በኢትዮጵያ ከፕሪቶሪያው ስምምነት ወዲህ አንፃራዊ የሰላም አየር እየነፈሰ ነው፡፡ የሕወሓት ኃይሎች ከሰሞኑ ከባድ መሣሪያዎቻቸውን ለመከላከያ ማስረከብ መጀመራቸው ተነግሯል፡፡ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናትን የያዘ የልዑካን ቡድን በትግራይ ክልል ጉብኝት ሲያደርግ ታይቷል፡፡ የአየር በረራ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ቴሌኮምና መብራትን ጨምሮ ሌሎች መሠረተ ልማቶች በትግራይ ክልል ሥራ ሲጀምሩ መታየታቸው እንደ ታላቅ የሰላም ፍሬ በመታየት ላይ ይገኛል፡፡ የተለያዩ የትግራይ አካባቢዎችን መከላከያ እየተቆጣጠረ ነው፡፡
ይህ የሰላም ጅማሮ ደግሞ በመላ አገሪቱ እንደሚሰፋ ተስፋ ያደረጉ በርካታ ናቸው፡፡ በትግራይ ክልል ያለው የሰላም ማስፈን እንቅስቃሴ ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ሰፍቶ ለማየት የሚጠብቁ ብዙ እንደሆኑ ይገመታል፡፡ ሰላም ሁሉንም አካታች ይሁን ከሚለው በተጨማሪ ዘላቂነት ወዳለው የሰላም ምዕራፍ እንዲሸጋገር የሚጠይቁም በርካታ ናቸው፡፡
‹‹ከአዙሪት እንውጣ›› (Let’s Avoid Deja Vu) በሚል ርዕስ ስለዘላቂና ሁሉንም አካታች ስለሆነ ሰላም የጻፈው ፖለቲከኛው ጃዋር መሐመድ፣ በትግራይ ክልል በዚህ ፍጥነት ሰላም ማስፈን ከተቻለ በሌሎችም የኢትዮጵያ ክፍሎች ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚቻል ምልከታውን አስነብቧል፡፡
በትግራይ ክልል የተፈጠረው አንፃራዊ ሰላም ሕወሓትን ብቻ አካቶ ሌሎችን ያገለለ ዓይነት ስሜት መፍጠር የለበትም ሲል ጃዋር ሞግቷል፡፡ የኤርትራ መንግሥት፣ የአማራና የአፋር ክልሎችና የሰሜኑ ጦርነት የነካቸው ኃይሎች በሙሉ የመገለል ስሜት ሊሰማቸው እንደማይገባም ያሳስባል፡፡ የሰላም ሒደቱ ሁሉንም አካታች በሆነ መንገድ መካሄዱ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር ወሳኝ እንደሆነም ያስረዳል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ በኦሮሚያና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎችን ማነጋገር ጠቃሚ ዕርምጃ መሆኑን ነው ጃዋር በዚህ ሀተታው ያሰመረበት፡፡
‹‹ዳግም የመሳሳት ዕዳ ብገባ›› በሚል ርዕስ ግልጽ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ብለው ባለ አሥር ነጥብ ሰፊ ጽሑፍ ከሰሞኑ ያስነበቡት ሌላኛው ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌውም ቢሆኑ፣ በተመሳሳይ ስለአካታችና ዘላቂ ሰላም ብዙ ብለዋል፡፡
በአሥረኛ ደረጃ ባስቀመጡት የለውጥ ዕርምጃ ባሉበት ነጥብ ላይ አቶ ልደቱ፣ ሀቀኛና ሁሉን አቀፍ የሆነ አገራዊ የውይይትና የድርድር ሒደት በአስቸኳይ እንዲጀመር ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡ ይህ የውይይትና የድርድር ሒደት የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በተመለከተ የሚደረስበትና የአገርን ህልውና ከጥፋት የመታደግ ዓላማም ያለው ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ሌላኛው እጅግ ሰፊ ትንተና የያዘ ጽሑፍ ያስነበቡት ዮናስ ብሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ የገጠሟትን ውስብስብ የፖለቲካ ችግሮች ለመፍታት አገር አቀፍ የምሁራን መማክርት መቋቋምና መፍትሔ ማፍለቅ እንደሚጠይቅ ነው ያሳሰቡት፡፡ በተለይ የብሔር ፖለቲካ የኃይል አሠላለፍ በኢትዮጵያ የፈጠረውን ቀውስ በሰፊው የሚዳስሱት ምሁሩ፣ አገሪቱ በፀጥታ ድምፁን አጥፍቶ የተቀመጠውንና ራሱን ከኢትዮጵያዊ ማንነት ነጥሎ ማየት የማይችለውን ብዙኃን ማኅበረሰብ የፖለቲካ ንቃት ትፈልጋለች ነው ያሉት፡፡
ከሰሞኑ ሦስቱ ሰዎች ያስነበቡትና የራሳቸውን ምልከታ ያጋሩበት ተከታታይ ጽሑፍ፣ የፖለቲካው መድረክ የመወያያ ርዕስ ሆኖ ነው የሰነበተው፡፡ የሦስቱም ግለሰቦች ጽሑፎች ‹ብለን ነበር› በሚሉ ፀፀት ቀስቃሽ ግሶችና ‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊሰሙ ይገባል› በሚሉ ሐረጎች የተሞሉ ቢሆኑም፣ አገሪቱ ስለገጠማት ችግር ጠቃሚ ነጥቦችን በየበኩላቸው አንስተዋል፡፡ ጸሐፊዎቹ ከራሳቸው ምልከታ በመነሳትም የኢትዮጵያ ችግሮችን ስለመፍታት፣ በተለይም ዘላቂና ሁሉን አካታች ሰላም ለመፍጠር ለውይይት የሚጋብዙ በርካታ ነጥቦችን ዘርዝረዋል፡፡
የሰላም ስምምነቱ መፈረምን ተከትሎ የትጥቅ መፍታት ጥያቄ ለሰላም ስምምነቱ ትግበራ ወሳኝ መሆኑ ሲነገር ሰንብቶ፣ በቀጣይ ጥቂት ቀናት የሕወሓት ታጣቂዎች የያዙትን ምሽግ ለቀው መውጣታቸው ተነገረ፡፡ ቀላል መሣሪያዎችንም አስረከቡ ተባለ፡፡ በቅርቡ ደግሞ ከባድ መሣሪያዎች ማስረከብ መጀመራቸው ተሰምቷል፡፡
የመከላከያ ሠራዊቱ ሙሉ ለሙሉ የትግራይ ክልልን የመቆጣጠሩ ሥራም ቀጣዩ ተጠባቂ ዕርምጃ ነበር፡፡ ትጥቅ የፈቱ ታጣቂዎችን ወደ ማሠልጠኛ አስገብቶ የተሃድሶ ሥልጠና የመስጠቱ ሥራም ከሰላም ስምምነቱ ቀዳሚ ዕርምጃዎች አንዱ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ በጦርነቱ የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ የመገንባትና የኢኮኖሚ ማገገም ሥራ የሚጀመርበት ሁኔታ ተጠባቂ ነው፡፡ በሌላ በኩል የሽግግር ጊዜ አስተዳደር በትግራይ ክልል ማቋቋም በመጠበቅ ላይ ካሉ ዕርምጃዎች አንዱ ነው፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ የሽግግር ጊዜ ፍትሕ ሥርዓት በማቋቋም ጦርነቱን የፈጠሩ መሠረታዊ ችግሮችን የመመርመር፣ በጦርነቱ ወቅት የተፈጸሙ ወንጀሎችን አጣርቶ የመዳኘቱ ሥራም ገና ምኑም ያልተነካ ከባድ የቤት ሥራ መሆኑ ይነገራል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የጦርነቱን እጅግ አጨቃጫቂ ጉዳዮችን ለመፍታት የተቋማትና የሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎችን የመመለሱ ሥራም፣ በቀጣይ የሚጠበቅ የሰላም ሒደቱ አካል ተደርጎ የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡
ከእነዚህ ሁሉ ጉዳዮች ባሻገር ግን የተጀመረው የሰላም ሒደት ዘላቂና ሁሉንም አካታች እንዲሆን ምን ይደረግ? የሚለው ጉዳይ ብዙ እያወያየ ነው የሚገኘው፡፡
በእሑድ ጥር 7 ቀን 2015 ዓ.ም. የሪፖርተር ዕትም ‹የትግራይ ክልል ቀጣይ ሁኔታና የኃይሎች አሠላለፍ አንድምታ› በሚል ርዕስ ሰፊ ትንተና ያስነበቡት ፖለቲከኛ ጊዴና መድኅን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ የራሳቸውን ምልከታ አጋርተዋል፡፡ የትግራይ ክልል የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ከአማራ ክልል ጋር አጨቃጫቂ በሆኑት በወልቃይት፣ በጠገዴ፣ በሁመራና በራያ አካባቢዎች ሊገጥመው የሚችለውን ግጭትና ፍጥጫ ያወሳሉ፡፡ በሌላ በኩል አብአላና ዳሎል በመሳሰሉ የወሰን አካባቢዎች የተነሳ በአፋርና በትግራይ ክልሎች መካከል አወዛጋቢ የይገባኛል ጥያቄ መነሳቱ እንደማይቀር አቶ ጊዴና ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡
የሰላም ሒደቱ በትግራይ ፖለቲካ ውስጥ አዲስ የፖለቲካ ኃይል አሠላለፍ እንደሚፈጥር ጠቁመው፣ በትግራይ ክልል የሚኖረውን የፖለቲካ ሽግግርም በተመለከተ ምልከታቸውን አጋርተዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተገናኘ በትግራይም ሆነ በኢትዮጵያ ዘላቂና ሁሉን አቃፊ የሰላም ስምምነት ስለሚፈጠርበት ሁኔታ የጠየቁት አቶ ጊዴና፣ የፖለቲካውን ገበያ ማስፋት አንዱ አማራጭ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
‹‹ሦስት ነገሮች በወሳኝነት መደረግ አለባቸው፡፡ የመጀመርያው የፖለቲካውን ገበያ ማስፋትና ለሁሉም ወገን እንዲሳተፍ ምቹ ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው የፖለቲካ ባህሉን መለወጥ አስፈላጊ ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ሕዝቡን በራሱ ዕጣ ፈንታ ላይ እንዲወስን ነፃ ማድረግና ዕድል መስጠት ነው፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ ጊዴና፣ ይህን ማድረጉ የትግራይን ብቻ ሳይሆን የሌላው ኢትዮጵያ ክፍል ፖለቲካም ሊለውጥ ይችላል ብለዋል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን ከሽብር መዝገብ ተሰርዞ በፌዴራል መንግሥቱ በኩል ሕወሓት የሥልጣን መጋራት ሊያገኝ እንደሚችል እየተወራ መሆኑን ያወሱት አቶ ጊዴና፣ ይህ መሰሉ ዕርምጃ ቢወሰድ ለዘላቂ ሰላም እንደማይበጅ ነው የተናገሩት፡፡
‹‹ሕወሓት በአገር ላይ የክህደት ወንጀል የፈጸመ ኃይል ነው፡፡ በምርጫ ቦርድ የተሰጣቸውን ዕውቅና ተቀምተው በሕግ መጠየቅ ነው ያለባቸው፡፡ የሕወሓት ኃይሎችን ሕጋዊ አድርጌ የማይበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ አሁን የምናየው የሰላም ሒደት እነሱን መልሶ ወደ ፖለቲካ መድረክ እንዲመጡ ዕገዛ የሚያደርግ ሊሆን ይችላል፡፡ እነሱን ሥልጣን አጋርቶ ወደ ፖለቲካው መድረክ ዳግም እንዲመለሱ የማድረጉ ፍላጎት ደግሞ በውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ የመጣ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም በእኔ አቋም ሕወሓት ከጠቀመን ይልቅ የጎዳን ይበልጣል፡፡ ስለዚህ ልክ እንደ ካምቦዲያው ኬሜሩዥ ከፖለቲካ ገጽ ቢወገድ ነው የተሻለ የሚሆነው፡፡ ይህ ሲደረግም ነው በትግራይ የተጀመረው የሰላም ሒደት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምም አስተዋጽኦ የሚኖረው፤›› በማለት አቶ ጊዴና ሐሳባቸውን አካፍለዋል፡፡
በትግራይ ክልል ጉዳይ በተለያዩ ሚዲያዎች አስተያየት በመስጠት የሚታወቁት አቶ ተስፋ ኪሮስ አረፈ ግን፣ ስለዘላቂ ሰላም ለመነጋገር ‹‹ወረራ›› ብለው ስለጠሩት የጦርነት መነሻ ተመልሶ መነጋገር እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡
‹‹የተደረገው የሰላም ስምምነት ሳይሆን ግጭት የማቆም ስምምነት ነው፡፡ ይህ ግጭት የማቆም ስምምነት ደግሞ ከአንድ ፓርቲ ከሕወሓት ጋር የተደረገ እንጂ፣ ከትግራይ መንግሥት ጋር አልተካሄደም፡፡ በትግራይ የተጀመረው የሰላም ሒደት ደግሞ ከሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ጋር የሚገናኝበት አንዳችም ምክንያት አይታየኝም፡፡ በእኔ ግምት በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ራሱን የቻለ የሰላም ሒደት ያስፈልጋል፤›› ሲሉ አቶ ተስፋ ኪሮስ ምልከታቸውን አጋርተዋል፡፡
በእሳቸው ግምት የኤርትራም ሆነ የአማራ ኃይሎችን የጋበዘው የፌዴራል መንግሥቱ ነው፡፡ ስለዚህ የሰላም ሒደቱ ሁሉንም ኃይሎች ያካት ከተባለ የሚመለከተው የፌዴራል መንግሥቱን እንጂ የትግራይን ክልል አይደለም ይላሉ፡፡
‹‹አሁን ትግራይ በተዳከመችበት ሁኔታ ክልሉን ለመቀራመት ያሰፈሰፈ ኃይል ነው የሚታየኝ፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ፣ የኤርትራም ሆነ የአማራና ሌላም ኃይል በትግራይ ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ ለማጠናከር ነው ሁሉም ያሰፈሰፉት፤›› በማለትም ይናገራሉ፡፡ ተስፋ ኪሮስ ሕጋዊው የትግራይ መንግሥት መመለስ እንደሚኖርበትና የትግራይ ዕጣ ፈንታ ለትግራይ ዜጎች መተው እንዳለበት ነው አቋማቸውን ያንፀባረቁት፡፡ ጦርነቱ በሕግ ማስከበር ስም የተጀመረ እንጂ ትግራይን የመቀራመት እንዳልሆነ አክለው ተናግረዋል፡፡
ከሰሞኑ ለፋይናንሻል ታይምስ አስተያየታቸውን የሰጡት የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ተወካይና ዋና አደራዳሪ የናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፣ የትግራይ ፖለቲካ ልሂቃን ደጋግመው የሚያነሱትን ስሞታ ውድቅ አድርገውታል፡፡ ‹‹የኤርትራ ጦርና የአማራ ኃይሎች ለቀው አለመውጣታቸው የሰላም ሒደቱ መሠረታዊ እንቅፋት ነው›› የተባሉት ኦሊሴጎን፣ እርሱ ችግር መታለፉን ተናግረዋል፡፡
‹‹የኤርትራ ጦር ወጥቷል፡፡ እሱን አለፍነው እኮ፡፡ ቀጣዩ ሒደት የሕወሓት ከሽብር መዝገብ መሰረዝ ነው፡፡ አሁን እኮ የጠብመንጃ ጩኸት በትግራይ ቆሟል፤›› በማለት ነበር የተናገሩት፡፡
አሁን የተጀመረው የሰላም ሒደት መልሶ የሚደፈርስና ዘለቄታዊ እንደማይሆን የሚናገሩ ቢበዙም፣ ጅምሩ የሰላም ሒደት ለኢትዮጵያ ዘላቂ የሰላም መሠረት እንደሚጥል የሚገምቱት ደግሞ እጅግ በርካታ ናቸው፡፡
ከሰሞኑ በአፋር ክልል በተካሄደ ስለኢትዮጵያ ሰላም በተመከረበት መድረክ ላይ ንግግር ያሰሙት የክልሉ ፕሬዚዳንት ሐጂ አወል አርባ፣ ይህን የብዙኃን ተስፋ የሚያጠናክር ምልከታ አጋርተዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ከአዕምሮ በላይ የሆነ አገር ነው የሚሉኝ ብዙዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ውስጣዊ ችግሮች አሉባቸው፡፡ ሆኖም ከባድ አገራዊ ጉዳይ ሲመጣ አንድም ቀን እንዳልተጋጨ ሰው ናቸው፡፡ ወደፊትም እንደማይጋጭ ሰው ሆነው ነው የሚሠለፉት፡፡ ያለ መደማመጥን፣ መሳሳብን፣ የተለጠጡ ሐሳቦችን መያዝን በመግባባት መፍታት አለብን፡፡ አገር የአሸናፊዎች ብቻ ሳትሆን የሁላችንም ናት፡፡ ያለፉ ችግሮችን አያልፉም፣ አበቃላቸው፣ አገሪቱም ትፈርሳለች ያሉ አሁን ሐሳባቸውን ለውጠዋል፤›› በማለት ነበር የተጀመረው የሰላም ሒደት ዘላቂ እንደሚሆን የተናገሩት፡፡