Monday, February 6, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማንኛውንም ከመሬት ጋር የተያያዘ አገልግሎት አገደ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሁሉም ክፍላተ ከተሞች የሚሰጠውን ማንኛውም ከመሬት ጋር የተያያዘ አገልግሎት ከጥር 1 ቀን 2015 ዓ.ም. በጊዜያዊነት አገደ፡፡

ሪፖርተር የተመለከተውና በከተማው የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ቀንአ ያደታ (ዶ/ር) ተፈርሞ ለሁሉም ክፍላተ ከተሞች የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤትና ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት የተመራው ደብዳቤ፣ ከዚህ ቀደም በማዕከል ከተወሰኑና ወደፊትም በልዩ ሁኔታ ከሚወሰኑ በስተቀር ከጥር 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ማንኛውም የመሬት አገልግሎት በጊዜያዊነት የታገደ መሆኑን ይገልጻል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የመሬት ወረራና ሕገወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቆ፣ ነገር ግን አሁንም የተለያዩ ሥልቶችን በመጠቀም በመሬት ወረራና በሕገወጥ ድርጊቶች እየተሳተፉ ያሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ስለመኖራቸው መለየቱን አስታውቋል፡፡

በከተማዋ በተለይም የመሬት ወረራንና ሕገወጥ ድርጊቶችን ለመከላከልና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሔ ማስቀመጥ ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ መገደዱን የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ በደብዳቤው ገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ቀንአ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በከተማዋ ውስጥ የሚደረገው የመሬት ወረራ እየጨመረ ስለሆነ ነገሮችን ለማስተካከል ተብሎ የተወሰነ ነው፡፡

ሕገወጥ የመሬት ወረራው የማስፋፊያ ክፍላተ ከተሞች በሚባሉት በተለይም ንፋስ ስልክ ላፍቶና ለሚ ኩራ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን የተናገሩት ቀንአ (ዶ/ር)፣ አልፎ አልፎ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ላይ ሕገወጥነቱ መስተዋሉን ገልጸዋል፡፡

ከጥር 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ማንኛውም ከመሬት ጋር የሚያያዝ አገልግሎት በጊዜያዊነት እንደተቋረጠ ያስረዱት የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊው፣ ነገር ግን በጋራ ዕውቅና የበላይ አመራሩ በተለየ የሚወስናቸው ውሳኔዎች ይኖራሉ ብለዋል፡፡

የመሬት ልማትና አስተዳደር ስትራቴጂክ ቢሮ ካውንስል የወሰናቸው፣ እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ የወሰናቸው ውሳኔዎች ተፈጻሚነታቸው የሚቀጥልና የማይቆም መሆኑ ተገልጿል፡፡

ዕርምጃው በከተማ አስተዳደሩ ከተጀመረው የሙስና ትግል ጋር ይያያዛል ያሉት ቀንአ (ዶ/ር)፣ ከዚሁ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እስኪጠሩ ተብሎ የተወሰደ እንጂ በቋሚነት የሚዘልቅ አለመሆኑን አብራርተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 30ኛውን የመሬት ሊዝ ጨረታ ሊያወጣ ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ሲገለጽ የነበረ ቢሆንም፣ ለጨረታ ይቀርባሉ የተባሉ ኪስ ቦታዎች በሕገወጦች መወረራቸው ተሰምቷል፡፡

ቢሮው የመሬት አገልግሎትን በጊዜያዊነት እንዲታገድ ያሳለፈው ውሳኔ፣ በከተማዋ የመሬት ወረራ እየጨመረ ስለመጣ መስተካከል የሚገባቸውን ጉዳዮች ለማስተካል የተወሰደ ዕርምጃ መሆኑን ኃላፊው ገልጸው፣ የተላለፈው ውሳኔ ከመሬት ሊዝ ጨረታ ጋር የማይገናኝና የሊዝ ጨረታ ሒደቱ ባለበት እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮው በዋናነት ሦስት ጉዳዮች ላይ አተኩሮ እየሠራ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፣ የመጀመሪያው የመሬት ልማትና አስተዳደርን ዘመናዊ ማድረግን ሲመለከት፣ ይህም ቴክኖሎጂን የመጠቀምና መሬት ወደ ካዳስተር እንዲገባ ማድረግ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

በሌላ በኩል መሬት የጋራ ሀብት በመሆኑ ለቁጥጥሩም የመንግሥት ተቋም ብቻ ሳይሆን፣ የኅብረተሰቡን ተሳትፎ ማጠናከር ስለሚያስፈልግ በዚያ ላይ እየተሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

እንደ ቀንአ (ዶ/ር) ማብራሪያ፣ ሦስተኛው ጉዳይ የሕግ የበላይነትን ማስከበር ነው፡፡ ሕግ የሚጥሱትንና በሕገወጥ መንገድ መሬት የሚወሩትን በፀጥታ ኃይሎችና በፍትሕ ተቋማት ወደ ሕግ ቀርበው እንዲጠየቁ ለማድረግ እየተሠራበት መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

በተያያዘም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኅዳር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ማንኛውም የቋሚ ንብረት ስም ዝውውር አገልግሎት እንዳይሰጥ ማገዱ የሚታወስ ሲሆን፣ ከተጠቀሰው ቀን ጀምሮ በሁሉም ክፍላተ ከተሞች አገልግሎቱ እንደታገደ ይገኛል፡፡

የከተማው አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ቢንያም ምክሩ በኅዳር ወር ለፍትሕ ቢሮ፣ ለመሬት ልማትና አስተዳደርና በሥሩ ላሉ ተቋማት፣ እንዲሁም ለ11 ክፍላተ ከተሞች በጻፉት ደብዳቤ፣ በአዲስ አበባ ሕገወጥነትን ለመከላከል እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ውጤታማ ለማድረግ የተወሰደ ዕርምጃ መሆኑን ማስታወቃቸው ይታወሳል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች