የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኮሙዩኒኬሽንና የጋዜጠኝነት መምህር አብዲሳ ዘርአይ (ዶ/ር)፣ ከኢፒድ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ላይ የተናገሩት፡፡ የሰላም ስምምነቱን ለማጽናት ሚዲያው አዳዲስ የመረጃ ምንጮች ላይ ማተኮር አለበት ያሉት መምህሩ፣ የተፈጠረውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ መገናኛ ብዙኃን በጦርነት ወቅት የአባባሽ ንግግር ተሳታፊ የነበሩትን አካላት በመተው አዳዲስ ምንጮች ላይ ማተኮር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ የተፈጠረው ሰላም እንዲዘልቅ እነዚህን ሰዎች ከዓውዱ ዞር ማለት አለባቸው ያሉት ዶ/ር አብዲሳ፣ ለጊዜው ዘወር ማለት ያለባቸው የቤተሰቡን አባል ያጣ ሰው እነርሱን ሲመለከት ስሜቱ ሊነካ ስለሚችል ነው ብለዋል፡፡ ተንታኝ ተብለው የሚቀርቡ ሰዎች በፊት አጥፉ፣ ግደሉ በማለት ሲያነሳሱ፣ ስለሰላም የሚያወራውን እንደ ወንጀለኛ ሲቆጥሩ የነበሩ መሆናቸውንም አስታውሰዋል።