የምሥራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ በሚያስመዝግበው ውጤት ልክ በዓለም አትሌቲክስ አመራር ውስጥ እንዲገባ መሠራት አለበት ተባለ፡፡
ይህ የተባለው የምሥራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሪጅን ጉባዔ በአዲስ አበባ ጥር 7 ቀን 2015 ዓ.ም. በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡
በጉባዔው ከኢትዮጵያ፣ ጂቡቲ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ዑጋንዳ የተውጣጡ የብሔራዊ ፌዴሬሽን ተወካዮች ተሳትፈውበታል፡፡ በመድረኩ እንደተወሳው፣ የምሥራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ እንደሚያስመዘግበው ውጤት ልክ በዓለም አትሌቲክስ ዘንድ ውክልናው የውጤታማነቱን ያህል ባለመሆኑ፣ የሚገባውን ሥፍራ እንዲያገኝ በርትቶ መሥራት ይገባል፡፡
በአሁኑ ወቅት በዓለም አትሌቲክስ የቴክኒካል አደረጃጀት ለውጦች በመኖራቸው የምሥራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ አባላትም ከአዲሱ የዓለም አትሌቲክስ አሠራሮች ጋር ራሳቸው ማዛመድ እንደሚገባቸውም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡
ከዚህም ባሻገር ስለአበረታች ቅመሞች አደጋ አስተያየት የተሰነዘረ ሲሆን፣ በጉዳይ ላይ ጨከን ተብሎ መሥራት እንደሚገባ፣ አደጋውም እየከፋ እንደመጣ ተነስቷል፡፡
በተለይ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያና ኬንያ በዓለም አትሌቲክስ በ “ኤ” ምድብ ውስጥ መሆናቸውና በዓለም ላይ ካሉ 213 አባል አገሮች ደረጃ ትልቁን ድርሻ ስለሚወስዱ ጉዳዩን በአንክሮ መመልከት እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
ከዚህም ባሻገር ጤናማ ወጣቶችን ለማፍራት የሥልጠና ማዕከላትን ከመገንባት ጋር በተያያዘ የተለያዩ አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን፣ በተለይ የአትሌት ተወካዮች በአሁኑ ሰዓት የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖችን የውሳኔ ሰጪነት ሚናን እጅግ እየተፈታተኑት እንደሆነም ተነስቷል፡፡
ጉባዔው ለቀጣይ አራት ዓመታት የምሥራቅ አፍሪካን የሚመሩ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫም አከናውኗል፡፡
በዚህም መሠረት የኬንያዊን ጃክሰን ቲዊ ፕሬዚዳንት፣ ዑጋንዳዊው ዶሚኒክ ኡትሲት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ እንዲሁም ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡