ሰዎች በተለያዩ ዘርፎች ላበረከቱት በጎ አስተዋጽኦ ሲሸለሙና ዕውቅና ሲያገኙ ይስተዋላል፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ አገሮች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ዕውቅናና ሽልማት ይገባቸዋል ለሚባሉ ሰዎች መሥፈርት አስቀምጠው ይሸልማሉ፡፡ በኢትዮጵያም በ1950ዎቹ የተመሠረተውና በ1960ዎቹ መገባደጃ የተቋረጠው፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሽልማት ድርጅት ይጠቀሳል፡፡ በ1990ዎቹ አጋማሽ የኢትዮጵያ የሥነ ጥበባትና የመገናኛ ብዙኃን ሽልማትም ላፍታዎች ታይቶ ከስሟል፡፡ የመሸለም ጉዳይ ዳግም አንሠራርቶ ከተጀመረበት ከ2000ዎቹ ወዲህ አበርክቶው ላላቸው ሰዎች ሽልማት መስጠቱ እየተለመደ መጥቷል፡፡ የበጎ ሰው ሽልማት፣ የጉማ ሽልማት፣ የአቢሲንያ ሽልማትና ሌሎችም በየዘርፉ ሲሸልሙ ይስተዋላሉ፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ሴቶች ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገና ሴቶች ዕውቅና የሚያገኙበት ‹‹ድንቅነሽ ሽልማት›› በየካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. እንደሚከናወን ተነግሯል፡፡ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን የሚከበርበትን ‹‹ማርች 8›› ምክንያት በማድረግ ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ ሊከናወን በታቀደው የሽልማት መርሐ ግብር ያዘጋጀው አርኪ ፕሮሞሽንና ኢቨንት ነው፡፡ አቶ ሸምሱ ከሪም የአርኪ ፕሮሞሽንና ኢቨንት ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ሴቶች ምሥጋናና ዕውቅና የሚያገኙበትን ሽልማት አስመልክቶ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡
ሪፖርተር፡- የዓመቱ ምርጥ ሴት የምትሸለምበትን ሥነ ሥርዓት ለማከናወን ዝግጅት አገባዳችኋል? ለምን ሴት ላይ ብቻ አተኮራችሁ?
አቶ ሸምሱ፡- ሴት ምሳሌዋ ብዙ ነው፡፡ ሴት በአገር ትመሰላለች፣ አገርም፣ እናትም፣ እህትም፣ ሚስትም፣ ልጅም ነች፡፡ ብዙውን ነገር የምትሸፍነው ሴት ነች፡፡ የሴት ውለታና ሥራዋ ብዙ ስለሆነ፣ እንደ ደረጃዋ ከፍ ለማድረግ አስበን ነው ሴትን የመረጥነው፡፡ የሴት ሥፍራን የበለጠ ከፍ ለማድረግ በሴት ላይ አተኩረን ሽልማትና ዕውቅና ለመስጠት ተነስተናል፡፡
ሪፖርተር፡- የዓመቷን ምርጥ ሴት የምትሸልሙት ‹‹ድንቅነሽ ሽልማት›› በሚል ነው፡፡ ምንን ይወክላል?
አቶ ሸምሱ፡- ሽልማቱን ‹‹ድንቅነሽ ሽልማት›› ብለን ስንሰይም፣ ሁለት ትርጉም ይዘን ነው፡፡ አንደኛ ሴት በተፈጥሮዋ ድንቅ ነች፡፡ ሁለተኛው የሉሲ ሁለተኛ ስሟ ድንቅነሽ ነው፡፡ የድንቅነሽ ስም ከፍ ስለሚልም በዚህ ስም ብንወክላት ብለን ነው ‹‹ድንቅነሽ ሽልማት›› ያልነው፡፡
ሪፖርተር፡- በምን ያህል ዘርፎች ትሸልማላችሁ?
አቶ ሸምሱ፡- ‹‹ድንቅነሽ ሽልማት››› አሥር ዓይነት ዘርፎች አሉት፡፡ በመምህርነት፣ በስፖርት፣ በጋዜጠኝነት፣ በበጎ አድራጎት፣ በአምባሳደርነት፣ በውትድርና፣ በኪነ ጥበብ፣ በፈጠራ፣ በአመራርና በሕክምና ዘርፎች ምርጥ ሴቶችን ለመሸለም ተዘጋጅተናል፡፡
ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም የበጎ ሰው ሽልማት፣ ጉማና ሌሎችንም አይተናል፡፡ ይኼኛው ሽልማት ከሌሎቹ በምን ይለያል?
አቶ ሸምሱ፡- በተለያየ የሙያ ዘርፍ ሆኖ ሴቶችን ብቻ ያማከለ መሆኑ ይለየናል፡፡ ይህ በቂ አይደለም፡፡ ወደፊት ሁኔታዎችን እያየን ዘርፎችን እያበዛን እንሄዳለን፡፡ ሌሎቹ ብዙ ጊዜ የሚያዘውሩት ኪነ ጥበብ፣ ስፖርት ላይ ወይም በጥቂት ዘርፎች ላይ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በሚከበርበት ‹‹ማርች 8›› ሰሞን መሆኑም ሌላው ለየት የሚያደርገው ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የሽልማቱ አካሄድ በቤት ውስጥም ሆነ በቢሮ እንደ ቦታው ሙያቸውን ተጠቅመውና ጫና ተቋቁመው የሚኖሩ ሴቶችን ወደፊት ለማውጣት እንዴት ያግዛል? በየመሥሪያ ቤቱና አካባቢ ሰው እንዲጠቁም ምን እየሠራችሁ ነው?
አቶ ሸምሱ፡- ሴቶችን በማውጣት ደረጃ ለተመረጡ ሴቶች አንቺ ጎበዝ ነሽ ብለን ስንሸልም ተደብቀው የነበሩ ሴቶችን ለማውጣት ያግዘናል፣ መልዕክት ያስተላልፋል፡፡ ዕውቅና ሲሰጥ ሌሎችም እኔም እንዲህ መሆንና ማድረግ እችላለሁ ብለው እንዲመጡ ይረዳል፡፡ የሠሩ ሰዎች ሥራቸው ዕውቅና ሲያገኝ ለበለጠ ሥራ እንዲነሳሱ ያደርጋል፡፡ ሥራዬ ታውቆልኛል፣ ሰው ዘንድ ደርሶልኛል፣ ልፋቴ ውጤት አምጥቷል እንዲሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ከኋላ ሆነው የሚያዩትም ምልከታ እንዲያደርጉ ያግዛቸዋል፡፡ ሴቶች ከፍ ባሉና እየወጡ በመጡ ቁጥር፣ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ጎበዝና ጠንካራ ሆነው፣ ግን ወደፊት ያልመጡና ያልታወቁትን ለማውጣት ያግዛል፡፡ እኛ ሴቶች ሕዝብ ፊት እንዲወጡ፣ የሠሩት ሥራ በሕዝብ ፊት እንዲመሰከርላቸው እንፈልጋለን፡፡ ሠርተው ያልታወቁ ሴቶች በርካቶች ናቸው፡፡ እነዚህን በየጊዜው ወደፊት በማውጣት ለሌሎች አርዓያ እንዲሆኑ እንፈልጋለን፡፡
ሪፖርተር፡- ቀጣዩ ዓመት ደርሶ ሁለተኛው ሽልማት እስኪሰጥ ባለው ጊዜ ከተመረጡና ከተሸለሙ ሴቶች ጋር ምን ትሠራላችሁ?
አቶ ሸምሱ፡- ከአሸናፊዎቹ ጋር የበጎ ፈቃድ ሥራ ለመሥራት አስበናል፡፡ የአሸናፊዎቹ ፈቃድ ከተገኘ ደግሞ በትምህርት ቤትና በመሥሪያ ቤቶች የሕይወት ተሞክሮዋን እንድታካፍል፣ ግንዛቤ እንድታስጨብጥ የምትሠራበትን ፕሮግራም እናመቻቻለን፡፡ አነቃቂ ንግግሮችን እንዲያደርጉ እንሠራለን፡፡
ሪፖርተር፡- ሴቶች በርካታ ሥራ ቢሠሩም፣ ቢመሩም፣ በኃላፊነት ቢቀመጡም፣ ይህን ያህል ወጥተው ሲናገሩ አይታዩም፡፡ ሴቶች እንዲወጡና እንደ አምባሳደር አድርጋችሁ እንዲሠሩ የምታደርጉበት አሠራር ይኖራል?
አቶ ሸምሱ፡- ሐሳቡ አለን፡፡ ከአንዳንድ ሰዎች ጋር እየተነጋገርንበት ነው፡፡ ጅማሬያችን ጥሩ ከሄደልን ሐሳባችንን የምናሳካ ይሆናል፡፡ ሒደቱ በራሱም ይመራናል፡፡ የተሸለሙ ሴቶች ተሸልመው እንዲቀሩ አንፈልግም፡፡ ከእኛ ጋር ሆነው ፕሮግራም እየቀረፅን፣ ሴቶችን በሥልጠና የማነቃቃትና ልምድ የማካፈል ሥራ ለመሥራት አስበናል፡፡ የትኛው ይቅደም የሚለውን ደግሞ አሸናፊዎች ከተለዩ በኋላ ከእነሱ ጋር በመምከር የምንሠራ ይሆናል፡፡ ሥራውን እንደ ተሸላሚዎቹ ዝግጅትና ፍላጎት የምንሠራው ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ያቀዳችሁትን የሽልማት ፕሮግራም ለመተግበር ፈተና ይሆንብናል ብላችሁ የምሉት ምንድነው?
አቶ ሸምሱ፡- የመጀመርያ ፕሮግራም በመሆኑ ሐሳቡን ሰው እስኪገዛው ጊዜ ይፈልጋል፡፡ የሴቶች ጉዳይ ሰፋ ያለ ስለሆነ ከእኛ ጋር የሚሠሩ ተቋማትን ማሳተፍ ያስፈልጋል፡፡ በሴቶች ላይ የሚሠሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን አሳምኖ አብሮ መሥራቱ ሊያስቸግረን ይችላል፡፡ አብዛኛው ስለሴት እንደሚጨነቅ፣ እንደሚያስብ፣ እንደሚሠራ እየሰማን ነው፡፡ እነዚህ ሐሳቡን ከገዙት ጥሩ ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- የሽልማት መርሐ ግብሮች ከጥቂቶች በስተቀር ተጀምረው ሲቋረጡ ታይቷል፡፡ የድንቅነሽ ሽልማት ቀጣይ እንዲሆን ምን ያህል ተዘጋጅታችኋል?
አቶ ሸምሱ፡- የመጀመርያውን ሽልማት ሰጥተን ግንዛቤ ከፈጠርን በኋላ፣ አብረውን የሚሠሩ አጋሮችን ለማሰባሰብና ለመወያየት ሐሳብ አለን፡፡ በሴቶች ላይ ‹የሴቶች ጉዳይ ጉዳዬ ነው› ብለው የሚሠሩ አሉ፡፡ ከእነሱ ጋር ተቀናጅተን ለመሥራት የሚያስችለንን ውይይት እናደርጋለን ብለናል፡፡
ሪፖርተር፡- የመጀመርያ ዙር በመሆኑ የሕዝብ አስተያየት አይገባበትም ብላችኋል፡፡ ሒደቱ በምን መልኩ ይከናወናል፡፡
አቶ ሸምሱ፡- የመጀመርያ ከመሆኑ አንፃር ጥቆማዎችን ከማኅበራትና ከመሥሪያ ቤቶች እንዲሆን አድርገን ዕጩ እያገኘን ነው፡፡ ሽልማቱ እስከሚከናወንበት የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ በእያንዳንዱ ዘርፍ አምስት ዕጩ እንይዛለን፡፡ ከአምስት ወደ ሦስት አድርገን፣ ከሦስት አንድ እንመርጣለን፡፡ ለዚህም ተቀባይነት አላቸው ብለን ያመንናቸው ዳኞችና የቦርድ አባላት አሉን፡፡
ሪፖርተር፡- የትኛው ዘርፍ ላይ በርካታ ተጠቋሚ አገኛችሁ?
አቶ ሸምሱ፡- ውትድርና ላይ ትንሽ ያንሳል፡፡ ኪነ ጥበብና መምህራን ላይ በብዛት አሉ፡፡ ጋዜጠኛና ሕክምና ላይ የተሻለ አግኝተናል፡፡ አምባሳደሮችና በጎ አድራጎት ላይ የተሰማሩ የተወሰኑ ናቸው፡፡ ፕሮግራሙ በደንብ ከተዋወቀ በኋላ በቀጣይ ጊዜያት በርካታ ዕጩ ይጠቆማል ብለን እናምናለን፡፡