Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየፌዴራል ሥርዓቱ መሠረታዊ ማስተካከያዎች ያስፈልጉታል

የፌዴራል ሥርዓቱ መሠረታዊ ማስተካከያዎች ያስፈልጉታል

ቀን:

በተካልኝ ጎዳና

በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥትም ይሁን ቋንቋን መሠረት ያደረገ ፌዴራል አወቃቀር፣ ላለፉት 30 ዓመታት በጣም አወዛጋቢ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አንዳንዶች እንደ መድኃኒት ሲቆጥሩት፣ ሌሎች ደግሞ የችግሮቻችን ሁሉ ምንጭ ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ መድኃኒት ነው ብለው የሚያምኑት እንኳ ሊሻሻል አይችልም ብለው የሚሞግቱ አይመስለኝም፡፡ ይህ አጭር ጽሑፍ የሚያተኩረው የፌዴራል መዋቅሩን ማስተካከል አስፈላጊነት ላይ ቢሆንም፣ በተጓዳኝ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻልንም አመላካች ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት 50 ዓመታት ሁለት ሥር ነቀል የሥርዓት ለውጦች አስተናግዳለች፡፡

ከእነዚህ ለውጦች ምን አተረፍን ምን ያህልስ አጣን? የሚለው ገና የሒሳብ ደብተሩ ያልተዘጋ ጉዳይ ነው፡፡ ትርፍና ኪሳራው ተወራርዶ ያለቀ ባይሆንም ማንም ሊክደው የማይችለው ሀቅ ግን የ50 ዓመታት የለውጥ ሒደት ከፍተኛ ዋጋ የተከፈለበት መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ ግንዛቤ ከተነሳን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሌላ አዲስ ሥር ነቀል ለውጥ፣ ተያይዞም የሚመጣውን ነውጥ መሸከም የሚችል ትከሻ ያለው አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ያለውን አክመንና አስተካክለን እያዘገምንም ቢሆን እንዴት ወደፊት እንራመድ ከሚል ዕሳቤ በመነሳት ሁለት የተለያዩ፣ ግን ተመጋጋቢ የሆኑ ምክረ ሐሳቦችን ለመሰንዘር እሞክራለሁ፡፡ አንደኛው ምክረ ሐሳብ የፌዴሬሽን አባላቱን ቁጥር በእጅጉ ማሳደግ ሲሆን፣ ሁለተኛው የፌዴራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ተቋማት ከአዲስ አበባ ወደ ሌሎች ከተሞች በማዛወር በርካታ የዕድገት ማዕከላትን (Growth Centers) ማበረታት ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ምክረ ሐሳብ አንድ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በቀጥታ ውክልና የሚኖራቸውን አካባቢዎች ቁጥር በእጅጉ ማሳደግ፣ ዛሬ ባለው የክልል አስተዳደር ዕርከን ቦታ በርካታ ቁጥር ያላቸው (ከ40 እስከ 45 የሚደርሱ) ራስ ገዝ የሆኑ አስተዳደሮች በፌዴራል ደረጃ ሙሉ ውክልና ቢኖራቸው ለአስተዳደር ምቹ ከመሆኑም ባሻገር፣ በአሁኑ አወቃቀር ውስጥ ያሉ አንዳንድ መሠረታዊ ችግሮችን ጭምር ይቀርፋል፡፡ እነዚህ ራስ ገዝ አስተዳደሮች በአብዛኛው አሁን ያሉትን የዞን አደረጃጀት መሠረት የሚያደርጉ ከሆነ፣ አዲዲስ የአስተዳደር ወሰኖች መቀየስ ሳያስፈልግ ቀላል ሽግግር ማድረግና ያስችላል፡፡ ይህ ምክረ ሐሳብ አስተዳደርን ለሕዝብ የበለጠ ቀረቤታ እንዲኖረው በማድረግና ዴሞክራሲን በማጎልበት፣ እኩልነትንና አንድነትን በፅኑ መሠረት ላይ ያቆማል በሚል የቀረበ ነው፡፡ በማስቀጠል የቀረበውን ምክረ ሐሳብ አጠር አድርጌ ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡

 ከክልሎች ወደ ዞን ራስ አስተዳደሮች ሽግግር ጠቀሜታው ምንድነው?

ዛሬ ያለው የክልል አወቃቀር ከምቹ የአስተዳደር መዋቅር ይልቅ ግልጽ የሆነ የፖለቲካ ግብን መሠረት ያደረገ እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ በሁለተኛ ነፃ አውጭ ግንባር ነን በሚሉ ድርጅቶች የተጠነሰሰ እንደ መሆኑ መጠን፣ ዋናው ትኩረቱ የወደፊት ነፃ አገሮች የድንበር የማካለል ቅድመ ዝግጅት ላይ መሆኑ የሚገርም አይደለም፡፡ ምንም እንኳ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የአስተዳደር ወሰኖች እንጁ ድንበሮች የሉም ቢሉም፣ በተጨባጭ ግን እንደ አገር ድንበሮች እየታየ ስለሆነ ዞኖች በቀጥታ የፌዴሬሽኑ አባላት መሆናቸው የተፈጠረውን የድንበርና የወሰን ዕይታ መቀላቀልን ሊያጠራው ይችላል፡፡ የዞን ራስ ገዝ አስተዳደሮች ማካለል በማያሻማ መንገድ በእርግጥም የአስተዳደር ወሰን እንጂ፣ ሌላ የተለየ ጥርጣሬም ይሁን ሥጋት ሊፈጥር አይችልም፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም በተጎራባች ዞኖች ውይይት የዞን ወሰኖች በቀላሉ ሊሸጋሸጉ ይችላሉ፡፡ ትልቁ ነገር አስተዳደራዊ ወሰኖችን ከነፃ አገር ምኞት የፖለቲካ ቀመር ማላቀቅ ያስችላል፡፡

ሁለተኛ የአስተዳደር ወሰን እንጂ ድንበር የለም የሚለው ላይ መስማማት ከተደረሰ የግዛት ይገባኛል ውዝግብም ዕልባት ያገኛል፡፡ ወልቃይት ወይም ሞት የሚለው የአማራና የትግራይ ፍልሚያም ፍፃሜውን ያገኛል፡፡ የራያ ጥያቄም እንዲሁ፡፡  ሁለቱም የማንም ግዛት ሳይሆኑ ራሳቸውን ችለው ራስ ገዝና የፌዴሬሽኑ አባል ይሆናሉ፡፡ በአማራ ክልል የኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚልም አይኖርም፡፡ ራስ ገዝና በቀጥታ የፌዴሬሽኑ አባል ስለሚሆን፣ ሌሎችም ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች በባለቤትነት ሳይሆን በአካታችነትና አሳታፊነት ለመፍታት ዕድል ይከፍታል፡፡

ሦስተኛ ዞኖች በራስ ገዝነት መዋቀር አጎራባች ዞኖች የጎንዮሽ (Horizontal) ትብብሮችን ማድረግ የሚያስችልና የሚያበረታታ ነው፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች እየታየ ያለው የተጎራባች ዞኖች ትብብር ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ ከውህደት በመለስም አጎራባች ዞኖች በተለያዩ መስኮች (የመጠጥ ውኃ አቅርቦት የመስኖ ልማቶች የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ የቱሪዝም ዕድገት በመሳሰሉት) ዙሪያ የጋራ ተጠቃሚነትን ሊያዳብሩ ይችላሉ፡፡ የጎንዮሽ ትብብሮች ቋንቋም ይሁን ሌላ ማንነት ሳይገድባቸው በተጎራባችነታቸው ብቻ ለጋራ ተጠቃሚነት ሲባል ሊደረጉ ስለሚችሉ የበለጠ አብሮነትን ያጎለብታሉ፡፡

አራተኛ የዞን አስተዳደሮች ዋናው ተግባራቸውና ተልኮዋቸው የነዋሪዎቻቸው ጥቅምና የአካባቢያቸው ዕድገትና ልማት ስለሚሆን ትኩረታቸው እዚያ ላይ ይሆናል፡፡ አንድ አካባቢ ሊያድግና ሊበለፅግ የሚችለው የነዋሪውን አቅም በመጠቀም ብቻ ሳይሆን ከአካባቢው ውጭም ሀብት፣ ጉልበትና ዕውቅትን በመሳብ ስለሆነ እያንዳንዱ አካባቢ ምቹና ተመራጭ የሆነ የመኖሪያና የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሆኖ ለመገኘት ከሌሎች አካባቢዎች ጋር ጤናማ ውድድር ይፈጥራል፡፡ አሁን የሚታየውን መገፈታተር አስወግዶ ሌሎችን ወደ መሳብ ፍላጎት ያዳብራል፡፡ ይህም አብሮነትንና አንድነትን ያጠናክራል፡፡

አምስተኛ እያንዳንዱ ዞን በፌዴሬሽኑ ቀጥታ ውክልና ስለሚኖረው አሁን ያለውን የክልል እንሁን ጥያቄ ያስቀራል፡፡ ትኩረቱ በነዋሪዎች ጥቅምና ፍላጎት ላይ እስከሆነ ድረስ አዳዲስ ዞኖችን መፍጠርም ሆነ፣ ከአጎራባች ዞኖች ጋር አብሮ መጣመር የሚፈጥረው ችግር የለም፡፡

ከክልሎች ወደ ራስ ገዝ ዞኖች ሽግግር ምን ሊመስል ይችላል?

በአሁኑ አወቃቀር በኢትዮጵያ ከ70 የበለጡ ዞኖችና አሥር ያህል ልዩ ዞኖች ይገኛሉ፡፡ ከሐረሪና ከሲዳማ በስተቀር ሁሉም ክልሎች በዞን ተከፋፍለዋል፡፡ ሆኖም ብዙዎቹ ዞኖች አነስተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው ናቸው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ከአንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሺሕ እስከ አምስት ሚሊዮን የሚደርስ የሕዝብ ብዛት ያላቸው ወደ 30 የሚጠጉ ዞኖች አሉ፡፡ በተለይም በአማራና በኦሮሚያ የሚገኙ ዞኖች ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ያላቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ አምስት ዞኖች በአማራ፣ ስድስት ዞኖች በኦሮሚያ እያንዳንዳቸው ከአራት ሚሊዮን በላይ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው ናቸው፡፡ በሌሎች አካባቢዎች እንደ ሶማሌና አፋር ክልሎች ዞኖች አነስተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው ስለሆነ የማጣመር ሥራ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ራስ ገዝነትን ዕውን ለማድረግ የአካባቢውን ሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶችን (ጤና፣ ትምህርት፣ የውኃ አቅርቦትና የመሳሰሉትን) ከአካባቢው የገቢ ምንጭ መሸፈን መቻል አንድ ዋና መመዘኛ ሊሆን ይገባል፡፡

የሕዝብ ብዛት የአካባቢውን የኢኮኖሚ ዕምቅ አቅም አመላካች ነው፡፡ ሆኖም እንደ አካባቢውና እንደ ጊዜው ሌሎች መሥፈርቶችም በተጨማሪ ግምት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ በተጨማሪም ልዩ ሁኔታዎች፣ ታሪክና የአናሳ ብሔረሰቦችን መብት የመጠበቅና የተለየ እንክብካቤ ማድረግ አስፈላጊና ተገቢም ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን የሚታዩት በርካታ ልዩ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ከዚህ ዕሳቤ የመነጩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ 30 ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ያላቸውን ዞኖች እንደ መነሻ በመውሰድ፣ በተጨማሪም ሌሎች አነስተኛ ዞኖች በመጣመር ሊፈጥሯቸው የሚችሉ አራት ወይም አራት ዞኖችን በማከልና በልዩ አስተያየት ሊታዩ የሚችሉ አካባቢዎችን በመጨመር፣ ከ40 እስከ 45 የሚደርሱ ራስ ገዝ የፌዴሬሽን አባላት ማዋቀር ይቻላል፡፡ ቁጥራቸው ከዚህ ይብዛም ይነስ ዛሬ ካለው የክልሎች ፌዴራል መዋቅር በእጅጉ የሰፋና የበለጠ አቃፊና አሳታፊ የሆነ ፌዴራላዊ ሥርዓት ማዋቀር ይቻላል፡፡

በክልል ሕገ መንግሥት ዕውቅና ያላቸው በሕዝብ የተመረጡና ለመረጣቸው ሕዝብ ተጠሪ የሆኑት የወረዳና የቀበሌ መስተዳደሮች ብቻ ናቸው፡፡ ዞኖች ከወረዳና ከቀበሌ በተለየ መንገድ በዞን አስተዳደር ማቋቋሚያ ደንብ የተደራጁ ናቸው፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ የአማራ ክልላዊ መንግሥት ባወጣው ደንብ ቁ33/1993 የዞን ምሥረታ አስፈላጊነትን እንደሚከተለው ይገልጸዋል፡፡ የክልሉን የቆዳ ስፋትና የሕዝብ ብዛት ታሳቢ በማድረግ ለክልሉ ኅብረተሰብ ብቃት ያለውና የተመጣጠነ አስተዳደራዊ አገልግሎት፣ የተፋጠነ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ብሎም መልካም አስተዳደርን ማስፈን በማስፈለጉ የዞን አስተዳደሮችን ማቋቋም ተገቢ ሆኖ አግኝተነዋል ይላል፡፡ ክልሉ እዚህ ግንዛቤ ላይ መድረሱ እጅግ ተገቢ ነው፡፡ ሆኖም የዞን አስተዳደሮችን ያዋቀረበት መንገድ የቀድሞውን የእንደራሴ አስተዳደር የሚያስታውስ ነው፡፡ የዞን መስተዳደሮች ተጠሪነታቸው ‹‹ለክልሉ መስተዳደር ምክር ቤትና ለርዕሰ መስተዳደሩ ጽሕፈት ቤት ሲሆን፣ ሥራቸውን የሚያከናውኑት እነዚህን አካላት በመወከል ይሆናል፤›› ሲል ይደነግጋል፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የዞን ነዋሪዎች በክልል እንደራሴዎች/ምስለኔዎች እንዲተዳደሩ መፍቀድ ዴሞክራሲያዊ ነው ብሎ መቀበል አስቸጋሪ ነው፡፡ የክልላዊ መንግሥቱ የዞኖችን አስፈላጊነትና የሚያከናውኑትን ተግባርም ዕውቅና እንደስጠ ሁሉ፣ የዞን አስተዳደሮችም በዞኑ ነዋሪዎች የሚመረጡና ተጠሪነታቸውም ለመረጣቸው ሕዝብ እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ የአማራ ክልላዊ መንግሥትን የዞኖች ምሥረታ እንደ ምሳሌ ያነሳሁት የሌሎችም ክልሎች አካሄድም ከዚህ ብዙም የተለየ አይሆንም በሚል ዕሳቤ ነው፡፡ እንደገና አጽንኦት ለመስጠት ከክልል መዋቅር ወደ ራስ ገዝ ዞኖች መሸጋገር ዴሞክራሲን የሚያጎለብት፣ ለሕዝብ የበለጠ ቀረቤታ ያለውና በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን ፍላጎትና አኗኗር ያገናዘበ ፌዴራላዊ ሥርዓትን ለመገንባት ያስችላል፡፡

ምን ዓይነት አስተዳደራዊ መዋቅር አስፈላጊ ነው የሚለውን ለመፈተሽና አማራጮችን ለመጠቆም፣ በዋነኝነትና በመሠረታዊነት በግባችን ወይም በጋራ ዕድላችን (Destination) ላይ ግልጽ ግንዛቤና አገራዊ ራዕይ ሊኖረን ይገባል፡፡ ‹‹ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎች›› ከሚለው መርሆ በመነሳት የናይጄሪያን ሕገ መንግሥት በመጥቀስ ሐሳቤን አጠቃልላለሁ፡፡ ለማስተዋስ ያህል ናይጄሪያ ከ200 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት፣ ከ500 ያላነሱ ቋንቋዎች የሚነገሩባት አገር ናት፡፡ ከኢትዮጵያ በበለጠ ብዙኃነት ያለባት ከኢትዮጵያ ሲወዳደር እጅግ አጭር (60 ዓመታት) የሆነ ብሔራዊ መንግሥት ምሥረታ ታሪክ ያላት አገር ናት፡፡ አሁን እያገለገለ ያለው የናይጄሪያ ሕገ መንግሥት የሚከተለውን ይደነግጋል፡፡ ‹‹Nigeria is one indivisible and indissoluble sovereign state to be known by the name of the Federal Republic of Nigeria››.

የናይጄሪያ ሕዝብ በማያሻማ ሁኔታ የማይከፋፈልና የማይበረዝ አንድነቱን እንዳወጀ ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብም አንድነቱ ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን በሕገ መንግሥቱ በግልጽ ማስቀመጥ ሊሳነው አይገባም፡፡ አንድነትን በቅድመ ሁኔታ፣ መገንጠልን ግን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የሚደነግገው አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ብዙም ሩቅ የሚያስኬደን እንዳልሆነ እየታየ ያለ ሀቅ ነው፡፡ ስለዚህም ያለው ሕገ መንግሥት በጥንቃቄ እንደገና ሊጤን ይገባዋል፡፡

ሌላው መስተካከል ያለበት መሠረታዊ የሕገ መንግሥቱ ይዘት የቋንቋና የባህል መንከባከብን ግዴታ የክልሎች ብቻ አድርጎ መደንገጉ ነው፡፡ ኅብረ ብሔራዊነት የኢትዮጵያ መለያና የጋራ ጌጣችን ነው እስካልን ድረስ፣ የተለያዩ ቋንቋዎችንና ባህሎችን መንከባከብ የአንዱ ወይም የሌላው ክልል ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን የጋራ ብሔራዊ ኃላፊነት ሆኖ መታየት አለበት፡፡  በመሆኑም የማንነትን ጥያቄን ከክልል አጥር ባሻገር በማየት ጠለቅ ያለ ግንዛቤን ለማዳበር አስፈላጊ ብሔራዊ መዋቅሮችን ማደራጀትና ማጠናከርን ያስፈልጋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው የባህልና የቋንቋ አካዴሚ አንድ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ የማንነትን ጥያቄና አንድምታውን ከጥራዝ ነጠቅ ፖለቲኮኞች አላቆ ወደ ፍሬያማ የምርምር መስክ መምራቱ አስፈላጊ ነው፡፡

ምክረ ሐሳብ ሁለት ከአዲስ አበባ በተጨማሪ ሌሎች አራት ወይም አምስት ከተሞችን የፊዴራል መንግሥት ማዕከሎች ማድረግ

በአሁኑ ጊዜ 22 የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ከ30 በላይ የሆኑ የተለያየ መጠሪያ ያላቸው ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ተጠሪ የሆኑ ተቋማት አሉ፡፡ ሁሉም በሚባል ሁኔታ የታጨቁት አዲስ አበባ ነው፡፡ ይህ አዲስ አበባ ተኮር የፌዴራል አስተዳደር የሌሎች ከተሞች ዕድገትን የማያበረታታ፣ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች መቀመጫ ከመሆን የሚገኘውንም የኢኮኖሚ ጠቀሜታ በአዲስ አበባ ተከልሎ እንዲቀር የሚያደርግ ነው፡፡ የግዴታ መቀመጫቸው አዲስ አበባ መሆን አለባቸው ቢባል እንኳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ብቻ ናቸው፡፡ ሌሎቹ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ተቀማጭነታቸውን በሌሎች ከተሞች ቢያደርጉ ከሥራ አኳያ የሚፈጥረው ችግር እምብዛም አይደለም፡፡ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች በፍጥነት እያደጉ ባለበት ሁኔታ የቦታ ርቀት ወሳኝነት አክትሟል፡፡ አዲስ አበባ ትልቅ የንግድ የፉይናንስ፣ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ከተማ ናት፡፡ በመሆኑም 15 ወይም 20 የሚደርሱ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ወደ ሌሎች ከተሞች ቢዘዋወሩ ለአዲስ አበባ ብዙም ጉዳት አይኖረውም፡፡ በአንፃሩ ግን ሁለት ወይም ሦስት የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች እንደ ነቀምት፣ ደብረ ማርቆስ፣ ጅማ፣ ሐዋሳ ወይም ሐረር ቢዛወሩ በእነዚህ ከተሞችና አካባቢዎቻቸው የሚፈጥረውን መነቃቃትና የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት መገመት አያዳግትም፡፡ የፌዴራል መንግሥት ተቋማትን ከአዲስ አበባ በማዛወር በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ ስበት ሊኖሪቸው የሚችሉ የዕድገት ማዕከሎችን (Growth Centers) መፍጠር ያስችላል፡፡

በተመረጡት ከተሞች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ፓርኮችን በመገንባት፣ ለመሥሪያ ቤቶቹ አስፈላጊውን መሠረታዊ አገልግሎት በጋራ ማቅረብ ያስችላል፡፡ ከአዲስ አበባ የማዛወሩ ጉዳይ ፓርላማውንም የሚመለከት መሆን ይኖርበታል፡፡ ደቡብ አፍሪካ ሦስት የመንግሥት መቀመጫ ከተሞች አሏት፡፡ ኬፕታውን የፓርላማው መቀመጫ ፕሪቶሪያ የሥራ አስፈጻሚው (Government) መቀመጫ ብሉምፎንቴይን ደግሞ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ መቀመጫ ናት፡፡ በተመሳሳይ ታንዛንያ የፓርላማው መቀመጫ፣ አሩሻ ሲሆን፣ የአስፈጻሚው አካል መቀመጫ ዳሬሰላም ነው፡፡ ይህን ምክረ ሐሳብ ከእነዚህ ሁለት አገሮች ለየት የሚያደርገው የመንግሥት አስፈጻሚ አካላትም፣ በአንድ ከተማ ማጨቅ ተገቢ አይደለም የሚለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ አምስት ወይም ስድስት የፌዴራል መቀመጫ ከተሞች ቢኖራት እጅግ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ ፓርላማው መቀመጫውን ከአዲስ አበባ ለማዛወር ፈር ቀዳጅ ቢሆን፣ ሌሎች መሥሪያ ቤቶች ምሳሌውን ለመከተል ይገደዳሉ፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው ተጨማሪ ከተሞችን የዕድገት ማዕከል የማድረግ ችሎታ ስለሚኖረው፣ ለተመጣጠነ የከተሞች ዕድገት አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ይህም ወደ አዲስ አበባ የሚደረገውን የዜጎች ፍልስት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሊቀንሰው ይችላል፡፡

ተግባራዊነቱስ እንዴት ይሆናል?

ምክረ ሐሳብ አንድ ቀደም ብሎ እንደተገለጸው መሠረታዊ የሕገ መንግሥት ማሻሻያዎችን የሚጠይቅ ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት መቀመጫ ከተሞችን በሚመለከት ግን ምንም ዓይነት ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ አያስፈልገውም፡፡ ሕገ መንግሥቱ አዲስ አበባ የፌዴራል መንግሥቱ ዋና ከተማ ናት ይላል እንጂ፣ የመንግሥት መቀመጫ ነች አይልም፡፡ ፓርላማውም ቢሆን የፌዴራል መሥሪያ ቤቶችን መቀመጫ የመወሰን መብት ያለው አይመስለኝም፡፡ ሥራ አስፈጻሚው በአስተዳደራዊ ትዕዛዝ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን በፈለገ ጊዜ ከቦታ ወደ ቦታ ማዘዋወር የሚከለክለው ሕግ ያለ አይመስለኝም፡፡ የሕግ እክል ባይኖረውም የአመራር ቆራጥ ውሳኔ የሚጠይቅ ነው፡፡ ሁሉም የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ወደ ሌላ ከተማ ለመዘዋወር ዕቅድና የጊዜ ሰሌዳ እንዲያቀርቡ መመርያ ሊሰጣቸው ይችላል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው tgodana@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...