- ጤና ይስልጥልኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ትላንት የቢሮ ስልክዎ ላይ ብደውል ለሥራ ወጥተዋል ተባልኩ፣ ዛሬም ስደውል ለሥራ ወጥተዋል ተባልኩ።
- ልክ ነው ክቡር ሚኒስትር ቢሮ አልገባሁም ነበር።
- እኔ ሳላውቅ የጀመሩት ነገር አለ እንዴ?
- እርሶ ሳያውቁ ምን እጀምራለሁ ክቡር ሚኒስትር?
- ለሌላ ከተማ መሥራት?
- ትላንትም ዛሬም የመስክ ጉብኝት ፕሮግራም ነበረኝ ክቡር ሚኒስትር። ለአስቸኳይ ጉዳይ ፈልገውኝ ነው?
- ሁለት ቀን ሙሉ ጉብኝት?
- ባለፈው የከተማውን ካቢኔ ሰብስበው የሰጡትን ማሳሰቢያ ዘነጉት እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- የምን ማሳሰቢያ?
- ብልፅግና የሚመጣው ቢሮ ቁጭ ብሎ በመዋል ወይም ቪኤይት እየነዱ በመዝናናት አይደለም፣ ፒክ አፕ እየነዱ ነው አላሉም?
- ስለዚህ?
- ስለዚህ ያለፉትን ሁለት ቀናት ፒክ አፕ እየነዳን ጉብኝት ላይ ነበርን።
- ከተማ ለመጎብኘት ገዛን እንዳይሉኝ?
- ምን?
- ፒክ አፕ?
- ወጪ ለመቆጠብ ብለን ከፌዴራል ተቋማት ለመዋስ ነበር ዕቅዳችን ነገር ግን
- ግን ምን?
- የፌዴራል ተቋማትም ለጉብኝት ሊጠቀሙባቸው እንደሚችሉ በማመን…
- ገዛን እንዳይሉኝ?
- ገዛን!
- ለከተማ ጉብኝት ፒክ አፕ?
- ብልፅግና የሚመጣው ፒክ አፕ እየነዱ ነው አላሉም እንዴ?
- ቆይ እሱ ይቆየንና ጉብኝት ላይ ነበርን ሲሉ ሙሉ ካቢኔውን ማለትዎ ነው?
- አዎ። ሁላችንም በመስክ ጉብኝት ላይ ነበርን።
- ምንድነው ስትጎበኙ የነበረው?
- ሁሉም የካቢኔ አባል የተመደቡለትን ፕሮጀክቶች በየክፍለ ከተማው እየተዘዋወረ ሲጎበኝ ነበር።
- ይህን ያህል ሰፊ ፕሮጀክት በከተማው አለ እንዴ?
- ሰፊ ባይሆንም፣ ፕሮጀክቶች አሉን።
- ሁሉንም የካቢኔ አባል ለጉብኝት የሚያስወጣ?
- በተናጠል አይደለም ለጉብኝት የወጣነው።
- እ…?
- ጥንድ ጥንድ ሆነን ነው።
- የባሰ አታምጣ አሉ!
- ምን አሉኝ ክቡር ሚኒስትር?
- እስኪ እርስዎ የጎበኙትን ፕሮጀክት ይንገሩኝ?
- እኔ የመረጥኩት የተጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ነው።
- ፕሮጀክቶቹ ምንድናቸው?
- እርስዎ ከካቢኔያችን ጋር በተወያዩበት ወቅት እንዲተገበሩ ያዘዟቸውን ፕሮጀክቶች ነው የጎበኘሁት።
- ዘነጋሁት፣ ምን ነበሩ?
- የ90 ቀን ፕሮጀክቶች፡፡
- እህ… ታዲያ ይኼንን መቼ ነበር ያዘዝኩት?
- እ… አዎ… አሁን ስድስተኛ ወሩን ጨርሶ ወደ ሰባተኛ ወሩን ይዟል።
- እናንተ ግን የፕሮጀክት ስም አደረጋችሁት?
- ምኑን?
- በ90 ቀን ይፈጸም ያልኩትን?
- እ… እንደዚያ ነበር እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- እርስዎን ጨምሮ ከካቢኔዎ ጋር አንድ ዙር ሳያስፈልገን አይቀርም።
- ምን?
- ውይይት!
- ጥሩ። ጎብኝቱን ስንጨርስ መገናኘት እንችላለን።
- ጎብኝቱም ይወስድባችሁ ይሆን?
- ምን?
- 90 ቀን!
[ክቡር ሚኒስትሩ የጎርጎራ ፕሮጀክትን ጎብኝተው ከተመለሱት ወዳጃቸው የቀድሞ ሚኒስትርና አምባሳደር ጋር እየተጨዋወቱ ነው]
- ጉብኝቱ እንዴት ነበር አምባሳደር?
- አምባሳደር ብለህ ባትጠራኝ ደስ ይለኛል?
- ለምን?
- በስሜ እንድትጠራኝ ነው የምፈልገው።
- እንደዚያማ ትክክል አይሆንም?
- ምን ችግር አለው?
- አገርዎትን በአምባሳደርነት ሲያገለግሉ ቆይተው?
- ቢሆንም በስሜ እንድትጠራኝ ነው የምፈልገው ካልሆነ ግን…
- እ… ካልሆነ ምን?
- ካልሆነ እኔም አንተን ክቡር ሚኒስትር ብዬ አልጠራህም፡፡
- ታዲያ ምን ብለው ሊጠሩኝ ነው?
- የወደፊት አምባሳደር!
- ኪኪኪኪ… ተጫዋች እኮ ነህ። ግን እንዴት ነበር?
- ምኑ?
- ለአምባሳደሮች የተዘጋጀው ጉብኝት?
- እኔ ለምን እንዳስጎበኙንም አልገባኝም።
- እንዴት?
- ብዙዎቻችን ሚኒስትር እያለን የምናውቃቸውን ፕሮጀክቶች ነው የጎበኘነው።
- ቢሆንም ፕሮጀክቶቹ አሁን የደረሱበትን ደረጃ መመልከቱ ችግር ያለው አልመሰለኝም። አለው እንዴ?
- አብዛኞቻችን ፕሮጀክቶቹን እናውቃቸዋለን። በዚያ ላይ ደግሞ እኔ ብዙም አይገባኝም።
- ምኑ?
- የፕሮጀክቶቹ ፋይዳ፡፡
- እንዴት እንደዚያ ይላሉ አምባሳደር?
- ወደፊት ፋይዳ ይኖራቸው ይሆናል ነገር ግን አሁን ላይ ካለው የአገሪቱ ሕዝብ ፍላጎት አንጻር የረባ ፋይዳ ይኖራቸዋል ብዬ አላምንም።
- እንዴት?
- በአጭሩ ልግለጽልህ?
- እሺ…
- የፓርኮቹ ግንባታና በአንድ ወቅት በመላ አገሪቱ የተገነቡ የእግር ኳስ ስታዲየሞች አንድ ናቸው ወይም ለእኔ ይመሳሰሉብኛል።
- ሁለቱን ደግሞ ምን ያመሳስላቸዋል?
- ሁለቱም ከሚፈለጉበት ጊዜ ቀድመው መገንባታቸው።
- አልገባኝም?
- የእግር ኳስ ስታዲየሞች በሁሉም ክልሎች ቢገነቡም አገልግሎታቸው ግን ሌላ ሆኗል።
- ምን ሆኗል?
- የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ማክበሪያ!
- ፓርኮቹ ግን የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ማክበሪያ አይሆኑም።
- ብሔር ብሔረሰቦችማ ቀናቸውን ማክበሪያ ቦታ አግኝተዋል።
- ፓርኮቹ ግን የቱሪስቶች መዳረሻ ይሆናሉ።
- መቼ?
- አገሪቱ ስትረጋጋ።
- ለዚያ እኮ ነው ለዚህ ትውልድ የሚጠቅሙ ፕሮጀክቶች አይደሉም የምልህ።
- እና ለዚህ ትውልድ የሚጠቅሙት ፕሮጀክቶች ምንድናቸው?
- ፓርኮቹን አቆይቶ ፋብሪካዎቹን መጨረስ፡፡
- የትኞቹን?
- ብዙ የቆሙ ፋብሪካዎች አሉ አይደለም እንዴ?
- እስኪ አንዱን ይንገሩኝ?
- ስኳር ፋብሪካዎቹ!