Tuesday, February 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ዝርፊያን መታደግ አልተቻለም

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም

በፋብሪካው ላይ ክስ መሥርቷል

  • ከ1,500 በላይ ሠራተኞች ከሥራ ተሰናብተዋል

በኢዮብ ትኩዬ

 የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የነበረው፣ በአፋር ክልል በሚገኘው ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ንብረት ላይ የሚከናወነውን ዝርፊያ ማስቆም እንዳልቻለና ከአቅሙ በላይ እንደሆነበት አስታወቀ፡፡

የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ንብረት እየተዘረፈ ቢሆንም ዝርፊያውን ማስቆም ከአቅሙ በላይ በመሆኑ መታደግ እንዳልቻለ፣ የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የሕዝብ ግንኙነትና ተሳትፎ ክፍል ዋና ኃላፊ አቶ ረታ ደመቀ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ሸንኮራ አገዳ ከዓመታት በፊት ተከስቶ በነበረ ድርቅ ምክንያት በከብቶች በመውደሙ፣ ከስድስት ዓመታት በላይ ሥራ እንዳቆመ፣ አገዳው ሲወድምም ምንም እንኳ ፋብሪካው የፌዴራል ተቋም ቢሆንም ክልሉ አብሮ መሥራት እያለበት ጥበቃ አላደረገም ሲሉ አቶ ረታ አስረድተዋል፡፡

‹‹አገዳው በመውደሙ ሳቢያ ፋብሪካው ምርት አቁሟል፡፡ ዝርፍያ እየተፈጸመ ስለመሆኑም መረጃዎች ደርሰውናል፡፡ የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ጉዳዩ ከአቅሙ በላይ ስለሆነ ለፌዴራል መንግሥትም፣ ለአፋር ክልል መንግሥትም አሳውቋል፤›› ብለዋል፡፡

በዚህ ምክንያት 500 ሠራተኞች በየሙያ ዘርፋቸው ወደ ተለያዩ ፋብሪካዎች ሲመደቡ ቀሪዎቹ ከ1,500 በላይ ሠራተኞች፣ ‹‹በሕጉ መሠረት የሁለት ወራት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ተሰናብተዋል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ፋብሪካው ሥራ ቢያቆምም በዓመት እስከ 24 ሚሊዮን ብር ለሠራተኞቹ ደመወዝ ሲከፍል እንደቆየና የተዘረፈው ንብረት መጠን ግን መጠኑ እንዳልታወቀ ተጠቅሷል፡፡

ከሥራ እንዲሰናበቱ የተገለጸላቸው ሠራተኞች በበኩላቸው ድርጊቱ ከሕግ አግባብ ውጪ ነው ብለዋል፡፡ ቅሬታቸውን ለሪፖርተር የገለጹ አምስት ሠራተኞች ከ1,500 በላይ ሠራተኞች ከሥራ ሲሰናበቱ፣ በሥራቸው የሚተዳደሩ የቤተሰብ አባላትም ችግር ላይ እንደሚወድቁ ታሳቢ መደረግ ነበረበት ብለዋል፡፡

‹‹የፋብሪካው ሕንፃ ሳይቀር እየፈረሰ ብረቱ እየተሸጠ ነው፡፡ ጥበቃ እያደረጉ ነው የተባሉ የመንግሥት አካላትም ዘረፋውን መከላከል አልቻሉም፤›› ሲሉ አንድ ሠራተኛ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው በአፋር ክልል የዱፍቲ ከተማ ከንቲባ የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዓሊ ሚራህ፣ እየተካሄደ ነው ስለተባለው ዝርፊያ ምላሽ መስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በበኩሉ ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞቹን እንዳያሰናብት በደብዳቤ ሲጠይቅ እንደነበር፣ ነገር ግን በጎ ምላሽ ባለመገኘቱ በፋብሪካው ላይ ክስ መመሥረቱን ገልጿል፡፡

የፋብሪካው ሠራተኞች ከሥራ ሊባረሩ መሆናቸውን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም እንዳሳወቁ፣ ተቋሙም ፋብሪካው ሠራተኞችን ከሥራ እንዳያባርር ጥያቄ እንዳቀረበ፣ ጉዳዩን የተከታተሉት የአፋር ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አበራ ከበደ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

 ‹‹ከ1,500 በላይ ሠራተኞች የሥራ ውል ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ እንደተቋረጠ፣ የሦስት ዓመታት የዓመት ፈቃዳቸው የተሰረዘ መሆኑን፣ ፋብሪካው ሠራተኞችን ሳያወያይ የሠራተኛ ማኅበሩን ብቻ በመያዝ የሪፎርም ምደባ ማድረጉንና መዋቅር መሥራቱ አላግባብ በመሆኑ፣ በተደጋጋሚ ብናመለክትም ምላሽ ሊሰጠን ስላልቻለ አስተዳደራዊ በደል ደርሶብናል፤›› ሲሉ ለኢትትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ማሳወቃቸውን ሠራተኞቹ የጻፉት ደብዳቤ ያሳያል፡፡

ተቋሙም የቀረበለትን አቤቱታ ጠቅሶ የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ በሰባት ተከታታይ የሥራ ቀናት ውስጥ ምላሽ እንዲሰጠው በደብዳቤ ገልጾለት እንደነበር፣ ሆኖም የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ ሠራተኞቹን የማሰናበት ውሳኔው አግባብነት ያለው መሆኑን ጠቅሶ ምላሽ እንደሰጠ አቶ አበራ አስረድተዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደወሰደው፣ ፋብሪካው ሠራተኞቹን ጥር 1 ቀን 2015 ዓ.ም. የሥራ መልቀቂያ ክሊራንስ ሲያስሞላ  የፍርድ ቤት ዕገዳ ወጥቶ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች