Tuesday, February 7, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ከፖለቲከኞች ዕርቅ በላይ የሕዝባችን ሰላም ይታሰብበት!

በዓለማችን ላይ የተከሰቱ አብዛኞቹ ትልልቅ ጦርነቶችም ሆኑ ግጭቶች የተቋጩት በሰላም ስምምነት ነው፡፡ ከጦርነት በፊት ለገላጋይ ያስቸገሩ ተፋላሚዎች ሠራዊታቸውንና ሕዝባቸውን አስፈጅተውና የአገር ሀብት አውድመው፣ በመጨረሻ የሚገናኙት የሰላም ስምምነቱን የሚፈራረሙበት ክብ ጠረጴዛ አጠገብ እንደሆነ የብዙዎቹ የታሪክ ድርሳናት ያብራራሉ፡፡ አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ ቢሆኑ እንኳ ዑደቱ እየተቀያየረ ወደ ስምምነቱ ጠረጴዛ ሲደርሱም፣ በፍልሚያዎቻቸው ምክንያት ግን ብዙዎች አልቀው የአገር አንጡራ ሀብት ወድሞ ነው፡፡ ይህ ታሪክ ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም፡፡ ከታሪኳ አብዛኛው ክፍል በጦርነቶች የተሞላው ኢትዮጵያ ሕዝቧ ለዘመናት ከሰላም ተራርቆና ድህነት ውስጥ ተዘፍቆ የኖረው፣ ገዥዎችም ሆኑ በየጊዜው የተነሱ የፖለቲካ ልሂቃን አርቆ ማሰብ ስለተሳናቸው ነው፡፡ እነሱ እርስ በርስ በሚኖራቸው የተበላሸ ግንኙነት ምክንያት ወዳጅነታቸውም ሆነ ጠባቸው በልኩ ስለማይሆን፣ መከራቸው የሚተርፈው የእነሱ የትርምስ አጀንዳ ቀማሪ ላልሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ አገር አተራምሰው ሕዝብን ለመከራ ከዳረጉ በኋላ እንደገና ሲታረቁ፣ ከምንም ነገር በላይ የሕዝብ ዘለቄታዊ ሰላም ሊታሰብበት ይገባል፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሠረት የተጠናቀቀ በመሰለበት በዚህ ወቅት፣ ከፖለቲከኞች ዕርቅ በላይ በሕዝብ መካከል የተፈጠረው የሻከረ ግንኙነት ትኩረት ሊሰጠው ያስፈልጋል፡፡ ጦርነቱ የተካሄደባቸው የትግራይ፣ የአማራና የአፋር ክልሎች አካባቢዎች ያሉ ኢትዮጵያውያን ለመግለጽ አዳጋች በሆኑ ሰቆቃዎች የተጎዱ በመሆናቸው፣ መልሰው እንዲያገግሙ ከፍተኛ ጥረት መደረግ ይኖርበታል፡፡ በውጭ ኃይሎች አሸማጋይነት አንዴ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ፣ ሁለቴ ደግሞ በኬንያ ናይሮቢ በተደረሱ ስምምነቶች መሠረት ፖለቲከኞች ሰላም ሲያወርዱ፣ በሦስቱ ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በፍጥነት አስተማማኝ ሰላም ማግኘታቸው የግድ መሆን ይኖርበታል፡፡ የሰላም ስምምነቱ ‹‹ግማሽ ልጩ ግማሽ ጎፈሬ›› ከመሆን ወጥቶ የተሟላና አስተማማኝ መሆን የሚችለው፣ በአስከፊው ጦርነት ከማንም በላይ የተጎዱት ወገኖች ዘለቄታዊ ሰላም ሰፍኖ ቁስላቸው እንዲሽር ሲደረግ ነው፡፡ ፖለቲከኞች ከዚህ ቀደም የነበራቸውን አጉል ባህሪ በመግታት፣ የሕዝባችንን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ኃላፊነታቸውን ይወጡ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለያዩ መድረኮችም ሆነ አጋጣሚዎች፣ ከምንም ነገር በላይ ለሰላም ቅድሚያ እንደሚሰጥ ድምፁን ሲያሰማ ነው የሚታወቀው፡፡

ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር የሚፈጠረው ‹‹ለሕዝብ ከእኛ በላይ ለአሳር›› በሚሉ ፖለቲከኞች እንደሆነ ማንም ማስተባበል አይችልም፡፡ ብዙዎቹ ፖለቲከኞች የረባ የፖለቲካ ምኅዳር ፈጥረው ልዩነቶቻቸውን ዕውቅና ለመሰጣጠትና በእኩልነት ለመፎካከር ትኩረት ስለማይሰጡ፣ እንደምንም ብለው ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ አንዱ ሌላውን ረግጦ መግዛት ነው የሚታያቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ ያለፉትን ሃምሳ ዓመታት ታሪክ በወፍ በረር ስንቃኝ የምናገኘው፣ በሕዝብና በሰላም ስም የተፈጸሙ ሸፍጦች መከራና ሰቆቃቸው የተረፈው ለምስኪኑ ሕዝብ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን ሕዝባችንን ስንመለከተው ሕግ አክባሪ፣ በሥርዓት ለመተዳደር ፍፁም ፈቃደኛ፣ ለፈጣሪም ሆነ ለመንግሥት ለመታዘዝ የማያመነታና ለአገሩ ሰላም መሆን ሲል ማንኛውንም መስዋዕትነት በደስታ ለመክፈል ሁሌም ዝግጁ ነው፡፡ ይህንን የመሰለ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ በሥርዓት መርተው ከድህነት ማጥ ውስጥ የማውጣት ኃላፊነት ያለባቸው ብዙዎቹ የፖለቲካ ልሂቃን፣ ሕዝባችንን ሰላም ከመንሳት ውጪ ፋይዳቸው እዚህ ግባ አይባልም፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለውን አንፃራዊ ሰላም ሊቀለብሱ የሚዳዱ አንዳንድ አላስፈላጊ እሰጥ አገባዎች እየተሰሙ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የሰላም ስምምነቱ ዋነኛ ዓላማ አውዳሚውን ጦርነት ለዘለቄታው በማስቆም ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ከየተሰደዱበት በማሰባሰብ መልሶ ማቋቋም፣ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ መገንባት፣ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በመደገፍ እንዲያገግሙ ማድረግ፣ የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ጠግኖ ሥራ ማስጀመር፣ በሽግግር ፍትሕ አማካይነት የተጎጂዎችን ጠባሳ ማከምና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን በማስቀጠል ሰላም ማስፈን ነው፡፡ ይሁንና ጦርነቱ ቆሞ በአንፃራዊነት የሰላም አየር ሽው ሲል፣ ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበሩ ቅራኔዎች ሊመልሱ የሚችሉ ንትርኮች በግራና በቀኝ እየተሰሙ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ለሁለት ዓመታት ያህል የተካሄደው አውዳሚ ጦርነት ወላፈን ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን፣ ሁለቱን እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ተፋላሚ ኃይሎች ጭምር ክንድ ያዛለና ጉልበት ያላመ እንደነበር የታወቀ ነው፡፡ በሰላም ሒደቱ ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሰከነ መንገድ በመነጋገር መፍታት የማይፈልጉ ግን፣ አሁንም ከሩቅ ሆነው እንደ ፊልም የሚያዩትን አውዳሚ ፍልሚያ እንደገና ለማስጀመር በሕዝብ ስም ሲቆምሩ ዝም ማለት ተገቢ አይደለም፡፡

አሁንም ደግመን ደጋግመን ለማሳሰብም ሆነ ለማስታወስ የምንፈልገው፣ በኢትዮጵያ ምድር በሕዝብ መካከል ምንም ችግር እንደሌለ ነው፡፡ በብሔርም ሆነ በእምነት አማካይነት በሕዝብ መካከል አንዳችም ግጭት ተቀስቅሶ አያውቅም፡፡ የፖለቲካ ልሂቃኑ አፋቸውንም ሆነ እጃቸውን መሰብሰብ ሲጀምሩ አገር ሰላም ሆና ሕዝብ ዕፎይ እንደሚል በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ማስተዋል የተሳናቸው ፖለቲከኞች ዘመን ባለፈበት አስተሳሰብ ላይ ተቸንክረው ሕዝብን ከሕዝብ ለማናከስ መርዝ መርጨት ሲጀምሩ፣ ሰላም የሰነበቱ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችና መደበኛ ሚዲያዎች በአንድ ጊዜ ወደ ጦር ሜዳነት ይለወጣሉ፡፡ ስለሰላም ሲሰብኩ የነበሩ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች እንደ እስስት ተለውጠው ደም ለማፋሰስ ይቅበዘበዛሉ፡፡ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ተቋማት ባህሪያቸው ተለውጦ፣ በሕዝባችን ላይ መከራ የሚያመጡ የጥላቻ ንግግሮች ይስተጋባሉ፡፡ ስለሰላም የሚያስተምሩ የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎች ይዘለፋሉ፣ ለሰላም የሚደክሙ የአገር ሽማግሌዎች ፋይዳ እንደሌላቸው ተደርገው ይሰደባሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሰላም እንዳይደፈርስ ሥጋቱን ሲናገር አዳማጭ የለውም፡፡ ግጭት ወይም ጦርነት ሲቀሰቀስ ግን ሰለባው እሱ ነው፡፡

ፖለቲከኞችና አጃቢዎቻቸው ከትናንት የገዘፉ ስህተቶች በመማር አገርን ለውድመት፣ ሕዝብን ደግሞ ለዕልቂትና ለመከራ ከዳረጉ አደገኛ ባህሪያት መለያየት አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ ከጦርነትና ከግጭት አዙሪት ውስጥ መውጣት የምትችለው፣ ብዙዎቹ ፖለቲከኞችና ደቀ መዝሙሮቻቸው ባህሪያቸውን ሲለውጡ ብቻ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ለሁለት ዓመታት ያህል የተካሄደው አውዳሚ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ‹‹በሕግ አምላክ›› ተብለው ሲለመኑ የነበሩ ፖለቲከኞች፣ ዋነኛ ችግራቸው ዕብሪትና ድንቁርና የተጠናወተውን ባህሪያቸውን ለመግራት አለመቻላቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በትዕቢትና በዕብሪት የተሞላውን ጭንቅላታቸውን የተቆጣጠረው ዕብደት የሰላም ፈላጊዎችን ተማፅኖ ማዳመጥ ባለመፈለጉ ብቻ፣ በመቶ ሺዎች አልቀው በሚሊዮኖች ከቀዬአቸው ተሰደው በየሜዳው ተበትነዋል፡፡ በጦርነቱ ወቅት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ለአካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ መከራና ሥቃይ በኋላ በውጭ ኃይሎች አሸማጋይነት አንፃራዊ ሰላም ሰፍኖ ፖለቲከኞች ለዕርቅ ሲነሳሱ፣ ከምንም ነገር በላይ በሰቆቃ ውስጥ አሳሩን ለበላው ሕዝባችን ዘላቂ ሰላም ትኩረት ይስጡ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...

አዲስ ሲኖዶስ አቋቁመዋል በተባሉና በኦሮሚያ መንግሥት ላይ ክስ ለመመሥረት ዕግድ ተጠየቀ

የፌዴራል ፖሊስና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽኖችም ተካተዋል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ቤተክህነት ባቀረበችው የይግባኝ አቤቱታ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለዕሮብ ተቀጠረ

የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሀገወጥ ነው በተባለው አዲሱ ሲኖዶስና...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ከገባችበት አረንቋ ውስጥ በፍጥነት ትውጣ!

የአገር ህልውና ከሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ አገር ሰላም ውላ ማደር የምትችለው ደግሞ የሕዝብ ደኅንነት አስተማማኝ ሲሆን ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥት በአገር ህልውና...

የፈተናው ውጤት የፖለቲካው ዝቅጠት ማሳያ ነው!

በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከአጠቃላይ ተፈታኞች ውስጥ 3.3 በመቶ ያህሉ ብቻ ማለፋቸው፣ የአገሪቱን የትምህርት ጥራት ደረጃ በሚገባ ያመላከተ መስተዋት እንደሆነ አድርጎ መቀበል ተገቢ ነው፡፡...

የምግብ ችግር አገራዊ ሥጋት ስለደቀነ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆችን አቅም በብርቱ እየፈተኑ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለማስቀደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የምግብና የሰላም...