Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበገዛ ፈቃዳቸው ለቀቁ በተባሉት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች ምትክ ሹመት ተሰጠ

በገዛ ፈቃዳቸው ለቀቁ በተባሉት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች ምትክ ሹመት ተሰጠ

ቀን:

  • ‹‹ሁለት ኃላፊዎች በአንድ ጊዜ መልቀቃቸው እውነት በፈቃደኝነት ነው?››

የፓርላማ አባላት

ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የተደረገውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ ወደ ሥልጣን የመጡት፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊና ምክትላቸው አቶ ሰለሞን አረዳ በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለቀቁ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥር 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው 8ኛ መደበኛ ስብሰባ፣ የቀድሞዋ ፕሬዚዳንትና ምክትላቸው በፈቃዳቸው ከሥልጣናቸው መልቀቃቸውን፣ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ለፓርላማው ተናግረው በአዲስ ፕሬዚዳንቶች ተተክተዋል፡፡

የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ምንም እንኳ ሁለቱም በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን መልቀቃቸውን ቢያሳውቁም፣ ያስገቡት የመልቀቂያ ደብዳቤ ምን ይዘት እንዳለውና በምን ምክንያት እንደለቀቁ አልተናገሩም፡፡ በዚህም በለቀቁት ኃላፊዎች ምትክ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የቀረቡ ሹመቶችን፣ ምክር ቤቱ መርምሮ እንዲያፀድቅ ጠይቀዋል፡፡

በዚህም መሠረት ምክር ቤቱ አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት ከበደን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አድርጎ በሦስት ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ፣ እንዲሁም በምክትል ፕሬዚዳንትነት ወ/ሮ አበባ እምቢአለን በሙሉ ድምፅ ሹመታቸውን አፅድቋል፡፡

የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ ባደረጉት ንግግር፣ ጠንካራ አገረ መንግሥት ለመገንባት ጠንካራ የሪፎርም ሥራዎች በየዘርፉ ስለመከናወናቸውና በዚህም የፍትሕና የዳኝነት ሥራው ቀልጣፋ፣ ውጤታማ፣ ከአድልኦ የፀዳና የዜጎችን እርካታ እያረጋገጠ የሚሄድ እንዲሆን ብዙ ሥራዎች ስለመጀመራቸው አስረድተዋል፡፡ በዚህም የዳኝነት ሥርዓቱ የሕግ የበላይነትን ያስከበረና የሕዝብ አመኔታን ያገኘ እንዲሆን የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ ቢሆንም፣ አሁንም የኅብረተሰቡን ጥያቄ በየዘርፉ በብቃት መመለስ ስላለበት መንግሥት ይህን ግምት ውስጥ ያስገባ አዲስ ሹመት ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

በዕጩነት ቀርበው የተሾሙት አቶ ቴዎድሮስ ከዚህ ቀደም በኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ በነገረ ፈጅነት፣ በፍትሕና ሕግ ሥርዓት ምርምር ኢንስቲቲዩት በሕግ ልዩ ባለሙያነት፣ በአቢሲኒያ ባንክ በነገረ ፈጅነት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ አገልግሎት ክፍል ኃላፊ፣ አንዲሁም በዚሁ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር በመሆን ማገልገላቸው ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም የብርሃን ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር ቦርድ ሰብሳቢ፣ የኢትዮጵያ ሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንትና የሕግና ፍትሕ ምክር ቤት አማካሪ በመሆን ማገልገላቸውን አቶ ተስፋዬ አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ በምክትል ፕሬዚዳንትነት የተሾሙት ወ/ሮ አበባ ከዚህ ቀደም በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዳኝነት፣ በፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በዓቃቤ ሕግነት፣ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤትና በከፍተኛ ፍርድ ቤት በዳኝነት ያገለገሉ መሆናቸውን፣ አሁን ደግሞ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዳኝነት ሥራ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

የምክር ቤት አባላት አዲስ የተሸሙት ግለሰቦች ማንነት በተገቢው ሁኔታ ለመገምገም ቀድሞ ስለግለሰቦቹ አለመነገሩን እንዲሁም ከዚህ ቀደም የነበሩት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት በምን ምክንያት እንደለቀቁ አለመብራራቱ ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡

አንድ የምክር ቤት አባል ከለውጥ በፊት የፍትሕ ተቋማት ተገደው ይወስኑ  እንደነበር በመግለጽ፣ ነገር ግን ለውጥ ተካሄደ በተባለ ማግሥትና የተሻሉ ተቀማት ተመሥርተው ሳለ እነዚህ ሁለት ኃላፊዎች በአንድ ጊዜ መልቀቃቸው እውነት በፈቃደኝነት ነው? ወይስ እንደ ድሮ ጣልቃ እየተገባባቸው ነው? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ አክለውም፣ ‹‹የሾምናቸው እኛ በመሆናችን በሚዲያ የተለያየ ነገር ከምንሰማ፣ ቁልጭ ያለው ነገር ለምን እዚሁ አይነገረንም?›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በአዲስ በፕሬዚዳንትነት የተሾሙት አቶ ቴዎድሮስ በዳኝነት በየትኛውም ደረጃ ያላገለገሉ መሆናቸውን በመጥቀስ በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ በዳኝነት ለረዥም ዓመታት ያገለገሉ ባለሙያዎች ጠፍተው ነው ወይ? በማለት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ በሌላ በኩል የዕጩ አቀራረቡን በተመለከተ ለአፈ ጉባዔው አስተያየት የሰጡት ደሳለኝ (ዶ/ር) በሌሎች አገሮች ተሞክሮ መሠረት እንዲህ ዓይነት ሹመት ሲታሰብ ቀድሞ ማንነታቸው ይፋ ተደርጎ ጀርባቸውና ማንነታቸው በተለያየ መንገድ የሚጠናበት አሠራር እንዳለ በመጥቀስ፣ በዚህ የምክር ቤት አሠራር ስለግለሰቡም ሆነ ሌሎች ከፍተኛ አገራዊ ኃላፊነት ስለለሚሰጣቸው ግለሰቦች ቀድሞ መረጃ ቢደርሳቸው አስተያየት ሊኖራቸው እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ ምክር ቤቱ የሚሠራው በሕግና ሥርዓት በመሆኑ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 7 እና 81 መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማው ዕጩ እንደሚያቀርቡና የምክር ቤት አባላቱ ተወያይተው እንድያፀድቁ የተቀመጠ ሕገ መንግሥታዊ አሠራር ስለመኖሩ እንጂ የተሳሳተ አሠራር አለመኖሩን፣ እንዲሁም በምክር ቤቱ አሠራርና ደንብ መሠረት ይኸው መከናወኑን አስረድተዋል፡፡  

በሌላ በኩል የሕዝብ ተዋካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔው ከኃላፊነታቸው ስለለቀቁት ኃላፊዎች ሲናገሩ፣ ‹‹የተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በየትኛውም ጊዜ ሥራቸውን አከናውነው እስከዚህ ድረስ ሠርቻለሁ ከዚህ በኋላ ይበቃኛል ካሉና መልቀቂያ ከጠየቁ ሊሆን የሚችለው፣ እስካሁን ላደረጋችሁት አስተዋጽኦ እናመሠግናለን ለአገራችሁና ለሕዝባችሁ ሠርታችኋል ብለን በምትካቸው መሾም ነው፤›› ብለዋል፡፡

የሕግ ባለሙያው አቶ ውብሸት ሙላት በራሳቸው ፈቃድ ስለለቀቁት ኃላፊዎችና የተተኩትን አዲስ ተሿሚዎች በተመለከተ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ ከጅምሩ የመንግሥት አሠራር ድፍን ያለ መሆኑን የሚያሳይና ድብቅብቅ ብሎ የመጣ የኃላፊነት መልቀቂያ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ የለቀቁት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት  ምክንያታቸው በግል ጉዳይም ይሁን በውጭ አካል ጫና በግልጽ ለሕዝብ አለማሳወቃቸው፣ ሕዝቡ ሁልጊዜ የሚጠብውን የግልጽነትና የተዓማኒነት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የፓርላማው የሕግና ፍትሕ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የለቀቁትንም ሆነ አዲስ የመጡትን ተሿሚዎች በተመለከተ በግልጽ ተወያይቶ ለፓርላማ ውይይት ይዞት የሚቀርበው ሐሳብ መኖር እንደነበረበት የገለጹት አቶ ውብሸት፣ ይህ ዓይነቱ ግልጽ ያልሆነ አሠራር ከመንግሥት አልፎ የለቀቁት ግለሰቦችም ቢሆኑ ምክንያታቸውን ቢናገሩ ኖሮ በቀጣይ በመንግሥት አሠራር ላይ እምነት ማሳደር ይቻል እንደነበር ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...