Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበመጠለያ ውስጥ ያሉ ዜጎች ለመጀመሪያ ጊዜ ለደቡብ ክልል ሕዝበ ውሳኔ ድምፅ ሊሰጡ...

በመጠለያ ውስጥ ያሉ ዜጎች ለመጀመሪያ ጊዜ ለደቡብ ክልል ሕዝበ ውሳኔ ድምፅ ሊሰጡ ነው

ቀን:

  • ከ1,700 በላይ ተፈናቃዮች ተመዝግበዋል

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በኮንሶ ዞን፣ በአሌና በደራሼ ልዩ ወረዳዎች በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የተጠለሉ ዜጎች፣ በክልሉ ሊካሄድ በታሰበው ሕዝበ ውሳኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፅ ሊሰጡ ነው፡፡

ከፌደሬሽን ምክር ቤት በተመራለት መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሊያካሂደው ባሰበው ሕዝበ ውሳኔ ተሳትፎ እንዲያደርጉ፣ ቦርዱ 790 ወንዶችና 937 ሴቶች በአጠቃላይ 1,727 ተፈናቃዮችን በሰባት የተፈናቃዮች ምርጫ ጣቢያዎች መመዝገቡን፣ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ አስታውቀዋል፡፡

የመራጮች ምዝገባ መጠናቀቅን በማስመልከት ከትናንት በስቲያ ሰኞ  ጥር 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ዋና ሰብሳቢዋ፣ ሕዝበ ውሳኔው በሚካሄድባቸው የክልሉ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ድምፅ ለመስጠት በአጠቃላይ 2.9 ሚሊዮን ዜጎች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹ዋና ከሚባሉት ሒደቶች አንዱ ነበር፤›› ብለው የገለጹትን ተፈናቃዮች ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፅ እንዲሰጡ የመመዝገብ ሒደት በሰባት ጣቢያዎች ሲያከናውኑ፣ ለምርጫ አስፈጻሚዎችም አስፈላጊውን ሥልጠና በመስጠት እንደሆነም አክለዋል፡፡

በስድስቱ ዞኖችና በአምስቱ ልዩ ወረዳዎች ከተቋቋሙት 11 የማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶች በተጨማሪ 31 ንዑስ ማስተባበሪያ ማዕከላት፣ እንዲሁም 3,769 የምርጫ ጣቢያዎች ሕዝበ ውሳኔውን ለማከናወን እንደተዘጋጁና እስከ ጥር 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ምዝገባ ሲያካሄዱ እንደነበር ተገልጿል፡፡ በምርጫ እስፈጻሚዎች በኩል፣ 11,485 አስፈጻሚዎች የመራጮች ምዝገባ በተመለከተ፣ እንዲሁም የሚጠበቅባቸውን ሥነ ምግባር በሚመለከት ሥልጠና ወስደው በየጣቢያዎቹ ተገኝተው ምዝገባ ሲያካሄዱ እንደነበር ዋና ሰብሳቢዋ ገልጸዋል፡፡

ሆኖም በ24 የምርጫ ጣቢያዎች ‹‹ከፍተኛ የሆነ የሕግና የአፈጻጸም ጥሰቶች›› መገኘታቸውን፣ በምዝገባ ሒደቱና አፈጻጸም ላይ ‹‹ቦርዱ እንደ ዋና ሳንካና ተግዳሮት የሚቆጥረው›› ችግር እንዳጋጠመ ተነግሯል፡፡ ምርጫ ቦርድ በራሱ ክትትል ያረጋገጣቸውና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያሰማራቸው ተከታታዮች በግንባር የተመለከቷቸው ጥሰቶች እንዳሉ ተነግሯል፡፡ እነሱም የመራጮች ካርድ ለማይገባቸው ግለሰቦች መሰጠት፣ በምርጫ ጣቢያ ያልተገኙ ሰዎችን በመራጭነት መመዝገብ፣ ከጣቢያ ውጪ ካርዶች ማደልና የመሳሰሉት እንደሆኑ በዝርዝር ተገልጿል፡፡

የአሠራር ጥሰቶች በታዩባቸው ጣቢያዎች ሲካሄድ የነበረው ምዝገባ ተሰርዞ እንደገና ሌላ የመራጮች ምዝገባ ከጥር 1 ቀን 2015 ዓ.ም. በኋላ ባሉት ጥቂት ቀናት በድጋሚ እንደሚካሄድ በመግለጫው ወቅት ተብራርቷል፡፡ ከምዝገባ ስረዛ በኋላ ቦርዱ በጣቢያዎቹ የነበሩትን የምርጫ አስፈጻሚዎች ኮንትራት መሰረዙን ወ/ሪት ብርቱካን ተናግረዋል፡፡

በሕግና በአፈጻጸም ጥሰት ተሳታፊ የነበሩ ሰዎች በወንጀል እንዲጠየቁ፣ ‹‹በተፈጸሙት የወንጀል ጥሰቶች ማን ምን እንደፈጸመ፣ የተባበሯቸውን የአስተዳደር ሠራተኞች እነ ማን እንደሆኑ›› በመዘርዘር ለፌደራል ፖሊስ ደብዳቤ በመጻፍ ቦርዱ መጠየቁ ተገልጿል፡፡ ቦርዱ እስከ ሰኞ ጥር 1 ቀን 2015 ዓ.ም. መግለጫው እስከሰጠበት ድረስ፣ መልስ አለማግኘቱንና በአፋጣኝ መልስ ማግኘት እንዳለበት ወ/ሪት ብርቱካን አሳስበዋል፡፡

‹‹ይህንን ለምርጫ ሒደት ትልቅ ችግር የሚኖረውና ዜጎች የሚኖራቸውን እምነት የሚያሳጣ የሕግ መተላለፍ በቶሎ መፍትሔ መሰጠት ይኖርባቸዋል፤›› ሲሉ ዋና ሰብሳቢዋ ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግና ፍርድ ቤት የሕግ ሒደቱን እንዲያፋጥኑ ጠይቀዋል፡፡

የፌደሬሽን ምክር ቤት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ባሳለፈው ውሳኔ በክልሉ የሚገኙት ስድስት ዞኖች (ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦና ጎፋ) ከአምስት ልዩ ወረዳዎች (ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮና ደራሼ) ጋር በመሆን ‹‹ደቡብ ኢትዮጵያ›› በሚባል የክልል አደረጃጀት እንዲዋቀሩ፣ ለዚህም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔ እንደሚያካሂድ አስታውቆ ነበር፡፡

ከዚህ በፊት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሥር ከነበሩት መሀል የሲዳማ ዞን ወደ ክልልነት አስቀድሞ በሕዝበ ውሳኔ ከተሸጋገረ በኋላ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በሕዝበ ውሳኔ አሥራ አንደኛው የአገሪቱ ክልል ሆኗል፡፡

ሁለቱ ክልሎች እንዲመሠረቱ በተካሄዱት ሕዝበ ውሳኔዎች የነበሩት ምርጫዎች ‹‹በነባሩ ክልል እንቀጥል አልያም እንደ ‹‹አዲስ ክልል እንመሥርት›› የሚል የነበረ ሲሆን፣ የአሁኑ ሕዝበ ውሳኔ ማስኬጃ ምርጫዎች ግን በአዲስ ክልል ለመደራጀት የተነሳውን ውሳኔ እንደግፋለን አልያም አንደግፍም የሚል ነው፡፡ ለዚህም ‹‹እንደግፋለን›› ለሚለው ነጭ እርግብ እንደ ምልክት የሚጠቀሙ ሲሆን፣ ‹‹አንደግፍም›› የሚሉ ደግሞ የጎጆ ቤት እንደ ምልክት እንዲጠቀሙት ይደረጋል፡፡

በፊት ተካሂደው ከነበሩት ሁለቱ ሕዝበ ውሳኔዎች አንፃር የዚህኛው ሕዝበ ውሳኔ የምርጫ አማራጮች መለያየት አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለተነሱላቸው ጥያቄ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሲያስረዱ፣ ከበፊቶቹ ትምህርት በመውሰድ ‹‹እንፈልጋለን›› አልያም ‹‹አንፈልግም›› ተብሎ መቅረቡ የተሻለ ለመራጮች ጥያቄውን ግልጽ ያደርገዋል ተብሎ እንደተዘጋጀ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ነባሩ ደቡብ ክልል በተለያዩ ሒደቶችና ለውጦች ውስጥ በመኖሩ፣ የተለያዩ ጥያቄዎችና ምርጫዎች እየታዩ በመሆናቸው ምን ዓይነት የአደረጃጀት ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል ለማወቅ እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም ደግሞ የፌደሬሽን ምክር ቤት ሕዝበ ውሳኔውን እንዲያካሂድ ለቦርዱ ሲመራለት፣ ‹‹በአዲስ ክልል የመደራጀት ሐሳብና ጥያቄ በሕዝብ ድምፅ እንደሚደገፍና እንደማይደገፍ መዝናችሁ ንገሩን›› በመባሉ እንደሆነ ዋና ሰብሳቢዋ ገልጸዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...