Thursday, November 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚዎች ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ አለመሆናቸው ተነገረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚዎች ድጎማውን ተቀብለው አገልግሎት እየሰጡ አለመሆናቸው፣ በተገልጋዮች ላይ ከፍተኛ መጉላላትን እያስከተለ መሆኑ ተገለጸ፡፡

መንግሥት ከ2014 ዓ.ም. ሰኔ ወር ጀምሮ ለሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ ተሽከርካሪዎች የነዳጅ ድጎማ እየሰጠ ቢሆንም፣ ድጎማውን ከተቀበሉ በኋላ አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑ ቅሬታ አስነስቷል፡፡

በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች በርካታ የነዳጅ ድጎማ የሚደረግላቸው ተሽከርካሪዎች ድጎማውን ከተቀበሉ በኋላ ቆመው እንደሚውሉ፣ አልፎ አልፎ አገልግሎት ሲሰጡም የሚጠይቁት ዋጋ ከታሪፍ በላይ በመሆኑ መማረራቸውን ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ፣ በባህር ዳር፣ በደሴ፣ ድሬዳዋን ጨምሮ በሌሎች የክልል ከተሞች የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ የሆኑ ተሽከርካሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ ቅሬታ አቅራቢዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳህረላ አብዱላሂ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ የነዳጅ ድጎማ ተቀብለው የትራንስፖርት አገልግሎት የማይሰጡ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ስለመኖራቸው ተናግረዋል፡፡

የነዳጅ ድጎማ ተቀብለው የትራንስፖርት አገልግሎት የመስጠት ግዴታቸውን የማይወጡ አሽከርካሪዎች ከመኖራቸውም በተጨማሪ፣ ነዳጅ ከዴፖ ተቀድቶ ማደያ እስከሚደርስበት ጊዜ ‹‹ቅሸባ›› እንዳለም አስረድተዋል፡፡

የነዳጅ ማደያ ለስርቆት የተመቻቹ ብዙ በሮች ያሉበት ቦታ መሆኑን፣ በተለይም ነዳጅ አመላላሽ ቦቴዎች በመንገድ ላይ ብዙ ጊዜ ነዳጅ እንደሚቀሽቡ ወ/ሮ ሳህረላ አስረድተዋል፡፡

‹‹የአውሮፕላን ነዳጅ ከዴፖ ወደ ዴፖ ነው የሚገለበጠው፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ፣ የተሽከርካሪ ነዳጅ ግን ከዴፖ ተጭኖ ከመጣ በኋላ ማደያ ስለሚገለበጥ በመሀል ‹‹ቅሸባ›› ይኖራል ብለዋል፡፡

በተለያዩ የክልል ከተሞች የሚገኙ ተገልጋዮች ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚዎች ነዳጁን ከተቀበሉ በኋላ የትራንስፖርት አገልግሎት የማይሰጡት ነዳጁን ከቀዱ በኋላ አየር በአየር ስለሚሸጡ ነው፡፡

የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን በበኩሉ ጉዳዩን በተመለከተ ከዚህ በፊት ቀርቦለት ለነበረው ጥያቄ፣ የነዳጅ ድጎማ ተጠቅመው አገልግሎት የማይሰጡ ካሉ በሒደት ተጠንቶ ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል አስታውቆ ነበር፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ አሽከርካሪዎች ስለጉዳዩ ሲናገሩም፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ከመስጠት ይልቅ ነዳጅን መሸጥ ያዋጣል ይላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚዎች እንሁን የሚሉት ተሽከርካሪዎች ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ መሆኑን መረጃዎች እያመለከቱ ነው፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ ጀምሮ እስከ ክልል ከተሞች የሚገኙ አስተያየት ሰጪዎች፣ አሽከርካሪዎች ከታሪፍ በላይ ከሚጠይቁት ገንዘብ በተጨማሪ አገልግሎት እየሰጡ አለመሆናቸው በዕለት ተዕለት ሥራቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረባቸው ነው፡፡ የሚመለከተው አካልም በፍጥነት መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የነዳጅ ተጠቃሚ ሆነው የትራንስፖርት አገልግሎት የማይሰጡ ተሽከርካሪዎች ስለመኖራቸው መረጃው እንደሌለው አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች