Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየትግራይ ክልል ቀጣይ ሁኔታና የኃይሎች አሠላለፍ አንድምታ

የትግራይ ክልል ቀጣይ ሁኔታና የኃይሎች አሠላለፍ አንድምታ

ቀን:

በጊደና መድኅን

በመጀመርያ አገሬ ኢትዮጵያ ውድ ልጆቿ በከፈሉት መስዋዕትነት ሕወሓት ጥርሱ እንዲወልቅና ወደ ድርድር እንዲገባ በመደረጉ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም መስፈን የጀመረበት ጊዜ በመሆኑ እንኳን ደስ አለን። ሕወሓት ሽንፈቱን አምኖና ተቀብሎ ወደ ድርድር ሲመጣ ማየትን እኔ ዳግም እንደመወለድ እቆጥረዋለሁ።

በዚህ አጋጣሚ በሕወሓት አመራር በትግሉ ወቅት፣ በ27 ዓመቱ የሥልጣን ዘመኑና በአሁኑ ትርጉም አልባ ጦርነት ሕይወታችሁን ያጣችሁ፣ አካላችሁ የጎደለ፣ የታሰራችሁ፣ ወዳጆቻችሁን ያጣችሁ፣ ሀብት ንብረታችሁን ያጣችሁ፣ በአጠቃላይ ለሥቃይና ለመከራ የተዳረጋችሁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለከፈላችሁት መስዋዕትነት ክብር አለኝ። የሕወሓት መሪዎችም ቢሆን ቢሆን ወደ ፍትሕ አደባባይ ይቀርባሉ ብዬ እመኛለሁ፡፡ ካልሆነ ግን ለህሊናና ለፈጣሪ ፍርድ መቅረባቸው አይቀርም፡፡ የአገራችንን አሁናዊ ሁኔታ ለተመለከተ እንግዲህ ያልገመትነውና ያልጠበቅነው ፖለቲካዊ ኩነትና ክስተት እየተፈጠረ ይመስላል።

ግብዓት

  1. የፕሪቶሪያውና የናይሮቢው የሰላም ስምምነት ሕወሓትን በትግራይ ፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ሕይወት እንዲኖረው አድርጎታል። አቤት የሕወሓት ዕድል!
  2. በሚመሠረተው የትግራይ ክልል የሽግግር መንግሥት ውስጥ ሕወሓት ከኢፌዴሪ መንግሥት ጋር ቦታ ይኖረዋል።
  3. ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) በሪፖርተር ጋዜጣ በቅርቡ ሕወሓት ስሙ ከአሸባሪነት ዝርዝር እንደሚነሳ በገለጹት መሠረት በምርጫ ቦርድ የተሰጠውን የፓርቲነት ምስክር ወረቀቱ አይቀማም። ታዲያ ይህ ያልተጠበቀ “ክስተት” በትግራይ ፖለቲካዊ ገበያ ውስጥ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን?

በፀጥታ ላይ

ስምምነቱ ላይ እንደተቀመጠው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኃይል ውጪ ያሉት ሁሉ (Non-ENDF) ከትግራይ ብሔራዊ ክልል ግዛት ይወጣሉ ስለሚል፣ የኤርትራ ጦር ሠራዊትና የአማራ ክልል ኃይሎች እንዲወጡ ይደረጋል ማለት ነው። ይህ ጉዳይ ብዙ ጣጣዎች ስላሉት በቀላሉ የሚፈጸም አይመስለኝም። “ለምን?” የሚለው ፖለቲካዊ ትርጉሙ ላይ እናየዋለን።

በፖለቲካዊ ጉዳይ

በተለይ ከአማራ ክልል የፀጥታ ኃይሎች መውጣት ጋር ተያይዞ እጅግ ውስብስብ፣ ፈታኝና ከባድ ሁኔታ የሚገጥመው ይመስለኛል። ይህ ጉዳይ እጅግ ውስብስብ የሚያደርገው ከወልቃይት፣ ፀገዴ/ጠገዴና ሑመራ፣ እንዲሁም ከራያ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ታሪካዊ፣ ጂኦግራፊያዊ፣ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ውስብስብነትና ጣጣ ስላለው እጅግ ፈታኝ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ሁለንተናዊ የኃይሎች አሠላለፍም የራሱ አንደምታ ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል። በተለይም፣

  1. በ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅና ሲፀድቅ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትን ግዛታዊ አቀማመጥና ዳርቻ ሲያመላክት አከራካሪዎቹ ወልቃይትን፣ ፀገዴ/ጠገዴን፣ ሑመራንና ራያ/አላማጣን በትግራይ ክልል እንዲካተቱ በማድረግ በተለምዶ ደርግ በሚባለው በኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዴሪ) መንግሥት፣ የትግራይ ክፍለ ሀገር ግዛት ሥር እንደነበሩ የሚታወቁትን የእንደርታና የኽልተ አውላዕሎ አውራጃዎች አካል የነበሩትን አብዓላ (ሽኸት)ን፣ ዳሎልን ሕወሓት/ኢሕአዴግ አዲስ ባቋቋመው የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሥር ከተታቸው። ስለዚህ በትግራይ ክፍለ ሀገር ሥር የነበሩ ወረዳዎችንም ለሌላ ሰጥቷል፡፡ በደርግ ጊዜ በበጌምድርና በወሎ ክፍለ ሀገሮች ውስጥ የነበሩ ወረዳዎችንም ወደ ትግራይ ክልል አካቷል ማለት ነው። በበጌምድርና በወሎ ክፍለ ሀገሮች ሥር የነበሩትን ግዛቶች፣ ሕገ መንግሥቱ ሳይፀድቅ ወደ ትግራይ ክልል እንደተካለሉም ይነገራል።
  2. ከዚህ ጋር ተያይዞ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ፣ በተለይም በ27 ዓመታት ሥልጣን ዘመኑ በሕዝባዊ አመፅ በተናጠባቸው የመጨረሻዎቹ አሥር ዓመታት በእዚህ ግዛቶች ከፍተኛ ጥያቄና ሕዝባዊ እንቢተኝነት ሲነሳባቸው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ከዚያም የሕወሓት አገዛዝ ተመቶ ወደ መቐለ ከሸሸ በኋላ፣ ብሎም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የሰሜኑ አጥር ጠባቂ የነበረውን የመከላከያ ሠራዊታችንን በግፍ ካጠቃው በኋላ ወልቃይት፣ ፀገዴ/ጠገዴ፣ ሑመራ፣ ራያ አላማጣ፣ ወዘተ. በአማራ ክልል ቁጥጥርና አስተዳደራዊ ግዛት ውስጥ ገብተው ይገኛሉ።
  3. ስለዚህ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት፣ “ሕገ መንግሥቱ ይከበራል” ሲባል ግዛቶችም ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበሩበት ሁኔታ (Status Quo Ante) ይመለሳሉ ማለት ነው። እንግዲህ እዚህ ላይ ነው እጅግ ፈታኝ ፖለቲካዊና ወታደራዊ እንቅፋቶች ይገጥማሉ ተብሎ የሚጠበቀው። አንደኛው ኃይል እነዚያ ወደ ትግራይ ክልል የተጨመሩት አካባቢዎች ከሕገ መንግሥቱ መፅደቅ በፊት በጉልበት የተወሰዱ ናቸው ብሎ ስለሚያምን፣ ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ የአማራ ክልል አካል ሆነው በዚህ ክልላዊ መንግሥት እንዲተዳደሩ በማድረግ እያስተዳደራቸው ይገኛል።

የአማራ ክልል ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ፋኖ ይህንን አካባቢ ለመቆጣጠርና የሕወሓት ኃይልን ለመምታት ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል። ስለሆነም በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት፣ ሕገ መንግሥቱ እንዲከበር የሚለውን የስምምነቱ ዕሳቤ እነዚህን አካባቢዎች ወደ ትግራይ ክልል እንዲካተቱ የሚያስገድድ ስለሆነ በአማራ ክልል ባለሥልጣናት፣ የፀጥታ ኃይሎች፣ ፖለቲከኞችና ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል ብሎ ማሰብ የዋህነት ይመስለኛል። በዚያውም መጠን የኃይል አሠላለፉን ይቀይረዋል ብሎ ማሰብ የኑክሌር ሳይንቲስት መሆንን አይጠይቅም።

  1. ሌላው ኃይል የኤርትራ መንግሥት የመከላከያ ሠራዊት ሲሆን፣ ወደ ትግራይ የገባበት ጊዜና ሁኔታ አከራካሪ ቢሆንም፣ የሕወሓት ኃይል ወደ አስመራ ሚሳይሎች ይተኩስ እንደነበር የሚታወስ ነው። አንዳንድ ሰዎች የሻዕቢያ ጦር ወደ ትግራይ መግባትን ሥጋት አለብኝ ብሎ በአቶ መለስ ዜናዊ ትዕዛዝ ወደ ሶማሊያ የገባው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር ያመሳስሉታል። ያኔ አቶ መለስ ከሶማሊያ ውስጥ በነበሩ የሃይማኖት አክራሪ ተዋጊዎች ለአገራችን ሰላም ጠንቅ ናቸው በሚል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ይሁንታ በማግኘት ወደ ሶማሊያ እንዲገቡ ማድረጋቸውን፣ የኤርትራ መንግሥት ከሕወሓት ይሰነዘርበት የነበረውን ሚሳይልና ዛቻ ለኤርትራ ሰላምና ደኅንነት ሥጋት ነው ብሎ ጦሩን ማዝመቱ ልክ ነው ይላሉ።

በሌላ በኩል ድንበሩን ለ20 ዓመታት የጠበቀውን የሰሜን ዕዝ በሕወሓት በመጠቃቱ፣ የኤርትራ ጦር ሰተት ብሎ እንዲገባ ሕወሓት ራሱ አመቻችቶለታል ይላሉ። ያም የሆነ ይህ አሁን ፕሪቶሪያ በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሠረት የኤርትራ ጦር መውጣቱ የግድ ስለሆነ፣ ይህ ኃይልም በዚህ ስምምነት መገዛቱ ያስቸግራል የሚሉ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም። በመሆኑም የኤርትራ መንግሥት ከኢፌዴሪ መንግሥት ይልቅ ከአማራ ክልል ጋር የበለጠ ሊወዳጅና ከኢትዮጵያ መንግሥት በተቃራኒው ሊሠለፍ ይችላል ይላሉ አንዳንድ ተንታኞች፡፡

  1. ሌላኛው ለመገመትም ይሁን ይሆናል ተብሎም የማይጠበቀው ፖለቲካዊ ቢሆን (Political Scenario)፣ የወልቃይትና የራያ ጉዳይ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ከጦርነቱ በፊት እንደነበረው ወደ ትግራይ ክልል ግዛት የሚካለል ከሆነ በእርግጠኝነት የኃይል አሠላለፉ ይቀየራል። ወዳጅ የነበረው ጠላት፣ ጠላት የነበረው ወዳጅ ይሆናል። በመሆኑም የአማራና የኤርትራ ኃይሎች ከኢፌዴሪ መንግሥት በተቃራኒው የሚሠለፉበት ዕድል ሰፊ ነው።

ሕወሓትም በእነዚህ ኃይሎች ካለው ቂም ተነሳስቶ ከኢፌዴሪ ጋር ሊሠለፍ ይችላል። መሠለፍ ብቻ ሳይሆን የሕወሓት ታጣቂዎች፣ የአማራንና የኤርትራን ኃይሎች ለመምታት ሊውሉ ይችላሉ። ይህ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ፍጥጫ የኤርትራ መንግሥትን እስከ መቀየርና ቀይ ባህርን ተቆጣጥሮ፣ የምዕራብ ኃያላን አገሮች የሚቆጣጠሩት መንግሥት በአስመራ እስከ መትከል ድረስ የሚሄድና ይህንን ቀጣናዊ ገዥ አካባቢ በቁጥጥራቸው ሥር ሊያውሉት ይችላል ተብሎ ይገመታል።   

አዲሱ የትግራይ ክልል የሽግግር መንግሥት

እንግዲህ በስምምነቱ ላይ እንደተመለከተው ገዥው ፓርቲና ሕወሓት በዋነኛነት ያሉበት የሽግግር መንግሥት በመቐለ ይቋቋማል ተብሎ ይጠበቃል። እዚህ ላይ በኢፌዴሪ መንግሥት (ብልፅግና ፓርቲ) በኩል ያሉ ሕጋዊ ተፎካካሪ ፓርቲዎች (ዓረና፣ ትዴፓ፣ ኢዜማ፣ ራዴፓ፣ ራዕይ) እና በመቐለ የከተሙት ፓርቲዎች (ባይቶና፣ ውናት፣ ሳልሳይ ወያነ፣ ዓሲምባ) በዚህ የሽግግር መንግሥት ይሳተፉ አይሳተፉ ያልታወቀ ሲሆን፣ መቼ ተመሥርቶ መደበኛ ሥራውን እንደሚጀምርም አልተነገረም።

ያሉ መላ ምቶች በተለይም ከሕወሓት የ48 ዓመታት የፖለቲካ ሕይወት ሕወሓትን አምኖ፣ በአንድ ክልል ውስጥ በተመሳሳይ ክልላዊ መንግሥት መዋቅር ሥር መሥራት ይከብዳል የሚሉ ፖለቲከኞች አያሌ ናቸው።

አዲሱ የትግራይ ክልል ፖለቲካዊ ምኅዳር ምን ይምሰል?

ሕወሓት ላለፉት 48 ዓመታት በሽምቅ ተዋጊነትና በመንግሥትነት በትግራይ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ናኝቶበታል። በብቸኝነት የፖለቲካ ገበያው ዘዋሪ ብቻ ሳይሆን ቀያሽና መሐንዲስ ነበር። ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ክልላዊ መንግሥታዊ ቅርፅ ድረስ በእሱ ዕሳቤና ቡራኬ ሲዘወር ቆይቷል። ነገር ግን በአብዮታዊ ዴሞክራሲና ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ሥር የሰነበተው የትግራይ ክልል ፖለቲካዊ ግዛት የሐሳብ አማራጭን፣ ብዝኃነትን፣ ልዩነትን፣ ተቃውሞን የማይሸከምና የማይቀበል ነበር። ይካሄዱ የነበሩት “ምርጫዎችም” በከፍተኛ ቁጥጥርና ጣትን ይዞ ንቢቱ ላይ እስከ ማስፈረም የሚሄድ እጅግ አምባገነንነት የሰፈነበትና ብቻውን ተወዳድሮ ብቻውን የሚያሸንፍበት የምርጫ ቴአትር ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም።

በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ከአሁን በፊት ሕወሓቶች የራሳቸውን የምርጫ ቦርድና ኮሚሽነሮች በመሾም ያካሄዱትን የጨረባ ምርጫ ተቀባይነት እንደሌለውና በዚህም መሠረት ያቋቋሙት ክልላዊ ምክር ቤትና መንግሥት እንደሚፈርሱ ይታሰባል። በሒደትም ነፃ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ ክልላዊ ምርጫ እንደሚካሄድ ይጠበቃል። በመሆኑም አዲስ የፖለቲካ ባህልና ሰሰማዊ አብዮት መካሄድ አለበት ብሎ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ያምናል።

በትግራይ ክልል ፋና ወጊና አዲስ የፖለቲካና የዴሞክራሲ ሒደት መጀመሩ ለትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን፣ ለአገራችን ኢትዮጵያም ታላቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስረግጦ መናገር ያስፈልጋል። ታዋቂው የሰው ልጅ መብቶች ተሟጋቹ ማርቲን ሉተር ኪንግ (ዶ/ር) ‹‹የሆነ ቦታ የሚከሰተው ኢፍትሐዊነት፣ ማንኛውም ቦታ ላለው ፍትሕ ሥጋት ነው፤›› ብለው ባስረገጡት መሠረት፣ ትግራይን ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ማኅበራዊ ፍትሕ የሰፈነባት፣ ኢኮኖሚያዊ ብልፅግናዋ የሚረጋገጥባት ክልል ማድረግ ለነገ የማይባል ሥራ ነው።

በተለይም ሕዝባዊ ሥልጣን በጥይት (Bullet) ሳይሆን በኮሮጆ (Ballot) ብቻ የሚወሰንባት፣ እንዲሁም የትግራይ ሕዝብ እንደራሴዎቹን በነፃነት የሚሾምባት ክልል ማድረግ እንደ ሕወሓት ያሉ ጦረኛና አምባገነን ቡድኖች ከፖለቲካ ምኅዳሩ እየከሰሙ እንዲሄዱ በማድረግ፣ የትግራይ ብሎም የኢትዮጵያ ሰላምና ብልፅግና ይረጋገጣል።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው goldenethiopiagid@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...