መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ድጋፍ የሚሰጠውን ወገን ብቻ ሳይሆን፣ በተቃውሞ ጎራ ያለውን ጭምር በአንክሮ ለማዳመጥ ዝግጁ መሆን አለበት፡፡ የዕለት ኑሮዋቸውን ለማሳካት ደፋ ቀና ከሚሉ ዜጎች ጀምሮ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩትን ጭምር ማዳመጥ ጠቃሚ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ምላሽ የሚፈልጉ ጥያቄዎች ያሉትን ያህል፣ ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሚያግዙ በርካታ ምክረ ሐሳቦችን ማቅረብ የሚችሉ አሉ፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በዲፕሎማሲ፣ በሰላምና ፀጥታ፣ እንዲሁም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በርካታ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ዛሬ የተፈጠሩ ብቻ ሳይሆኑ፣ ከሁለትና ከሦስት ትውልድ ዕድሜ በላይም የሚሻገሩ ናቸው፡፡ በርካታ ዓመታት ያስቆጠሩትና ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት የተፈጠሩት ጥያቄዎች ምላሽ ይሻሉ፡፡ ሁሉንም ጥያቄዎች ደግሞ መንግሥት ብቻውን ሊመልሳቸው አይችልም፡፡ በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካይነት ለሚዘጋጁ መድረኮች የሚቀርቡ ብዙ ጥያቄዎች ያሉትን ያህል መንግሥት ከየመስኩ ምሁራንና ልሂቃን፣ ከእምነት መሪዎች፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ለአገር እናስባለን ከሚሉ ዜጎች ጋር በመመካከር መፍትሔ የሚፈልግላቸው ይኖራሉ፡፡ እስከዚያው ግን መንግሥት ዜጎችን ማዳመጥ አለበት፡፡
መንግሥት የዕለት ተዕለት ሥራውን ሲያከናውን ቀዳሚውን ከተከታዩ ማወቅ ይኖርበታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የብዙዎች ሞጋቾች ትችት መንግሥት ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡትን አንገብጋቢ ጉዳዮችን ትቶ፣ ያን ያህል አስፈላጊ ያልሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ የአገሪቱን አንጡራ ሀብት ያባክናል የሚል ነው፡፡ ሥራዎች አንዳቸው ከሌላው ቅድሚያ አግኝተው መከናወን የሚችሉት፣ በዕቅድና በጥናት ላይ በመመሥረት የሕዝቡን ፍላጎት ማዕከል ሲያደርጉ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲም ሆነ የሚመራው መንግሥት ቀደም ሲሉ ከነበሩ ስህተቶች በመማር የሕዝቡን ኑሮ የሚለውጡ፣ የኑሮ ውድነቱን የሚያረግቡ፣ አስተማማኝ ሰላም የሚያሰፍኑ፣ በእኩልነትና በነፃነት ለመኖር የሚያስችሉና መሰል ተግባራት ላይ እንዲያተኩር በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ዜጎች ምክረ ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡ ለግጭትና ለውድመት በር የሚከፍቱ አላስፈላጊ እንቅስቃሴዎችን በመግታት፣ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በእኩልነት የምታስተናግድ ኢትዮጵያ እንድትገነባ ማሳሰቢያ ሲቀርብ ማዳመጥ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ከማንኛውም ግለሰብና ስብስብ በላይ ስለሆነች፣ ስለዕጣ ፈንታዋም ሆነ ስለህልውናዋ መነጋገርም ሆነ መደማመጥ የግድ መሆን አለበት፡፡ መንግሥት ዜጎችን ሲያዳምጥ ቅራኔዎች ይረግባሉ፡፡
በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ ከሚስተዋሉ በርካታ ችግሮች መካከል በዋናነት የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የፍትሕ መጓደልና ሙስና በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ በግልጽነትና በተጠያቂነት ያለ መኖር ምክንያት ሕዝብ ላይ የሚፈነጩ ችግሮች የአገር ሥጋት እየሆኑ ነው፡፡ ቁርጠኝነት ካለ በቁጥጥር ሥር መዋል የሚችሉት እነዚህ አደገኛ ተግዳሮቶች፣ በጠንካራ የሥነ ምግባር መርህና በሕግ የበላይነት ሊገቱ ይችላሉ፡፡ ለተግባራዊነታቸውም ተጠያቂነት የሰፈነበት ሥርዓት ሙሉ በሙሉ መዘርጋት ይኖርበታል፡፡ ተጠያቂነት የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ በዓለማችን ላይ ትልቅ ትኩረት ያገኘበት ምክንያት፣ በምርጫ የሕዝብ ድምፅ አግኝተው ሥልጣን የሚይዙ ፓርቲዎች የሚያገለግሉት ሕዝብ ለሚያቀርብላቸው ማንኛውም ጥያቄ መልስ የመስጠት ግዴታ ስላለባቸው ነው፡፡ በመሆኑም ተጠያቂነት የሥነ ምግባር፣ የሕግ የበላይነት፣ የዴሞክራሲና የመርህ መገለጫ በመሆኑ ትልቅ ግምት አለው፡፡ ተጠያቂነትን የማስፈን ጉዳይ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ለይስሙላ ብቻ የሚነገር ሳይሆን፣ በተግባር የተረጋገጠ ውሳኔ የሚሻ ነው፡፡ መንግሥት በተቺዎችም ሆነ በሒሳዊ ደጋፊዎቹ ከሚቀርቡበት ጥያቄዎች አንዱ፣ አሠራሩን በግልጽና በተጠያቂነት እንዲያደርግ መሆኑን በተለያዩ መድረኮች ላይ ይሰማል፡፡
መንግሥት የሚደመጠው ሕዝብን ማዳመጥ ሲችል ብቻ ነው፡፡ ሕዝብን የማያዳምጥ መንግሥት ማንም አያዳምጠውም፡፡ መንግሥት በሕዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት የሚጨምረውም የሚቀንሰውም፣ ከሕዝብ ካለው ቅርበትና ርቀት አንፃር ነው፡፡ በተደጋጋሚ መንግሥት ሕዝብን ማዳመጥ እንዳለበት፣ የሕግ የበላይነት መከበር እንደሚኖርበት፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚያግዝ መደላድል እንዲፈጠር፣ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች መከበር እንዳለባቸው፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ሕጎች ተግባራዊ እንዲደረጉ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ይቀርባሉ፡፡ መንግሥት የመረጠውን ሕዝብ ድምፅ ብቻ ሳይሆን፣ የሌሎችንም ጭምር ማዳመጥ እንዳለበትና ይህም ለአገር እንደሚበጅ ተደጋግሞ ተስተጋብቷል፡፡ በዚህ መሠረት መራመድ ሲቻል የመንግሥት አሠራሮች በሙሉ ግልጽ ይሆናሉ፡፡ ፍትሕ ለሁሉም ተደራሽ ይሆናል፡፡ የአገሪቱ ሀብት ለሁሉም ዜጎች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ይከፋፈላል፡፡ ልማትና ዕድገት የጋራ አጀንዳ ይሆናሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒ በሚደረግ ጉዞ ግን ሕዝብ ይቆጣል፡፡ አንፃራዊው ሰላም ይደፈርሳል፡፡ መላው የአገሪቱ ሕዝብም ሆነ የአገር ጉዳይ ይመለከተናል ብለው ጥያቄም ሆነ ሐሳብ የሚያቀርቡ ሲኖሩ፣ መንግሥት በቀና ልቦና ማዳመጥ ይጠቅመዋል እንጂ አይጎዳውም፡፡
በኢትዮጵያ ‹‹ከሰው መርጦ ለሹመት ከእንጨት መርጦ ለታቦት›› የሚለው ዕድሜ ጠገብ አባባል ይታወቃል፡፡ በዘመናዊ የመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ከፓርቲ ፖለቲካ ትስስር በተጨማሪ፣ ለትልቅ ኃላፊነት ይመጥናሉ ተብለው የሚፈለጉ ግለሰቦች በትምህርታቸውና በሥራ ልምዳቸው፣ እንዲሁም በሥነ ምግባራቸውና በማኅበረሰቡ ዘንድ በሚሰጣቸው ከበሬታ አንቱታን ያተረፉ መሆን አለባቸው፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን መሥፈርቶች ከግምት በማስገባት ሹመት ያገኙ ሰዎች ፓርላማ ቀርበው ቃለ መሃላ እየፈጸሙ በግልጽ ታሪካቸው ሲዘከር፣ በሆነ ወቅት ከሹመታቸው ተሽረው ሲነሱ ግን አንዳችም ምክንያት አለመነገሩ እየተለመደ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ሦስት ሚኒስትሮችና አንድ የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ከሹመታቸው ተነስተው፣ ‹‹በክብር መሸኘታቸው›› ሲነገር ተሰምቷል፡፡ ቀጥሎም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ፕሬዚዳንትና ምክትላቸው በቃን ብለው በአዲስ ተሿሚዎች ተተክተዋል፡፡ መንግሥት ሲሾም ስለግለሰቡ ማንነት ማብራሪያ እንደሚሰጠው ሁሉ፣ ሲሽር ወይም ሲያሰናብት ደግሞ ምክንያቱን በግልጽ የማስታወቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ግልጽነት ከሌለ ግን ሐሜቱና አሉባልታው እየቀደመ መተማመን ያጠፋል፡፡
በዓለም ተቀባይነት ካላቸው አሠራሮች አንዱ የተመረቱ ምርቶች ለተጠቃሚዎች በግልጽ መቅረብ መቻላቸው ነው፡፡ ማንኛውም ምርት የተመረተበት ጊዜ፣ አገልግሎቱ የሚያበቃበት ጊዜና የተመረተባቸው ንጥረ ነገሮች በግልጽ ይሰፍራሉ፡፡ መድኃኒት፣ ምግብ፣ ውኃ፣ የመዋቢያ ቁሳቁሶችና የመሳሰሉ ምርቶች መግለጫዎቹ በግልጽ ካልሰፈሩባቸው ለተጠቃሚዎች አይቀርቡም፡፡ ለገበያ እንዲቀርቡም አይደረጉም፡፡ ይህ ዓይነቱ የግልጽነት ጥንቃቄ የሚደረገው በሕዝብ ጤና ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ነው፡፡ ማንኛውም ኅብረተሰብ አኗኗሩ ግልጽነት ከጎደለው ለተለያዩ ችግሮች ይጋለጣል፡፡ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር መሠረታዊ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ በግልጽ ካልተነጋገሩ የልጆቹ አስተዳደግ ይበላሻል፡፡ የንግድ ተቋማት ከደንበኞቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት በግልጽነት ላይ ካልተመሠረተ አገልግሎታቸው ይስተጓጎላል፣ ለኪሳራ ይዳረጋሉ፡፡ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሥራቸውን በግልጽነት ካላከናወኑ ማኅበረሰቡን ይጎዳሉ፡፡ የትምህርትና የምርምር ተቋማት ግልጽነት ከሌላቸው ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያመዝናል፡፡ ሚዲያው የሕዝብ አመኔታ ካጣ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ ሕዝብና መንግሥትም ግንኙነታቸው በግልጽነት ላይ ካልተመሠረተ በአገር ላይ ችግር ይፈጠራል፡፡ የመንግሥት አንደኛው ኃላፊነት ደግሞ ዜጎችን ማዳመጥ ነው፡፡