Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የታኅሳስ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት አኃዝ ባለበት ቀጠለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የታኅሳስ ወር አጠቃላይና የምግብ ዋጋ ግሽበት አኃዝ በሰላሳ ቤቶች ውስጥ እንደቀጠለ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

አገልግሎቱ ይፋ ያደረገው የታኅሳስ ወር የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች ካለፈው ዓመት የታኅሳስ ወር ጋር ሲነፃፀር 32.9 ከመቶ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

የኢትዮጵያ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት በታኅሳስ ወር ከሰላሳ ቤቶቹ ውስጥ ዝቅ አለማለቱ የታወቀ ሲሆን፣ በኅዳር ወር 35.1 ከመቶ የነበረው አኃዝ በተጠናቀቀው የታኅሳስ ወር 33.8 በመቶ ሆኖ መመዝገቡን አገልግሎቱ ይፋ አድርጓል፡፡

ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክስ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲመሳከር የ35.2 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ በልብስና ጫማ፣ የቤት መሥሪያ ዕቃዎች በሆኑት ሲሚንቶ፣ የቤት ክዳን ቆርቆሮ፣ ነዳጅ፣ የቤት ዕቃዎች፣ እንዲሁም ወርቅ ላይ የተስተዋለው የዋጋ ጭማሪ ለዋጋ ግሽበቱ አስተዋፅኦ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡

ላለፉት አራት ዓመታት ባለሁለት አኃዝ ዋጋ ግሽበት ከመመዝገብ አልፎ፣ የዋጋ ግሽበት ላለፉት 12 ወራት ከ30 በመቶ በላይ ሆኖ መቆየቱ የመንግሥት የነጠላ አኃዝ ዕቅድ እንዳይሳካ ማድረጉ እየተገለጸ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለረዥም ጊዜ ሲከተለው የነበረውን የዋጋ ግሽበትን ወደ ነጠላ አኃዝ ለመመለስ የሚደረገው ጥረት የመሳካቱ ዕድል እየተመናመነ በመምጣቱ፣ የመንግሥትን ዕቅድ በድጋሚ ለመከለስ መገደዱ ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ግጭትና በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩክሬንና በሩሲያ መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት፣ የዋጋ ግሽበት ከቁጥጥር ውጪ እንዲሆን አስተዋጽኦ እንዳደረገ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች አስታውቀዋል፡፡

የዋጋ ግሽበት በአገሪቱ ባለሁለት አኃዝ ሆኖ ከተመዘገበ ዘለግ ያሉ ዓመታት መቆጠራቸውን፣ ከዚህ ቀደም የኢኮኖሚክስ አሶሴሽን አዘጋጅነት በተካሄደ የፖሊሲ ውይይት መድረክ ላይ መገለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ በዓለም ላይ ከሚገኙ አገሮች በዋጋ ግሽበት ኢትዮጵያ የመጀመሪዎቹ አሥር ዝርዝር ውስጥ የምትገኝ እንደሆነች፣ በአፍሪካ ደግሞ ከሱዳንና ከዝምባቡዌ በመቀጠል ሦስተኛዋ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ያለባት አገር መሆኗ ተጠቁሞ ነበር፡፡

እንደ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ምክረ ሐሳብ በአገሪቱ አኃዙን የሰፋውን ዋጋ ግሽበትንና መዘዞቹን ለማስወገድ በአምራቹና በሸማቹ መካከል የአቅርቦት ሰንሰለቶችን ማጥበብ አንዱ ዘዴ ሲሆን፣ ይህም በሁለቱ አካላት መካከል እዚህ ግባ የሚባል እሴት ሳይጨምሩ፣ ነገር ግን በርከት ያለ ትርፍ በማጋበስ የምርት ዋጋ እንዲንር ምክንያት የሚሆኑትን ደላሎች ከሒደቱ ለማውጣት የሚረዳ መሆኑን በማስረዳት ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ምርቶችን በአገር ውስጥ በማምረት ከውጭ የሚገቡትን መተካት ዋጋን በማረጋጋት ረገድ ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው በተደጋጋሚ ይገለጻል፡፡ በሌላ በኩል በመንግሥት በኩል በርካታ የውጭ ምንዛሪ ፈሰስ ተደርጎባቸው ከውጭ የሚገቡ፣ ነገር ግን ለኢኮኖሚው ምንም የማይፈይዱ የቅንጦት ምርቶችን በመቀነስ ለምርቶቹ ግዥ የሚውለውን ምንዛሪ ለሌላ አስፈላጊ ዓላማ በማዋል ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ብሎም የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር ይቻላል የሚል መፍትሔ ይቀርባል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች