Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበቅሬታ የታጀበው የወሳኝ ኩነት አገልግሎት

በቅሬታ የታጀበው የወሳኝ ኩነት አገልግሎት

ቀን:

የመዲናዋ ነዋሪዎች ቅሬታ ከሚያነሱባቸው ተቋሞች ውስጥ አንዱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ነው፡፡ የመታወቂያ እድሳት፣ የልደት ሰርተፊኬት፣ የጋብቻ የምስክር ወረቀት በፈለጉት ጊዜ ለማግኘት ያዳገታቸው አገልግሎቱን ለማግኘት እጅ መነሻ እየተጠየቁ መሆኑን የሚናገሩም አሉ፡፡

በየክፍላተ ከተሞች ከሚገኙ የወሳኝ ኩነት ቅርንጫፎች ውስጥ በአግባቡ አገልግሎት የማይሰጡ፣ እጅ መንሻ የሚፈልጉ መኖራቸውን ከሠራተኛ ሥነ ምግባር ጀምሮ አስቸጋሪ መሆኑን የሚገልጹም አሉ፡፡ በተለያዩ ቅርንጫፎች መብራት ጠፍቷል፣ ሲስተም አይሠራም በሚሉና በሌሎች ምክንያቶች ተገልጋዮች ሲስተጓጎሉና በምሬትም ሲናገሩ ይሰማል፡፡

በተለይ በፀጥታ ምክንያት በአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪዎች መታወቂያ መሰጠት ከተቋረጠና በኋላም ከኅዳር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የነዋሪዎች የመታወቂያ እድሳትና ሌሎች አገልግሎቶች ከተጀመሩ በኋላ፣ በሚስተዋሉ ችግሮች ምክንያት ነዋሪዎች ቅሬታ እያቀረቡ ነው፡፡  

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ዓለማየሁ፣ ከባለሙያዎቻቸው ውስጥ የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸው አሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ ሠራተኞች እየተባረሩ ነው፡፡ በቅጣትና በእስር ምክንያት ሠራተኛው ከ50 በመቶ በታች እንዳይሆን ሥጋት አለ፡፡

ኤጀንሲው በአሥራ አንዱም ክፍላተ ከተሞች የሚገኙ ሠራተኞችን ጨምሮ በአጠቃላይ በ56 በመቶ ሠራተኞች ብቻ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በቀናነት አገልግሎቱን የሚሰጡ ባለሙያዎች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ዮናስ፣ ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ችግር የሌለባቸው ባለሙያዎችም በሥጋት እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሕገወጥ አሠራርን በተመለከተ ኤጀንሲው በሐሰተኛ መታወቂያ እንደተቸገረ፣  ማኅበረሰቡ የወረቀት መታወቂያ (የማኑዋል) መስጠት ማቆሙን ማወቅ እንዳለበት፣ እየተሰጠ ያለው የዲጂታል ካርድ ብቻ መሆኑንና ችግሩን ለመቅረፍ የተለያዩ አሠራሮች መዘርጋቱን አስረድተዋል፡፡

መታወቂያ በአቃቂ ቃሊቲ፣ ለሚ ኩራና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍላተ ከተማዎች በሚገኙ 14 ወረዳዎች ለጊዜው እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከነዋሪዎች የሚቀርቡትን ቅሬታዎች ለመፍታት የአሠራር ሥርዓት መዘርጋቱን፣ በፊት የነበረውን መታወቂያ እንደ ገንዘብ ኖት በአዲስ መቀየሩን፣ ካርዶች በደላሎች ቤት ውስጥ መገኘቱን ተከትሎ የቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋቱ ችግሮቹ የጎሉ እንደማይኖሩ ጠቁመዋል፡፡

ከባለሙያዎች ጋር ተመሳጥረው የነዋሪዎች መታወቂያ እንደሚያሰጡ በማስመሰል ሐሰተኛ መታወቂያ እንደሚነገድ፣ በተራ ወረቀት ሐሰተኛ የነዋሪዎች መታወቂያ እየተሠራ ከኤጀንሲው የወጣ ነው ብለው የሚሸጡ ደላሎች መኖራቸውን፣ ለዚህም ከተቋሙ ባለሙያዎች ጋር የተመሳጠሩ ባለሙያዎች መያዛቸውን ጠቁመዋል፡፡

ለሐሰተኛ የነዋሪዎች መታወቂያ ከደንበኞች እስከ 25,000 ብር ድረስ የሚቀበሉ መኖራቸውን በመጠቆም፣ ዜጎች በአቋራጭ መታወቂያ ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት እንዲያቆሙ መክረዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ጊዜ በሕገወጥ መንገድ የሚሠሩ መታወቂያዎች ከኤጀንሲው ውጪ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

ሕገወጥ መታወቂያዎች እንዴት ይገኛሉ?

የመጀመርያው ከኤጀንሲው ውስጥ በሐሰተኛ መንገድ ወጥቶ፣ ኦርጅናል ዶክመንት ሆኖ በአቋራጭ የሚያወጣ መታዊያ መኖሩን አቶ ዮናስ ገልጸዋል፡፡

 ሁለተኛው ደላሎች በተራ ወረቀት የነዋሪዎች መታወቂያ አስመስለው በመሥራት የሚሸጡት ነው፡፡ ሁለቱም ችግሮች በኤጀንሲው መዋቅር ውስጥ መኖሩን የተናገሩት አቶ ዮናስ፣ አሁን ላይ ችግሩ ከሞላ ጎደል መቀነሱን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ የተጠረጠሩትን በአንድ ዶክመንት ሕገወጥ በመሆኑ ብቻ በርካታ ባለሙያዎች ላይ ኤጀንሲው ዕርምጃ መውሰዱንና ካሉት የቅርንጫፍ አመራሮች ውስጥም 72 የጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጆች ከሥራ ገበታቸው መነሳታቸውን ጠቁመዋል፡፡

አሁን ላይ እንደ ከዚህ ቀደሙ በተቋሙ ውስጥ የጎላ ሕገወጥነት እንደሌለ፣ ነገር ግን በተወሰነ ሁኔታ ችግር ሊኖር እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ማኅበረሰቡ በወረዳና በዋና መሥሪያ ቤት ችግሮች ሲገጥሙት ኤጀንሲው ባዘጋጀው 7533 ነፃ የስልክ መስመር በመደወል ቅሬታ ማቅረብ የሚችልበት አሠራር መዘርጋቱን ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ዮናስ፣ በመታወቂያ ዙሪያ አሁን ላይ በጣም ችግር የሆነባቸውና ዋጋ እያስከፈለ ያለው የሕገወጥ ደላሎች መበራከት ነው፡፡ ማኅበረሰቡ በሕገወጥ መታወቂያ ዙሪያ ግንዛቤ አለመኖሩም ይነሳል፡፡

በአሁኑ ወቅት ሰነድ ላይ የሚሠሩ ወንጀሎች እየተራቀቁ በመምጣቸው በመንግሥት ሥርዓት ውስጥ የሚተገበሩ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በተመሳሳይ ሁኔታ በሕገወጦችም እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

ሐሰተኛ ዶክመንት በሚሠሩትና በመንግሥት መካከል የአቅም መገዳደር እኩል እየሆነ በመምጣቱ፣ መንግሥት ለአሠራር የሚመቸውን አዲስ ሥራ ሲሠራ፣ በጎን   ሕገወጦችም ይሠሩታል ብለዋል፡፡

ተቋሙ ከገጠሙት ችግሮች ውስጥ ከዚህ ቀደም ሕገወጥ በመሆናቸው የተሰናበሩ ሠራተኞች የነዋሪዎች መታወቂያ የሚሠሩበትን ካርዶች ደብቀው አስቀምጠው መያዛቸው ይገኙበታል፡፡

ኤጀንሲው አሁን ላይ ችግሮች ያሉባቸውን ባለሙያዎች በመከታተል ላይ እንደሚገኝና በቅርቡ ለሕግ እንደሚያቀርብ ለችግሩ መፍትሔ ይሆናል የተባለ የአሠረር መመርያ መውጣቱን፣ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

ይህ መመርያ ከዚህ ቀደም አገልግሎት ሲሰጥበት የነበረውን የሚተካ መመርያ ሲሆን፣ አገልግሎቱን የተሻለ ለማድረግና አዳዲስ አማራጮች ያካተተም ነው ብለዋል፡፡

የመታወቂያ፣ የልደት፣ የጋብቻና ያላገባ ማስረጃዎች ላይ የሚስተዋለው ሕገወጥነት በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚቀረፍ ለዚህም የወረቀት መታወቂያ የሚሰጡት 14 ወረዳዎች በቅርቡ ወደ ዲጂታል የሚገቡ መሆኑ ማጭበርበሮችና ሕገወጥ አሠራሮችን ለማስቀረት እንደሚያግዝ አክለዋል፡፡

እንደ አቶ ዮናስ፣ ከተማ ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ባለሀብቶች መክፈል ያለባቸውን ከፍለው ማኑዋል መታወቂያ እንዲታደስላቸው እንደሚፈልጉና መስጠት የማይፈልጉ አሉ፡፡

የተገልጋይ ቅሬታዎች መኖራቸውን ነገር ግን የበዛ ጩኸት የሚያሰሙት ዲጂታል እንዳይሆን የሚፈልጉ ሕገወጦች መሆናቸውን በማስታወስ፣ የፍላጎትና የአቅርቦት አለመጣጣም ችግሩን እንዳጎደለው ተናግረዋል፡፡

ወደ ከተማዋ የሚደረገው የዜጎች ፍልሰት የወሳኝ ኩነት አገልግሎቱን በተገቢው መንገድ እንዳይሰጥ ማድረጉን፣ በቀን በአማካይ ከ12,500 እስከ 13,000 ነዋሪዎች አገልግሎት እንደሚገያኙ፣ በአሁኑ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ የወሳኝ ኩነት ጽሕፈት ቤቶች ከዛሬ አሥርና 20 ዓመታት በፊት በነበረው የነዋሪዎች ቁጥር ልክ መሆኑን፣ ገልጸዋል፡፡

አገልግሎትን ማዘመን፣ ሠራተኞንችን መቅጠርና ሌሎችም ክፍተቶች መሙላት ከኢትዮጵያ አቅም ጋር የሚያያዝ ቢሆንም፣ በሒደት የሚስተካከሉ ችግሮች ናቸው ብለዋለ፡፡

ከስድስት ወራት በኋላ ጊዜው ቢያልፍበትም፣ ባያልፍበትም የነዋሪነት መታወቂያ ዲጂታላይዝድ ማድረግ ግዴታ የሚሆን ሲሆን፣ ባንክ፣ መሬት ማኔጅመንትና ሌሎችም ተቋማት ላይ አገልግሎት ለማግኘት ዲጂታል መታወቂያ እንዲጠየቅ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ኤጀንሲው የሚቀርበውን ቅሬታ በሕግ አግባብ መሠረት እየፈታ መሆኑን፣ ከዚህ በኋላ የሚመጡ በርካታ ቅሬታዎችን ለመፍታት እንደሚተጋ አዲስ የተጀመረው የዲጂታል መታወቂያ በሁሉም ወረዳዎች መሰጠት ሲጀምር ሕገወጥነት ችግር እንደሚቃለል ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፍትሕ ቢሮ የወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አብዮት ጅፍራ በበኩላቸው፣ ወሳኝ ኩነትና ምዝገባ ኤጀንሲ በሕገወጥ መታወቂያ ጋር ተያይዞ የላካቸው መረጃዎች አሉ ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በጉለሌ፣ በአቃቂ ቃሊቲና በቦሌ ክፍላተ ከተሞች የወሳኝ ኩነት ጽሕፈት ቤት የተፈጸሙ ወንጀሎች በአራት መዝገብ እየተጣራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በዚህም የፍትሕ አካላት በመታወቂያና መታወቂያ ነክ ጉዳዮች የሚሠሩ ወንጀሎችን ተከታትሎ ለሕግ እንደሚቀርቡ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...