Wednesday, November 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበዓለም አቀፍ የጎዳና ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል

በዓለም አቀፍ የጎዳና ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል

ቀን:

በሳምንቱ መጨረሻ በተለያዩ የዓለም አገሮች የጎዳና ውድድሮች ተከናውነው አልፈዋል፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም በ10 ኪሎ ሜትር፣ በግማሽ ማራቶን፣ እንዲሁም በማራቶን ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን በተካፈሉባቸው አብዛኛው ውድድሮች ላይ ድል ቀንቷቸዋል፡፡

ከእነዚህም መካከል በቫሌንሺያ በተደረገ የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር የዓለምዘርፍ የኋላ በቀዳሚነት ማጠናቀቅ የቻለችበት ተጠቃሽ ነው፡፡

ከወራት በፊት የለንደን ማራቶን ማሸነፍ የቻለቸው የዓለምዘርፍ የቫሌንሺያውን 10 ኪሎ ሜትር ውድድር 29፡19 በሆነ ጊዜ ማሸነፍ ችላለች፡፡

ዓምና 29፡14 በመግባት አዲስ ክብረ ወሰን መያዝ የቻለችበትን የቫሌንሺያ 10 ኪሎ ሜትር ውድድር፣ ዘንድሮ አምስት ሰከንድ ዘግይታ ብትገባም በበላይነት ማጠናቀቅ ችላለች፡፡

የአትሌቷ አምስት ሰከንድ ዘግይታ መግባት በውድድሩ መነሻ ላይ ዘግየት ማለቷና የመጀመርያውን 2 ኪሎ ሜትር 5፡56 በሆነ ሰዓት ማጋመሷ እንደ ምክንያትነት ተነስቷል፡፡

ሆኖም የሩጫው ፍጥነት እየጨመረ በመምጣቱ፣ የ3 ኪሎ ሜትር ርቀቱን 8፡51 በሆነ ጊዜ ውስጥ ስትሮጥ፣ በሒደት ፉክክሩ እየጨመረ መጥቶ የዓለምዘርፍ 4 ኪሎ ሜትሩን 11፡52 በሆነ ሰዓት እንድትሮጥ አስገድዷታል፡፡

አትሌቷ ግማሽ ኪሎ ሜትሩን ካጋመሰች በኋላ ፍጥነት እየጨመረች መምጣት የቻለች ሲሆን፣ አንዱን ኪሎ ሜር 2፡53፣ 2፡54 በሆነ ጊዜ በመሮጥ 8 ኪሎ ሜትር 23፡90 በሆነ ጊዜ ውስጥ መሮጧ ተጠቅሷል፡፡

ከውድድሩ በኋላ ለጋዜጠኞች አስተያየት የሰጠችው የዓለምዘርፍ ክብረ ወሰን መስበር አለመቻሏ እንዳበሳጫት ገልጻ፣ ጥረቷን ግን ማድነቋን አውስታለች፡፡

የዓለምዘርፍ ዓምና ከነበራት የክብረ ወሰን ሰዓት 5 ሰከንድ ብትዘገይም፣ ሁለተኛውን የምንጊዜም ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ ችላለች፡፡

በአሜሪካ ሒውስተን በተደረገ የግማሽ የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል፡፡ በወንዶች ልዑል ገብረሥላሴ 1፡00፡34 በሆነ ሰዓት አንደኛ ሲወጣ፣ በሴቶች ሕይወት ገብረማርያም 1፡06፡28 በሆነ ጊዜ በበላይነት ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡

ከአራት ዓመት በኋላ ወደ ውድድር የተመለሰችው ጥሩነሽ ዲባባ 1፡11፡35 በሆነ ጊዜ16ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች፡፡

የጥሩነሽ ዲባባ ታናሽ እህት አና ዲባባ 1፡09፡22 በሆነ ጊዜ አራተኛ ወጥታለች፡፡ በተመሳሳይ ቀን በሒውስተን በተደረገ የማራቶን ውድድር በወንዶች ፀጥታ አያና 2፡10፡37 በሆነ ጊዜ ሁለተኛ ሲወጣ፣ ተሾመ መኮንን 2፡11፡05 በሆነ ጊዜ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡

በሴቶች ሙልዬ ከበደ 2፡25፡35 ሁለተኛ፣ ስንታየሁ ለውጠኝ 2፡26፡33 ሦስተኛ ደረጃ ይዞ መውጣት የቻሉበት ሳምንት ነበር፡፡

ከዚህም ባሻገር በህንድ ሞምባይ በተደረገ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታ ተቆጣጥረውት ውለዋል፡፡

በወንዶች ለሚ ብርሃኑ 2፡07፡32 አንደኛ ሲወጣ፣ በሴቶች አንቺዓለም ሃይማኖት 2፡24፡16 በሆነ ጊዜ ማሸነፍ ችላለች፡፡ በሴቶች ውድድር ከአንድ እስከ አሥር ያለውን ደረጃ መቆጣጠር የቻበሉት የውድድር ሳምንት ነበር፡፡

በሌላው የጎዳና ሩጫ በስፔን የተከናወነ ሲሆን፣ በአሥር ኪሎ ሜትር ውድድር በወንዶች ሐጎስ ገብረ ሕይወት 27፡57 አንደኛ፣ ብርሃኑ በለው 28፡25 ከባህሬን ሁለተኛ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያዊው ሙክታር እድሪስ 28፡29 ሦስተኛ ደረጃን ይዘው በመውጣት በበላይነት አጠናቀዋል፡፡

በሴቶች ለምለም ኃይሉ 31፡37 አንደኛ፣ ኬንያዊቷ ሩት ቻብቼንጊች 31፡39 ሁለተኛ፣ እንዲሁም ትዕግሥት ገዛኸኝ 32፡06 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ ደረጃን ይዘው በማጠናቀቅ ሳምንቱን በድል ያሳለፉበት አጋጣሚ ነበር፡፡

በቅርቡ እየተስተዋለ እንደመጣው አብዛኛው አትሌት ፊቱን ወደ ጎዳና ሩጫ ያተኮረበት ዘመን መሆኑ፣ በየሳምንቱ እየተደረጉ የሚገኙ የጎዳና ውድድሮች ማሳያ ናቸው፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...