Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ ወርቅ የሚረከብበትን ዋጋ ለማሻሻል በቀረበለት የውሳኔ ሐሳብ ላይ ሊወስን መሆኑ ተጠቆመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብሔራዊ ባንክ ከአገር ውስጥ አምራቾች ወርቅ የሚገዛበትን ዋጋና አጠቃላይ የወርቅ ግብይት ሥርዓትን ለማሻሻል በቀረበለት የውሳኔ ሐሳብ ላይ ሊወስን ነው።

የወርቅ ግብይት ሥርዓትን በአጠቃላይ ለማሻሻል እንዲሁም አሁን እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለይቶ የመፍትሔ ሐሳብ ለማቅረብ፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና ከማዕድን ሚኒስቴር በተወጣጡ ባለሙያዎች የተዋቀረ የጥናት ቡድን አጭር የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ፣ የተለያዩ የመፍትሔ አማራጮችን ያካተተ የውሳኔ ሐሳብ ለባንኩ ማቅረቡን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

በውሳኔ ሐሳቡ ከተመለከቱት አማራጮች አንዱ ከጥቅምት እስከ ኅዳር 2015 ዓ.ም. በሕጋዊ የዶላር ምንዛሪና በጥቁር ምንዛሪ ተመን መካከል የተመዘገበውን የ75 በመቶ ልዩነት ታሳቢ በማድረግ፣ በዓለም አቀፍ የወርቅ ገበያ ዋጋ ላይ 75 በመቶ ጨምሮ በማስላት ብሔራዊ ባንክ የአገር ውስጥ ወርቅ እንዲገዛ የሚል ነው።ብሔራዊ ባንክ ወርቅ የሚረከብበትን ዋጋ ለማሻሻል በቀረበለት የውሳኔ ሐሳብ ላይ ሊወስን መሆኑ ተጠቆመ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ሁለተኛው አማራጭ የመግዣ ዋጋ ደግሞ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የሚመዘገበውን አማካይ የውጭ ምንዛሪ ተመን ልዮነት ታሳቢ በማድረግ፣ በዓለም አቀፍ ዋጋ ላይ የ85 በመቶ ጭማሪ በማስላት ብሔራዊ ባንክ እንዲገዛ የሚል መሆኑን ሪፖርተር ካገኘው የሰነድ መረጃ ለመረዳት ችሏል።

የተዋቀረው አጥኚ ቡድን ያቀረበው የጥናት ጭብጥ በባህላዊ አምራቾች ተመርቶ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚቀርበው የአገር ውስጥ የወርቅ መጠን፣ ከዓመት ዓመት በአሳሳቢ ደረጃ እየቀነሰ መምጣቱ፣ ከዚህም አገሪቱ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ በእጅጉ መጎዳቱ ነው። 

እንደ ጥናት ቡድኑ ትንታኔ፣ የአገር ውስጥ የወርቅ አቅርቦትን እየወሰኑ ካሉት ምክንያቶች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው የውጭ ምንዛሪ ተመን ልዩነት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ ውስጥ በሚታየው የውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ በሕጋዊው የውጭ ምንዛሪ ተመንና በሕገወጡ ምንዛሪ ተመን (በጥቁር ገበያው) መካከል የሚስተዋለው ከፍተኛ ልዩነት፣ የአገር ውስጥ ወርቅ አምራቾች ያመረቱትን ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ የመሸጥ ሕጋዊ ግዴታቸውን ወደ ጎን ትተው በሕገወጥ መንገድ ከአገር በማውጣት እንዲሸጡ እያበረታታ መሆኑን አጥኚ ቡድኑ ለይቷል። 

ይህንን ሁኔታም አጥኚ ቡድኑ በዝርዝር ዳሶታል። የቡድኑ የጥናት ግኝት እንደሚያመለክተው ባለፉት ስድስት ዓመታት ለብሔራዊ ባንክ የቀረበው የወርቅ መጠንና በዓለም ገበያ ተሽጦ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ በንፅፅር ሲታይ፣ በ2019 የቀረበው የወርቅ መጠንና የተገኘው የውጭ ምንዛሪ በእጅጉ ዝቅተኛ ነበር። 

እ.ኤ.አ. በ2019 አምስት ወራት ውስጥ የቀረበው ወርቅ በዓለም ገበያ ተሸጦ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ 8.4 ሚሊዮን ዶላር አንደነበር ሰነዱ ያመለክታል። በዚህ ዓመት በነበረው ዝቅተኛ የወርቅ አቅርቦትና የውጭ ምንዛሪ ገቢ ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይከፍል የነበረውን የአምስት በመቶ ማበረታቻ በመከለስ እ.ኤ.አ. ከሚያዚያ 2020 ጀምሮ የሚቀርብለት የወርቅ መጠንን መሠረት በማድረግ በዓለም አቀፍ ዋጋው ላይ ከአሥር እስከ 29 በመቶ የማበረታቻ ክፍያ በመክፈል የአገር ውስጥ መረከብ ጀምሯል። በዚህም ምክንያት እ.ኤ.አ. በ2020/2021 አምስት ወራት ውስጥ የቀረበለት የወርቅ መጠን በከፍተኛ መጠን በመጨመሩ 306 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደተገኘ ሰነዱ ያመለክታል። በ2021/2022 አምስት ወራት የተገኘው ገቢ ከቀደመው ዓመት ዝቅ ብሎ 180 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ሰነዱ ይገልጻል። ከዚህ ወቅት በኋላ ደግሞ የወርቅ አቅርቦቱና የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ቅናሽ እያስመዘገበ በመሄድ በ2022/2023 አምስት ወራት፣ ከወርቅ የተገኘው ገቢ ከቀደመው ዓመት በ81 በመቶ በማሽቆሎቆል 33.2 ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንደተገኘ ሰነዱ ያብራራል።

ከዚህም በመነሳት የአገር ውስጥ ወርቅ አቅርቦት በሕጋዊው የዶላር ምንዛሪ ተመንና በጥቁር ገበያ መካከል ባለው ልዩነት የሚወሰንበት ሁኔታ መፈጠሩን የጥናት ግኝቱ ይገልጻል።

‹‹ምንም እንኳ ብሔራዊ ባንክ በተጠቀሰው ወቅትም ሆነ አሁን ከአገር ውስጥ ወርቅ አቅራቢዎች የሚገዛበት ዋጋ ከዓለም የወርቅ ገበያ የ35 በመቶ ብልጫ ያለው ቢሆንም፣ የአገር ውስጥ ወርቅ አቅራቢዎች በጥቁር ገበያው የዶላር ምንዛሪና በሕጋዊው የምንዛሪ ተመን መካከል ባለው ከፍተኛ የዋጋ ልዩነት ሳቢያ፣ ያመረቱትን ወርቅ በኮንትሮባንድ ከአገር ውጪ በመሸጥ የበለጠ ገቢን ማግኘት እንዲመርጡ አድርጓል፤›› በማለት አጥኚ ቡድኑ የደረሰበትን ድምዳሜ በውሳኔ ሐሳቡ አመላክቷል።

አጥኚ ቡድኑ በሰጠው ማጠቃለያ የውሳኔ ሐሳብም ‹‹ከላይ ከቀረቡት ሁለት አማራጮች የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ሲባል ብቻ ሁለተኛውን አማራጭ ማለትም በዓለም አቀፍ የወርቅ ገበያ ዋጋ ላይ የ85 በመቶ ማበረታቻ በየስድስት ወሩ እየተከለሰ ለሁሉም ወርቅ አቅራቢዎች በተመሳሳይ ደረጃ ባንኩ እንዲተገብር የሚል ሐሳብ እናቀርባለን፤›› ብሏል።

ነገር ግን ይህ አማራጭ በብሔራዊ ባንክ በጀትና በአገሪቱ የገንዘብ ፖሊሲ ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚያስከትል አጥኚ ቡድኑ አመልክቷል።

ሁለተኛውን አማራጭ ተቀብሎ ቢወስን በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ለአጠቃላይ ለወርቅ መግዣ 10.1 ቢሊዮን ብር ሊያወጣ እንደሚችል፣ ይህም ከነባሩ የማበረታቻ ወጪ አንጻር የስድስት ቢሊዮን ልዩነት እንደሚኖረው ገልጿል።

በመሆኑም ይህ የሚያስከትለውን ጫና ግንዛቤ መወሰድ እንደሚገባ አጥኚ ቡድኑ ያሳሰበ ሲሆን፣ ለዚህ መፍትሔ ይሆናል ያለውንም የመፍትሔ ሐሳብም አካቶ አቅርቧል።

‹‹በዚህም በባንኩ ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ በጣም ከፍተኛ ስለሆነ፣ እንደ መፍትሔ የሚቀርበው፣ ሁለተኛው አማራጭ ዋጋ ተግባራዊ ከሆነ ብሔራዊ ባንክ ለውጭ ገበያ አቅርቦ ከሚሸጠው ወርቅ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ በተለየና ለዚህ ተብሎ በሚከፈት የባንክ ሒሳብ ውስጥ በማስቀመጥ፣ ያገኘውን የውጭ ምንዛሪ የባንኩን ኪሣራ በሚቀንስ መልኩ ለውጭ ምንዛሪ ፈላጊዎች በጨረታ መልክ መሸጥ የሚቻልበትን መንገድ ቢያመቻች የሚደርስበትን ጫና መቀነስ ይችላል›› የሚል የመፍትሔ ሐሳብ በአጥኚ ቡድኑ ቀርቧል።

በተጨማሪም ሁለተኛው አማራጭ ውጤታማ እንዲሆን የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች የኮንትሮባንድ ንግድን ለመቀነስ የሚያስችል የቁጥጥር ሥራ በልዩ ሁኔታ ማከናወን እንዳለባቸውም አሳስቧል።

ይህ ካልተሰራ ወደ ብሔራዊ ባንክ ሊመጣ የሚችለው የወርቅ መጠን ጊዜያዊ ጭማሪ ብቻ ሊያሳይ የሚችል በመሆኑ መታየት እንዳለበት አጥኚ ቡድኑ መክሯል።

በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ግን ባንኩ በቅርቡ በቀረበለት የውሳኔ ሐሳብ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች