Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበእስር ላይ የሚገኙት የኢሰመጉ ሠራተኞች ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ

በእስር ላይ የሚገኙት የኢሰመጉ ሠራተኞች ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ

ቀን:

ከታሰሩ ሰባተኛ ቀናቸውን ያስቆጠሩት አራት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ሠራተኞች ዛሬ በሰበታ ወረዳ ፍርድ ቤት ለሁለተኛ ጊዜ ይቀርባሉ፡፡ ሠራተኞቹ በአስቸኳይ እንዲፈቱ 12 የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ባወጡት መግለጫ ጠይቀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዙሪያ ዓለምገና አካባቢ እየተካሄደ ባለው ቤት የማፍረስ ዘመቻ ምክንያት ቤታቸው የፈረሰባቸው ግለቦች ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት ጉዳዩን የሚያጣሩ ኢሰመጉ ሦስት ባለሙያዎችን ወደ ቦታው ልኮ እንደነበረ የገለጹ ሲሆን፣ ባለሙያዎቹና የድርጅቱ ሾፌር በፖሊስ ተይዘው ዓለምገና አካባቢ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ እንደታሰሩ ታኅሳስ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ኢሰመጉ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡

ሠራተኞቹ ፍርድ ቤት ቀርበው ከተጠየቀባቸው 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ውስጥ አምስት ቀናት ተፈቅዶ በዛሬው ዕለት ለሁለተኛ ጊዜ በሰበታ ወረዳ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ፡፡

ሠራተኞቹ ባለፈው ሳምንት ፍርድ ቤት በቀረቡበት የመጀመሪያ ቀን ፖሊስ ‹‹ለምንድነው ፈቃድ ሳልሰጣችሁ ገብታችሁ የምትመረምሩት፣ የትብብር ደብዳቤ ሳትይዙ ነው የመጣችሁት›› የሚሉ ሁለት ጥያቄዎች አቅርቦላቸው እንደነበር ኢሰመጉ አስታውቋል፡፡

ኢሰመጉ በተጨማሪም ከሚሠራው ሥራ ጋር በተገናኘ ጫናና ማስፈራራት እየደረሰበት እንደሚገኝ ታኅሳስ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ገልጾ የነበረ ሲሆን፣ ይህ ድርጊት ድርጅቱ የተቋቋመበትን ዓላማ እንዳይፈጽምና ሠራተኞቹም የሙያ ነፃነታቸውን ጠብቀው እንዳይሠሩ የሚያደርግ ነው ሲል ወቀሳ አቅርቦ ነበር፡፡

ድርጊቱ ከዚህም ባሻገር የሲቪክ ምኅዳሩን የሚያጠብና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የሚያከናውኑትን ሥራ የሚያደናቅፍ፣ በሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ላይ የሚሠሩ ሌሎች ተቋማትንም የሚያሸማቅቅ ድርጊት መሆኑን ማሳወቁ የሚታወስ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት (ኢሰመድኅ)፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)፤ የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)፣ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች (LHR)፤ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ሴቶች ማኅበር (EWLA)፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል (EHRDC)፣ የኢትዮጵያ ሴቶችና ሕፃናት ማኅበራት ኅብረት (UEWCA)፣ ሴታዊት ንቀናቄ (Setaweet)፣ ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ (IAG)፣ ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ (AHRE)፣ የሴቶች ኅብረት ለሰላምና ለማኅበራዊ ፍትሕ (WASP) እና የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት (NEWA) በበኩላቸው ሠራተኞቹ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቀው ድርጊቱን በጋራ ባወጡት መግለጫ ኮንነዋል፡፡

የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶቹ ስም በጋዜጣዊ መግለጫው ግርጌ በዝርዝር የተቀመጠ ሲሆን፣ ‹‹የታሰሩት የኢሰመጉ ሠራተኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣ እንዲሁም የዘፈቀደ እስራቱን የፈጸሙት የመንግሥት አካላት በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ አበክረን እንጠይቃለን፤›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

አሥራ ሁለቱ የሲቪክ ማኅበራት ባወጡት ጋዜጣዊ መግለጫም፣ ‹‹በቅርቡ የተከለሰው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 በኢትዮጵያ ለመብቶች የመሟገት ሥራ ለሚሠሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ቢሆንም፣ ከዚህ በፊት ከተስተዋሉ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ጫናዎች በተጨማሪ የኢሰመጉ ባለሙያዎች እስር የሲቪክ ምኅዳሩ ላይ የማይገባ አሻራ እያሳረፉ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትንና የአፍሪካ ኅብረትን ዓለም አቀፍና አኅጉራዊ የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶችን አፅድቃለች፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም ከአንቀጽ 29 እስከ 31 የመናገር ነፃነትን፣ የመሰብሰብ ነፃነትንና የመደራጅትና ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ መብትን በግልጽ አስቀምጧል፤›› በማለት፣ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶችን የሚከበሩበትን ሁኔታ የማሟላት ኃላፊነት እንዳለባትም በመግለጫቸው ተጠቅሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...