Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየጥምቀት በዓል አከባበር በወልዲያ ከተማና አካባቢዋ

የጥምቀት በዓል አከባበር በወልዲያ ከተማና አካባቢዋ

ቀን:

በአበበ ፍቅር

የጥምቀት በዓል አከባበር በኢትዮጵያ ታቦትን ተሸክሞ ወንዝ ወርዶ የክርስቶስን በዓለ ጥምቀት ማክበር የተጀመረው በዘመነ አክሱም በአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን እንደነበር ይነገራል፡፡

ከዚያን ዘመን ጀምሮ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ እንደ አካባቢው ወግና ባህል ወይዛዝርቱና መኳንንቱ አምረውና ደምቀው አደባባይ የሚወጡበት፣ ልጃገረዶችና ወጣቶች ሎሚ የሚወራወሩበት፣ ወጣቱ ልቡ የከጀላትን ኮረዳ ሎሚ በመወርወር ይሁንታዋንና ዕንቢታዋን የሚለይበት የአደባባይ በዓል ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

 የጥምቀት በዓል አከባበር በኢትዮጵያ ከሃይማኖታዊ ከንውኑ ጋር ባህላዊ ክብረ በዓሉ እያደገ መጥቶ፣ ከኢትዮጵያ አልፎ የባህር ማዶ ሰዎችን ትኩረት መሳብ ከጀመረም ሰነባብቷል፡፡

ጥምቀት ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ተመሳሳይ ይሁን እንጂ፣ በማኅበረሰቡ የሚደረጉ ባህላዊ ሁነቶች ከቦታ ቦታ የተለያዩ እንደሆኑ መረዳት ይቻላል፡፡

ከመዲናዋ አዲስ አበባ በ520 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የሰሜን ወሎ ዋና መቀመጫ የሆነችው ወልዲያና አካባቢዋ ያሉ የእምነቱ ተከታዮች፣ የእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስን የጥምቀት በዓል በምን መልኩ አስውበውት እንደሚውሉ ለመቃኘት ወደናል፡፡

 ወልዲያ የበዓሉ ቀን ከመድረሱ ቀደም ብሎ ነው ገበያው የሚደራው፡፡ የበሬና የበጉ፣ የዶሮና የዕንቁላሉ የአሪቲና የቄጤማው፣ የብርጉድና አድሩስ፣ የልብሱና የጫማው ገበያ ቁሞ ገዥና ሻጭን ሲገበያዩ ለተመለከተ ሁሉ ዳግም ገበያ የለም እንዴ? ያስብላል፡፡

 ወጣት ሴቶችና ልጃገረዶች አምስትና ከዚያ በላይ በመሆን በሠፈር ወይም በጓደኛ በመቧደን ተመሳሳይ የጥምቀት ቀሚስን ቀድመው ያሰፋሉ፡፡ ከአልቦ እስከ ጆሮ ጌጥ ከአንገት ድሪ እስከ እጅ አምባር ያሉ ጌጣጌጦች ለበዓሉ ይሰናዳሉ፡፡

‹‹እንጀራው ወልዲያ እየተጋገረ

ወጡ ጉባላፍቶ ሲሸተኝ አደረ››

የተባለለት ወጥና እንጀራ፣ ዳቦና ጠላው ከየአቅጣጫው የሚመጡ የበዓሉ ታዳሚዎችን ታሳቢ በማድረግ በገፍ ይደገሳል፡፡

‹‹እንኳንስ ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ›› እንደሚባለው፣ ወለዬዎች እንኳን የሚያሳብቡበት በዓል አግኝተው እንዲሁም በሞቴ! አፈር ስሆን ብሉልኝ፣ ጠጡልኝ ማለት የቆየ ባህላቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡

የበዓሉ ክዋኔ የሚጀመረው የከተራ ማለትም ጥር 10 ቀን ፀሐይ ስታዘነብል በከተማዋ በቅርብ ርቀት የሚገኙትን ጨምሮ ከ11 በላይ ታቦታት ከመንበራቸው በክብር በካህናት ዝማሬ፣ በቀሳውስት ሽብሸባና በሰንበት ትምህርት ቤት ሕፃናትና ወጣቶች ዝማሬ ታጅበው በወጣቶች ሆታና ጭፈራ፣ በእናቶች እልልታና ጭብጨባ ደምቀው፣ ከተለያየ የከተማዪቱ በሮች ተነስተው በተለምዶ ‹‹መልካ ቆሌ›› ተብሎ በሚጠራው ሜዳ ላይ ወደተዘጋጀው ባህረ ጥምቀት ይሸኛሉ፡፡

በሥፍራው በአባቶች መንፈሳዊ ትምህርቶች ይሰጣሉ፡፡ መንፈሳዊ ዝማሬዎችና ልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ክንውኖች ሲካሄዱ ያድራሉ፡፡

የሃይማኖቱ አስተምሮ እንደሚያስረዳው፣ በዕለተ ጥምቀት የሃይማኖቱ ተከታዮች ሁሉ በተገኙበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሐዋርያው በመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ እጅ በፈለገ ዮርዳኖስ በውኃ እንደተጠመቀ ካህናት አባቶች ለቡራኬ የተሰበሰበውን ምዕመን ፀበሉን ይረጫሉ፡፡

ከጥምቀቱ ክብረ በዓል በኋላ ከቅዱስ ሚካኤል ታቦት በስተቀር ሁሉም ታቦታት ወደ መንበራቸው በክብር ይሸኛሉ፡፡

ወጣቶች ታቦተ ሕጉ ጉዞ በሚያደርግበት መንገድ ላይ ምንጣፍ በመዘርጋት ከመነሻ እስከ መድረሻ ያደርሳሉ፡፡

 በወልዲያና በዙሪያዋ ያሉ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ከበዓለ ጥምቀት በበለጠ በጉጉትና በናፍቆት የሚጠብቁት ቃና ዘገሊላ ወይም ጥር ሚካኤልን እንደሆነ ወጣት ጥላሁን አሻግሬ ይናገራል፡፡

ጥምቀት የበዓላቸው መዳረሻና መቃመሻ ነው፡፡ ቃና ዘገሊላ (ጥር ሚካኤል) በአራቱም የከተማዋ በሮች ከደጋውም ከቆላውም ተጠራርተው የሚሰባሰቡባት፣ አቧራው እስኪጨስ የሚጨፈርበት፣ ጉብልና ኮረዳ የሚተያዩበት፣ የተለያዩ ብሔረሰቦች ጭፈራዎችና ባህላዊ አለባበሶች ደምቀው የሚታዩበት ውብ የሆነ ሃይማኖታዊና በውስጡም ልዩ ልዩ ባህላዊ እሴቶችን የያዘ በዓል እንደሆነ የአካባቢው ወጣቶች ይመሰክራሉ፡፡

ከሦስት ዓመት ወዲህ በአገሪቱ አለመረጋጋት በመፈጠሩ፣ ከዚያን ዓመት ጀምሮ ከአላማጣ ጫፍ፣ ከቆቦና ሮቢትን ጨምሮ ለበዓሉ ይመጡ የነበሩ ወጣቶች ቁጥራቸው እንደቀነሰና አሁን ላይ የአንዳንድ የብሔረሰብ ጭፈራዎች እንደቀሩ፣ በበዓሉ ላይ ለረዥም ጊዜ ተሳታፊ የነበሩት አቶ ሀብታሙ ሰጠ ይናገራሉ፡፡

ይሁን እንጂ አሁንም የራያ ማይማያ ለብሰው የሚጨፍሩ፣ ባህልና ወጋቸውን የሚያስተዋውቁ ወጣቶች በበዓሉ ዕለት ደምቀው ይታያሉ፡፡

 ወጣቶች በዘፈንና በጭፈራ የተሰማቸውን የፍቅርም ሆነ የፖለቲካ ቃላት እንዲህ በማለት ይገልጻሉ፡፡

‹‹አምጡልኝ በሬዎቼን አርጄ ልብላቸው

ደሞ እንደ መሬቱ አንዱ ሳይወስዳቸው›› በማለት ከቅርብም ከሩቅም መሬትን እየቆረሱ የሚሸጡትን ሸንቆጥ ያደርጋሉ፡፡

አባቶችና እናቶችም በፊናቸው፣

‹‹አሞራው በሰማይ ሲያይሽ ዋለ

ይህች የማናት ቆንጆ ብሎ እያለ›› በማለት ከወጣቱ ጎን በመሆን በዕልልታና በጭፈራ ታቦቱን ያጅባሉ፡፡ ልጃገረዶችም ቀደም ብለው በግልም በጋራም ያሠሩትን የጥምቀት ቀሚስ ለብሰው፣ ፀጉራቸውን ቀጭን ሹርባ ተሠርተው፣ እጅና እግራቸውን በእንሶስላ ወይም በጉሽርጥ በማቅላት ከመቼውም በበለጠ አምረውና ተውበው የሚታዩበት፣ ከእኩዮቻቸው ጋር በነፃነት አደባባይ ወጥተው የሚቦርቁበት፣ በዘፈንና በእስክስታ ሐሳብና ችሎታቸውን የሚገልጹበት የነፃነት በዓላቸው እንደሆነ ወጣት ሙሉሴት ንጋቴ ትናገራለች፡፡

ወንዶችም ቢሆኑ ከወትሮው በተለየ አምረውና ተውበው የሚታዩበት በሴቶች ዘንድ ሙገሳና ውደሳ የሚያገኙበት፣

‹‹ክምክም ጎፈሬው ላይ ሚዶውን ሰክቶ

ጉድ አረገኝ የጁ መገን ጉባላፍቶ›› ተብሎ የተዜመላቸው ወጣቶች ጎፈሬያቸውን አበጥረው መፋቂያቸውን ሰክተው ትከሻቸው ላይ ሽልም መዋጣቸውን (ዘንግ) ጣል አድርገው፣ በከተማው ደምቀው የሚታዩበት ቃና ዘገሊላ (ጥር ሚካኤል) እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

በወጣቱ አለባበስና ጎፈሬ አበጣጠር የተማረከች ወጣት፣ እንዳትጠራው በድንገት ነው ያየችው፣ ስሙንም አታውቀው ታዲያ ይች ኮረዳ ስሙን የምታውቁ ንገሩኝ ስትል በዘፈን ግጥሟ፣

‹‹ጎፈሬውን ባደስ የከመከመው

ስሙንም አላውቀው ማን ብዬ ልጥራው›› ስትል ትማፀናለች፡፡ በበዓሉ በለስ የቀናው ቀልቡ የከጀላትን ጉብል የማግኘትና የወደፊት ውኃ አጣጩን የማግኘት አጋጣሚ እንዳለና የቅርብ ጓደኞቹ በዚሁ አጋጣሚ ተገናኝተው ለቁምነገር እንደበቁ ወጣት ሃይማኖት አያሌው ይናገራል፡፡

ሃይማኖታዊ ሥርዓቱም ቢሆን የሰንበት ተማሪዎች በልዩ አልባሳት ደምቀው፣ ዲያቆናት በወረብና በሽብሸባ ታቦቱንና ካህናት አባቶችን አጅበው ከመነሻ እስከ መድረሻው ያለ ምንም ድካምና መሰላቸት በክብር ያደርሳሉ፡፡

 ሌላው ታቦቱ በሰላም ሲገባ ‹‹አልሃምዱልላሂ ታቦታችን በሰላመ ገባ›› ማለት ምናልባት ለሰሚዎች አዲስ እንደሆነ እንጂ ለወለዬዎች የቆየ ባህላችን ነው ይላሉ፡፡

መስጊድና ቤተ ክርስቲያን በጋራ መሥራት አረፋና መውሊድ ጥምቀትና ፋሲካን በጋራ ማክበር መደገስ አብሮ መብላትና መጠጣት ለወሎ ሙስሊምና ክርስቲያኖች የዕለት ተዕለት ተግባራቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

 ከዚህም አለፍ ሲል፣

‹‹አንቺም በሃይማኖትሽ እኔም በሃይማኖቴ

አብረን እኖራለን አይጠበንም ቤቴ›› እንዳለው ዘፋኙ፣ ወሎ ላይ ሙስሊምና ክርስቲያን አረፋና ጥምቀትን በጋራ ከማሳለፍ በዘለለ በአንድ ጣራ ሥር ትዳር መሥርተው ልጅ ወልደው አንደኛው የሌላውን ሃይማኖት አክብሮና ተከባብረው ይኖራሉ፡፡

የጥር ሚካኤል በዓል በወልዲያ መቋጫው እንግዶችን በፍቅር ተቀብሎ በማስተናገድ ነው፡፡

 በጭፈራና በዘፈን በእስክስታና በሆታ በዝማሬና በውዳሴ በዓሉን አክብረው ታቦቱን ሸኝተው የሚመለሱ የሩቅም የቅርብም እንግዶች ‹‹በሞቴ አፈር ስሆን›› ተብለው ሳይሆን ልባቸው ወደ ከጀለው ቤት ገብተው በልተው ጠጥተው ቢወጡ እንደ ነውር ሳይሆን እንደ ክብር ነው የሚቆጠረው፡፡

በዚህ መልኩ ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው ቤት በመዘዋወር በጭፈራና በዘፈን ከተማዋ ደምቃ ታመሻለች፡፡ ለከርሞም ያድርሰን ትላለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...