ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ዋዜማ አመሻሽ ላይ በግ ለመግዛት ወደ ሾላ ገበያ ብቅ ብዬ ነበር፡፡ የሾላ ገበያና እኔ ትውውቃችን በትንሹ 30 ዓመት ይሆነዋል፡፡ በዓላት በደረሱ ቁጥር ለበግ ወይም ለፍየል ግዥ የምሄደው ሾላ ገበያ ነው፡፡ በ1985 ዓ.ም. በ80 ብር የገዛሁት ሙክት በ1995 ዓ.ም. 300 ብር ነበር የተሸጠው፡፡ በአሥር ዓመት ውስጥ የ220 ብር የዋጋ ጭማሪ መታየቱ በወቅቱ ገዥዎችን ብቻ ሳይሆን ሻጮችን ጭምር ያነጋገረ እንደነበር አይዘነጋኝም፡፡ ደም አፋሳሹ ምርጫ 97 ታልፎ በነበሩ ዓመታት እንደ ሮኬት ወደ ላይ የሚወነጨፈው የኑሮ ውድነት፣ በ2000 ዓ.ም. የሚሊኒየም በዓል ማግሥት የበለጠ ተባብሶ ለገና በዓል ለመጀመሪያ ጊዜ የበግ ሙክት አንድ ሺሕ ብር ሲሸጥ የዓለም መጨረሻ የደረሰ ነበር የመሰለን፡፡
ከዚያ በኋላ ባሉት 15 ዓመታት ለሙክት ሳይሆን ለጠቦትም ሆነ ለወጠጤ በሺዎች ቤት ዋጋ መጥራት ተለመደ፡፡ የበግ ገበያ የዋጋ አጠራር (15፣ 20፣ 30፣ 40፣ 80…) ተቀይሮ ዛሬ እዚህ ግባ የማይባል ፍየል ወይም በግ ከአሥር ሺሕ ብር በላይ ዋጋ እየተጠራበት ነው፡፡ በቀደም ዕለት እንደተለመደው መካከለኛ ከሚባሉት በጎች ጀምሮ ዋጋ መጠየቅ ስጀምር፣ ‹‹አሥራ ሁለት ሺሕ፣ አሥራ አራት ሺሕ፣ አሥራ አምስት ሺሕ…›› እያሉ ነጋዴዎቹ በሙሉ ዋጋ ሲጠሩ እንደ ቀልድ ነበር፡፡ ማን ነበር ‹‹ደመወዛችን ሃምሳ ጉዳያችን መቶ›› ያለው ያኔ በደጉ ዘመን፡፡ አሁንማ ገቢያችንን የሚያስንቅ የኑሮ ውድነት የሚሉት ሰደድ እሳት ላያችን ላይ እየነደደ እንዴት እንደምንሆን እንጃ ያስብላል፡፡
አንዲት እናት ከገበያ መልስ፣ ‹‹አምላኬ እባክህን ይቅር ብለኸን ታረቀን…›› እያሉ ወደ ቤታቸው ሲሄዱ መንገድ ላይ አገኘኋቸው፡፡ ‹‹እናቴ ምን ገጥመዎት ነው አምላክዎን እያነጋገሩ ያሉት…›› በማለት ቀረብ አልኳቸው፡፡ በቀኝ እጃቸው የያዙትን ዘንቢል እያመለከቱኝ፣ ‹‹ይኼ ዘንቢል ዕድሜ ልኩን ከእኔ ጋር ነው የኖረው፡፡ ድሮ በደጉ ዘመን በ20 ብር ይሞላ የነበረ ዘንቢል አሁን በ1,500 ብር የያዘውን ተመልከት፡፡ አንዲት ዶሮ፣ ቅመማ ቅመምና የወይራ እንጨት ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ደግሞ ሩብ የሚሆነውን የዘንቢል አካል አልሞሉትም፡፡ እሱ ባለቤቱ ዘንድሮ ካልታረቀን በቀር ከዚህ እሳት ከሆነ ኑሮ ማንም አያስጥለን…›› እያሉ መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡
እናቴ ፈጣሪ ነፍሷን በአፀደ ገነት ያሳርፈውና በ1977 ዓ.ም. በአንዱ ቀን መርካቶ ውላ ስትመጣ ለመቀበል እኔና ወንድሜ አውቶቡስ ፌርማታ ስንጠብቃት ሳለ፣ የተሳፈረችበት የአንበሳ አውቶቡስ ደርሶ ሰዎችን ሲያራግፍ በሁለት ወጣቶች ዕርዳታ አንዳች የሚያህለው ዘንቢሏ ሲወርድ ተሯሩጠን ተቀበልናት፡፡ እኔና ወንድሜ መርካቶ ስለነበረው ውሎዋ እየጠየቅን ያንን በሸቀጦች የተሞላ ዘንቢል ተሸክመን ወደ ቤት ስናመራ፣ ‹‹ልጆቼ ድሮ በአሥር ብር ይሞላ የነበረ ዘንቢሌ ይኸው እንደምታዩት ሰላሳ ብር ፈጀ… ለማንኛውም እሱ አምላካችን ይታረቀን እንጂ የወደፊቱ ነገር ያስፈራል…›› ያለችን ፈፅሞ አይረሳኝም፡፡ ያንን አንዳች የሚያህል የሰሌን ዘንቢል ዛሬ በሰላሳ ሺሕ ብር ለመሙላት የሚቻል አይመስለኝም፡፡
ባለፈው ሰሞን ትዝ ይላችሁ እንደሆነ ባለ አምስት ሊትሩ ዘይት በአንዴ አንድ ሺሕ ብር ሲገባ የነበረው ድንጋጤ አይዘነጋም፡፡ ይኸው እሱም ተረስቶ ሕይወት ቀጥሎ ኑሮ እየለበለበን ነው፡፡ የሌሎች ምርቶች ዕለታዊ የዋጋ ጭማሪ ሳይዘነጋ ማለት ነው፡፡ ሰላሳ ስምንት ያህል ከውጭ የሚመጡ ምርቶች ጊዜያዊ ገደብ ተጥሎባቸው በነበረ በማግሥቱ ዶቭ ሳሙና ለመግዛት መደብር እሄዳለሁ፡፡ ከሦስት ቀናት በፊት የገዛሁት ሳሙና በሦስት እጥፍ ዋጋው ጨምሯል፡፡ ባለመደብሩን ምነው ስለው፣ ‹‹በገደቡ ምክንያት ምርቱ እየጠፋ በመሆኑ፣ ከቦታው ማግኘት ስላልተቻለ በውድ ዋጋ ገዝተን ነው የምሸጠው…›› ብሎ የአቅርቦትና የፍላጎት የኢኮኖሚ ትንተናውን ሲጀምር ትቼው ሄድኩ፡፡ ሌሎች ሸቀጦችም በአቅርቦት እጥረትና የአቅርቦት ሰንሰለቱ በጥቂቶች ተጨምድዶ መያዝ ምክንያት በየቀኑ ብቻ ሳይሆን፣ በየሰዓቱ ዋጋቸው ወደ ላይ እየተተኮሰ መከራችንን እያየን ነው፡፡
እኔ ‹‹አይ ድሮ…›› እያልኩ ለማላዘን አይደለም ይህንን ገጠመኝ የምጽፈው፡፡ ይልቁንም ይህንን አደገኛ የኑሮ ውድነት እንዴት እንቀልብሰው የሚል መፍትሔ ፍለጋ ያስፈልጋል ለማለት ነው፡፡ እርግጥ ነው በዓለም አቀፍ ደረጃ የኑሮ ውድነቱ ከፍተኛ ችግር የፈጠረ መሆኑን ብረዳም፣ እኛ ግን በገቢም ሆነ በአጠቃላይ የኑሮ ሁኔታችን ሌላው ቀርቶ ከሰሃራ በታች ካሉት በኢኮኖሚ ደካማ ከሆኑት የአፍሪካ አገሮች ሳይቀር በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ስለሆንን፣ ከማንም በላይ እየተደቆስን ለመሆኑ እማኝ መጥራት ያለብኝ አይመስለኝም፡፡ ይህችን የመሰለች የምድር ገነት አገር ይዘን ለምን እንራባለን? ለምን ለማያባራ የዋጋ ጭማሪ እንዳረጋለን? ከዚያም አልፎ ተርፎ ችግራችንን ለማስወገድ ለምን መሥራት አቃታን? ወዘተ ስንል አንድ ችግር ገዝፎ ይታየኛል፡፡
የኑሮ ውድነቱንም ሆነ ሌሎች ችግሮችን መንግሥት ይቀርፍልናል ብለን የምናደርገው ወሰን አልባ ጥበቃ መቆም አለበት፡፡ ይልቁንም መንግሥት የሚባለው አካል ራሱን በብቁ አመራሮች፣ ዕውቀትና ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች ታግዞ ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲያወጣ ግፊት ማድረግ አለብን፡፡ የኢኮኖሚ አመራሩ በካድሬ ወይም የረባ ልምድ በሌላቸው አማተሮች ሳይሆን፣ በተግባር ሊፈተን የሚችል ልምድ ባላቸው የዕውቀት ሰዎች እንዲያዝና የተፈጥሮ ፀጋዎቻችንን በአጭር ጊዜ ለበረከት ለማብቃት የሚያስችል ሥራ መከናወን ይኖርበታል፡፡
ሰፊ ለም መሬት፣ ከፍተኛ የውኃ ሀብት፣ በርካታ ማዕድናት፣ በአፍሪካ ወደር የሌለው የቀንድ ከብት፣ ሰፊ የቱሪዝም ሀብቶች፣ ለሥራ ብቁ የሆነ የሰው ኃይልና ሌሎች ፀጋዎችን ታቅፎ በማይረቡ የፖለቲካ ንትርኮች ጊዜን ማጥፋት መቆም አለበት፡፡ የረባ ምግብ፣ ልብስ፣ መኖሪያ፣ ሕክምና፣ ትምህርትና ሌሎች አገልግሎቶች የሌላት አገር ውስጥ እየኖሩ መሠረታዊ የኢኮኖሚ ለውጥ ማድረግ አለመቻል ለባሰ ድህነት ይዳርጋል፡፡ በዓላት በደረሱ ቁጥር በማዕድ ማጋራትና በገበያ ተቆጣጣሪ ግብረ ኃይል እርስ በርስ እየተዳለሉ ለመቀጠል መሞከር፣ ራስን በራስ ከማጥፋት የማይተናነስ አውዳሚ ድርጊት ነው፡፡ ስለዚህ እንደ ወርቅ በእሳት የተፈተኑ ተሞክሮዎችን በመቀመር ኢትዮጵያን የልማት አምባ ማድረግ፣ ካልሆነ ደግሞ እጅን አጣጥፎ የሚመጣውን መዓት መቀበል ዕጣ ፈንታችን መሆኑን በመረዳት ለመፍትሔ በአንድነት እንነሳ፡፡
(ዘውዳለም ደምሴ፣ ከእንግሊዝ ኤምባሲ አካባቢ)