በትራንስፖርት አገልግሎት የተሰማሩ በርካታ ተሽከርካሪዎች በታለመለት የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት ውስጥ እየገቡ በመሆናቸው፣ በመንግሥት ለተደጓሚዎች የሚመለስላቸው ገንዘብ ‹‹እጅግ አሳሳቢ›› በሆነ ደረጃ መጨመሩን የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አስታወቁ።
ዋና ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ሳህረላ አብዱላሂ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ድጎማን ከነዳጅ ላይ የማንሳት ሒደት ሲጀመር፣ በታለመለት ነዳጅ ድጎማ ሥነ ሥርዓት ውስጥ ተካተው የነበሩት የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ትንሽ የነበረ ሲሆን፣ የነዳጅ ዋጋ በመስተካከል ሒደት ውስጥ ግን የተደጓሚ ተሽከርካሪዎች ቁጥር አሻቅቧል፡፡
የታለመለት ነዳጅ ድጎማ በተጀመረ ጊዜ በተደረገው የዋጋ ማስተካከያ ድጎማው በሚነሳባቸው ተሽከርካሪዎችና በሚደጎሙት ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች መካከል የነበረው የዋጋ ልዩነት፣ በሊትር ለቤንዚን ስድስት ብርና ለናፍጣ ስምንት ብር ነበር። የገንዘቡ ብዙ አለመሆን ያላሳሰባቸው በርካታ ተሽከርካሪዎች በድጎማ ሥርዓት ውስጥ በፈቃዳቸው ሳይመዘገቡ እንደቀሩ ነበር ዋና ዳይሬክተሯ የገለጹት።
ነገር ግን የነዳጅ ዋጋ በመስከረም ወር ላይ ሲከለስ በሚደጎሙትና በማይደጎሙት ተሽከርካሪዎች መካከል ያለው የዋጋ ልዩነት በሊትር ለቤንዚን ወደ 15 ብር፣ ለናፍጣ ደግሞ ወደ 17 ብር ከፍ ብሏል።
ይህንን ተከትሎም በድጎማ ሥርዓት ውስጥ ለመግባት ወደ 50 ሺሕ የሚጠጉ ተሽከርካሪዎች በመስከረም ወር ተመዝግበው፣ በዚሁ ወር መጨረሻ ላይ ግን ቁጥራቸው ወደ 65 ሺሕ አድጓል ተብሏል። በታኅሳስ ወር መጨረሻ ሦስተኛው የዋጋ ማስተካከያ ሲደረግ፣ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ከድጎማው ለመጠቀም የተመዘገቡ ተሽከርካሪዎች ቁጥር 191 ሺሕ መድረሱን ወ/ሮ ሳህረላ ተናግረዋል።
‹‹በድጎማ የሚመለስላቸው ገንዘብ ትልቅ ስለሆነ ብዙዎች ወደ ድጎማ ሥርዓት እየገቡ ነው፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፣ ከመንግሥት ለድጎማው የሚወጣው የገንዘብ ‹‹ዕድገት እጅግ አሳሳቢ እየሆነ ነው የመጣው፤›› ሲሉ ገልጸዋል።
መንግሥት ለትራንስፖርት ሰጪ ተሽከርካሪዎች በድጎማ ተመላሽ የሚያደርግላቸው ገንዘብ እስከ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ በአንድ ቀን ከአምስትና ስድስት ሚሊዮን ብር እንደማይበልጥ፣ ቆይቶ ግን ለተሽከርካሪዎች ተመላሽ የሚሆነው ገንዘብ በቀን ወደ 30 ሚሊዮን ብር ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ጀምሮ በሒደት ድጎማው እየተነሳባቸው ላሉት ተሽከርካሪዎች፣ መንግሥት በአጠቃላይ 16 ቢሊዮን ብር ለድጎማ ማዋሉን፣ ለትራንስፖርት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ደግሞ በድጎማ ተመላሽ የተደረገላቸው ገንዘብ ደግሞ አራት ቢሊዮን ብር መድረሱንም ወ/ሮ ሳህረላ አስረድተዋል፡፡
ከሚደጎሙት ተሽከርካሪዎች ውስጥ 40 በመቶው ሚኒባሶች ሲሆኑ፣ እንደ ከተማ ታክሲ የሚያገለግሉት ደግሞ 12 በመቶ መሆናቸው ታውቋል፡፡
‹‹ሙሉ ለሙሉ የድጎማ አተገባበሩን ስናይ የፌዴራል መንግሥት ቁጥጥር ስለሚያደርግባቸው ሦስት ካታጎሪዎች ብቻ ናቸው በደንብ በታሪፋቸው እየሠሩ ያሉት፡፡ እነሱም የፐብሊክ ባሶች፣ አገር አቋራጮችና የከተማ አውቶቡሶች ብቻ ናቸው፤›› ሲሉ ወ/ሮ ሳህረላ በተወሰኑ ካታጎሪዎች ላይ የሚታዩ የአጠቃቀም ክፍተቶች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በባጃጅ፣ ታክሲ፣ ሚኒባስና ሚዲባሶችን ግን ሕገወጥ አተገባበሮች ይታያሉ፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡