በያሬድ ነጋሽ
የሃይማኖትን ደግ እውነታ መመልከቻው የደጋጎች ልብ ነው፡፡ የማንም ይሁን፣ ሃይማኖት ግን የእውነት፣ የሚዛናዊነት፣ የሥርዓት፣ የስምምነት፣ የሕግ፣ የሥነ ምግባርና የፍትሕ ጽንሰ ሐሳቦች መገኛ ነው፡፡ ነገር ግን ሐሳቦቹ ህልው ሆነው በግዝፈት የምንመለከታቸው፣ ከሰው ልጅ ልብ ሠፍረው፣ ነፀብራቁ ለሚያምንም ይሁን ለማያምንም ደርሶ ስንመለከት ብቻ ነው፡፡ ያኔ መጽሐፍ ቅዱስም ይሁን ቅዱስ ቁርዓን ይዞ ስብከት ላያስፈልግ ይችላል። ምክንያቱም ከሰዎች ልቦና የሚነሱ ማራኪ ነፀብራቆች የማንንም እምነት አምኖ ለመቀበል በቂ የሚሆኑበት በርካታ አጋጣሚዎች ስለሚኖሩ።
ዓምር ኢብኑል ዓስ፣ በዑመር ኢብኑን ኸጧብ (የነብዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) ተከታይ የነበረ ሰሐባ) አስተዳዳሪነት ዘመን በ640 የግብፅ አዛዥ ሆኖ ተሾመ፡፡ ዓምር ኢብኑል ዓስ መስጊድ የመሥራት ዕቅድ በነደፈ ሰዓት ለሥራው ከሚያስፈልገው መሬት ጎን የአንዲት ኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ የሆነችው ሴት የግል ቤት ይገኝ ነበርና ቤቷን ለመግዛት የሚያጓጓ ዋጋም አቀረበላት። ሴትየዋ ግን የቱንም ያህል ገንዘብ ቢቀርብላትም ለመሸጥ አለመስማማቷን ገለጸች፡፡ በመጨረሻ ግን የሙስሊሙን የመስገጃ ቦታ ፍላጎት ከግንዛቤ በማስገባት ለአብዛኛው ማኅበረሰብ ጥቅም ሲባል የሴትየዋን የግል ቤት ወደ መስጊድ ይዞታ አጠቃለለው። ሴትየዋም ውሳኔውን አምርራ አወገዘች። የኦርቶዶክስ ሃይማኖት መነኮሳት፣ ቀሳውስትና ምዕመናን እንዲሁ አወገዙ። አቤቱታ እንድታቀርብም መከሯት፡፡ ኢስላም ለተበዳይ ጥብቅና የመቆሙ ድንበር እስከምን ድረስ እንደሆነ ለማየት ጓጉ።
በዚህ መሠረት መዲና በመሄድ ጉዳዩን ለዑመር ኢብኑል ኸጧብ እንድታሰማ ጎተጎቷት። አብሯት የሚሄድ ሰው፣ ስንቅና መጓጓዣ ካዘጋጁላት በኋላ ወደመዲና ተጓዘች። በዚያ ደርሳ ‹‹የሙስሊሞች መሪ የሆኑት ዑመር ኢብኑል ኸጧብ ቤተ መንግሥት የት አካባቢ ነው?›› ስትል፣ በአቅራቢያዋ ባለው ዛፍ ጥላ ሥር ጫማውን ትራስ አድርጎ የተኛውን ሰው ጠቆሟት። ‹‹እሱ ሙሉ የሶሪያና የዓረብ ባህረ ሰላጤ እንዲሁም ግብፅና ሌሎችንም ሰፊ ግዛት በአመራሩ ሥር ሆነው፣ እራፊ ጨርቅ ከላዩ ላይ በመጣል ጫማውን ትራስ አድርጎ መሬት ላይ የተኛው ሰው እንዴት ሊሆን ይችላል?!›› በማለት ነገሩ አልዋጥላት አለ፡፡ ወደተኛበት ተጠግታ በእግሯ ነካ አደረገችው።
‹‹አንቺ የአላህ ባሪያ ሆይ ምን ልርዳሽ?!›› አላት ከእንቅልፉ ነቅቶ።
‹‹አንተ የሙስሊም መሪ የሆንከው ዑመር ኢብኑል ኸጧብ ነህን?›› ጠየቀች።
“አዎ አላት፡፡
እሱ መሆኑን ማመን እያቃታትም ቢሆን የመጣችበትን ጉዳይ አስረዳችው። የዑመር ፊት ፍም እሳት መሰለ። የቁጣው ስሜት ከፊቱ ላይ ይታያል። ዙሪያውን ቃኘ። በአቅራቢያው የወደቀ የአጥንት ስባሪ ተመለከተ። አነሳውና ከአጥንቱ ላይ ‹‹ከዑመር ኢብኑል ዓስ . . . ቀጥተኛውን ፍኖት በተከተለ ሁሉ ላይ የአላህ ሰላም ይስፈን። . . . ዐምር ኢብኑል ዓስ ሆይ! ፍትሕን በማስፈን የፐርሺያው ንጉሥ ኪስራ ከእኛ የተሻለ ከቶ ሊሆን አይችልም፡፡ ሰላም ባንተ ላይ ይስፈን!›› የሚል አጭር መልዕክቱን በአጥንት ስባሪው ላይ አስፍሮ ለዐምር ኢብኑል ዓስ እንድትሰጠውም ነገራት።
ሴትየዋ በአጥንት የተጻፈው መልዕክት አልገባትም፡፡ የመጣችበት ጉዳይ እንደመከነ ተሰማት፡፡ አጥንቱን ሜዳው ላይ ጥላው ጉዞ ጀመረች። ከኋላዋ የነበረው አብሯት የተጓዘው ሰው ግራ በመጋባት የመጡበትን ዓላማ እንደጣለችው ቢነግራትም ሳትሰማው መንገድ ቀጠለች። የጉዞ ባልደረባዋ ግን ሳታየው ኮሮጆ ውስጥ ከተተው። ግብፅ ስትደርስ በክብር ለተቀበሏት ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ ነገሩን አጫወተቻቸው፡፡ መንገድ ላይ አጥንቱን በመጣሏ ግን በምሬት ተቆጡ። እሷም በቁጭት ታመሰች። ነገር ግን የጉዞ አጋሯ አጥንቱን አውጥቶ በማሳየት አስገረማቸው። ‘የጉዳዩ ባለቤት በዕለተ ዓርብ ከመስጊድ በር ላይ በመቆም ለዐምር ኢብኑል ዓስ አጥንቱ እንዲደርሰው ታድርግ!’ በሚል ተስማሙ።
ዕለቱ ዓርብ ነው። ዐምር ኢብኑል ዓስ ግርማ ሞገስ በተላበሰ አካሄድ ወደ መስጊድ በር እየተጠጋ ሳለ አንድ ሰው እንቅስቃሴውን ገታው፡፡ ከዑመር ኢብል ኸጧብ ለእሱ የተላከ መልዕክት እንዳለና ጉዳዩ በአቅራቢያው ፈንጠር ብላ ስለቆመችው ሴት መሆኑን ነገረው፡፡ ኦርቶዶክሳዊቷም አጥንቱን ሰጠችው። ዐምር መልዕክቱን ሲመለከት ፊቱ በቅፅበት ተለዋወጠ፡፡ ራሱን መቆጣጠር ሰነፈ፡፡ የመስጊዱን ግድግዳ በእጆቹ በመደገፍ መላ ሰውነቱን ይዞ መሬት ላይ ቁጭ አለ። ለተወሰኑ ደቂቃዎች ፀጥ አለ። ኃይሉን አሰባስቦ ቀና በማለት ‹‹የጁሙዐን ሶላት ሰግደን እንደጨረስን መስጊዱን እናፈርሰዋለን። ቤትሽንም በአዲስ መልኩ በመገንባት ወደ ቀድሞ ይዞታው እንመልስልሻለን። ሶላቱን እስከ ምናጠናቅቅ ድረስ ልትታገሺን ትችያለሽ? ነው ወይስ ሶላት ከመስገዳችን በፊት አሁኑኑ መስጊዱ እንዲፈርስ ትፈልጊያለሽ? ምርጫው የአንቺው ነው፡፡ እኔ ትዕዛዙን አስተላልፋለሁ!›› አላት።
እሷና ተከታዮቿ ከዐምር ኢብኑል ዓስ አንደበት የወጣውን ቃል ሲሰሙ ሐውልት መሰሉ፡፡ ከቆሙበት ቦታ አልተነቃነቁም፡፡ ሴትየዋ ከገባችበት ሰመመን ነቃች። ከዐምር ኢብኑል ዓስ ማብራሪያ ከጀለች። ‹‹አሁን ያቀረብከውን ሐሳብ ያገኘኸው በዚህ አጥንት ስባሪ ላይ ከሰፈረው አጭር መልዕክት ነው?›› ብላ በአግራሞት ተውጣም ጠየቀች፡፡ የዐምር ኢብኑል ዓስ ዓይኖቹ ዕንባ አቀረሩ። ጉንጮቹ ድንገት በዕንባ ታጠቡ፡፡ የሚከተለውን ታሪክ ነገራት፦
‹‹በድንቁርና ዘመን እኔና ዑመር ኢብኑል ኸረጧብ ወደ ፐርሺያ ተጉዘን ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረው ንጉሥ ኪስራ ይባላል። በዘመኑ ኃያልና አስፈሪ ንጉሥ ነበር። በለስ ቀንቶን በቤተ መንግሥቱ ቅጥር ክልል አገራዊ ክብረ በዓል መሠረት ያደረገ ዝግጅት ለመታደም በቃን፡፡ ከጠዋት እስከ ማታ የሚዘልቅ ድል ያለ ድግስ ነበር። ሞቅ ብሎ እየሄደ የነበረው ዝግጅት ረፋዱ ላይ ለተወሰነ ሰዓት ተቋረጠ። የፐርሺያውያን የዕደ ጥበብ ውጤት ያረፈበት ረዣዥም ውብ ምንጣፎች ከወለሉ ላይ ተነሱ፡፡ በጎን መግቢያና መውጫ ባለው መተላለፊያ መንገድ አንዲት አሮጊት ከኋላዋ ላም አስከትላ አለፈች። በመውጫው በር እንደወጣች መግቢያውና መውጫው በሮቹ በፍጥነት ተዘጉ። ለፅዳት የተሰማሩት ሰዎች ላሚቱ የጣለችውን ፅዳጅ ከወለሉ ላይ አፀዱ። በሐር የተንቆጠቆጠ ምንጣፍ መልሰው ዘረጉት፡፡ ምንም እንዳልተፈጠረ በሚመስል ሁኔታ ዝግጅቱ ወደ ነበረበት ሙቀት ተመለሰ።
አሮጊቷ ይህንን ተግባር ፀሐይ ከመጥለቋ ቀደም ብሎ ደገመችም። የፅዳት ሠራተኞቹም መንገዱን አፀዱ። ዝግጅቱም ይበልጥ እየጋለ መጣ። ‘ኪስራ እያወቀ፣ ለዚህች አሮጊት ሲባል የዝግጅቱ መቋረጥ ምስጢር ምንድነው?’ ብለን ሰዎች ጠየቅን፣ እነሱም አስረዱን። ኪስራ ቤተ መንግሥቱን ከመገንባቱ በፊት በቦታው ላይ አሮጊቷ ትንሽ ቤት ነበራት። ቤትሽን እንግዛሽ የሚል ጥያቄ ሲያቀርብ ዕምቢ አለች። የሚያጓጓ ዋጋ ቢሰጣት በዕንቢታ ፀናች። ልመናው ሲበዛባት አንድ ሐሳብ አቀረበችለት። ምንም ገንዘብ አልቀበልህም፣ ቤቱን አፍርሰህ ቤተ መንግሥት መገንባት ትችላለህ። ግን የእኔን ፍላጎት የሚያሟላ አንድ ቅድመ ሁኔታ አቀርብልሃለሁ። እሱም ላሜን በፈለግኩት ወቅት ከቤተ መንግሥቱ ጎን ባለው መንገድ ማሳለፍና መመለስ እንድችል ፈቃድህ መኖር አለበት አለችው፡፡ ንጉሡ በሐሳቧ ተስማማ። ለካ አሮጊቷ ዛሬ ድረስ እየተፈጸመላት ያለው ተግባር በንጉሡና በእሷ መካከል ያለው የቃል ውጤት ነበር። ዐመር ኢብኑል ኸጧብም ይህን ታሪካዊ ክስተት በማውሳት በአጥንቱ ስባሪ ላይ ከትቦ የላከልኝ መልዕክት ፍትሕን በማስፈን ኪስራ ከእኛ ከቶም የተሻለ ሊሆን አይችልም! የሚል ነበር። ይኼው ነው ምስጢሩ፤› ብሎ ያሻትን የመወሰን ሥልጣን በእጇ እንዳለ ነገራት።
ውዳቂ የአጥንት ስባሪ ላይ የተከተበች አጭር መልዕክት የግብፅን አገር ገዥ የእምባ ከረጢት አስፈትታ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ላይ እንዲደርስ አቅም ሊኖር እንዴት ቻለ? ትራስና ፍራሽ ከሌለው አንድ መናኛ ሰው የተላከ መልዕክት ግርማ ሞገሱ የሚያስፈራውን የዐምር ኢብኑል ዓስ ልብ እንዴት ሊረታ ቻለ? በሴትየዋ አዕምሮ ተመላለሱ። ለዐምር ኢብኑል ዓስ ደፋር ጥያቄ አቀረበችለት።
‹‹ለመሆኑ ኢስላም ማለት ይህ ነው?›› ጠየቀች።
ዐምር ኢብኑል ዓስ ራሱን በአዎንታ ነቀነቀ። ሴትየዋ ደግሞ ደፋር ውሳኔ ወሰነች። ቤቷን ሙሉ ለሙሉ ለመስጊዱ ለገሰች፡፡ እስልምናንም ተቀበለች፡፡
* * *
በዚህ መልኩ ክርስትና ልባቸውን ነክቷቸው ክርስቲያን የሆኑ ሙስሊሞችንም ታሪክ ማንሳት ይቻላል። ሆኖም የዚህ አንቀጽ ዝግጅት ዓላማው ከዚህ ያልፋል። ከላይ ባየነው ታሪክ ውስጥ ለመስጊድ ሲባል የክርስቲያን ቤት ፈረሰ የሚለውን ብቻ በተናጥል በመውሰድ ‹‹የግብፁ ሙስሊም ንጉሥ በክርስቲያኖች ላይ የፈጸመው በደል›› የሚል ሐሳብ የሚሰጥ ይኖራል። ‹‹የኢትዮጵያ ክርስቲያን ንጉሥ በሙስሊሙ ላይ ያደረሰውን ማን በነገረህ!›› የሚል መሟገቻውን የሚያቀርብም አይጠፋም። አሁንም የአንቀጹ ዝግጅት ዓላማ ከዚህ ይልቃል። ከላይ ባየነው የታሪኩ አንድ ክፍል ተገርመን ወደ ቀጣዩ እንሸጋገራለን፡፡ ‹‹የፐርሺያው ንጉሥ ከእኛ ሊበልጥ አይችልም፤›› ማለት፣ ለሞተው ክርስቲያን ይሁን ሙስሊም፣ ለተቃጠለውም ቤተ ክርስቲያን ይሁን መስጊድ መልስ ለመስጠት ከእነሱ አላንስም የሚል አስተሳሰብ እንዳለ ሁሉ፣ በደግነት ከእኔ እነሱ አይበልጡም፣ ላደረጉት አንድ ደግነት (የደጉን ዘመን ቆጥሮ)፣ ስድስት እጥፍ እከፍላቸዋለሁ ብሎ መፎካከርም አለ ለካ? ይገርማል!
የሰው ልጅን የሚያገፋፋው ንፍገት እንጂ ክብር፣ ፍቅር፣ ፍትሐዊነት፣ ሌሎች የሃይማኖትና የፈጣሪ ትዕዛዛት ነፀብራቅ ከልባችን ወጥቶ ለዓለም ቢበራ ለአምልኮ ሥፍራ የሚሆን ቦታ ለመለገስ ቤቱን አፍርሶ፣ እርሻውን ገምሶ ለመስጠት ይቅርና ልቡን አፍርሶ የሚሰጥ በሽ ነበር። ይህቺ ሴት በኢስላም ተማርካ ቤቷን ይቅርና የክርስቶስ ቤተ መቅደስ የሆነውን ልቧን አላፈረሰችም?። መነፋፈግ ሆኖ እንጂ ለአምልኮ ቦታ ግንባታ በሚል የሰው መኖሪያ ቤት ቢፈርስም፣ ለፍትሕ ሲባል መስጊድ ፈርሶ የክርስቲያኒቱ ባልቴት ቤት ሊገነባ አልነበረም? የመንግሥት ግብዝነት፣ የሃይማኖት መሪና አገር ሽማግሌ አድር ባይነት ገኖ እንጂ፣ በኃይሉ የበረታ አገረ ገዥ ከምስኪን የሃይማኖት አባትና የአገር ሽማግሌ በአጥንት ስባሪ ‹‹እያደረክ ያለው ነገር ፍትሐዊ አይደለምና አድም›› ቢለው በፀፀት ሲንበረከክ፣ ፍትሕን ለማስፈን ሲሽቀዳደም አላየንም? ‹‹መንግሥት ሆይ ቀንበርህን ከሕዝብ ላይ አንሳ›› የሚል የሃይማኖት አባት ወይም የአገር ሽማግሌ ብናይ ወይም ተግሳፁ የሚያስደነግጠው አገረ ገዥ ቢኖር ችግራችን ከቁጥጥር ውጪ ይሆን ነበርን? ችግራችን አንድም የሕዝብ ለሕዝብ ንፍገት፣ ሁለት የሃይማኖት መሪም ይሁን የአገር ሽማግሌ አድርባይነት፣ ሦስት የፖለቲከኛ ለፖለቲከኛ ግብዝነት አይደለምን?
ወደ ቀጣዩ የአንቀጹ ሐሳብ እንሻገር፡፡ የነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) ተከታይ የሆኑት ዑመር ኢብኑል ኸጣብ በመባል የሚታወቁት ሶሐባና ፃድቁ አቡነ ዘርዓ ብሩክ በአንድ የታሪክ ውርሰ ድግምግሞሽ አንፅረን ልናያቸው ወደድን፡፡ ዑመር ኢብኑል ኸጣብ የተወለዱት በ585 በመካ ነው፣ ያውም ታላቅ የሙስሊም መሪ፡፡ ፃድቁ አቡነ ዘርዓ ብሩክ የተወለዱት ከክርስቶስ ልደት በኋላ በስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ በነሐሴ 27 ቀን ያውም የኦርቶዶክስ ትልቅ ፃድቅ። ምን አገናኛቸው? ልንል እንችላለን። በፈጣሪ በመታበይ በዓባይ ወይም በናይል ወንዝ ላይ የፈጸሙት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽ የሆነ ገቢራቸው በአንድነት እንድናነሳቸው አስገድዶናል።
‘ኢብኑል ዓስ ግብፅን የተቆጣጠረው በ642 (20ኛው ዓሒጅራ) ነው’ ይላሉ። የግብፅ ነዋሪዎች ናይል ወንዝ እንዳይደርቅ ልጃገረድ ለወንዙ የመሰዋት ልምድ እንዳላቸውና በዚህ መሠረት እንዲፈቅድላቸው ጠየቁት። እሱም ይህ ዓይነት ዘግናኝ ድርጊት አልፈቅድም፡፡ ኋላ ቀርነትና ጭካኔ የተሞላበትን ድርጊት ሴት ልጅን፣ ያውም ከእነ ሕይወቷ ወደ ወንዝ እንድትወረውሩ እንዴት እፈቅዳለሁ? እንዲህ ያለ አረመኔያዊ ድርጊት ኢስላም አይፈቅድም፡፡ ኢስላም ሴት ልጅ ከእንዲህ ዓይነት የባርነት ቀንበር ነፃ ሊያወጣት መብቷን ሊጠብቅላት ያዛል በማለት አይሆንም አላቸው። አጋጣሚ ሆኖ በዚያው ዓመት የዓባይ የውኃ መጠኑ ከመቀነሱ የተነሳ አካባቢውን ድርቅ ቢጤ አንዣቦበት የአገሩ ሕዝብ ለመሰደድ በዝግጅት ላይ እያለ ኢብኑል ዓስ ሁኔታውን አብራርቶ ለዑመር ኢብኑል ኸጣብ ጻፈለት። ኸሊፋውም በምላሹ ለወንዙ ደብዳቤ ጽፈው ወደ ናይል ወንዝ እንዲጣል አዘዙ።
ደብዳቤው እንዲህ ይላል
‘የአላህ አገልጋይና የሙስሊሞች መሪ ከሆነው ከዑመር፣ ለግብፁ የናይል ወንዝ፣ ናይል ሆይ ከራስህ ፍላጎት የምትፈስ ከሆነ አንፈልግህም። በአላህ ትዕዛዝ የምትፈስ ከሆነ ደግሞ ፍሰትህን ቀጣይ ያደርግ ዘንድ ለእሱ (ለአላህ) ዱዓ እናደርጋለን።’ ደብዳቤው ለወንዙ ተሰጠው ወይም ወደ ወንዙ ተጣለ። ውኃውም በዚያው ዓመት ተትረፍርፎ ፈሰሰ ይላል ‹‹ዓባይ በኢስላም›› በሼህ ሙሐመድ ኢብራሂም 2012፡፡ (ይህንን ጉዳይ በሳይንስም ይሁን በሥጋዊ ነሻጣ ልመርምርህ እንዳንለው ያወሳዋል)።
‹‹ፃድቁ አቡነ ዘርዓ ብሩክ የፅድቅ አገልግሎት ከኢትዮጵያም አልፎ ግብፅ ድረስ የደረሰ ነበር። ከአሌክሳንድሪያ ተመልሶ ወደ አገሩ መጣ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተመላለሰ ወንጌልን አስተማረ። እጅግ ሥጋን በሚያስጨንቅ ትጋትም የኢትዮጵያን ሕዝብ ማርልኝ እያለ እያለቀሰ ይፀልይ ነበር። አንድ ቀን አባታችን በንጉሥ ወታደሮች ተይዘው ሲሄዱ ዳዊታቸውን ለግዮን ወንዝ (ዓባይ) አደራ ሰጥተውት ከአምስት ዓመታት በኋላ ሲመለሱ ግዮን ሆይ ዳዊቴን ግሺ (መልሺልኝ) ቢሏት አንድም የውኃ ጠብታ ሳይኖርባት ዳዊታቸውን ብትመልስላቸው ለደቀ መዝሙራቸው ዘሩፋኤል አሳዩትና ግዮንንም “ግሽ ዓባይ” ብለውታል። እስካሁንም በዚሁ ስም የሚጠራው ከዚህ በመነሳት ነው፤›› ይላል ‹‹አትሮንስ ዘተዋሕዶ›› በመምህር ቀሲስ ንጋቱ አበበ (ይህንንም ጉዳይ በሳይንስም ይሁን በሥጋዊ ተመስጦ ልመርምርህ እንዳንለው ያወሳዋል)።
በጣምራ አዛምደን ልናነሳው የወደድነው፣ በዓባይ መድረሻ ሜዲትራንያንና ከመነሻው ሰከላ ላይ፣ በአላህና በእግዚአብሔር ክንድ የተማመኑና በዕዝነቱ የተማፀኑ ብፁዓን የፈጸሙትን ገድል ነበር። ዓባይን ዳዊቱን ይዞ የሚመለከተው እንዳለ ሁሉ፣ ኪታቡን ይዞ የሚመለከተውም አለ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኦሪቱ፣ በነቢያት ዘመን፣ በሐዲሱ፣ በሐዋርያት ዘመን ያለሁ፣ በአገሪቱ የጭንቅ፣ የረሃብ፣ የስደት ዘመን አብሬ ተርቤ፣ አብሬ ተሰድጄ፣ በወረራው አብሬ ዘመቼ፣ . . . እያለች መናገሯና መሰነዷ፣ የመውደቅና የመነሳቷን ታሪክ ለትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ ስለነበረባት እንጂ፣ ‹‹ማንም ከእኔ ውጪ አልነበረም፣ ዛሬም ማንም የለም፣ ነገም እንዲሁ›› ማለቷ ግን አልነበረም። ሲከፋት ወረቀት ላይ ቃል አስፍሮ ቀብሯን ለማስፈጸም ቀን፣ ወርና ዓመታት የሠፈረበት በራሪ ወረቀት ሲበተን ስትመለከት ‹‹በአስተማርኩት ፊደል፣ በቀመርኩት የጊዜ ቀመር ቀብሬን?›› በሚል ማስታወሷ ሌሎቻችን ላይ ለመታበይ ሳይሆን፣ የበደለችው ነገር እንደሌለ እውነቷን ማስቀመጧ ነበር (ሙስሊም ሆነ ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን እንዲሁ፣ በዓረቡ ዓለም በኢትዮጵያን ላይ የሚደርሰው ያልተገባ ግፍ [በአሸባሪ ቡድን በሃይማኖታቸው ሳቢያ አንገታቸውን የተቀሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ያስታውሷል]፣ ኢትዮጵያ ዛሬ በዓለም በእጅጉ በዝቶ ለምናየው እስልምና፣ ቁጥሩ ውስን የነበረውን አማኝ ታቅፋ ያቆየች ባንክ ቤት ናት [ኢትዮጵያ ባትኖር እስልምና አይስፋፋም የሚል መደምደሚያ ለመስጠት አልሞከርንም]። ኢትዮጵያ ኢስላም በዓለም በርክቶ ለመታየቱ ወይም ለእምነቱ ፀር ብትሆን አያቶቻችን ለምን ሶሐባዎቹን ፊት አልነሱም? ልንል፣ ልንሟገት፣ ምንድነው ያጠፋነው? ብለን ልንጠይቅ ተገቢነት አለው።
የኢማም አሕመድ ኢብራሂምም (ግራኝም) – የአዳል ንጉሥ እና የንጉሥ ሐሰን ኢንጃሞን (የቀድሞ የጉራጌ ማለትም የጉራጌና ሥልጤ ንጉሥ) ዘመን ቤተ ክርስቲያኗ የጭንቄ ጊዜ ብላ ታነሳዋለችና ‹‹የኢትዮጵያ ክርስቲያን ነገሥታት በሙስሊም ማኅበረሰቡ ላይ ያደረሱት በደል፤›› በሚል ከተጨባጭ መረጃ ጋር ሰንዶ መያዙ በኢትዮጵያ የኢስላም ቤተ እምነት ውስጥ የመውጣትና የመውደቅ ዘመኑን የመሰነድ ግዴታ ሆኖ መቅረብ ይችላል፡፡ የሁለቱንም ቤተ እምነቶች የፈተና ወቅት ቤተ መጻሕፍት መገኘታቸው ጉዳት የለውም። ነገር ግን ‹‹ዓባይ በኢስላም›› በሚል በሼህ ሙሐመድ ኢብራሂም የተጻፈችው መጽሐፍ ትልቅ ትርጉም ያላትና ላለንበት ወቅት አርዓያ በሆነ መልኩ መነሳት የምትችል ናት። ዓባይን በክርስትና ዓይን ብቻ ሳይሆን፣ በኢስላምም ጭምር እንድንመለከተውና ከሶሐባ ዑመር ኢብኑል ኸጣብ እና ከፃድቁ አቡነ ዘርዓ ብሩክ ወገን ሆነን ያለመነጣጠል በጥንድ ሊታዩ በሚችል መልኩ ማስቀመጥ እንዲቀለን አስችሏል።
በቀጣይም ቢሆን የሙስሊሙ ማኅበረሰብ፣ ዘመን ሠፍሮና ቆጥሮ በተመሳሳይ ሜዳ ተመሳሳይ ትርጉም ላለው ዓላማ ለአገሩ የተዋደቀበት፣ የኢትዮጵያን ሕማማት አብሮ የታመመበት፣ የአገሪቱን ወረራ ዘምቶ የቀለበሰበት፣ ስደት መከራውን አብሮ ያሳለፈበት በርካታ የታሪክ ምዕራፍ በእጃችን ነውና ያንን ታሪክ መምዘዝና መሰነድ፣ ተራራውና ወንዙን ኢስላም ተራምዶበት የሰጠውን ትርጉም ማውሳት (ንጥቂያ እንዳይመስል ጥንቃቄ ይሻል)፣ ከመድረሳው ትምህርት ቤት ወጥተው ለአገሪቷ ውለታ ስለዋሉላት ልጆቿ፣ በጦር ስለተሰዉ ሙስሊም ጄኔራሎች መዘከርና ‹‹እኔ የሌለሁበት የት ነው? እኛም እናንተም አብረን አልነበርን? ኑ እንዋቀስ!›› ማለት በሚያስችል መልኩ ማስቀመጥ ይገባዋል። ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ይህንን ሲያደርግ ደግሞ ታሪኩን መሰነዱ እንጂ ‹‹ከእኔ ውጪ ሌላ የለም›› እያለ አለመሆኑን ሌሎቻችን መገንዘብ ይገባናል።
ዛሬ ላይ የዘመኑ ወጣቶች፣ ደራስያን፣ ሰባክያንና የሕዝብ አስተዳዳሪዎች፣ ይህንን የሁለቱ ቤተ እምነቶች ሰነድ ማዋረስ፣ ማዛመድ፣ አንዱ ከአንዱ ተነጥሎ የማይታይ ወይም አገሪቱን በሁለት ገጽና ከዚያ በላይ የምትታይ መሆኗን ማስረገጥና ‹‹ነጥለን ልናይ ከሞከርን ተቃርኖው ያይላል›› ልንል ይገባል፡፡ ነጥሎ ለማየት በመሞከራችን የተፈጠረውን ትልቁን ተቃርኖ እንመልከተው።
‹‹ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት›› የሚል ወገን ለመነሳቱ መነሻ ምክንያት፣ ‹‹በአገሬ አገሬው እንዳልሆንኩ ተቆጥሬያለሁ፣ መብቴ ተገፎ፣ ከዜጋ በታች ታይቻለሁ፤›› የሚል አብዛኛውን የሙስሊም ማኅበረሰብ የሚወክል ሐሳብ መነሳቱ እንዳለ ሆኖ፣ ለመፍትሔ እንቅስቃሴው፣ እንደ ዜጋ መብቴን አስከብራለሁ ብሎ ተቀባይነት ያለው ሐሳብ ይዞ የተነሳ እንዳለ ሁሉ (ይህንን ሐሳብ ለመደገፍ ሙስሊም መሆን አይጠይቅም)፣ ከመብት መጋራት ይልቅ፣ ያበደሩኝን ጨምሬ እከፍላለሁ የሚል ወገን ተነስቶ፣ ንጥቂያ የሚመስልና ነገ ደግሞ ክርስቲያኑ ተነስቶ ‹‹በሙስሊሙ ተረግጫለሁ›› በሚል በቀል የሚያስታጥቀውና በበቀል እንዲነሳ የሚያደርግ እንቅስቃሴ ማቆጥቆጡን በተጨባጭ መመልከት በመቻሉና ክርስቲያን በአገሩ የመኖር መፃኢ ዕድል ሥጋት ውስጥ መጣል በመጀመሩ ነበር (በደሉኝ የሚለውን ንጉሥ ከማኅበረሰብ ለይቶ ማየት ያልቻለ ይህ የጥቂቶች ሐሳብ በፕሮፖዛል ደረጃ ረቂቅ ተዘጋጅቶለት፣ ሰንደቅ ዓላማው ላይ ሳይቀር ጨረቃና ኮከብ ታትሞበት [በአሁን ጊዜ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወጣቶች ዘንድ የጥምቀት በዓል አከባበር ላይ የተለያዩ ዓርማዎች በሰንደቅ ዓላማ ላይ ታትመው እየተመለከትን ነው] እና ለተግባራዊነቱ በመንግሥታዊ የኃላፊነት ደረጃ ያሉ አንዳንድ ግለሰቦች ሳይቀር ተሳታፊ መሆናቸውን፣ መረጃው ክርስቲያኑ እጅ ድረስ ደርሶ ተመልክቷል)። ሥጋቱ ተጨማሪ ጡዘትን አስከተለ። ክርስቲያኑ ለሙስሊሙ ‹‹እኔ ነኝ በአገሬ እንግዳ አድርጌ የተቀበልኩህ!›› ይለው ጀመር። አሁንም ጉዳዩን በጉልህ አንጥሮ በመመልከት ‹‹እንግዶቹ የውጭ ዜጎች እንጂ እኔ ኢትዮጵያዊው አይደለሁም፣ የውጭ እንግዶቹንም የተቀበልካቸው አንተ ሳትሆን የእኔና የአንተ አባቶች ናቸው፤›› ማለትና መጋፈጥ ቢገባውም፣ ከዚህ ይልቅ ተገፍቻለሁ ከሚለው አስተሳሰብ ላይ ተጨማሪ ባይተዋርነት ያደረበት በመፈጠሩ፣ በመስጊድ ጉባዔ ላይ፣ ያውም በግልጽ ኢስላማዊ መንግሥት እስኪመሠረት ድረስ እንደሚዋደቅ የሚሰብክ ኡስታዝ ብቅ አለ። በቤተ ክርስቲያኖች ዓውደ ምሕረት ላይ ‹‹በቅዱሳኑ ምድር ይህ ሲፈጸም ከምመለከት አንገቴን እሰጣለሁ፤›› የሚል ሰባኬ ወንጌል ተመለከትን፡፡ የኢኮኖሚ የበላይነቱ ሹክቻውና መንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር መጣሩ አየለ (ይህንን ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ ባንገባበትም፣ ሽኩቻው ከዘመናዊ የንግድ ሥርዓትም ይሁን ከሃይማኖት ጽንሰ ሐሳብ ጋር በፅኑ የሚጣረስ መሆኑን ያወሳዋል)።
መንግሥት ደግሞ ነገሩን ከማብረድ ይልቅ ወደፊት ያለ እክል ለመገስገስ የሚያስችል ምቹ ሰጋር አድርጎ ሲሠፍርበት መመልከታችን፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ጆሮ ተከልክለው፣ በጉብዝና ወቅታቸው ላይ የሚገኙ አፍላዎች (በሃይማኖትና በዘመናዊ ትምህርት የላቁትን ጨምሮ) ጋሻውን ከተሰቀለበት አውርደው አቧራውን ሲያራግፉ፣ ጦሩን ሲስሉ፣ የበጀት ድጋፍ ሲያደርጉ መመልከታችን ደግሞ፣ ጉዳዩ ሃይ ባይ ያጣ እየሆነ ለመምጣቱ ጉልህ ምስክር መሆን ቻለ። ቀጣዩን ማወቅ የሚሻ ቢኖር፣ ከዚህ እልፍ ካለ በመደበኛ የጦርነት ሕግ የማይዳኝ፣ ባለኝ ሀብትና የሰው ቁጥር ድል እመታለሁ የማይሉት፣ ሚሊዮኖችን የሚቀጥፍ፣ እናትና አባቱን ከእነ ወንድሞቹ ያጣ ጨቅላ፣ ባሏን ከእነ ልጆቿ ያጣችን እናት ለቅሶ ለማስቆም በሚያዳግት መልኩ የሚበራከትበት፣ ለዛሬ ግጭት ለነገ ግን ቁጭት የሚሆንና ማናችንንም ቢሆን አላስፈላጊ ታሪካዊ ውርደት ውስጥ የሚያሸጋግረን እንደሆነ አበክራለሁ (‹‹የክርስቲያን ደሴት ወይም ኢስላማዊ መንግሥት›› ሲባል ያልደነገጡና መፍትሔውም ይህ እንዳልሆነ የሚያምኑ በርካታ ሚሊዮኖች ከሁለቱም ወገን እንዳሉ ያስታውሷል)።
መፍትሔው የሚሆነው የተቃርኖው መነሻ እምነቶቻችን ሳይሆኑ፣ ንፁህ አስተምህሮታችን በልባችን ነጥሮ ለሌሎቻችን መታየት ከመቻሉ ይልቅ፣ መነፋፈጋችን ከመበርታቱ የመነጨ መሆኑን ተረድተን፣ የዓባይ መነሻ ላይ የአቡነ ዘርዓ ቡሩክ ገድል የሚዘክር እንዳለ ሁሉ፣ በመድረሳው ዑመር ኢብኑን ኸረጧብ የሚያነሳ መኖሩን አምነን ወይም ሁለቱ ቤተ እምነቶች ወድቀው ያልተነሱበት የኢትዮጵያ ምድር እንደሌለና አንዱ ባዳ ሆኖ የሚኖርበትና አንዱ ለአንዱ የመኖር ሥጋት ሆኖ የቀረበበት ምዕራፍ ተዘግቶ፣ ኢትዮጵያን ከተናጠል ይልቅ በጣምራ፣ ከመዘርዘር ይልቅ በማሰናሰል፣ ከልዩነት ይልቅ በአንድነት የሚያወሱ ሰነዶች ከተጨባጭ ማመሳከሪያ መረጃዎች ጋር በማዘጋጀት፣ ለሕዝብ ተደራሽ ማድረግ ይገባናል። ለመፍትሔው መሳካት የዘመኑ ወጣቶች፣ ደራስያን፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት ሰባኪያንና የአገር ሽማግሌዎችን ደልዳላ ጫንቃ ይፈልጋል። ሚዲያ የማስተጋባቱን ድርሻ በሁለተኛነት ይወስድና ሦስተኛ ቢሆንም፣ ነገር ግን ዋነኛው ሁሉን ጠቅልሎ የማስተባበሩ ሚናና አደረጃጀታችን ከሕግ በታች እንዲያድር የማድረጉ ተግባርና ዕውቀቱ አቅሙ ያለውና ልሳን ከተግባር ያዋሀደ ልበ ቀና የአገር አስተዳዳሪን ይሻል።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው habeshaw2022@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡