Wednesday, November 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገት‹‹አላዋቂ ሳሚነት››

‹‹አላዋቂ ሳሚነት››

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

ተግባራዊ ሳይንስና ስነት (አርትስ) ተዛማዷቸው ጥንታዊ ነው፡፡ ሳይንስ የኑሮ ፈተናዎችን የሚያቀሉ መፍትሔዎችን ይፈልጋል፣ ይመረምራል፣ መፍትሔ ሰጪ ነገሮችን ይፈለስፋል፡፡ ፍልሰፋዎች ቁሳዊ ቅርፅ ይዘው ይወጣሉ፡፡ ቁሳዊ ነገሮች ሲፈበረኩ ደግሞ አነሰም በዛ ሳቢና ውብ እንዲሆኑ አድርጎ የመሥራት ፍላጎት አብሮ ይመጣል፡፡ ሳይንስ ዋና ጉዳዩ የሆነ የኑሮ እክልን መወጣት ነውና ማስዋብ ሁለተኛ ነገር ነው፡፡ ይህ በሳይንስና በስነት መሀል ያለው መስተጋብር በተለያየ ምክንያት ሊጋጭ ይችላል፡፡ ቁሳዊ ነገሮች የሚሰጣቸው ውበት የነገሮቹን መሠረታዊ አገልግሎት የሚያዳምቅ ሊሆን እንደሚችል ሁሉ እስከ መሰወር ሊሄድም ይችላል፡፡ ለምሳሌ በስለላ ዓለም ውስጥ የመሰለያዎችን አገልግሎት በቅርፅ መሰወር ሆን ተብሎ የሚፈለግ የፍልሰፋ ዒላማ ነው፡፡ በስነት ውስጥ ደግሞ ዋናው ጉዳይ ሥነ ውብት ነው፡፡ ሥነ ውበት የስነት (አርትስ) ዋና ጉዳይ ነው ስንል የአሰሳ፣ የምርመራና የእርካታ ዒላማ ሆኖ የሚመጣው የኑሮ ውጫዊ ስንክሳር ሳይሆን ውስጣዊ (የልቦና) ስንክሳር ነው፡፡

አንድ ፈላስፋ እንዳለው ሳይንስ በኑሮ ጉዳዮች ላይ የሚጠበብ ‹‹ስነት›› እንደሆነ ሁሉ፣ ስነት ደግሞ የሰውን ልቦና የሚበረብር የልቦና ምግብና መተንፈሻ የሆነ ‹‹ሳይንስ›› ነው፡፡ ሠዓሊው፣ ቀራፂው፣ የሥነ ጽሑፍ ጸሐፊው ልቦናዊ ንካቱን በስናዊ ሥራው ሲገልጥ በነባራዊ እውነታ ያሉ ሕግጋትን፣ ይዘቶችንና ቁመናዎችን እስከ መጣስ ሊሄድ ይችላል፡፡ ከስነታዊ መጠበብ ውስጥ መልዕክትን መደበቅ ራሱ የሥራው ግብ ሆኖ ሊመጣ እንደሚችል ሁሉ፣ ኅብረተሰባዊ ሥርዓት ላይ ቁጣና ኩርፊያ ባለውና ያንን በሚገልጽ ስነት ውስጥ ደግሞ ይዘት የለኝም፣ ፋይዳ እነፍጋችኋለሁ የሚል መልዕክት ራሱ ዋና ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ በሳይንስም ሆነ በስነት ከጠቃቀስናቸው ጫፍ የወጡ የይዘትና የቅርፅ ጥሎች ውጪ ይዘትና ቅርፅ ይተጋገዘሉ፡፡ አንዱ የሌላው አድማቂና አስተጋቢ ሆኖ ይሠራል፡፡

ለምሳሌ ለሰዎች በሚደረግ ንግግር ውስጥ የታለመለትን መልዕክት ወደ ሰሚዎቹ ማድረስ ዋና ጉዳይ ነው፡፡ የታለመለት መልዕክት ዓላማም ለሆነ ተልዕኮ ወኔ ማነሳሳት፣ አሳምኖ አቋም ማስለወጥ፣ ማስተማር፣ የተጣራ መረጃ መስጠት ወይም ማዝናናት ሊሆን ይችላል፡፡ ዓላማው ምንም ሆነ ምን ንግግርን እንዳያሰለች መልዕክትንም አይረሴ አድርጎ ማቅረብ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህን ለማሳካት ልዩ ልዩ የንግግር ጥበቦችን መጠቀም (ዝርዝርን የማፍታታት፣ ዓብይ ነጥቦችን የመጭመቅ፣ አፅንኦት የመስጠት፣ ቁልጭ አድርጎ የማሳየት፣ ወዘተ) በአጠቃላይ አዕምሮንና ስሜትን ኮርኩሮ መልዕክት በሰዎች ዘንድ ውሎ እንዲያድር ለማድረግ መሥራት ያሻል፡፡ ይህንን ዋና የተግባቦት ጉዳይ ሌላ ግብዝ ዓላማ ተደርቦ ሲሻማው ልፋት ከንቱ ይቀራል፣ ወይም ጉዳት ይደርስበታል፡፡

ለምሳሌ ተናገሪው መልዕክትን አይረሴ አድርጎ የማድረስ ሥራውን ስቶ፣ በጣም የተማርኩ ነኝ/እንግሊዝኛ አውቃለሁ የሚል አባዜ ውስጥ ሲገባ ተግባቦት ይወላከፋል፡፡ ንግግሩ የሚቀርብለት ሰው የተነገሩትን ባዕድ ቃላት የማያውቅ ከሆነ መልዕክት ይጎድልበታል፣ ትኩረቱ ይጠፋል፡፡ የንግግሩ አድማጮች የተማሩ ሆነውም፣ ተናጋሪው የወታተፋቸው የፈረንጅ ቃላት በአባባልም ሆነ በአገባብ የፈረንጁን ቋንቋ በወጉ ያለማወቁን የጠቆሙ ከሆነም፣ የአድማጩ ትኩረት ከዋናው የተግባቦት ጉዳይ ወጥቶ ወደ ትዝብትና ሽርደዳ ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ አንድ ሰሞን፣ ‹‹ያለንበት የለውጥ እንቅስቃሴ ወደ አምባገነንነትም፣ ወደ ሥርዓት አልባነትም፣ ወደ አዲስ ምዕራፍም የሚወስዱ መንገዶች ያሉበት መስቀለኛ ሥፍራ ላይ ነውና አጥፊዎቹን መንገዶች ትተን ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደምን እንጓዝ?›› የሚል ውይይትና ንግግር ‹‹ዴስቲኒ ኢትዮጵያ›› በተሰኘ ቡድን አማካይነት ተካሂዶ ነበር፡፡ ንግግሩ ከእነ ጥረቱ የሁላችንንም ጉጉት የሳበ ነበር፡፡ የለውጥ ተስፋው የተሰጠውም ‹‹ንጋት›› የሚል ስም ማራኪ ነበር፡፡ አንዳንድ ፖለቲከኞቻችን ግን ከአማርኛው ይበልጥ የእንግሊዝኛው ቃል ጥሟቸውም እንደሆን አላውቅም፣ ‹‹Dawn›› ፊደላት ኖረውት ‹‹ዶውን›› የሚል ጎተት ያለ አጠራር ያለውን ቃል ‹‹ዳወን›› እያሉ ሲሉ፣ ምነው እንግሊዝኛው በቀረባቸው እያልን ስለእነሱ የተሰቀቅንበት ጊዜ ነበር፡፡ የውኃ ጋንን ‹‹ታንከር›› ብሎ መጥራት የት ድረስ እንደሰፋ ባናወራው ይሻላል፡፡

ወደ ዋና ጉዳያችን እንመለስ፡፡ የተግባቦት ዒላማን በአግባቡ የመታ ንግግር ማድረግ ክህሎት ነው፡፡ ይህንን ክህሎት የመጎናፀፍ ነገር የንግግር ጥበብን በደንብ ያወቀ ሥልጠናን/ልምምድን ይፈልጋል፡፡ የንግግር ክህሎትን ጨብጦ ሁለ ነገሩን በመግባባት ዒላማ ላይ ያነጣጠረ ንግግር እንደ ጣፋጭ ሙዚቃ ነጥቦቹን እያፈሰሰ፣ ለአድማጮቹ ደልቶ በስሜታቸውና በአዕምሯቸው ይፈሳል፡፡ መርቻ ነጥቦቹን በደንብ አደራጅቶ በተገቢው ቦታና ጊዜ ይወረውራል፣ ጥቅሉን ይተረትራል፣ የተረተረውን ደግሞ ሄዶ ሄዶ ይጠቀልላል፡፡ ይህንን የማድረጉ ሥልት ሙዚቃ ነው፡፡ ተናጋሪ ይሞዝቃል፡፡ ‹‹ይህ ምን ማለት ነው?/አንድ ታዋቂ ሰው ምን አለ መሰላችሁ!…›› በሚሉ ዓይነት አባባሎች ጆሮን አቁሞ ንግግሩን ቀጥ በማድረግ የአድማጮችን ጉጉት ከአሁን አሁን ያቁለጫልጭና አይረሴ ማራኪ አነጋገር ያስከትላል፡፡ ልብ በሉልኝ የሚለውን ሁነኛ ነጥብ አዋዝቶ ያቀርበዋል፣ ወይም ረገጥ ጎላ በተደረገ ድምፅ አድምቆ ይናገረዋል፣ ወይም ሙዚቃውን ወደ ሹክሹክታ መሰል ዝቅታ አውርዶ ሁነኛ ፍሬ ሐሳቡን የያዙትን ሐረጎች አብጠልጥሎ ይጠራቸውና ለአድማጮቹ የማወራረጃ ፋታ ሰጥቶ ንግግሩን ይቀጥላል፡፡ ተከታይ ንግግሩም የተጀመረ ነጥብን የሚያፍታታና የሚሰልቅ፣ ሰልቆም የሚሰበስብ ወይም አዲስ ነጥብ የሚያስተዋውቅ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ሁሉ ሥራ ውስጥ ፋታ መውሰድ፣ ዕረፍት ማድረግ፣ ድምፅን ማንሳትና መጣል፣ ንግግርን ማፍጠንና መጎተት፣ ወዘተ ሁሉ መልዕክትን እንደሚጨበጥና እንደሚስብ አድርጎ የማስተናበሪያ ዘዴዎቹ ናቸው፡፡

ንግግር በጽሑፍ መልክ በሚመጣበት ጊዜ፣ በቋንቋ ፊደላት ሊጻፉ የሚችሉ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ በሥርዓተ ነጥብ የሚጻፉ ነገሮችም አሉ፡፡ ማለትም በቋንቋ ውስጥ ቃላት ትርጉማዊ ፋይዳ እንዳላቸው ሁሉ ነጥቦችም ትርጉማዊ አገልግሎት አላቸው፡፡ ይህ ትርጉማዊ ተራክቦ በተለያየ ምክንያት ሊፋለስ ይችላል፡፡ በጊዜያት ውስጥ አጠቃቀም ላሽቆ የነበሩ ሊቀነሱ ያልነበሩ ሊታከሉ ይችላሉ፡፡ የአጠቃቀም መማገጥ ሊመጣ ይችላል፡፡ ተፈላጊ ለውጦችን እየያዙ የማይፈለጉትን እየጣሉ የመሄድ ቅልጥፍናን በቋንቋዎች ዘንድ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም የቋንቋ አጠቃቀም መማገጥ በተጠቃሚው ሁሉ ዘንድ ሊከሰት ይችላል፡፡ ያንን ሁሉ በመደበኛ ትምህርትና አጠቃቀም መግራት አስቸጋሪ ነው፡፡ በጊዜያት ውስጥ ምግጠት ደርሶ ትርፍ ነገሮች/ የተለወጡ አጠቃቀሞች ከተባዙ በኋላ ለማረም ሲሞከር ዘልማድ ይተናነቃል፡፡

ምሳሌ ለመስጠት እንግሊዝኛና ፈረንሣይኛ ውስጥ መግባት አያስፈልገንም፡፡ አማርኛ ውስጥ የድምፅ ንባብ ልዩነታቸውን ያጡ ትርፍ ፊዳላትን ያቃለለ የፊደል ገበታ በቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል ቢወጣ እንኳ የሚሰማ ጠፍቶ፣ ዛሬ ድረስ በትርፍ ፊደሎች መጻፍ ሙጥኝ ተብሎ እንደተያዘ ነው፡፡ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ሲሰጥ የቆየው የአማርኛ ትምህርት ከይስሙላ ያለፈ አለመሆኑ ብዙ ስህተቶች ልክ መስለው እንዲዘወተሩ አግዟል፡፡ ‹‹በዚህ አንፃር›› የመሠረት ትርጉሙ፣ ‹‹በዚህ ትይዩ/በዚህ ተቃራኒ›› የሚል ቢሆንም፣ ዛሬ ‹‹በዚህ አኳያ›› ማለት መስሏል፡፡ ‹‹የሰብዓዊ›› ትርጉምና ‹‹የሰውኛ›› ትርጉም ተቀላቅሎ ሞክሼ መስሏል፡፡ ‹‹ጎዶሎ›› ገላጭ ቃል ቢሆንም ‹‹ጉድለታችንን እናርም›› የሚለው ነባር አሰካክ ተገፍቶ፣ ‹‹ጎዶሏችንን እናርም›› ሲባል እንሰማለን፡፡ ‹‹ሰው›› እና ‹‹ሰዉ››፣ ‹‹መጽሐፍ›› እና ‹‹መጽሐፉ›› የማለት ያህል የትርጉም ልዩነት ያላቸው ቃላት ናቸው፡፡ ይህን የትርጉም ልዩነት ባወቀና በጠበቀ መልክ ‹‹ው›› እና ‹‹ዉ››ን መጻፍ ግን ቀውስ በቀውስ ሆኗል፡፡ ‹‹በላሁ፣ አየሁ›› ዛሬ ዛሬ ‹‹በላው፣ አየው›› ተብሎ መጻፉ ተበራክቶ፣ በ‹ሶሻል ሚዲያ› ላይ፣ በጋዜጣ ላይና በቴሌቪዥን የጥብጣብ ዜና ላይ ሁሉ ዘልቆ እናገኘዋለን፡፡ ‹‹እኔ በላው/አየው…›› እያሉ የሚጽፉ ሰዎች የቃላቱን ዕርባታ በጽሑፍ አማርኛ እንዳልተማሩ የሚጠቁም ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ አጻጻፍ ከቀጠለ በአንደኛ ሰውና በሦስተኛ ሰው መካከል ያለውን ‹‹በላሁ›› እና ‹‹በላው›› መለየት የማይቻልበት ሁኔታ መፈጠሩ አይቀርም፡፡

እነዚህ ቋንቋውን አጣርቶ ሳይማሩ የማሳሳት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ሌላም ዓይነት በ‹አዋቂ› አላዋቂዎች የሚሠሩ ስህተቶችም አሉ፡፡ የትኛውም ቋንቋ አካባቢያዊና ማኅበራዊ አሻራ ያላቸው ዘዬዎች አሉት፡፡ ቋንቋው መደበኛ እየሆነ (ቋንቋው የትምህርትና የጽሑፍ ቋንቋ እየሆነ) ሲመጣ ደግሞ ከማኅበራዊና ከአካባቢያዊ ዘዬዎች ውስጥ ከመለመድ ብዛት ወደ መደበኛው ዘዬ የሚገቡ አሉ፡፡ ይህንን ባህርይ ያልተገነዘቡና ራሳቸው የተቀረፁበትን ዘዬ ከሌላው ዘዬ ይበልጥ ልክ አድርገው የሚያስቡ ሰዎች በኅትመት ውስጥ አሰናጅ (‹‹አርታኢ››) ሆነው ሲመጡ፣ ስህተት ያልሆነውን እንደ ስህተት ቆጥረው ያርማሉ፡፡ ‹‹ገበና››ን በጽሑፍ ውስጥ ሲያገኙት ወደ ‹‹ገመና›› ይቀይራሉ፡፡ ‹‹ፋንታ››ን ‹‹ፈንታ›› ብለው ‹‹ያስተሳክላሉ››፡፡ ‹‹ስልሳ››ን በ‹‹ስድሳ›› ይቀይራሉ፡፡ ‹‹ብጤ››ን ‹‹ቢጤ››፣ ‹‹ይኸ››ን ‹‹ይኼ›› ብለው ‹‹ያርማሉ››፡፡ ይህን መሳዩ ‹‹አራሚነት›› የመልዕክት ልዩነት የማያመጣ ጥፋት ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ሰዎች፣ ዘዬ ማንነትን የመግለጽ ሥራም በሥነ ጽሑፍ ውስጥ እንዳለው ስለማይረዱ እነሱ የአራሚነት ወንበር በያዙበት ኃላፊነት ማንነትን እስከ ማረምም የሚሄድ ገልቱ ባለሙያነታቸውን ያሳያሉ፡፡ የአዲስ አበበ አራዳ ሆኖ የተሣለ የልብ ወለድ ሰው በሚናገረው ንግግር ውስጥ ‹‹ስልሳ››ን ‹‹ስድሳ›› ብሎ እንዲናገር፣ ‹‹ከንደገና››ን ሰርዘው እንደገና እንዲል፣ ‹‹ገረድ›› ያለ አንደበቱን ‹‹የቤት ሠራተኛ›› እንዲል ሲያደርጉ፤ ‹‹ወደድኩክ/እወድካለሁ›› ያለችውን ጉብል፣ ‹‹ወደድኩህ/እውድሃለሁ›› ሲያስብሉ ደራሲው የገነባውን ገፀ-ባህርይ የማፍረስ ሥራ ነው የሚሠሩት፡፡ የዚህ ዓይነት ጥፋት በሆነ ሰው መጽሐፍ ላይ አድርሶ፣ ሙያ እንደሠራ ሰው ስሙን ‹‹አርታኢ›› ብሎ ያስቀመጠ ሰው አውቃለሁ፡፡

የአማርኛ ሥርዓተ-ነጥብ ውስጥ ከገባን ደግሞ፣ አነጣጠባችን ቅጥ አምባሩ ጠፍቷል ማለት ይቻላል፡፡ የሥርዓተ-ነጥብ ደንቦች የቋንቋ ሊቃውንት ለየቋንቋው ይኸ በዚህ ደንብ፣ ይኸ በዚህ ደንብ ይተዳደር እያሉ የሚጽፏቸው ድንጋጌዎች አይደሉም፡፡ በየትኛውም ቋንቋ ዘንድ ከአንደበት የሚወጡ ንግግሮች በቃላት ብቻ የተገነቡ አይደሉም፡፡ መልዕክቶች የሚተላለፉት በቃላት ድርድር አማካይነት ብቻ አይደለም፡፡ ቃላት እየተቀናበሩ በሚሠሩት ትርጉማዊ ሠልፍ ውስጥ ትርጉም ጠርቶ እንዲተላለፍ የሚያግዙ የድምፅ አነሳስና አወዳደቅ፣ ፋታዎች፣ ዕረፍቶች፣ ስሜቶችና የአነጋገር አረጋገጦች አሉ፡፡ አንድ ቋንቋ በአንደበት ተነጋሪ ከመሆን አልፎ የሚጻፍ ቋንቋ ወደ መሆን ሲሸጋገር የቋንቋው መነጋገሪያ ድምፆች በፊደላት እንደሚወከሉ (እንደሚጻፉ) ሁሉ በዚያ ቋንቋ የንግግር ሥርዓት ውስጥ ትርጉም ጠርቶ ከሰው ወደ ሰው እንዲተላለፍ የሚያስተናብሩት የአነጋገር ፋታዎች፣ ስሜቶችና የአነጋገር ውጣ ውረዶች በሥርዓተ-ነጥቦች ይወከላሉ፡፡ በአጭሩ ነጥቦች እንዳሻ ማንም የሚፈነጭባቸው የጽሑፍ ምልክቶች ሳይሆኑ የሚነበቡ (ትርጉማዊ ሥራ ያላቸው) ነገሮች ናቸው፡፡

በየትኛውም ቋንቋ ውስጥ መልዕክቶች በሐረጎችና በዓረፍተ ነገሮች ይቀናበራል፡፡ በየትኛውም ቋንቋ ውስጥ ሐሳብን መተርተር፣ ዝርዝርን መቋጠር፣ ወሬ መንገር፣ መጠየቅ፣ መገረም፣ ቁጣ፣ ሹፈት፣ ወዘተ አለ፡፡ እነዚህን የመልዕክት ዘሮች በተቻለ መጠን በሥርዓተ-ነጥቦች ጠቋሚነት ለማስተላለፍም ይሞከራል፡፡ እናም፣ አነሰም በዛ በቋንቋዎች ያሉ ሥርዓተ-ነጥቦች ከቋንቋ ወደ ቋንቋ መገናዘብ ይችላሉ፡፡ በሆነ ቋንቋ ውስጥ ያሉ ሥርዓተ-ነጥቦች ያላቸውን አገልግሎት በቅጡ ያወቀ ሰው (ነጥቦች እንደሚነበቡ የገባውና በሚቻለው ሁሉ የነጥቦች አጠቃቀሙን መልዕክትን በደንብ ከማስተለለፍ አኳያ የሚለካ ሰው)፣ በሌላ ቋንቋ ውስጥም ሥርዓተ-ነጥቦች ያላቸውን ፋይዳ አስቀድሞ የተረዳ ያህል ነው፡፡ አነጣጠብ ከትርጉም ጋር ያለው መስተጋብር የደረቀ ነገር አይደለም፡፡ ‹‹ማሰሪያ ግስ የሌለው ሐረግ ዓረፍተ ነገር ሊሆን አይችልም/ባለቤትና ማሰሪያ ግስ ያለው ሐረግ ግን ዓረፍተ ነገር ነው›› የሚል የደረቀ ግንዛቤ ያላቸው ሰዎች አሉ፡፡ የመልዕክቶች ትልልፍ በዚህ ዓይነት የደረቀ ደንብ አይመራም፡፡ የነጥቦች አጠቃቀምም የደረቀ ግንዛቤን የሚከተል ሳይሆን የመልዕክት አፈሳሰስን የሚከተል ነው፡፡

አንድ ዓረፍተ ነገር ባለ ብዙ ቃላት ሊሆን እንደሚችል ሁሉ፣ ባለ አንድ ቃልም ሊሆን ይችላል፡፡ የዓረፍተ ነገር በአራት ነጥብም ሆነ በድርብ ሰረዝ የመጻፍ ነገር በቁመት አይወሰንም፡፡ ባለቤትና አሳሪ መሰል ግስ ያለው ሐረግም የግድ ዓረፍተ-ነገር ነው ሊባል አይችልም፡፡

  • በመዝገበ ቃላት የቃላት ትርጉም ድርደራ ውስጥ የመጣ ዓረፍተ ነገር መሰል የትርጓሜ ዝርዝር እንደ ማንኛውም ተራ ዝርዝር በነጠላ ሰረዝ (በአጭር ፋታ) ሊዘረዘር የሚችል ነው፡፡ ለምሳሌ፣ የ‹‹መገበ›› ትርጉም አበላ፣ ገበታ አጋራ፣ ማዕድ አካፈለ፣ ተብሎ ቢዘረዘር አነጣጠቡ ልክ ነው፡፡ ‹‹ሰው ደካማ ነው››/‹‹ዓለም ተለዋዋጭ ነች›› የሚሉ አባባሎች በየብቻቸው ዓረፍተ ነገር ሊሆኑ እንደሚችሉ ሁሉ፣ የአንድ ዓረፍተ ነገር ሐረጋዊ አገዳ ሆነውም ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ፣‹‹ሰው ደካማ ነው››፣ ‹‹ዓለም ተለዋዋጭ ነች›› የሚሉ ዕሳቤዎች የነተቡ ናቸው፡፡ ይህ አንድ ዓረፍተ ነገር ነው፡፡ መሀል ላይ የተቀመጠውም ነጠላ ሰረዝ ትክክል ነው (አንባቢው የተንጠለጠለ ፋታ እንጂ ዕረፍት እንዳያደርግ የሚመራ ነው)፡፡ በነጠላ ሰረዙ ፋንታ ድርብ ሰረዝ ወይም አራት ነጥብ የሚያደርግ ‹‹አራሚ›› አነጣጠብ ያልገባው ነው፡፡ ‹‹በእርማቱም›› ዓረፍተ ነገር የተደመደመ አስመስሎ መልዕክት ያወላክፋል፡፡
  • የአንድ ቁሳቁስ ወይም ነገር ስም ዓረፍተ ነገር የሚሆንበትም ሁኔታ አለ፡፡ ለምሳሌ፣ በተውኔትና በልብ ወለድ ቃለ ምልልሳዊ ጽሐፍ ውስጥ ‹‹ምን እየፈለግህ ነው?›› ለሚል ጥያቄ ‹‹ጭልፋ›› የሚል መልስ ቢሰጥ፣ ‹‹ጭልፋ፡፡›› አራት ነጥብን አይከለከልም፡፡ ጥያቄውን ተንተርሶ በውስጠ ታዋቂ ‹‹-እየፈለግሁ ነው›› የሚል ሐረግ ስላዘለ መልዕክት በብቃት አስተላልፋል፡፡
  • የሥርዓተ ነጥብን አጠቃቀም ሀሁ ያወቀ ሰው ሥራዬን በደንብ እሠራለሁ፤ ከሥራ ውጪ አነባለሁ፤ አሰላስላለሁ፤ እጽፋለሁ የሚሉ ዓርፍተ ነገሮችን በነጠላ ሰረዝ አይደረድራቸውም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ዓረፍተ ነገሮች በእንጥልጥል የሚዘረዝሩ ሳይሆኑ፣ ሐሳብን ዝግት ዝግት እያደረጉ የሚሮጡ መሆናቸውን መለየት መሠረታዊ ዕውቀት ነው፡፡
  • በአንድ ዓረፍተ ነገር ውስጥ በሚመጣ ዝርዝር ውስጥ ሌላ ዝርዝር ሲኖር፣ ለመልዕክት ትልልፍ እንዲቀና ትልቁን ዝርዝር በድርብ ሰረዝ እየለዩ የውስጠኛውን ዝርዝር በነጠላ ሰረዝ መለየትም በአማርኛ ሥርዓተ-ነጥብ ውስጥ መሠረታዊ ዕውቀት ነው፡፡ ለምሳሌ፣ በደንብ ልብ በል! የምትገዛልኝ ነገሮች፡- ከአትክልት ዘር ጎመን፣ ቆስጣ፣ ካሮት፤ ከጥራጥሬ ስንዴ፣ ባቄላ፣ ሽምብራ፤ ከበሰሉ ነገሮች ደግሞ እንጀራ፣ አንባሻና የተቀቀለ በቆሎ፡፡ ይህ ዓረፍተ ነገር በውስጠ ታዋቂ ‹‹ናቸው››ን ይዞ ሐሳቡን ይደመድማል፡፡ የተዘረዘሩት ነገሮች ሁሉም በቃል ሲነበቡ በአንድ ዓይነት አነጋገር አይደለም፡፡ በነጠላ ሰረዝ የተቀመጡት በእንጥልጥል ይዘረዘሩና ድርብ ሰረዞች ደግሞ ሐሳብ የመዝጋት ያህል የሆነ አጭር እረፍት ይደረግባቸዋል፡፡ በጽሑፉ ውስጥ ዝርዝሮቹ ሁሉ በነጠላ ሰረዝ ተቀምጠው ቢሆን ኖሮ፣ አንባቢው በየፈርጁ በየፈርጁ ሐሳቦችን ለማጤን የሚያስችል የአነጣጠብ ዕገዛ አያገኝም ነበር፡፡
  • ኑሮዋ ቢከሳ እንኳ ደግነት የማያልቅባት ሰው ነች፡፡ በአንድ ትንፋሽ ሊነገር የሚችል ዓረፍተ ነገር ነው፡፡ ተናጋሪው የሴትየዋን ደግነት አጠንክሮ ለመናገር ሲፈልግ አነጋገሩን ወደ እሚከተለው አሠላለፍ ሊቀይረው ይችላል፡፡ ከሰውም ሰው ነች፣ ኑሮዋ ቢከሳ እንኳ ደግነት የማያልቅባት፡፡ በዚህ ዓረፍተ ነገር ውስጥ በሰረዝ የተጠቆመው አጭር ፋታ ዓረፍተ ነገሩ አለማለቁን ከመጠቆም ይበልጥ ለአፅንኦት የሚደረግ ፋታን ይወክላል፡፡ የነጠላ ሰረዙን ቦታ ዓብይ ጭረት ቢይዘው ደግሞ አፅንኦቱ ይበልጥ ጠርቶ ይወጣል፡፡
  • በጥቅስ መልክ የተነገረ ነገር ሁሉ በጥቅስ ውስጥ የግድ አይቀነበብም፡፡ ለምሳሌ፣ቶሎ እንድትመጣ ተብያለሁና አልቀመጥም በሚል ዓረፍተ ነገር ውስጥ ‹‹ቶሎ እንድትመጣ›› በጥቅስ ምልክት ውስጥ መግባት አያስፈልገውም፡፡ ተናጋሪው መጥቀስ የፈለገው ንግግር የለውም፡፡ በጥቅስ መልክ ትዕዛዝ እንዳለበት መናገር ነው የፈለገው፡፡
  • የሥርዓተ-ነጥብ አጠቃቀም የደረቀ ደንብ ሳይሆን ለመልዕክት ፍካት የሚያገለግልና የሚታዘዝ መሆኑ የገባው ሰው በሚከተሉት ዓረፍተ ነገሮች ውስጥ ነጥቦቹ እየሠሩ ያሉትን ሥራ ለመረዳት አይቸገርም፡፡
  • እኔን የሚያህል ባለዕድሜ ‹‹አፈር አባክ ግባ!›› አለኝ እኮ፡፡ (በዚህ ዓረፍተ ነገር ውስጥ አውሪው በቁዘማ ዓይነት ስሜት ሲሆን፣ የኃይለ ቃል ስሜት ያለው ደግሞ ስድቡ ውስጥ ነው)፡፡
  • እኔን የሚያህል ሰው ‹‹አፈር አባክ ግባ›› ይበለኝ!! (ይህ ዓረፍተ ነገር ማሳየት የፈለገው ደግሞ የተሰዳቢውን ክፉኛ መበሳጨት ነው)፡፡
  • እኔን “አፈር አባክ ግባ”! (በዚህም ዓረፍተ ነገር ውስጥ ያለው አነጣጠብ ተናዳጁ ስድቡን የጠቀሰው ሰው መሆኑን የሚጠቁም ነው፡፡ የቃለ አጋኖን ምልክት ከጥቅስ ምልክት ውጪ ሲውል ዓይቶ የማያቅና መልዕክቱን ያልተረዳ ሰው ግን ‹‹ደንብ ተጣሰ›› ብሎ የቃለ አጋኖ ምልክቱን ጥቅስ ውስጥ ሊያስገባው ይችላል)፡፡

ለአንድ የማውቀው የአማርኛ መምህር ኃያል ምሥል ያለው ባለሁለት ስንኝ ግጥም አሳየሁት፡፡ መምህሩ ሁሏን ነገር ከደንብ አኳያ የሚፈትሽ ዓይነት ሰው ነበር፡፡ የወል ግጥም፣ ‹‹የሰንጎ መገንና››፣ ‹‹የሆያሆዬ›› ቤት ግጥሞችን የሚለካበትን ‹‹ማስመሪያ›› በመጠቀም የሰጠሁትን ግጥም ለካት፤ እንደገና ደግሞ ለካት፤ ግጥሚቱ ከእሱ ማስመሪያ ጋር አልስተካከል ስትለው፣ ‹‹ይኸማ  የግጥም መሥፈርት የማያሟላ ነው›› አለኝና አረፈ፡፡ ግጥሙ ከሥነ ቃል የተገኘ ነው ብለውም አላጎነበሰም፡፡ የራሱን ማስመሪያ በስህተተኛነት ከመጠርጠር ይልቅ ግጥሚቱን ስህተተኛ አደረገ፡፡ እንደዚህ ሰውዬ የማይጎብጡ ሰዎች በጋዜጣና በመጽሐፍ አሰናጂነት ሥራ ውስጥ አሉ፡፡ እኔ በተደጋጋሚ አጋጥመውኛል፡፡ ብዙ ጊዜም ታግሼ አልፍ ነበር፡፡ በሆነ ጽሑፌ ላይ የነበረ አነጣጠቤን ፍልስልሉን ከማውጣት የማይተናነስ ጥፋት ተደርጎ በማየቴም ነው ይህን የአነጣጠብ ሀሁ ማተት ውስጥ የገባሁት፡፡ በአንድ ቃልና በሁለት ቃላት የተገለጹ ዓረፍተ ነገሮች ውስጥ የነበሩ ድርብ ሰረዞች በነጠላ ሰረዝ ተቀየሩ፡፡ እንዲህ ያለ ስኬት ላይ ለመድረስ የሚከተሉን ነጥቦች ማጤን ያስፈልጋል የሚል ዓይነት ዓረፍተ ነገርን ተመርኩዘው በረዣዥሙ የተዘረዘሩና በውስጠ ታዋቂ ሐሳብ እየዘጉ የተቀመጡ ሐሳቦች ድርብ ሰረዛቸው ተነስቶ ነጠላ ሰረዝ ተደረገባቸው፡፡ ወደ ዝርዝር የሚመራውና በሁለት ነጥብ ከጭረት (፡-) የተቀመጠው መነሻ ዓረፍተ ነገር በአራት ነጥብ ቢቀየር እንኳ በአማረ ነበር፤ እሱም በነጠላ ሰረዝ ‹‹ታረመ››፡፡ እንዲህ የምታደርጉ ሰዎች ለመልዕክት የማይታዘዝ ደረቅ ማሰመሪያችሁን ወደ ቅርጫት ጥላችሁ በቅጡ የነጥቦችን ‹‹ዳይናሚክስ›› ብትማሩ ይሻላል፡፡

እንዲህ ያለ አላዋቂነትን የማመናመኑ መሠረታዊ ሥራ የሚሠራው ደግሞ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው፡፡ የነጥቦችንና የንግግርን ግንኙነት በደንብ የሚያሳይ ትምህርት ከተሰጣቸው ስለአነጣጠብ የሚያቁባቸው መንገዶች ብዙ ናቸው፡፡ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውን ሲማሩ፣ የፌዴራል ሥራ ቋንቋዎችንም ሆነ እንግሊዘኛን ሲማሩ ትምህርታቸው ይበለፅጋል፤ ይጠራል፡፡ያ ሁሉ ሆኖ የአነጣጠብ ሚስጥር ካልተጨበጣቸው በሁሉም በኩል ያገኙት ትምህርት ያጠያይቃል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...