(በድሉ ዋቅጅራ )
መጋረጃ ጨርቋን!
የገመና ግንቧን!
ምን ነካው እምነቷን?!
ካልጠፋ ሲባጎ፤
ኑሮ እንዴት አድርጎ፤
ዳዋ ሆኖ ቢያጥራት፣
ማቅ ሆኖ ቢያዘቅጣት፤
ትሸሸው ቢያቅታት፣
ትጋፋው ቢደክማት፤
ግርማና ሞገሷን፣
መሸሸጊያ ካቧን፣ ገመናዋን ንዳ፣
ህይወቷን አጠፋች፣ መጋረጃ ገምዳ?!
‹‹ልጄ ገመናህን፣ በብብቻህ ያዘው፤
እንደ ቅባ ቅዱስ፣ ከራስህ ሸሽገው፡፡
እንኳን ማጀትህን፣ የጓዳህን ወረት፣
እንኳን ሌማትህን፣ የወስፋትህን ቁመት፣
እንኳን መኝታህን፣ የምትሞትበትን፤
ከጀማው ተጋፍተህ፣ የረገጥክበትን፣
የተመኘኸውን፣ አይንህ ያረፈበትን፤
ከአዳሜ ሸሽገው፡፡ . . . .››
ትለኝ የነበረ፤
ምን ነካት እምዬን፣ ምን ነካው እምነቷን?!
የውሸቷን ኖራ፣ ሞተች የእውነቷን?!
—————
የካቲት፣ 2012፣ አዲስ አበባ