Thursday, November 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሐሰተኛ የብር ኖት ኅትመት የሚሳተፉ የውጭ ዜጎችን መቆጣጠር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመጣው ሐሰተኛ የብር ኖት ኅትመትና ሥርጭት ላይ በብዛት የሚሳተፉ የውጭ ዜጎችን ለመቆጣጠር፣ የፖሊሲ ማዕቀፍ ማሻሻያዎች እንደሚያስፈልጉ ተገለጸ፡፡

በአዲስ አበባ በርካታ የውጭ አገሮች ዜጎች በተለይም የምዕራብ አፍሪካ አገሮች ዜጎች ከፋይናንስ ወንጀል ጋር በተገናኘ በቁጥጥር ሥር ቢውሉም ችግሩ በእስር ብቻ እንደማይፈታና የፖሊሲ ማሻሻያ የሚያስፈልገው መሆኑን፣ በፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት የፋይናንስ ወንጀሎች ትንተና ኃላፊ አቶ ዮናስ ማሞ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጋር በመሆን በሐሰተኛ የብር ኖት ኅትመት ዝውውር ላይ ከወራት በፊት ጥናት ማድረጉን፣ በዚህም በወንጀሉ ላይ በብዛት የሚሳተፉት በርካታ የአፍሪካና የሌሎች አገሮች ዜጎች መሆናቸው ተረጋግጧል ተብሏል፡፡

በውጭ ዜጎች የሚደረገው የሐሰተኛ የብር ኖት ኅትመትና ሥርጭት በየጊዜው እየሰፋ ከመምጠቱ ባሻገር በተጨማሪ፣ የአደገኛ ዕፅ ዝውውር፣ የሞባይል፣ የኢንተርኔት፣ የቪዛ ካርድ ማጨበርበሮችና ሌሎች የፋይናንስ ነክ ወንጀሎች ላይ የሚሳተፉ በርካታ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

ለአብነትም ወንጀል ፈጻሚ ግለሰቦቹ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት በቱሪስት ቪዛ ሲሆን፣ በአብዛኛው በወንጀል ድርጊት የሚሳተፉት የተፈቀደላቸውን የቆይታ ጊዜ የጨረሱና ለሌላ ዓላማ ወደ አገር የገቡ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በቱሪስት ቪዛ ወደ አገር ውስጥ የገቡ የውጭ ዜጎች ጊዜያቸውን ሲጨርሱ ከአገሪቱ መውጣት አለመውጣታቸውን፣ አገሪቱ ውስጥ ከሚገኙት ምን ያህሉ ናቸው ጊዜያቸውን ጨርሰው በተለያየ መንገድ አሳድሰው ወይም በማጭበርበር በአገር ውስጥ የሚገኙት የሚለውን የኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ (ኢሚግሬሽን) መሥራት እንዳለበትና ወይም መስተካከል ያለበት ፖሊሲ ካለም በጥልቀት ታይቶ አስፈላጊው ዕርምጃ መወሰድ እንዳለበት አቶ ዮናስ አስረድተዋል፡፡

በበዓላት መዳረሻ ወቅት የሚደረግ ግብይት ላይ ሐሰተኛ የገንዘብ ዝውውር በስፋት እንደሚስተዋል የሚገለጽ ሲሆን፣ ከሰሞኑም በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ክፍላተ ከተሞች በዓልን በማስታከክ በሐሰተኛ የብር ኖት ግብይት ሲፈጽሙ የተገኙ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል፡፡

የወንጀል ጉዳዮች ትንተና ኃላፊው እንደተናገሩት፣ ሐሰተኛ የገንዘብ ዝውውር ወይም በሐሰተኛ የብር ኖት የሚደረግ ግብይት በበዓላት ወቅት ቢጎላም በማንኛውም ጊዜ እየተፈጸመ ያለ ወንጀል ነው፡፡

ፖሊስን ጨምሮ የብሔራዊ መረጃ ደኅንነት አገልግሎት ከዚህ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የሚያውላቸው ተጠርጣሪዎች እንዳሉ በማስታወስ፣ በተለይ የወንጀል ድርጊት ለመፈጸም በዓላት መልካም አጋጣሚዎች እንደሚሆኑላቸው አቶ ዮናስ አስረድተዋል፡፡

ችግሩ በአዲስ አበባ ከተማ የሰፋ ቢሆንም በሌሎች ከተሞችም መኖሩን የሚናገሩት አቶ ዮናስ፣ በሚዲያ በዚህ ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች አለመሠራታቸው አንደኛው ተፅዕኖ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከወራት በፊት የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጋር ባደረገው ጥናት የተለዩ በርካታ ክፍተቶች እንዳሉ፣ ጉዳዩ በሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች መወሰድ ያለባቸው ዕርምጃዎች ተለይተው የቀረቡ መሆናቸውን፣ የቀረበውን ምክረ ሐሳብ መሠረት በማድረግ የሚገኘውን ውጤት ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ጠቅሰዋል፡፡

ሐሰተኛ የገንዘብ ዝውውር ወይም በሐሰተኛ የብር ኖት የሚደረግ ግብይት ከሚከናወንባቸው ተግባራት ውስጥ ሕገወጥ የሃዋላ አገልግሎት አንዱ መሆኑን ያስረዱት የፋይናንስ ወንጀሎች ትንተና ኃላፊው፣ ሃዋላ ባንክ በመጠቀም ብቻ የሚፈጸም ሳይሆን የገንዘብ ቅብብሉ እጅ በእጅ የሚፈጸም መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም በሕገወጥ ሃዋላ ተሳታፊ የሆነ ግለሰብ የሚኖረው በአዲስ አበባ ከተማ ከሆነ ገንዘቡን ለተላከላቸው ሰዎች ባሉበት ቦታ የሚሰጠው በጥሬ ገንዘብ ሲሆን፣ ለዚህም ምክንያቱ ወደ ባንኮች ቢያመራ ማንነቱ ስለሚመረመርና የሚያስተላልፈው የገንዘብ መጠን ከፍተኛ ስለሚሆን ያንን ለመሸሽ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ በዚህ ሒደትም ሐሰተኛ የብር ኖት ሊሰጥ የሚችልበት ዕድል ሰፊ መሆኑ ተገልጿል፡፡ገንዘቡን የተቀበሉ ሰዎች ሕጋዊ ባልሆነ ሁኔታ ስለተቀበሉ ቢጭበረበሩም ወደ ሕግ ለመምጣት እንደማይደፍሩ ተጠቅሷል፡፡   

እንደ አቶ ዮናስ ገለጻ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ውይይቶችን በማድረግ ፖሊሲዎችን መከለስ፣ ባንኮችም ሐሰተኛ የብር ኖቶች ይዘው የተገኙ ግለሰቦች አካውንት ሲከፍቱ መታወቂያቸውን (የሚያቀርቡትን ሰነድ) በደንብ ማረጋገጥ እንደሚገባቸው፣ ለኅብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨባጫ ሥራዎች መሥራት እንደሚገባና ያ የማይሆን ከሆነ ግን የወንጀል ድርጊቱ የሚቆም አይደለም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች