Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበትግራይ ክልል በባለሙያዎች የሚመራ ባለአደራ የሽግግር መንግሥት በአስቸኳይ ይቋቋም

በትግራይ ክልል በባለሙያዎች የሚመራ ባለአደራ የሽግግር መንግሥት በአስቸኳይ ይቋቋም

ቀን:

በመርስዔ ኪዳን

የትግራይ ጦርነት በክልሉም ሆነ በተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ላይ ከፍተኛ ቀውስ አስከትሏል። ጦርነቱ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ከሚካሄዱ ጦርነቶች ሁሉ ከፍተኛውን ጥፋት ያደረሰ ጦርነት ነው። ከሚሊዮን በላይ ሕይወት ተቀጥፏል፣ ወደ አራት ሚሊዮን ሕዝብ ከቀዬው ተፈናቅሏል፣ ትምህርት ቤቶችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወድመዋል፣ እንዲሁም በሕይወት የተረፈው ሕዝብ ለከፍተኛ የሥነ ልቦና ቀውስ ተጋልጧል። ይህን የዓለማችንን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማስቆም የአውሮፓ ኅብረትና የአሜሪካ መንግሥት ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በመተባበር ባደረጉት ጫና፣ ሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች በደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ በፕሪቶሪያ ዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት ተፈራርመዋል።

በዚህ ውል ሕወሓት የትግራይን ሠራዊት ትጥቅ እንዲያስፈታ፣ ለፌዴራል መንግሥቱ ሙሉ ዕውቅና እንዲሰጥ፣ ከፌዴራል መንግሥቱ ፈቃድ ውጪ ያደረገው ምርጫ ሕጋዊ አለመሆኑን፣ በእሱ የሚመራው መንግሥትም ሕጋዊ አለመሆኑን ተቀብሎ ሲፈርም፣ የፌዴራል መንግሥቱ ደግሞ ትግራይን በሕገ መንግሥቱ መሠረት መልሶ ለማቋቋም፣ መሠረታዊ አገልግሎቶችን በአስቸኳይ ለማስጀመር፣ እንዲሁም ሕወሓትን ከሽብርተኞች ዝርዝር አውጥቶ በሁለቱ ስምምነት መሠረት የሽግግር መንግሥት ለማቋቋም ተስማምቷል። ከዚያ በኋላ በናይሮቢ በትግራይ ሠራዊት ወታደራዊ መሪዎችና በኢትዮጵያ ሠራዊት ወታደራዊ መሪዎች መካከል የስምምነቱን ትግበራ በተመለከተ የጋራ መግባባት ተፈጥሯል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በናይሮቢው የወታደራዊ መሪዎች ውል መሠረት የወታደራዊ ስምምነቱ ትግበራ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ቢቆይም፣ በሁለቱም በኩል ባሉ የፖለቲካ መሪዎች ግን የተሟላውን ስምምነት ለመፈጸም ዳተኝነት ታይቷል። በፌዴራል መንግሥቱ በኩል የእሱ ሠራዊት ከተቆጣጠራቸው ቦታዎች (ከእነሱም እጅግ በጣም ውስን በሆኑት) በስተቀር መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለማስጀመር ፍላጎት አለመኖር፣ በሕወሓት በኩል ደግሞ በውሉ በትግራይ የተካሄደውን ምርጫ፣ እንዲሁም የሕወሓት መንግሥትነት ኢሕጋዊ መሆናቸውን ፈርሞ ተመልሶ መቀሌ ከገባ በኋላ ዛሬም መንግሥት እኔ ነኝ የሚሉ መግለጫዎችን መስጠት ቀጥሏል።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከአፍሪካ መሪዎች ጋር ባደረጉት ጉባዔ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ገጥሟት ያለውን የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ እጥረት ለመቀነስ ከጆ ባይደን ጋር ባደረጉት ውይይት የፕሪቶሪያን ውል በአስቸኳይ ተግባራዊ ካላደረጉ አይደለም የፋይናንስ ድጋፍ ሊያገኙ በሒደት ላይ ያሉት ሌሎች ከፍተኛ የማዕቀብ አዋጆች በፍጥነት እንደሚወሰኑ፣ እንዲሁም የትግራይ የዘር ማጥፋትን ዕውቅና በመስጠት ፈጻሚዎቹም በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንደሚከሰሱ ስለገለጹላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አበባ እንደደረሱ ሁሉም ነገር በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት በአስቸኳይ እንዲፈጸም ቀጭን ትዕዛዝ ሰጥተዋል። በዚህ መሠረት የሁለቱም ተወካዮች በናይሮቢ ተገኝተው የስምምነቱን አፈጻጸም የሚከታተልና የሚቆጣጠር ኮሚቴና የባለሙያዎች ቡድን አቋቁመው የሚተዳደርበትን መግባቢያ ሰነድ ተፈራርመው ተመልሰዋል። አሜሪካውያኑ ባሉት መሠረትም የአውሮፓውያን አዲስ ዓመት ከመግባቱ በፊት በመቀሌ የተለያዩ አገልግሎቶች ጀምረዋል። 

ነገር ግን እስካሁን ከሚታዩት አስቀድሞም መደራደርያ መሆን ያልነበረባቸው የመሠረታዊ አገልግሎቶች መጀመር ባሻገር፣ ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ የሆኑ ሁለት የስምምነቱ አካሎች አስፈላጊውን ትኩረት እያገኙ አይደለም። አንዱ የስምምነቱ አካል የፌዴራል መንግሥቱ በትግራይ የሚገኙትን ከመከላከያና ከትግራይ ፖሊስ ውጪ ያሉ ኃይሎችን የማስወጣት ጉዳይ ነው። በዚህ ጉዳይ ምንም የተቀየረ ነገር የለም። ዛሬም ከሰባ በመቶ በላይ የሚሆነው የትግራይ አካል በወራሪው የኤርትራ ሠራዊትና በአማራ ታጣቂ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ይገኛል። ሁለተኛው ጉዳይ በውሉ መሠረት ኢሕጋዊ የተባለው የትግራይ መንግሥትን በሽግግር መንግሥት የመተካት ጉዳይ ነው። ሕወሓት አብዛኛውን የሰላም ስምምነት አካሎች ያለ ምንም ማቅማማት ሲቀበል፣ ሥልጣኑን ለሽግግር መንግሥት የማስረከቡን ጉዳይ ግን ላለመተግበር የቻለውን ሁሉ እያደረገ ይገኛል። ይህ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም። የፌዴራል መንግሥቱም ሆነ ሕወሓት በተስማሙት መሠረት አዲስ የሽግግር መንግሥት የማቋቋም ግዴታ አለባቸው።

የሚቋቋመው የሽግግር መንግሥት ምን መምሰል እንዳለበት የተለያዩ አስተያየቶች  በመሰጠት ላይ ይገኛሉ። የሽግግር መንግሥት የሚቋቋመው ቀውስ ባጋጠመ ጊዜ ነው። የሕገ መንግሥት ቀውስ ባጋጠመ ጊዜ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎችና የማኅበረሰብ ክፍሎች ያካተተ አካታች መንግሥት ማቋቋም ያስፈልጋል። ለምሳሌ ደርግ በወደቀ ማግሥት የተቋቋመው የሽግግር መንግሥት ሙሉ በሙሉ አካታች ነው ባይባልም፣ ለይምሰልም ቢሆን ከሁሉም የማኅበረሰብ ተወካይ እንዲኖር ተደርጓል። ሆኖም ሁለቱም ኃይሎች በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት ለመገዛት በመስማማታቸው፣ አሁን በትግራይ አጋጥሞ ያለው ቀውስ የሕገ መንግሥት ቀውስ አይደለም። በትግራይ አጋጥሞ ያለው ቀውስ ሁለት ዓይነት ነው። በአንድ በኩል ሕወሓት አደረገ የተባለው ምርጫ ኢሕጋዊ ነው ስለተባለ፣ ሕወሓት መንግሥት ሆኖ መምራት አይችልም፡፡ ብልፅግናም ሆነ ሌላ ፖለቲካዊ ኃይልም በትግራይ ስላልተመረጠ ትግራይን ሊመራ አይችልም፡፡

ስለሆነም አንዱ ቀውስ የመንግሥትነት ክፍተት ነው። ሁለተኛው አስከፊው ጦርነት የፈጠረው ሰብዓዊ ቀውስ ነው። እነኝህን ቀውሶች ለመፍታት ማቋቋም የሚያስፈልገው የሽግግር መንግሥት በባለሙያዎች የሚመራ ባለአደራ መንግሥት ነው። ለምሳሌ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ የአዲስ አበባ ከተማን ያሸነፈው ቅንጅት የአዲስ አበባን አስተዳደር አልረከብም በማለቱ የመንግሥትነት ክፍተት ቀውስ ተፈጥሮ ነበር። ይህን የመንግሥትነት ክፍተት ቀውስ ለመፍታት በጊዜው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የወሰኑት ውሳኔ፣ አዲስ አበባን በባለአደራ መንግሥት እንድትተዳደር ማድረግ ነው። አሁንም ያለው የትግራይ መንግሥትነት ክፍተት ቀውስ የባለአደራ የሽግግር መንግሥት በማቋቋም ሊፈታ ይገባል።

የሚፈጠረው የባላደራ የሽግግር መንግሥት ደግሞ ትግራይን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ሥራ ለመሥራት ብቃት ባላቸው ባለሙያዎች የሚቋቋም መሆን አለበት። ከዓመታት በፊት በዓረብ አገሮች ከተቀጣጠለው የዓረብ አብዮት በኋላ የተፈጠረውን ቀውስ ለመሻገር፣ የተቋቋሙት የሽግግር መንግሥታት ላይ የተደረገ ጥናት እንደሚያመላክተው በባለሙያዎች የሚመራ የሽግግር መንግሥት ያቋቋመችው ቱኒዚያ ከሁሉም በተሻለ በአጭር ጊዜ ወደ መረጋጋትና ወደ ተሻለ ደረጃ እንደ ደረሰች ነው። አካታች የሆነ የሽግግር መንግሥት ያቋቋሙ አገሮች የሽግግር መንግሥቱን የፖለቲከኞች መጨቃጨቂያ መድረክ ነው ያደረጉት፡፡ በፖለቲከኞቻችን መካከል ያለው አለመተማመንና የአስተሳሰብ ልዩነት ተቀራርበው ለመሥራት የሚያስችላቸው አይደለም።

የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችን ያካተተ መንግሥት ማቋቋም የሽግግር መንግሥቱ ትግራይን መልሶ ከማቋቋም ይልቅ፣ የፖለቲካ ሴራና ሽኩቻ መድረክ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ስለሆነም የፖለቲከኞች ስብስብ ከሆነ መንግሥት ይልቅ የባለሙያዎች ስብስብ የሆነ መንግሥት ትግራይን መልሶ ለማቋቋምም ሆነ ለወደፊቱም የተሻለ የፖለቲካ ምኅዳር ለመፍጠር ይጠቅማል። በተለይም ሕወሓት ላለፉት አርባ ዓመታት የተከለው የአንድ ፓርቲ ፍፁም የበላይነትን የሚያረጋግጥ ቢሮክራሲ ለመቀየር ያስችላል። ሰዎች በፓርቲ አባልነታቸው ሳይሆን በብቃታቸው የሚሠሩባቸውን ቢሮዎችና መሥሪያ ቤቶችን በማቋቋም ወደ ተሻለ ፖለቲካዊ ሥርዓት ለመሻገርም ይቻላል።

ባለአደራ የሽግግር መንግሥት ከተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችም ሆነ ሌሎች ኃይሎች ተፅዕኖ ሊደርስበት ስለሚችልና የሚሸከመው ትግራይን መልሶ የማቋቋምም ኃላፊነት ከፍተኛ ችሎታ ስለሚጠይቅ፣ ባለአደራ የሽግግር መንግሥቱን የሚመሩት ግለሰቦች በሕዝቡ፣ በፖለቲካ ኃይሎችም ሆነ በሌሎች ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ከበሬታ ያላቸው ሊሆኑ ይገባል። ምንም እንኳ ትግራይ ብዙ እንዲህ ያለ ብቃት ያላቸው ሰዎች ቢኖሯትም ሦስት ሰዎች ያላቸው ልምድ፣ ብቃትና ክብር ለቦታው የሚመጥኑ ያደርጋቸዋል።

አንዱ የትግራይን ባለአደራ መንግሥት አቋቁመው ሊመሩ የሚችሉት አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) ናቸው። አርከበ  (ዶ/ር) በሥራ ብቃታቸው የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት የሚችሉ መሪ ናቸው። ከዚህ ቀደም የትግራይ ክልልንም በምክትል ፕሬዚዳንትነት አገልግለዋል። በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ባሳዩት ብቃት ምክንያትም፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት መሪ ለመሆን ከታጩት ታላላቅ መሪዎችም አንዱ ናቸው። ምናልባት አርከበ (ዶ/ር)  የሚኖራቸው ጉድለት በጦርነቱ የትግራይ ሕዝብ ያ ሁሉ ጥፋት ሲደርስበት በመላው ዓለም ያሉ የትግራይ ተወላጆች ድምፃቸውን ሲያሰሙ፣ እሳቸው ድምፅ አለማሰማታቸው በትግራይ ሕዝብ ዘንድ የፈጠረባቸው ቅያሜ ነው። ሆኖም ይህ ዕድል ከተሰጣቸው ባላቸው ብቃት የትግራይን ሕዝብ ለመካስም ዕድል ያገኙ ይሆናል።

ሁለተኛው ይህን ኃላፊነት ለመውሰድ ብቃት ያላቸው ሰው ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ ናቸው። ጄኔራሉ በወታደራዊ፣ መንግሥታዊ፣ እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ አመራር ብቃታቸው የተመሰከረላቸው ናቸው። ብዙ የአፍሪካ አገሮችንም ከቀውስ እንዲሻገሩ በማማከር የሚታወቁ ናቸው። ከሁሉም በላይ የጄኔራሉ ትልቅ ችሎታ ግና ሀቀኝነት ነው። ጄኔራሉ ያመኑበትን ነገር ለማራመድ ወደኋላ የማይሉ፣ እንዲሁም ቃላቸውን የሚያከብሩ ሰው ናቸው። በዚህ ምክንያት በሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ሊታመኑ ይችላሉ። ምናልባት በጦርነቱ ወቅት በትግራይ ወገን ከነበሩት ከፍተኛ አመራሮች አንዱ በመሆናቸው በፌዴራል መንግሥቱ በኩል ጥርጣሬ ሊያስነሳ ቢችልም፣ ጄኔራሉ ታማኝነታቸው ለትግራይ ሕዝብ እንጂ ለሕወሓት አለመሆኑ ሥጋቱን ይቀንሰዋል።

ሌላው ይህን ኃላፊነት ሊወስዱ ብቃት ያላቸው ሰው ታደሰ የማነ (ኢንጂነር) ናቸው። ኢንጂነሩ የየትኛውም ፖለቲካዊ ፓርቲ አባል ያልሆኑ ሲሆኑ፣ የትግራይ ልማት ማኅበርን በመሩበት ወቅት ማኅበረሰቡን በማስተባበር ከፍተኛ እመርታ እንዲኖር ያደረጉ ሰው ናቸው። ትግራይን ለማልማት ያላቸው ከፍተኛ  ራዕይ፣ ፍላጎትና ብቃት ለዚህ ቦታ ብቁ ያደርጋቸዋል። አንድ ሊኖራቸው የሚችለው ድክመት በፖለቲካ ወይም መንግሥታዊ አመራር ደረጃ ያልተፈተኑ መሆናቸው ነው፡፡ በተለይ በትግራይ ሕወሓት የዘረጋውን ሥር የሰደደ ኔትወርክ ተቋቁመው ለውጥ ለማምጣት ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል።  ሌሎችም እንደ ሙሉጌታ ገብረ ሕይወት (ዶ/ር)፣ አሰፋ አብረሃ ያሉ ባለልምድና ባለዕውቀት ሰዎችን ማካተትም ይቻላል።

በአጠቃላይ የተጀመረው የሰላም ጉዞ ዘላቂ እንዲሆን ከተፈለገ ሁለት የፕሪቶሪያ ስምምነት ጉዳዮቸ በአስቸኳይ ተግባራዊ መደረግ አለባቸው። እነሱም ከመከላከያ ውጪ ያሉ ኃይሎችን በሙሉ ከትግራይ ሕገ መንግሥታዊ ክልል እንዲወጡ ማድረግና የትግራይን የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ናቸው። በትግራይ የተፈጠረው ቀውስ የሕገ መንግሥት ቀውስ ሳይሆን የመንግሥትነት ክፍተት ቀውስና አጠቃላይ ሰብዓዊ ቀውስ በመሆናቸው፣ በሕገ መንግሥት መሠረት ምርጫ ተካሂዶ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ፓርቲዎች ሥልጣን እስኪይዙ ድረስ በባለሙያዎች የሚመራ ባለአደራ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ግድ ይላል።

የባለአደራ መንግሥቱ የሚጠይቀውን ከፍተኛ ኃላፊነት መወጣት የሚችሉ ብዙ የትግራይ ተወላጆች ቢኖሩም አርከበ (ዶ/ር)፣ ጄኔራል ፃድቃንና ታደሰ (ኢንጂነር)  የተሻለ ብቃት አላቸው። ከእነዚህ አንዳቸው ወይም ሁሉንም ያካተተ ባለአደራ የሽግግር መንግሥት ትግራይን ከገባችበት ቀውስ ለማሻገር፣ በኢትዮጵያም ሰላም ለማስፈን በፖለቲከኞች ከሚመራ የሽግግር መንግሥት ይልቅ የተሻለ ዕድል አለው።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የለውጥ አመራር ባለሙያ፣ በአሜሪካ ሜትሮፖሊታን ስቴት ዩኒቨርሲቲ በሥራ አስተዳደር (ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን) የዶክትሬት ዕጩ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው mersea.kidan@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...