በኤሌክትሪክ የሚሠሩ 1,300 የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ አውቶብሶችን ከውጭ አቅራቢዎች በዱቤ ለመግዛት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር መግባባት ላይ መደረሱን፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ኃላፊዎች አስታወቁ፡፡
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን አጠቃቀም በተመለከተ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ፈጠርኩት ባለው ግንዛቤና የሕግ ማሻሻያዎች በርካታ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ መሆኑን የተናገሩት፣ የትራንስፖርት ዘርፍ አገልግሎት ሚኒስትር ደኤታ አቶ በርኦ ሐሰን ናቸው፡፡ በመስከረም ወር የገንዘብ ሚኒስቴር ካደረገው በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች የታክስ ማሻሻያ በኋላ፣ ከ7,000 በላይ ተሽከርካዎች አገር ውስጥ እንደገቡ አቶ በርኦ ገልጸዋል፡፡
ከብሔራዊ ባንክ ጋር የኤሌክትሪክ አውቶብሶች እንዲያስገቡ መግባባት ላይ ተደርሶ እንቅስቃሴዎች እንደተጀመሩ የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ‹‹አውቶቡሶቹን የማስገባት ሒደትና አስመጪዎቹን የማወዳደር ኃላፊነት ለከተማው መስተዳደር ሰጥተን እንዲከታተል አድርገናል፤›› ሲሉ ሒደቱ አልቆ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቀጣይ ኃላፊነቶች እንደሚቀሩ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በቅርቡ 1,300 የኤሌክትሪክ አውቶቡሶች ወደ አገር ቤት ይገባሉ፤›› ብለዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ባቀረበው ከተሽከርካሪዎች የሚለቀቁ የሙቀት አማቂ ጋዞች ልኬትና ቁጥጥር ሥርዓት አፈጻጸም የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኙት የሚኒስቴሩ ኃላፊዎች፣ ታዳሽ ኃይልን በትራንስፖርት ዘርፍ ለማስፋፋት ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የጥረቶቹ ዋነኛ አካልም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ማበረታታት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ሰኞ ጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን ሪፖርት አስመልክተው ላነሷቸው ጥያቄዎች መልስ ከሰጡት ኃላፊዎች መካከል አንዱ የሆኑት ሚኒስትር ደኤታው አቶ በርኦ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ የማስገባት ዕቅድ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የአሥር ዓመት ዕቅድ 48,000 የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ የኤሌክትሪክ አውቶብሶችን፣ በተጨማሪም 148,000 የኤሌክትሪክ አውቶሞቢሎችን አገር ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ነው፡፡ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መሠረተ ልማት ላይም በሰፊው መሥራት የዕቅዱ አካል መሆኑን፣ የግል ባለሀብቶችም በዘርፉ እንዲሳተፉ የማድረግ ሒደት መጀመሩን አስረድተዋል፡፡
የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ይዘንጋው ይታይህ ለቋሚ ኮሚቴው እንዳስረዱት፣ በአሁኑ ጊዜ ሌሎች የሕግ ማዕቀፎችን እየተዘጋጁ ነው፡፡ ‹‹የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ስታንዳርድ፣ የቻርጅ ማድረጊያ ታሪፍ፣ የፈቃድ አሰጣጥ መመርያና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ምቹ ሁኔታ እንዲፈጥሩ እየተዘጋጁ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያና ለሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎች የግሉ ባለሀብት ተሳትፎ ፍላጎት ከአሁኑ እየታየ እንደሆነ ገልጸው፣ ቻርጅ ማድረጊያዎችን በአዲስ አበባና በሌሎች የክልል ከተሞች ለመገንባት ፍላጎት ካሳዩት መካከል በነዳጅ ንግድ ሥራ የተሰማራው ታፍ ኦይል (TAF Oil) ኩባንያ አንደኛው እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ በመውሰድ ጥናት አጥንተው ለገንዘብ ሚኒስቴር በማቅረብ፣ በመስከረም ወር ይፋ የሆነውን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ ማስገቢያ ማሻሻያን እንደፀደቀ አቶ ይዘንጋው ለቋሚ ኮሚቴው ተናግረዋል፡፡ በማሻሻያው መሠረት ሳይገጣጠሙ የሚገቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከማንኛውም ቀረጥ ነፃ ሲደረጉ፣ በከፊል የሚገጣጠሙት ደግሞ አምስት በመቶ የጉምሪክ ቀረጥ ይከፍላሉ፡፡ ሙሉ ለሙሉ ተገጣጥመው ለሚገቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ደግሞ 15 በመቶ ቀረጥ ይከፈላል፡፡
የብዙኃን ትራንስፖርት ዘርፉን በማስፋፋትና ማበረታቻዎችን በማቅረብ በኩል ክፍተቶች እንደነበሩ አቶ በርኦ ተናግረው፣ በሳሎን ታክሲ ላይ ተግባራዊ ተደርጎ የነበረው የቀረጥ ነፃ መብት በአውቶብሶች ላይም እንዲደረግ ጥናት ተሠርቶ ለገንዘብ ሚኒስቴር እንደሚቀርብ ገልጸዋል፡፡
‹‹ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ [ከገንዘብ ሚኒስቴር] ኃላፊዎች ጋር ባደረግነው ንግግር አዎንታዊ ዕይታ እንዳላቸው አረጋግጠናል፤›› ሲሉ አቶ በርኦ አስረድተዋል፡፡