Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ብዙ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች እንደሚፈጠሩ እምነታችን ነው›› ፍፁም አረጋ (አምባሳደር)፣ በካናዳ  የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር

ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለውጥ ከመጣ በኋላ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን እንደመጡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር፣ ቀጥሎም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ (ቺፍ ኦፍ ስታፍ)፣ ከዚያም በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ለሦስት ዓመታት ሲያገለግሉ ቆይተው፣ ከ2014 ዓ.ም. ወዲህ በካናዳ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው እያለገሉ የሚገኙት ፍፁም አረጋ (አምባሳደር) ናቸው፡፡ ሲሳይ ሳህሉ  በኢትዮጵያ ላይ ስሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች፣ ስለዲፕሎማቲክ እንቅስቃሴዎችና ስለዳያስፖራው ሚና፣ እንዲሁም በኢትዮጵያና በካናዳ መካከል ስላለው የንግድና የኢንቨስትመንት ሁኔታ ከእሳቸው ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- በዲፕሎማሲ ተልዕኮ መሳተፍ የጀመሩት አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ወደ አሜሪካ፣ በኋላም የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እየተካሄደ በነበረበት ወቅት ወደ ካናዳ አቀኑ፡፡ የዲፕሎማቲክ ተልዕኮውን እንዴት አገኙት?

አምባሳደር ፍፁም፡- አመሠግናለሁ፡፡ እንግዲህ ይህንን ቃለ መጠይቅ እያደረግሁ ያለሁት በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የሰላም ስምምነት በተፈረመበት፣ ውጤቱም አበረታች የሚባል ሒደት ላይ በሆነበትና የሰላም ትሩፋቶችን እየሰማንና እያየን ባለንበት ወቅት በመሆኑ መገናኘታችንን ልዩ ያደርገዋል፡፡ እንግዲህ እኔ ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ፣ ከዚያም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ከሚያዝያ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ  የጠቅላይ ሚኒስትሩ የልዩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ (ቺፍ ኦፍ ስታፍ) በመሆን አገልግያለሁ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ያው ቀደም ሲል የምንመኘው ለውጥ በአገራችን ዕውን እንዲሆን በሙሉ ልቤ ስደግፍ ቆይቻለሁ፡፡ በዚህም በተሰጠኝ ኃላፊነት የመጀመርያዎቹን የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ጥቂት ወራት ትልልቅ ለውጦች ሲካሄዱ በቅርብ ተገኝቼ የመመስከር ዕድል አጋጥሞኛል፣ በለውጦቹ ውስጥም አልፌያለሁ፡፡ እናም በቅርብ ሆኜ የተረዳሁት ኢትዮጵያ በጣም ትልቅ ዕድል ያላት፣ ግን ደግሞ ያን ዕድል በተለያዩ ምክንያቶች ማሳደግ ያልቻልንበት ሁኔታ ነበር፡፡ ዕድል ሲባል የተማረ የሰው ኃይልና የተፈጥሮ ሀብት ያላት የታሪክ ባለቤት ነች፡፡ ምንም እንኳ የካፒታል እጥረት ቢኖርባትም ለመነሻ የሚሆን ግን ማጣት አትችልም፡፡ እነዚህን አቀናጅቶና የውጭውን አሰባስቦ ትልቅ ሀብት በመፍጠር ፈጥና ማደግ የምትችል ዕድል ያላት አገር ሆና ሳለ ያንን እንዳንጠቀምበት፣ ከውጭ በብድርና በድጋፍ የሚገኘውን አካቶ ፈጥና ማደግ የምትችል አገር ሆና ሳለ በራሳችን የአስተሳሰብ እንቅፋት ውስጥ በመዳከር ጊዜያችንን ያባከንን ነበርን፡፡ ለውጡ ይህንን ችግር የሚቀይር እንደነበነር በቅርብ ሆኜ ተመልክቻለሁ። የፖለቲካ ለውጥ፣ እንደ አገር የማሰብ ለውጥና አካታች የሆነ ለውጥ የማምጣት እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡

ለውጡ በተደጋጋሚ ሲጠየቁ የነበሩ የፖለቲካ ምኅዳር የማስፋት፣ በተለይ የታገዱ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሚዲያዎች አካታችነትን በተመለከተ ምላሽ የሰጠ ነው፡፡  አላሠራ ያሉ የምርጫና መሰል መሠረታዊ ሕጎች እንዲሻሻሉ ወይም እንዲቀየሩ በመደረጋቸው፣ በዚህም የተነሳ በስደት የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገር ቤት ተመልሰው እንዲሳተፉ ዕድል ያገኙበት ሁኔታ ስለነበር በዕድሜያችን እናያቸዋለን ብለን የማንጠብቃቸው ሁኔታዎችን ዓይቻለሁ። በአገር ውስጥ በኃላፊነት የተሰጡኝ ሥራዎችን በማከናወን፣ እንዲሁም የውጭውንም ኃላፊነት በተሰጠኝ ተልዕኮ ልክ ለመሥራት በሙሉ ልቤ ተንቀሳቅሻለሁ፡፡ በዚህም የቦታ ለውጥ እንጂ በውስጤ የነበረው አገርን የማገልገል ፍላጎትና ጥረት ምንጊዜም በውስጤ እየተቀጣጠለ ነበር፡፡ ስለዚህ አቅሜ በፈቀደው መጠን ሌሎችን አስተባብሬ በውጭ አገር ዳያስፖራውን በጋራ በማንቀሳቀስ፣ ለአገራዊ ለውጡ ለአገራችን መልካም ነገር ለማድረግ ነው ስሠራ የነበረው፡፡ ልዩነቱ የቦታ መቀያየርና የተልዕኮ ልዩነት ካልሆነ በቀር፣ አገርን የማገልገል ጉዳይ ስለሆነ በየትኛውም መንገድ በደስታና በሙሉ ፍላጎት ነበር ስሠራ የቆየሁት፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ በፊት በነበሩበት አሜሪካና አሁን ባሉበት ካናዳ ያለው የዳያስፖራው ማኅበረሰብ ተሳትፎ  ምን ይመስላል? በተለይ አገር የተቸገረችበትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመፍታትና የሠለጠነ የሰው ኃይል ወደ አገር ቤት ለማምጣትና በልማት ለማሳተፍ ያለው ተነሳሽነትስ እንዴት ይገለጻል?

አምባሳደር ፍፁም፡- የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገሩን ይወዳል። በቻለው ሁሉ ለመደገፍም ይሞክራል። ነገር ግን ሁሉም ዳያስፖራ አንድ ዓይነት አይደለም፡፡ አንዳንዱ ዳያስፖራ በትምህርት የገፋና ሻል ያለ ገቢ ያለው ሲሆን፣ አንዳንዱ ደግሞ ከዚህ የተለየ ነው። አንዳንዱ ኑሮውን እዚያው በመግፋት በርቀት ለመርዳት የሚሞክር ሲሆን፣ አንዳንዱ ደግሞ ጠቅልሎ በመግባት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት ወይም መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በመክፈት በትምህርት፣ በጤና ወይም በሌላ ማኅበራዊ ችግሮችን በሚቀርፍ ዘርፍ ለመሰማራት የወሰነ ነው፡፡ ስለሆነም ካላበት ሆኖ የሚረዳውም ካለበት እንዲረዳ፣ ጠቅልሎ ለመግባት የሚፈልገውም ይህንኑ ምኞቱ እንዲሳካ የበኩላችንን ድጋፍ ስናደርግ ቆይተናል። ይህንኑ አጠናክረን የምንደግፍም ይሆናል። ለምሳሌ ካሉበት ሆነው በውጭ ምንዛሪ የባንክ አካውንት ለመክፈት ለሚፈልጉ ይህንኑ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ እየተመላለሱም ሆነ ጠቅልለው በመምጣት በመረጡት ዘርፍ ለመሳተፍ ለሚፈልጉትም ተገቢውን ድጋፍ እናደርጋለን። ኑሯቸውን በዚያው አድርገው ዘመዶቻቸውን መርዳት የሚፈልጉ ወይም በአድቮኬሲና በፐብሊክ ዲፕሎማሲ መስኮች መሳተፍ የሚፈልጉ ይህንኑ ዕገዛ ማድረግ እንዲችሉ እናመቻቻለን፡፡ በጋራም እንሠራለን። ዋሽንግተንና አካባቢው ከናይጄሪያ ቀጥሎ ትልቁ ቁጥር የኢትዮጵያ ዳያስፖራ እንደሆነ መረዳት ችለናል። ገቢ በማመንጨት እያደገ የሚሄድ አቅም አለው። በዚያ አገር ፖለቲካ ውስጥም ተመራጭ ሆነው በማገልገል፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂም ላቅ ያለ ቦታ በመድረስ  እዚያ ያለውን አስተዋጽኦ አሳድጎ ለአገርም የሚተርፍበት ሁኔታ እንዲኖር የተለያዩ ቅስቀሳዎችን እያደረግን ቢሆነም በቀጣይ ጠንክሮ መሥራት ይጠይቃል።

በተለይ ደግሞ እዚያ የተወለዱትን ስናይ በዚህ አገር የኢኮኖሚና የሳይንስ እንቅስቃሴ ተወዳዳሪ ሆነው የማደግ ዕድላቸው በጣም ትልቅ ነው፡፡ እዚያ እኛ ልንሠራ የምንችለው ወላጆቻቸው የሠሩት እንዳለ ሆኖ፣ በቀጣይ ደግሞ ኢትዮጵያን ይበልጥ እንዲወዱ የተለያዩ ፕሮግራሞችን፣ ለምሳሌ በክረምት እዚህ በሚመጡበት ጊዜ በተለያዩ ጉዳዮች እንዲሳተፉና የእንግሊዝኛ ቋንቋና ሌሎች ትምህርቶችን እንዲያስተምሩ፣ ከአገራቸው ጋር እንዲያስተዋውቁ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ግን በቂ አይደለም፣ መጠናከር ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ ከሌሎች ጋር ስናወዳድረው የገቢ ማመንጨቱ ላይ አነስተኛ ስለሆነ ነው እንጂ የሚቻለውን ነገር እያደረጉ ነው፡፡ ሌላው በሽግግር ሁኔታ ውስጥ ስላለን የፖለቲካ ሁኔታው ወዴት ይሄድ ይሆን? የፀጥታ ሁኔታው ወዴት ይሄድ ይሆን? በሚል ቆም ብለው የሚያስቡም አሉ። ግን ደግሞ መቼም ቢሆን የአገራችን ሁኔታ መሻሻሉ አይቀርም በሚል በተስፋ፣ ለምሳሌ ዶክተሮች በቡድን ተሰባስበው በአዲስ አበባ ከተማ ሆስፒታል እየገነቡ ነው። ሌላ ቡድን ደግሞ በሐዋሳ  ሞል እየገነባ ነው። በግልም በቡድንም ሆነው በብዙ ጉዳዮች በተለይም አዲስ በተከፈተው የፋይናንስ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ላይ፣ እንዲሁም በ‹‹ፊንቴክ›› ኢንቨስት እያደረጉም ነው። አሁን ደግሞ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ብዙ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች እንደሚፈጠሩ እምነታችን ነው።

ሪፖርተር፡- ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተገናኘ  ከአሜሪካና ከካናዳ በኩል ጫናዎች ምን ይመስሉ ነበር? እዚያ ሆናችሁ እንዴት ትከታተሏቸው ነበር? ባህሪያቸውስ እንዴት ይገለጻል?

አምባሳደር ፍፁም፡- የአሜሪካ አስተዳደር ጫና የጀመረው ከህዳሴ ግድብ ድርድር ጋር በተያያዘ፣ በተለይም በቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ወቅት ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ግብፅ ባደረገችው ግፊት የዓለም ባንክና የአሜሪካ መንግሥት በጋራ ሆነው ግብፅ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያን እኛ እናሸማግላለን ብለው ነበር፡፡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት የፋይናንስ ሚኒስትራቸውን ወክለው የነበረው ሒደት ድርድር አይደለም እያሉ፣ ነገር ግን ድርድር ሲያካሂዱ ቆይተው አካሄዳቸው ስላላማረን ጉዳዩ ወደ አፍሪካ ኅብረት እንዲመለስ ብዙ ታግለናል፡፡ የዳያስፖራው ድጋፍ፣ የመንግሥትና የኢትዮጵያ ወዳጆች ጥረት ታክሎበት ጉዳዩ ወደ አፍሪካ እንዲመለስ ሲደረግ የመጀመርያውን ዕርምጃ ወስደዋል፡፡ በዚህም በጀት ሆኖ ፀድቆ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ ባለበት እንዲታገድ ነው የተደረገው፡፡ ከዚያ በኋላ እንደሚታወቀው የሰሜኑ ጦርነት ሲጀመር የአሜሪካ የምርጫ በጥቅምት ወር ነበር፡፡ በዚያን ወቅት አዲሱ አስተዳደር እስከ ጥር ወር ይቆይ ነበር፡፡ በሰሜኑ ጦርነት ላይ የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ግልጽ አቋም አራምደው ነበር፡፡ ሕወሓት የወሰደው ዕርምጃ ሕገወጥና ተገቢ እንዳልሆነና በአካባቢው ፀብ ለመፍጠር ወደ ኤርትራ፣ ወደ ባህር ዳርና ሌሎች ቦታዎች የተኮሳቸው ሚሳይሎች ፀብ አጫሪነት ነው ብለዋል፡፡ ጦርነቱ መጀመሩም ልክ አይደለም በሚል ሲያወግዙት ነበረ፡፡

በህዳሴ ግድብ ላይ የነበራቸው አቋም በግብፅ ተዋናዮችም፣ በአንዳንድ እነሱ ውስጥ ባሉ የግል ፍላጎቶችም ጭምር የብሔራዊ ጥቅም ፍላጎት አድርገው ለእኛ ይሰጠን የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ ያገዱበት ሁኔታ ነበር፡፡ ነገር ግን የሰሜኑ ጦርነት በጥቅምት ተጀምሮ እስከ ጥር አዲሱ አስተዳደር እስከገባ ድረስ በነበራቸው ጊዜ፣ ለኢትዮጵያ እውነት ያደላ አስተያየት ሲሰጡ እንደነበር እናውቃለን፡፡ በዚያን ጊዜ ግን የአዲሱ መጪው አስተዳደር ሰዎች የተለያዩ ለሕወሓት ድጋፍ የሚመስሉ መግለጫዎችን ያወጡ ነበር፡፡ በተለያዩ የሚዲያ አማራጮቻቸው እንደ እነ ሱዛን ራይስና ሌሎችም ትልልቅ አሁንም ድረስ በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች በተለይም በትዊተር ገጾቻቸው ላይ ኢትዮጵያን የሚያስጠነቅቅ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትን የሚያስፈራራና ለአንድ ወገን ያደሉ ዓይነት መግለጫዎችን ነበር ሲያወጡ የነበረው፡፡ ያ እንግዲህ በተለያየ ሁኔታ ተባብሶ ቀጥሎ በመጀመርያው ዙር ጦርነት የአሜሪካ ተቋማት በተባበረ መንገድ በሚመስል ሁኔታ፣ የሕወሓት ኃይል በገፋበት ወቅት ወደ ኢትዮጵያ እንዳትበሩ በተለይ ወደ አዲስ አበባ ስትበሩ ከመሬት በቅርብ ርቀት በመሣሪያ ልትመቱ ትችላላችሁ በሚል የአሜሪካው የአቪዬሽን መሥሪያ ቤት ሳይቀር ማስጠንቀቂያ አውጥቷል፡፡ የአሜሪካ ታዋቂ ሚዲያዎች እንደ ሲኤንኤን፣ ኒውዮርክ ታይምስና ዋሽንግተን ፖስት የሚባሉ፣ በተለይም እነዚህ ሦስት ዓለም አቀፍ ሚዲያዎቻቸው በዋናነት እንደ ትልቅ ፕሮግራም ይዘው ይሠሩ ነበር፡፡ ያን ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ተደጋጋሚ የሆነ ውግዘት በኢትዮጵያ ላይ ያወጣበት፣ እኔ ደግሞ ይህ ተገቢ አይደለም ብዬ በማስረዳበት ጊዜ እኛ እኮ ሚዲያዎች ናቸው የሚገፋፉን የሚል ምላሽ ይሰጡ የነበረበት፣ ለሚዲያዎቹ ምላሽ ስንሰጥ ደግሞ የማያወጡት በስንት ጥረት የተገኙ ቃለ መጠይቆችን ደግሞ የእነሱን ትርክት ወይም የሚያስቡትን ፕሮግራም ከእኛ መረጃ ቀንጥበው በማገናኘት እያቀረቡ፣ ትክክለኛ ያልሆነና በአገራችን ሰላም እንዳይመጣ የሚያደርግ ለአንድ ወገን ያደላ እንቅስቃሴ ነው ሲያደርጉ የነበረው፡፡

የመጀመሪያው ልዩ መልዕክተኛ ተብለው የተሾሙት ጄፍሪ ፊልትማን (አምባሳደር) በተሾሙ ማግሥት የሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ  በጋራ ሆነው መሥራታቸው በአካባቢው በተለይ ለአፍሪካ ቀንድ ትልቅ ሥጋት ነው የሚል መግለጫ ነበር የሰጡት፡፡ ሰላምን ለማምጣት ከተሾመ ሰው የማይጠበቅ መግለጫ መሆኑን በወቅቱ ለማስረዳት ሞክሬያለሁ፡፡ እሳቸውም ብዙ አልተሳካላቸውም፡፡ ምናልባት በቅርቡ ፎሬይን ፖሊሲ በተባለ መጽሔት ባወጡት ጽሑፍም አሁንም በአካባቢው ሰላም እንዳይመጣ የሚያደርግ አስተያየት ነው እየሰጡ ያሉት፡፡ ይህም ተገቢ አይደለም፡፡ በመሀል የነበሯቸውን የተለያዩ ተግባራት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ጄፍሪ ፊልትማንን ተክተው የመጡትም ብዙ አልቆዩም፡፡ አሁን ደግሞ ያሉትንም ማየት ይቻላል፡፡ ሲገፏቸው ከነበሩ ሐሳቦች መካከል አንደኛ ሰላም እንዲሰፍን እንፈልጋለን በሚል ይጠይቁ የነበረው የተኩስ አቁም ነው፣ እሱ ተደርጓል፡፡ ሁለተኛ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ያለማቋረጥ እንዲዳረስ የሚል ነበር እሱም ተሳክቷል፡፡ ሌሎች ከተጠያቂነት ጋር የተያያዙ የነበሩ ሲሆኑ፣ እነሱንም በሚመለከት ኢትዮጵያ በምን አግባብ እንደምትሄድበት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለዚህ ሥልጣን በተሰጠው አካል አማካይነት እየሠራን እንደሆነ የተቀመጠበት ሁኔታ አለ፡፡ ያን ተከትለን እየሄድን ነው፡፡ ግን አሁንም ከዚህ በተፃራሪ ሌላ የተመድ ቡድን የሚባል ቡድን አዋቅረው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኩል እየገፉ ያሉበት ሁኔታ አለ፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ልዩነቶች ካልሆነ በስተቀር እነሱ ከገመቱት ፍጥነት በላይ የሰላም ሒደቱ እየተቀላጠፈ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኞች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሦስት ጊዜያት መቀያየራቸው ይታወቃል፡፡ የሚንፀባረቁት አቋሞች ከግለሰቦቹ በሚመነጭ ችግር ነው? ወይስ አሜሪካ በያዘችው አቋም ምክንያት ነው?

አምባሳደር ፍፁም፡- እሱን በትክክለኝነት ለመናገር ያስቸግራል። ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ሊሰጥ የሚችለው የመደበው አካል ብቻ ነው። በአጠቃላይ ግን ልዩ መልዕክተኛ የሚለው አሠራር በራሱ የተወሰኑ ትኩረት ይሻሉ ያሏቸውን ጉዳዮች እንደ ፕሮጀክት በመያዝ፣ በቀጥታ ከመሪ ወደ መሪ መልዕክት በፍጥነት በማድረስ ጫና ፈጥሮ በቶሎ የማስፈጸሚያ መንገድ ነው፡፡ ሦስቱም ልዩ መልዕክተኞች በተለያዩ ጊዜያት ራሳቸውና ከውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤታቸው ይሰጡ የነበሩ መግለጫዎች እንደሚያሳዩት፣ የአሜሪካን ጫና የተሞላበት መልዕክትና አቋም ነው ሲያራምዱ የነበረው። በደቡብ አፍሪካ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የታየው የተለያዩ አገሮች መግለጫና የሚዲያ ሽፋን፣ በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ መሆኑንም ታዝበናል።    ኢትዮጵያ ከአሜሪካ፣ ከካናዳ ወይም ከአውሮፓና ከሌሎች አገሮች ጋር በሰጥቶ መቀበል መርህ በጋራ መሥራት ትፈልጋለች፡፡ የተለየ ግፊት ያደረጉ አገሮችን በተገቢው ሁኔታ በማስረዳት ጊዜው ሲደርስ ደግሞ ሰላም እንዲመጣ የሚቻላትን በማድረግ ለዚህ በቅተናል፡፡ በአሜሪካ በኩል የተደረጉ የተለያዩ ድጋፎች ይኖራሉ። ሆኖም የአፍሪካ ኅብረት የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡ ‹‹ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ›› በሚል መርህ የተጀመረው ጥረት ፍሬ እንዲያፈራ ኢትዮጵያ ትልቅ ሚና ተጫውታለች። ስለዚህ የተለያዩ አገሮች ትክክል ያልሆኑ ጥያቄዎች ሲያቀርቡ እያስረዳን፣ አብረን ልንሠራባቸው በምንችላቸው ጉዳዮች ደግሞ አብረን እየሠራን እዚህ ደርሰናል፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ነዎት፡፡ ካናዳ በኢትዮጵያ ላይ ያላት አቋም ምን ዓይነት ነው?

አምባሳደር ፍፁም፡- እንግዲህ አሜሪካኖች ወደ ሰላም መምጣት አለባችሁ፣ ተኩስ አቁም ላይ መድረስ አለባችሁ በሚል እነሱ በፈለጉት መንገድ ብዙ ግፊት አድርገዋል፡፡ እነሱ ባሰቡት መንገድ አልመጣ ሲላቸው ቀድሜ እንዳልኩህ በቀድሞው አስተዳደር በህዳሴው ግድብ ላይ፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ በአሁኑ አስተዳደር በአጎዋ ላይ ማዕቀብ የጣሉበትን አካሄድን እናያለን፡፡ በፕሬዚዳንቱ አማካይነት ለፋይናንስ ሚኒስትራቸውና ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው በተሰጠ ሥልጣን ሲፈጸሙ የነበሩ ናቸው፡፡ ይኼንን ደግሞ የአሜሪካ ፍላጎት ቀጣናው አደጋ ውስጥ ወድቋል በሚል  እንጂ ፕሬዚዳንቱ ትዕዛዝ የሰጡት፣ ለትግራይ ክልል ሕዝብ በማሰብ አይደለም ወይም በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በማሰብ አይደለም፡፡ ነገር ግን ድፍን ባለ ሁኔታ እነዚህን ማዕቀቦች ያደረጉትና ትዕዛዝ የሰጡበት አሠራር ነበር፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ካናዳ ሰላም እንዲፈጠር ትፈልጋለች፡፡ አሜሪካ ይኼ ብቻ አይደለም ‹‹ኤምሲሲ›› በሚባል ድጋፍ ትሰጠን ነበር፣ ይህንን እንዲቆም አድርገዋል፡፡ በዓለም ባንክና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት እንደ አባል አጋርነታችን የሚገባንን መብት እንዳናገኝ አዘግተውብናል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከኤግዚም ባንክ የኢትዮጵያ መንግሥት ራሱን ችሎ የሚበደረውን በማስተጓጎል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብድር እንዳይዘገይ አድርገዋል፡፡ ምንም እንኳን በቅርቡ የተለቀቀ ቢሆንም፡፡ ስለዚህ ያደረጉት ጫና ከባድም ኢፍትሐዊም ነው፡፡

ይህ ነገር እንዲያውም በእነሱ አገር ከአሁን ቀደም ገጥሟቸው ከነበረው አደጋ ጋር፣ በተለይም በፕሬዚዳንት አብረሃም ሊንከን ጊዜ ገጥሟቸው ከነበረው አደጋ ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ አብርሃም ሊንከን ፕሬዚዳንት በነበሩት ጊዜ ሳውዝ ካሮላይና የሚባል ስቴት ውስጥ ‹‹ፎር ሳማትር›› የሚባል የወታደሮች ካምፕ በደቡብ አማፂያኖች ሲወረር ተጠቅቶ ነበር፡፡  ከዚህ በፊት  በሌላም ቦታ በነበሩ ኃይሎች የተቀናነበረ ከፍተኛ ጥቃት ደርሶበት ካምፑ ወታደሮቹ ተወረው በነበረበት ጊዜ አብረሃም ሊንከን የወሰዱት ዕርምጃ ይታወሳል፡፡ እነዚህ አማፂያን በምንም መንገድ መሸነፍ አለባቸው በሚል በአሜሪካ ታሪክ ረዥሙ የሚባለው የእርስ በርስ ጦርነት ተካሂዶ ነበር፡፡ ከራሳቸው ታሪክ ለሕገ መንግሥታቸው ወደኋላ እንደማይሉ ያረጋገጡበት ሁኔታ የታወቀ ነው፡፡ የመንግሥት ሉዓላዊነት ሲደፈር በምርጫ ሥልጣን ላይ የወጣ አካል ሲደፈር ትክክል አይደለም ብለው እስከ መጨረሻው የተሟገቱበት ጊዜ ነበር፡፡ ይኼ ደግሞ በዘመናችን ተከስቶ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕን እንደግፋለን የሚሉ ኃይሎች እ.ኤ.አ. በጥር 2020 የሕዝብ ወተካዮች ምክር ቤት ወይም ኮንግረንስ በሚሉት ዙሪያ ተሰባስበው የምርጫ ድምፅ ውጤት እንዳይቆጠር ለማደናቀፍ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ የምክር ቤቱን በር ሰብረው ገብተዋል፣ መስታወቶችን አውድመዋል፣ ሕንፃው ውስጥ ገብተዋል፡፡ የምክር ቤት ተመራጮች ወንበር ውስጥ እስከ መደበቅና መግቢያ መውጪያ እስከሚያጡ ድረስ እስኪርበደበዱ ድረስ ማለት ነው፡፡ ያኔ ያሉት ምን ነበር? አብረሃም ሊንከን ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ እሆናለሁ ብሎ እዚህ ድረስ አቆይቶልናል፡፡ የአሁኑ ትውልድ ይህን ማበላሸት የለበትም ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ይህን ባለማስቆማቸው ምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ አካሂዶ ክስ እስከ መመሥረትና በሥልጣኑ ላይ እስከ መወሰን ድረስ የደረሰበት ጊዜ ነው የታየው፡፡ ያ ክስ እስከ ዛሬ ድረስ አልቆመም፣ እንደቀጠለ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ የምንማረው ለራሳቸው ሲሆን ሕገ መንግሥታቸው ተከብሮ እየሠራ እንዲቀጥል፣ ለእኛ ሲሆን ግን እነሱ ባሉን መንገድ እንድንቀበል የሄዱበት መንገድ በራሱ ከራሳቸው መርህ ጋር የሚጋጭ ነው፡፡ ከራሳቸው ታሪክም ጋር ከራሳቸው አሁናዊ ታሪክም የሚጋጭ ሁኔታ ነው፡፡

ወደ ካናዳ ስንመጣ እንደ ፖሊሲ ካየን እንግዲህ በአሜሪካ ሲመራ የነበረው ቀኝ ዘመም ወይም ወደ ቀኝ ያዘነበለ ፓርቲ ነው፡፡ ትራምፕ የሚመራው፡፡ የትራምፕ እንቅስቃሴ ሲጨመር ጽንፍ እንዲይዝ አድርጎታል ማለት ነው፡፡ አሁን የመጣውም በኢትዮጵያ ላይ የተከተለው ፖሊሲ ተገቢ ያልሆነ ነው፡፡ የካናዳ መንግሥት ሲታይ ወደ ግራም ወደ ቀኝም ያላዘነበለ መሀል ላይ ያለ ሊበራል ፓርቲ ነው እየመራ ያለው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ፓርቲ በተቻለ መጠን አገር ውስጥ የሚያካሂደው ፖሊሲ ነፀብራቅ ነው፡፡ የካናዳ መንግሥት ነፃ ገበያ ሥርዓት የሚከተል ቢሆንም፣ ሌሎች እንደ ሶሻሊዝም አድርገው ይቆጥሩባቸዋል፡፡ ያም የሆነበት ምክንያት ብዙ ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን አስተባብረው፣ ከማንነት ጋር ያሉ ጉዳዮችን አክብረው፣ ቀደም ሲል እዚያ የነበሩ ሕዝቦችን በተለይም ነባር የሚባሉ ሕዝቦችን ባህላቸውንና ወጋቸውን አክብረው የሚሄዱበት ሥርዓት አላቸው፡፡ እናም ብዙ የድጋፍ ሥርዓቶች አሏቸው፡፡ በተለይም ሕክምና፣ ትምህርትና ሌሎች ሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮችን ይደግፋሉ፣ በዚህም ‹‹ዌልፌር ስቴት›› ይሏቸዋል፡፡ ሕዝቡ ወደ ጽንፍ እንዳይሄድ ወደ መሀል በማምጣት ይሠራሉ እንጂ፣ እንደ አሜሪካ አገሪቱን በሁለት ትልልቅ ፓርቲ የሚከፍል ሥርዓት የላቸውም፡፡ ካናዳ ቢያንስ ሦስት ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያሉበት አገር ነው፡፡ ያን ፖሊሲያቸውን ነው ወደ ውጭ የሚያንፀባርቁት፡፡ በሌላ በኩል አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገው ድጋፍ ሰብዓዊ ነው እንጂ በቴክኖሎጂ መስክ ድጋፍ የለም፡፡ ለልማት የሚሆን ድጋፍም የለም፡፡ ምናልባት ከሰብዓዊ ድጋፍ አልፎ ለመከላከያ የሚያደርጉት ድጋፍ አለ፡፡ እንግዲህ ያንኑ ነው የቀጠሉት፡፡ ሰብዓዊ ድጋፍን ቀጥለው ሌላውን ግን በማቋረጥ የገቢያቸውንም ዕድል ዘግተው ነበር፡፡ በተቃራኒው ካናዳን ስታይ በፊትም የምታደርጋቸው ድጋፎች ለዕድገታችን የሚበጁ ናቸው፡፡ በቀጥታ ለመንግሥት በመስጠትና በበጀት ድጋፍ ሳይሆን በራሳቸው አግባብ ነው የሚያካሂዱት፡፡ ይህንንም በጦርነቱ ጊዜ አላቋረጡም፡፡ አሁን እንዲያውም ለመልሶ ግንባታ ሊያግዙንና ሊደግፉን ሥራ ጀምረዋል፡፡

ሌላው ካናዳ በብዙ ጉዳዮች ከአሜሪካና ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በጋራ ትሠራለች፡፡ የኢትዮጵያን ጉዳይ ግን በጥንቃቄ ነው የያዘችው፡፡ በአፍሪካ ኅብረት መሠረት እንዲያልቅ፡፡ ነገር ግን ፈጥኖ መፍትሔና ሰላም እንዲመጣ ነበር ስትገፋፋ የነበረችው፡፡ በምን መልክ ላግዝ እችላለሁ? ዳር ሆኘ ልመለከት አልፈልግም በሚል ግፊት ስታደርግ ነው የነበረው፡፡ ከእኛም በኩል በአፍሪካ ኅበረት በኩል ድጋፍ ልታደርጉ ትችላላችሁ የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸው በዚያ በኩል ሲሠሩ ነበር፡፡ ሰላሙ እንዲመጣ፣ ስምምነቱ እንደተፈጸመ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው አማካይነት ዕውቅና የሰጡበትና ደስታቸውን የገለጹበት፣ በቀጣይ ለመደገፍ ቁርጠኝነታቸውን የገለጹበት ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በስልክ የተነጋገሩበት አይረሳም፡፡ እንዲያውም እኔ ከሄድኩ እንኳ ሁለት ጊዜ በስልክ ተገናኝተዋል፡፡ በአጠቃላይ ላለፉት አራት ዓመታት ሰባት ጊዜ አካባቢ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ ማለት ነው፣ ከስልኩም ባለፈ በአካል ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡ ያ በከፍተኛ መረጃዎች ደረጃ ያለው ግንኙነት በየደረጃው ላሉ ግንኙነቶች ጥሩ መሠረት ጥሎልናል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያና በካናዳ መካከል ያለው የኢንቨስትመንትና የንግድ ግንኙነት ምን ይመስላል?

አምባሳደር ፍፁም፡- ብዙ ማደግ አለበት፡፡ አሜሪካ በጣም ትልቅ አገር ናት፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካን ሕዝብ ቁጥር ወደ 333 ሚሊዮን አካባቢ ነው፡፡ የካናዳ ደግሞ 33 ሚሊዮን ነው፡፡ አሥር እጥፍ ማለት ነው፡፡ የካናዳ ሕዝብ ቁጥር ትንሽ ቢሆንም እንኳን በቆዳ ስፋት ከአሜሪካ ይበልጣል፡፡ ግን ደግሞ በቆዳ ስፋት ከአሜሪካ ቢበልጥም፣ የሚኖርበት መሬትና ቤት በጣም ትንሽ ነው፡፡ ብዙ ቦታው ለኑሮ አመቺ ያልሆነ፣ በበረዶ የተሸፈነ፣ በጨፌና በውኃ አካላት የተሸፈነ ነው፡፡ ለምሳሌ ለአገር ውስጥና ለቅርብ አገሮች የአውሮፕላን በረራ የምናካሂድባቸው ቦምባርዲየር በመባል የሚታወቁ አውሮፕላኖች ግዥና ጥገና ከካናዳ ነው የምንፈጽመው፡፡ እስካሁን 25 አውሮፕላኖችን ከካናዳ ገዝተናል፡፡ ሌላው በገበያ ተደራሽነት አሜሪካ በአጎዋ በኢትዮጵያ ላይ ቢኖርም፣ የዘጋችው ገበያ ካናዳ ከቀረጥና ከታክስ ነፃ ለኢትዮጵያ የሰጠችው ዕድል ከ2,000 በላይ የሆኑ የምርት ዓይነቶችን ያካትታል፡፡ ይህም ሁሉንም ምርቶች ከመሣሪያ ውጪ በሚል የአውሮፓ ኅብረት ለታዳጊ አገሮች የሰጠው ዕድል በካናዳም ተፈጻሚ በመሆኑ ነው ይህን ዕድል ኢትዮጵያ ያገኘችው፡፡ የአሜሪካ ሲዘጋ ወደ ካናዳ የዞርንበት ሁኔታ አለ፡፡ ኢትዮጵያና ካናዳ የሚገናኙበት ሌላው መንገድ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ገበያ የምትልካቸው የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች ቡናና ሌሎች ቅመማ ቅመሞችና የቅባት እህሎች በምንፈልገው መጠን ያህል ባይሆንም በቀጥታ እየላክን ነው፡፡ ያን ለማሳደግ አሁንም ዕድሉ አለ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካናዳ የንግድ ከተማ ወደ ሆነችው ቶሮንቶ ቀጥታ በረራ በሳምንት አምስት ቀን አለው፡፡ አሁን ተጨማሪ በረራ ለማድረግና ሙሉ ሳምንቱን ለመብረር ክትትል እያደረግንበት ነው፡፡ ሌላው ኩቤክ ውስጥ የሚገኝ ሞንትሪያል የሚባል ትልቅ ከተማ አለ፡፡ ይህ ከተማ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሲቪል አቪዬሽን መሥሪያ ቤት ያለበት ነው፡፡ የኢትዮጵያም ጽሕፈት ቤት አለ፡፡ ወደዚህ ከተማም በምዕራብ አፍሪካ በኩል አድርገን በሳምንት ሦስት ጊዜ ለመብረር ጥያቄ አቅርበን እየተከታተል ነው ያለነው፡፡

እንዲሁም ካናዳ በኢትዮጵያ ምን ልታደርግ ትችላለች ካልን፣ ካናዳ በቴክኖሎጂና በከፍተኛ ትምህርት በጣም ጥሩ የሚባል አገር ነው፡፡ በግብርም እንዲሁ የሚገርመው በአሁኑ ጊዜ እስከ 50 እና 60 ሴንቲ ሜትር በረዶ ያለበት አገር ነው፡፡ ምናልባትም ከአሥራ ሁለት ወራት ውስጥ ከአምስት ወራት ያላነሱ ለግብርና የማይመቹ ወራት ናቸው፡፡ ነገር ግን በግብርና ምርት በጣም ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ አገር ነው፡፡ ስለዚህ ቴክኖሎጂን ተጠቅመው የሚያመርቱ በመሆናቸው በግብርና ዘርፍ በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ክትትል እያደረግን ነው፡፡ አሁን የአንድ ኩባንያ ባለቤት በቅርብ ጊዜ ጉብኝት ያደርጋሉ ተብለው ይጠበቃሉ፡፡ በግብርና ትልቅ ቦታ ወስደው ኢንቨስት ማድረግ ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ የኩባንያውን ማንነት ወቅቱ ደርሶ ፈቃድ ሲያወጣ እንገልጸዋለን፡፡ ሌላው ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ የአውሮፕላን ውስጥ ሳኒታይዜሽን ማለትም በኬሚካል ቫይረስና ባክቴሪያን ማከም በተመለከተ፣ ሁልጊዜ በረራ ከመካሄዱ በፊት አውሮፕላን ውስጥ የሚነፋው ኬሚካል ሦስትና አራት ሰዓት የሚወስድ ነው፡፡ ነገር ግን ያን የኬሚካል ርጭት በአምስት ደቂቃ ውስጥ ምንም ዓይነት ኬሚካል ሳይጠቀም በጨረር የሚሠራ ቴክኖሎጂ ይፋ አድርገው በአገራቸው መሥራት ጀምረዋል፡፡ ቴክኖሎጂው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ውይይት አድርገናል፡፡ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሟል፡፡ ማሽኑ ኢትዮጵያ ውስጥ መጥቶ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚገጣጠምበትና ከዚያ የበለጠ ገበያ የሚገኝበት ዕድል እንዲኖር ጠይቀናል፡፡ 

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ ውኃ በኬሚካል ነው የሚታከመው፡፡ ነገር ግን አሁን በጨረር ቴክኖሎጂ ከፀሐይ በሚገኝ ጨረር በቴክኖሎጂ በመታገዝ ሕክምና ማድረግ እንደሚቻል ሳይንሱ ደርሶበት፣ ብዙ አገሮች ከክሎሪንና ከሌሎች ኬሚካሎች ወጥተው ወደ እዚህ እየገቡ ነው፡፡ ስለዚህ የውኃ የባክቴሪያ ሕክምና የምናደርግበት ማጣራት ከሚሠራ ኩባንያ ጋር ተነጋግረናል፡፡ ሌላው ደግሞ የሕክምና ቴክኖሎጂ ሲሆን፣ ይህ የጀርባ ሕመምን ቀዶ ጥገና ሳይደረግ በድምፅ ሞገድ ብቻ ሕክምና የሚሰጥ ቴክኖሎጂ ያለው ኩባንያ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ካናዳ ቶሮንቶና በተወሰኑ ዓረብ አገሮች ሕክምና የሚሠራ ኩባንያ ዋና ሳይንቲስት አነጋግረናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት አላቸው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለ በነርቭና በጀርባ ሕክምና ላይ እየሠራ ከሚገኝ ክሊኒክ ጋር ትብብር እንዲያደርጉ በቀጣይ ጥር ወር ለማገናኘት አስበናል፡፡ ስለዚህ የኩባንያው ተወካይ ወይም ራሳቸው ዋና ሳይንቲስቱ ይመጣሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡ ስለዚህ እነዚህ አራት ተጨባጭ የሆኑ የቅድመ ኢንቨስትመንት ጥናቶች እየተከናወኑ ነው ማለት ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ እኔ በግሌ በተለያዩ የቢዝነስ ፎርሞችና መድረኮች በመገኘት፣ በኢትዮጵያ ስላሉ አማራጮችና የኢንቨስትመንት ቦታዎች ለማስረዳትና ለማሳወቅ በመድረክ ሐሳቦችን በማቅረብና በግል በማነጋገር ለማቀራረብ ሞክሬያለሁ፡፡

አፍሪካ በአጠቃላይ ከዚህ በኋላ መሠረተ ልማት መገንባት ግዴታዋ ነው፡፡ የአፍሪካ ነፃ ገበያ ስምምነት ተግባር ላይ እንዲውል ከተፈለገና አፍሪካውያን እርስ በርሳቸው የሚገበያዩ ከሆነ መንገድ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የባቡር መስመሮች ያስፈልጉናል፡፡ ስለዚህ የውጭውን ካፒታል በግልና መንግሥት አጋርነት አምጥተን እንዲሠሩ ማድረግ ግድ ይለናል፡፡ ካናዳውያንም ሆኑ የሌሎች አገሮች ባለሀብቶች የግልና የመንግሥት አጋርነቱን የሚመርጡት የቢዝነስ አደጋን እንደ መቀነስ አድርገው ስለሚወስዱት ነው፡፡ ይህም የተጠና ፕሮጀክት ስለሚሆንና የተሻለ መተማመን ስለሚፈጥርላቸው፣ በዚህ እንዲሰማሩ ይህን ዕድል ለመፍጠር በተለያዩ አጋጣሚዎች ለማሳወቅ ሞክሬያለሁ፡፡ ካናዳውያን በማዕድን ዘርፍ ትልቅ የሆነ አቅም አላቸው፡፡ ልምዱም ቴክኖሎጂም አላቸው፡፡ ወርቅና ሌሎች የከበሩ ማዕድናትና ነዳጅ የመሳሰሉትን ለማስተዋወቅና በእነዚህ ላይ ኢንቨስት የሚያደርጉ ኩባንያዎችን ለመለየት፣ በመጪው መጋቢት ወር በቶሮንቶ ከአፍሪካና ከካናዳ የተውጣጡ ኩባንያዎችና ከመንግሥት አካላት ከተውጣጡ አካላት ይሳተፋሉ፡፡ በእኛም በኩል ኤምባሲያችንና የማዕድን ሚኒስቴር ኃላፊዎች ይገኛሉ፡፡  ስለዚህ በዚያ መድረክ ላይ ከፍተኛ ሥራ በመሥራት ኢንቨስተሮችን የማግኘት ዕድል እንፈጥራለን፡፡

ሪፖርተር፡- የሁለቱ አገሮች የንግድ ሚዛን ምን ይመስላል?

አምባሳደር ፍፁም፡- የካናዳን ስታይ ቅድም እንዳልኩህ የአውሮፕላን ሽያጩ ብቻ ከፍ ያደርገዋል፡፡ ነገር ግን ይህን ለማጥበብ የእነሱን ኢንቨስተሮች ወደ እዚህ በመሳብ በኢትዮጵያ እንዲያለሙ በማድረግ መሠራት አለበት፡፡ የእነሱ ኢንቨስተሮች ብዙ ጊዜ የሚታወቁት ምርቶቻቸውን ወደ አገራቸው በመላክ ነው፡፡ ያ ደግሞ የንግድ ሚዛኑን ለማስተካከል ይረዳል፡፡

ሪፖርተር፡- የንግድ ሚዛኑ በጣም የሰፋ ነው ማለት ነው?

አምባሳደር ፍፁም፡- እንዲያውም የሚገባውን ያህል ግብይት እየተካሄደ አይደለም ማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ በቶሮንቶ ከተማ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በንፅፅር  ኤድመንተን፣ ካልጋሪ፣ ቫንኮቨርና ኦተዋም አሉ፡፡ ነገር ግን የቶሮንቶን እንኳን ብንወስድ ከዳያስፖራ ጋር የሚገናኝ ግብይት ቀላል አይደለም፣ እሱን ማሳደግ ይቻላል፡፡ አንድ መንገድ ራሱን ችሎ የኢትዮጵያውያን የቢዝነስ ተቋማት ታያለህ፡፡ ይህ ምናልባት ለንግድ ሚዛኑ ላይረዳ ይችላል፡፡ ነገር ግን ብዙ ዕድሎች እንዳሉ ማሳያ ነው፡፡ ለምሳሌ ወደ አውሮፓና አሜሪካ በአውሮፕላን ካርጎ እንደሚሄደው ወደ ካናዳ በዚያ ልክ የለም፣ ነገር ግን ፍላጎቱ አለ፡፡ በቀጣይ ይህን መሥራት እንዳለብን አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከቀደሙት ጊዜያት ጀምሮ ከኢትዮጵያ ወደ ተለያዩ አገሮች የሚላኩ ዲፕሎማቶች፣ መንግሥት አንድም ከማዕከላዊ መንግሥት ለማሸሽ፣ አለፍ ሲልም ለዕረፍትና እንደ ጡረታ መውጫቸው ነው ተብሎ ይነገራል፡፡ ዲፕሎማቶችም አገርን ወክለው ሲሄዱ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እምብዛም አይወጡም ይባላል፡፡ በዚህ ዕሳቤ ላይ ምን ይላሉ?

አምባሳደር ፍፁም፡- በፊት ያው ብዙ አገልግለው ወደ ጡረታ የሚጠጉ ሰዎች ወደ ውጭ የሚላኩበት ሁኔታ ነበር፡፡ ያ ማለት ወደ ጡረታ የሚጠጉ ሰዎች ብዙ ልምድ ስላላቸው ብዙ ሥራ ሊሠሩ ይችላሉ፣ ያንን ማሰብም ይቻላል፡፡ ወጣት የተባለ ጥሩ የሚሠራ፣ ዕድሜው የገፋ ሁሉ የማይሠራ ተብሎ መወሰድ የለበትም፡፡ የውስጥ ተነሳሽነትና ከዋናው መሥሪያ ቤት የሚሰጥህ ድጋፍ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ እኔ አሁን ለምሳሌ ድጋፍ ቢኖረኝም ባይኖረኝም እሠራለሁ ብዬ እራሴን አሳምኜ ነው ስንቀሳቀስ የነበረው፡፡ ትንሽ ለመፍጨርጨር ስሞክር ደግሞ በዙሪያህ ያሉ አገር ወዳድ ዳያስፖራዎች ስላሉ የእነሱን ዕገዛ ይዞ ብዙ ርቀት መሄድ ይቻላል፡፡ አቅማችን እያደገ ሲሄድ ደግሞ በፋይናንስም በሌላም ድጋፍ ማግኘት እንችላለን፡፡ ዲፕሎማቶች ለኤምባሲዎች በውጭ አገር የሚኖረን በጀት ምናልባት በዓለም ላይ ካሉ አገሮች ዝቅተኛው ነው ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ ያ ደግሞ እንደ ድክመት እንዳይታይ አገራችን ያለችበት የድህነት ሁኔታ ሲሆን፣ ያንን ለመቀየር መሥራት አለብን በሚል እንጥራለን፡፡ ለዚህ አንተ ያነሳኸው አስተያየት ይደመጣል፡፡ ግን ደግሞ ሰውን በሥራው መመዘን መልካም ነው፡፡ ሌት ተቀን ይሠራል፣ የተሳሳቱ ትርክቶችን ፊት ለፊት ወጥቶ ይጋፈጣል፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ይሞግታል፣ የተሳሳቱ ዕሳቤዎችን ለማስተካከል ይሠራል፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ ታሪክ መጀመሪያ ለኮቪድ፣ ከዚያ ለህዳሴ ግድብ፣ ከዚያ ለተጎዱ ወገኖቻችን በሦስት ዓመታት ውስጥ ከአሥር ሚሊዮን ዶላር በላይ በዕርዳታ ማስገባት ችለናል፡፡ ይህ እንግዲህ በአሜሪካ ብቻ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በራሳቸው አደረጃጀት ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ አስገብታለች፡፡ በእስልምና እንዲሁ በድር ኢትዮጵያ የሚባል በሰሜን አሜሪካ ያለ ተቋም ከፍተኛ ገንዘብ አሰባስቧል፡፡ ግን ደግሞ አንዳንዶቹ የተለያዩ ተቃውሞዎች ውስጥ ሆነው  ተስፋ የቆረጡ ነበሩ፡፡ እኛ ደግሞ ጥያቄዎቻቸውን በማዳመጥ፣ ሲሰድቡን ችለን በመነጋገር ሐሳባቸውን እንዲቀይሩ ወይም ሐሳባቸውን እንደያዙ አገራቸውን እንዲረዱ በመግባባት የተሠራ ሥራ አለ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዳያስፖራው እንደሚናገረው አይደለም፡፡ ልቡ አገሩን ይወዳል፣ ስለዚህ የተቆጣበትን ነገር አድምጠን፣ አንዳንዴ እኛም የምንቆጠብበት ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ለምን እዚህ ቦታ ሰዎች ይሞታሉ? ሲል ትክክል አይደለም ሳይሆን የምንለው የተፈጠረውን ሁኔታ እያስረዳን አብረን መሥራት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በድር ኢትዮጵያ ያልኩህ ለተቃውሞ የወጡ ሰዎች ሠልፍ ላይ አብረን ቁጭ ብለን፣ ኤምባሲ ውስጥ አብረን አፍጥረን ነገሮችን መለወጥ ችለናል፡፡ አንዳንዱ ዳያስፖራ የአገሩን ጉዳይ እንደ ምግቡና እስትንፋሱ ያስታውሳል፣ ዘወትር ይከታተላል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከጨረታ በስተጀርባ ያሉ ድርድሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው›› ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር)፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞ ሜቴክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ ከጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ...

‹‹ባለፉት 25 ዓመታት ባለን አቅም ሁሉ የተለያዩ አጀንዳዎችን ለመዳሰስ ሞክረናል›› የራስወርቅ አድማሴ (ዶ/ር)፣ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› በመባል የሚታወቀውን በኢትዮጵያ ታሪክ ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ አካል ገለልተኛ ሆኖ የተቋቋመ ሐሳብ አመንጪ የጥናት ተቋም (ቲንክ ታንክ) ከመሠረቱት አንዱ መሆናቸውን...

‹‹ብሔራዊ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን ሊያግዙ የሚችሉ ወጥ የሆኑ ሕጎች ያስፈልጉታል›› አቶ ኑሪ ሁሴን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት (ከወለድ ነፃ ባንክ...

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስጀመር ብርቱ ትግል ተካሂዷል፡፡ ከብዙ ጥረት በኋላ አገልግሎት በመስኮት ደረጃ እንዲሰጥ ተወስኖ፣ ከዚያም ከለውጡ ወዲህ ሙሉ በሙሉ ከወለድ...