Friday, March 1, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት የነዳጅ አዳዮች የትርፍ ህዳግ ማስተካከያ ቢያደርግም አዳዮችን አላስደሰተም

ተዛማጅ ፅሁፎች

ነዳጅ አዳዮች ከሁለት ዓመታት በላይ ሲጠይቁ ለነበረው የትርፍ ህዳግ ማስተካከያ ጥያቄ መንግሥት መልስ የሰጠ ቢሆንም፣ አዳዮቹ ግን በጭማሪው አለመደሰታቸውን ተናገሩ፡፡

አዳዮች ከአንድ ሊትር ነዳጅ የሚያገኙት ትርፍ በ64 ሳንቲም ያደገ ሲሆን፣ በተደረገው የጭማሪ መጠን አሁንም ቅሬታ እንዳላቸውና መጠኑ እንደሚያንስ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ኃላፊዎች በበኩላቸው ጭማሪው በጥናት የተደረገና አሁናዊ ሁኔታዎችን  ያገናዘበ በመሆኑ እንደሚበቃቸው ገልጸዋል፡፡

የነዳጅ ማደያ ባለቤቶች በአንድ ሊትር ሲያገኙ የነበረው የ23 ሳንቲም ትርፍ እንዲያድግላቸው ለበርካታ ጊዜያት ሲጠይቁ የነበረ በመሆናቸው፣ ከታኅሳስ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በሊትር ወደ 88 ሳንቲም ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ ሆኖም ግን የተደረገላቸው ጭማሪ አሁንም በትርፍ ለመሥራት እንደማያስችላቸውና አዳዲስ በዘርፉ ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ የሚፈልጉ ባለሀብቶችን እንደማይጋብዝ በመናገር ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳህረላ አብዱላሂ ለሪፖርተር እንደገለጹት የትርፍ ህዳጉ ሲከለስ አዳዮች ተሳትፎ አድርገው ነበር፡፡ ባለሥልጣኑ ጥናት ሲያካሂድ በወሰደው መሥፈርት ላይም ተግባብተውና ጥናቱ ካለቀም በኋላ ዓይተውት የተለየ አስተያየት እንዳልነበራቸው ተናግረዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ፣ የተወሰዱት መሥፈርቶች የ2013 ኦዲት ሪፖርት፣ አጠቃላይ ወጪያቸውና ሌሎች በርካታ ነገሮች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ በ2013 የነበረው የነዳጅ መግዣ ዋጋ ወደ አንድ ሚሊዮን ብር አካባቢ ሲሆን፣ አሁን ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡ ይህንንም ከግምት በማስገባት በዚህኛው ዓመት መስከረም ወር ላይ የነበረውን 2.4 ሚሊዮን ብር መግዣ ዋጋ በጥናቱ እንደተካተተ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ወ/ሮ ሳህረላ ስለ አጨማመሩ ፍትሐዊነት ሲያስረዱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከአንድ ዓመት በፊት ያፀደቀው የትርፍ ህዳግ አሠራር ውሳኔ መሠረት ማደያዎች ከ0.5 በመቶ እስከ አምስት በመቶ ማትረፍ እንዲችሉ ነው፡፡ አሁን ከተደረገው ማስተካከያ በፊት አዳዮች ያገኙ የነበረው የወጫቸው 0.25 በመቶ የሆነው ትርፍ ወደ 1.5 በመቶ ማደጉ ፍትሐዊ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ማስተካከያ በየዓመቱ እንዲደረግ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ደንግጎ የነበረ ሲሆን፣ ውሳኔውም ተግባራዊ የሆነው ልክ ውሳኔው በፀደቀ በአንድ ዓመቱ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማኅበር የሥራ አመራር ቦርድ አባል የሆኑት አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ በማደያዎቹ በኩል ያለውን ቅሬታ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ይህንንም ሲያስረዱ ከሁለት ዓመት በፊት አንድ 45,000 ሊትር የሚይዝ ነዳጅ ጫኝ ተሳቢ ተሽከርካሪ የአንድ ሚሊዮን ብር ነዳጅ አራግፎ ሲሸጡ የሚያገኙት በሊትር 0.23 ሳንቲም ተሰልቶ የወጪያቸውን አንድ በመቶ ትርፍ ነበር፡፡ ይህ ትርፍ የነዳጁ ወጪ እየጨመረ በመጣ ቁጥር ወርዶ የወጪያቸውን 0.25 በመቶ ደርሶ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን የሚደረገው ማስተካከያን ተከትሎ ወደ 1.3 በመቶ ማደጉን አምነዋል፡፡ እንደ አቶ ኤፍሬም ገለጻ ጭማሪው የትርፍ ማደግን ሳይሆን የሚያሳየው ለሁለት ዓመታት ሲጠራቀም የነበረውን ክምችትና ጫና፣ እንዲሁም በፊት ሲያገኙ የነበረውንና አሁን እያጡ ያለውን የሚያስተካክል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹የተደረገው ማሻሻያ የዛሬ ሁለት ዓመት ነዳጅ አዳዮች ያገኙት ወደነበረው ትርፍ ተመለሰና ጫና አቃለለ እንጂ ተጨባጭ ማሻሻያ አልተደረገም፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ማኅበሩ በበኩሉ በርካታ ጊዜያት መንግሥት ጭማሪ እንዲያደርግ ግፊት ሲያደርግ የነበረ ሲሆን፣ ይህም በስተመጨረሻ ምላሽ ማግኘቱ በጥሩ ጎኑ እንዳዩት፣ ባለሥልጣኑም አሳታፊ ሒደቶችን አካሂዶ ከረዥም ጊዜያት በኋላ ውሳኔ ላይ መድረሱ እንደሚያስመሰግነው አቶ ኤፍሬም ተናግረዋል፡፡

አክለውም ዘርፉ አዳዲስ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ የሚፈልጉ ባለሀብቶች እንዳይገቡበት የሚጋብዝ፣ አነስተኛ መጠን ያለው ነዳጅ የሚሸጡ ማደያዎች በሥራው እንዳይበረታቱ የሚያደርግ፣ በተጨማሪም ከሌላው የቢዝነስ ዘርፎች ጋር ሲነፃፀር ሳቢ አለመሆኑን አሁንም እንደሚቀጥል አቶ ኤፍሬም ተናግረዋል፡፡ በተለይ ክፍለ አገር ያሉ ማደያዎች ትንሽ መጠን ያለው ስለሆነ የሚሸጡት ባለማዋጠቱ ተጨማሪ ብር በትርፍ ህዳጉ ላይ እየጨመሩ እንደሚሸጡ፣ በከተማ አካባቢ ግን ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ ስለሚሸጥና ሌላም እንደ ካፌ ዓይነት ሥራ ስለሚሠራ ተጨማሪ ትርፍ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

‹‹በከተማ ቢሆንም ተፈላጊ ቦታዎች ላይ ባለሀብቶች ሕንፃ ከምንሠራ ብለው ነው ማደያ የሚገነቡት፡፡ መሬቱን ከማደያ በሌላ ቢዝነስ ላይ ቢያውሉት ስለሚጠቀሙ አይገነቡም፤›› ሲሉ የማደያ ቢዝነስ በከተማ ላይ አትራፊነቱ ጥያቄ ውስጥ መግባቱን አቶ ኤፍሬም ይገልጻሉ፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳህረላ እንደገለጹት በማደያ ላይ ያለው ኢንቨስትመንት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን አምነው፣ ምክንያቶቹም የትርፍ ህዳግ ጉዳይ፣ የነዳጅ መግዣ ዋጋ ከ2014 ዓ.ም. ወዲህ እየጨመረ መምጣቱንና ሌሎች በብድር መግዛት መቆም ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች