልቅ የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ሥራቸውን ለማከናወን መቸገራቸው ተጠቁሟል፡፡
ከቆቃ ከተማ 14 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሉና እርሻ ይዞታ ውስጥ ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት በቦታው ላይ የተገኘ ቢሆንም፣ ከቀናት በኋላ መልሶ በመውጣቱ የሉና ሠራተኞች ተረጋግተው ለመሥራት ባለመቻላቸው ሥራው ሊስተጓጎል መቻሉንም ምንጮች ገልጸዋል፡፡ እንደ ምንጮች ገለጻ ከሆነ፣ በሉና እርሻ ውስጥ ያሉ ቢሮዎችና መሰል ግንባታዎች በታጣቂቹ ወድመዋል፡፡ ከፍተኛ ዋጋ ያወጣሉ የተባሉ ጄኔሬተሮችና ሌሎች የእርሻ ልማቱ መሣሪያዎች በመውደማቸውም፣ ሥራቸውን መቀጠል ቢፈለግ እንኳን የወደመውን መሠረተ ልማት መልሶ መገንባት የሚያስፈልግ መሆኑን ምንጮች ተናግረዋል፡፡
ከሁሉም በላይ ግን በሉና እርሻ ላይ የደረሰው ውድመት በአካባቢው ያሉ ሌሎች ትልልቅ የውጭና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች የሚያለሟቸው እርሻዎች ላይም ሥጋት በመፍጠሩና ተረጋግተው ለመሥራት በመቸገራቸው፣ መንግሥት በእርሻ ኢንቨስትመንቶቹ ላይ ተጨማሪ ጥቃት እንዳይደርስ እንዲከላከልላቸው ተጠይቋል፡፡
አሁን ጥቃት የደረሰበት አካባቢ ከአበባ፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ኩባንያዎች ያሉበት በመሆኑ፣ እንዲህ ያሉ ችግሮችን በቅርብ ተከታትሎ ከለላ የማይደረግ ከሆነ በእርሻ ልማቶቹ ላይ የሚደርሰው ጉዳት በአገሪቱ በወጪ ንግድ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ጉዳዩን እየተከታተሉ ካሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አስተያየት ሰጪዎቹ እንደሚሉት ከሆነ ከዚህ ጥቃት ቀደም ብሎ፣ የሸኔ ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች ከአንዳንድ የእርሻ ልማት ጥበቃ ሠራተኞች ላይ መሣሪያ ነጥቀዋል፡፡ ሰዎችንም በማገት ገንዘብ ካላመጣችሁ በማለት ችግር እየፈጠሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ እንድሪስ ስለጉዳዩ የደረሳቸው ምንም መረጃ የሌለ መሆኑን ጠቁመው፣ ለኢንቨስተሮች ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑንና ሁሉ ነገር ሰላም መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተጠቀሰው ደረጃም ጉዳት ደርሶብኛል ብሎ ያመለከተ አለመኖሩንም ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሰሞኑን በሰጠው ሳምንታዊ መግለጫው እንዳስታወቀው፣ የሸኔ የሽብር ቡድን በኦሮሚያና አጎራባች አካባቢዎችና በአጠቃላይ በአገር ላይ የፈጠረውን የሰላም ሥጋት፣ ያስከተላቸውን ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳቶች ለመግታት መንግሥት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ የተቀናጀ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል ብሏል፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) ኦነግ ሸኔን በተመለከተ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ በክልሉ የሸኔ እንቅስቃሴ የታየባቸው አካባቢዎች ወደ ነበሩበት ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ የፌዴራልና የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ግብረ ኃይል ተደራጅቶ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ሁሉንም ዓይነት አማራጮች ያካተተ ዕርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሕገወጥ ታጣቂዎችን በማሰማራትና በማቀናጀት ከሌሎች የሥጋት ኃይሎች ጋር ጥምረት በመፍጠር፣ በንፁኃን ዜጎች ሀብትና ንብረት፣ እንዲሁም በመሠረተ ልማቶች ላይ የደቀነውን አደጋ ለመቀልበስም የተቀናጀ ዕርምጃዎች እየተወሰደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሉና በዚህ አካባቢ ካለው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ባሻገር በሥጋ የወጪ ንግድ ላይ በመሰማራት የሚታወቅ አገር በቀል ኩባንያ ሲሆን፣ ፍሬሽ ኮርነር በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ሱፐር ማርኬት እህት ኩባንያ ነው፡፡
ሉና በሊበን ጭቋላ ወረዳ ከ200 ሔክታር መሬት ላይ አትክልትና ፍራፍሬዎች በማምረት ለዓመታት ሲሠራ የቆየ ስለመሆኑ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡ በመረጃው መሠረት በዚህ አካባቢ ብቻ ሉናን ጨምሮ ከሰባት በላይ የአትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ከሰባት ሺሕ ያላነሱ ሠራተኞችን በመያዝ ተሰማርተዋል፡፡
በአካባቢው ከሚገኙ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ ከተሰማሩ ኩባንያዎች መካከል ኢትዮ ፍሎራ፣ ሬድ ፎክስ ዱሚ፣ ፍሎረንስ ሲዲንታ፣ ሼር ብሌንና አልሜታ የእርሻ ልማቶች ይገኛሉ፡፡