Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ወልቃይት የአማራ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያም እስትንፋስ ነው›› አቶ ዓብዩ በለው፣ የልሳነ ግፉአን ድርጅት ፕሬዚዳንት

ለወልቃይት የአማራ ማንነት መከበር የሚታገለው የልሳነ ግፉአን ድርጅት ፕሬዚዳንት የወልቃይት ጥያቄን ለመመለስ መንገዱ ቀላል ነው ይላሉ፡፡ የሪፖርተር ቆይታ ዓምድ እንግዳ የሆኑት አቶ ዓብዩ በለው፡፡ የወልቃይት ችግር በፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅጣጫ፣ በሪፈረንደምም ሆነ በድርድር ሳይሆን በፖለቲካ ውሳኔ ነው የሚፈታው ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ ከሰሞኑ ትኩረት እየሳበ ካለው የወልቃይት ጉዳይ ጋር በተገናኘ ዮናስ አማረ ከአቶ ዓብዩ ጋር ካሉበት ኦሀዩ ኮሎምበስ በዋትስአፕ ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- የወልቃይት ጥያቄ የሁለት ክልሎች ፀብ ነው? ወይስ የአማራና የትግራይ ማኅበረሰቦች በጋራ ለመኖር በመቸገራቸው የተፈጠረ ጥያቄ?

አቶ አብዩ፡- የሁለቱ ማኅበረሰቦች በጋራ የመኖር ችግር በፍፁም አይደለም፡፡ ሁለቱ ማኅበረሰቦች ወልቃይትን ለረዥም ዘመን በሰላም፣ በፍቅርና በአንድነት ኖረውበታል፡፡ ወልቃይት በታሪክ አጋጣሚ ሰፋፊ የመስኖ እርሻ ቀድሞ የለማበት አካባቢ ነበር፡፡ ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም በአንድ ወቅት ለቪኦኤ በሰጡት ቃለ መጠይቅ እንደገለጹት፣ በተለይ በጃንሆይ ዘመን ለእርሻ ሥራዎች እስከ 30 ሺሕ የትግራይ ተወላጆች ወደ ወልቃይት ይመጡ ነበር፡፡ እንደ ሑመራ ባሉ የእርሻ ልማቱ ቀድሞ ወደ ተስፋፋባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የትግራይ ተወላጆች እየመጡ ይሠሩ ነበር፡፡ ከትግራይ ተወላጆች በተጨማሪ ነጋዴዎች፣ አራሾች፣ ባለሀብቶች፣ ሠራተኞችና ሌሎችም ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ይመጡ ነበር፡፡ የኤርትራ ተወላጆች ከማንም ቀድመው መምጣት እንደጀመሩ ይነገራል፡፡ የሱዳን ተወላጆችም ይመጡ ነበር፡፡ ከሌላው የጎንደር ክፍልና ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎችም ለንግድ ለሥራ የሚመጣው ሁሉ ወልቃይት በሰላምና በፍቅር ኖሯል፡፡ በሰላምና በአንድነት ሠርቷል፡፡ የትግራይ ተወላጆች ለወልቃይት ማኅበረሰብ ቋንቋቸውን ማስተላለፍ የቻሉት በዚህ መሰሉ ማኅበራዊ መስተጋብር ነው፡፡ ሁለቱ ማኅበረሰቦች ውስጥ ችግር የለም፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጋራ ነው የኖሩት፡፡ ወልቃይቴው አማራ እንደሆነና መሬቱም ርስቱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የትግራይ ተወላጁም ከትግራይ መጥቶ እንደሚኖር ይታወቃል፡፡ ይህ ግን በሰላም የመኖር መሰናክል ሆኖ አያውቅም ነበር፡፡ ዋና የችግሩ ፈጣሪ ሕወሓት ነው፡፡

ሕወሓት ከጥንስሱ ጀምሮ በያዘው ኢትዮጵያን የማፈራረስ ዕቅድና አማራን በጠላትነት ፈርጆ ዕረፍት በመንሳት ለማጥፋት አቅዶ መነሳቱ ነው ትልቁ ችግር የተፈጠረው፡፡ ሕወሓት ታላቋን ትግራይ ለመፍጠርና አገር አድርጎ ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ባለው ፍላጎት ወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት የመሳሰሉ አካባቢዎችን መያዝ ወሳኝ ነው ብሎ ተነሳ፡፡ ከደርግ ጋር በሚዋጋበት ዘመን ወደ ሱዳን መውጫ በር ለማግኘት ሲል ወልቃይትን በማንኛውም መንገድ መያዝ ዓላማ አድርጎ መነሳቱንም፣ የሕወሓት መሥራች ታጋዮች እነ አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ተናግረውታል፡፡ ሕወሓቶች ወልቃይትን በጉልበት የያዙትም ሆነ በአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ የዘር ማፅዳትና ዘር ማጥፋት በመፈጸም አካባቢውን የትግራይ ለማድረግ የፈለጉት ከዚህ አንፃር እንጂ፣ በማኅበረሰቡ መካከል ምንም አለመግባባት ተፈጥሮ አይደለም፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ ምንም ችግር አልነበረም፡፡ ኖሮም አያውቅም፣ ወደፊትም አይኖርም፡፡ ማኅበረሰቡ በደንብ ያውቃል፡፡ ወልቃይት የማን እንደሆነ የትግራይ ተወላጅ በደንብ ያውቀዋል፡፡ ወልቃይት የአማራ መሬት ነው፣ ሕዝቡም አማራ ነው፡፡ ተከዜን ተሻግሮ የሚመጣ ትግሬያዊነት የለም፡፡ ማኅበረሰቡ ጋ ችግር አለ ብለን አናውቅም፣ ወደፊትም ይኖራል ብለን አንገምትም፡፡

ሪፖርተር፡- የወልቃይት ጉዳይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚያስቀምጠው አቅጣጫ እንደሚፈታ መንግሥት በቅርቡ ግልጽ አድርጓል፡፡ እናንተ ይህን መፍትሔ እንደማይሆን በመግለጫ ተቃውማችኋል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት መንገድ መፍትሔ አይሆንም የምትሉበትን ምክንያት ቢያብራሩት?

አቶ ዓብዩ፡- በቅርቡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) የተናገሩትን ማንሳት ይኖርብናል፡፡ ሕወሓት በጉልበት ወልቃይትን መውሰዱን ሬድዋን (አምባሳደር) በግልጽ አውስተዋል፡፡ ሕወሓት በጉልበት መሬቱን ሲወስድ ደግሞ ዝም ብሎ ሳይሆን ብዙ ግፍ ፈጽሞ መውሰዱን እኛ እናውቃለን፡፡ እኛ የዘር ማፅዳትና የዘር ማጥፋት ወንጀል በዚያ አካባቢ ተፈጽሟል ነው የምንለው፡፡ ሕወሓት የወሰደውን መሬት፣ እንዲሁም የጨፈለቀውን ማንነት ሕጋዊ ለማድረግ ይጠቅመኛል ብሎ የራሱን ሕገ መንግሥት አውጥቷል፡፡ ሕወሓት ለራሱ ብሎ ባወጣው ሕገ መንግሥት ደግሞ የወልቃይት ችግርን ለመፍታት አይቻልም፡፡ ይህ ምናልባትም አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ እንደሚባለው ነው የሚሆነው፡፡ ሕወሓት ጉዳዩን ለማወሳሰብ ብሎ በፈጠረው አካሄድ ችግሩን መፍታት አይቻልም፡፡ የወልቃይት ጉዳይ ቅሚያ ነው፡፡ በጉልበት መወሰዱን የመንግሥት ኃላፊዎች አምነውታል፡፡ ስለዚህ በጉልበት የተወሰደውን ወደ ነበረበት መመለስ ነው መፍትሔው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይፍታው ማለት ችግሩን ያወሳስባል፡፡ አንደኛ ጉዳዩ የተፈጠረው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሌለበት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱም ሆነ ፌዴሬሽን ምክር ከመቋቋማቸው በፊት ነው በጉልበት የተወሰደው፡፡ ሕግ ደግሞ ወደኋላ ተመልሶ ባልነበረበት ቦታ የሆነ ችግርን አይፈታም፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ችግሩን ያወሳስበዋል እንጂ ይፈታዋል ብለን አናምንም፡፡ ምናልባት እነሱ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና አሠራሩን እንዲሻሻል አድርገው ችግሩን ለመፍታት የተሻለ መፍትሔ ይዘው ከቀረቡ እኛ አናውቅም፡፡ በእኛ እምነት ግን ወልቃይት በወረራና በጉልበት ነው የተወሰደው፡፡ ችግሩ መፈታት ያለበትም በፖለቲካ ውሳኔ ወደ ነበረበት በመመለስ ነው፡፡ የተቀማን ማንነት፣ የተጨፈለቀን ማንነት ዕውቅና ሰጥቶ መመለስ ነው፡፡ የወልቃይት ጉዳይ የፍትሕ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን የፍትሕ ጥያቄ አሳንሶ የድንበር ጉዳይ ማድረግ፣ የሁለት ክልሎች ግጭት ማድረግ ተገቢነት አይኖረውም፡፡ ብዙ ጭፍጨፋና ዕልቂት የተፈጠረበትን የፍትሕ ጉዳይ የሁለት ክልሎች ወሰን ወይም መሬት ግጭት አድርጎ ማየት ችግሩን ማቅለል ነው፡፡ ችግሩን አሳንሶ ወይም በተዛባ መንገድ መመልከት ደግሞ የችግሩን አፈታትም ያወሳስበዋል፣ እንዲሁም ያከብደዋል ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- የወልቃይትን ችግር ለመፍታት ሦስት አማራጮች ተደጋግመው ይጠቀሳሉ፡፡ ድርድር፣ ሕዝበ ውሳኔ፣ እንዲሁም የፖለቲካ ውሳኔ እየተባሉ በተደጋጋሚ ይቀርባሉ፡፡ እነዚህ አማራጮች መፍትሔ የሚሆኑበት ወይም የማይሆኑበትን መንገድ በዝርዝር በማስቀመጥ የትኛው ነው የሚበጀው ትላላችሁ?

አቶ ዓብዩ፡- ሕዝበ ውሳኔ ላይ እንምጣ፡፡ ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታ ከተፈለገ የችግሩን መሠረታዊ ምንጭ መመልከት ይኖርብናል፡፡ መንግሥትም ዕውቅና በሰጠው መሠረት ወልቃይት የተወሰደው በጉልበት ወይም በወረራ ነው፡፡ በወረራ ሲወሰድ ደግሞ ሕግ ተጥሶ ነው የተወሰደው፡፡ ሕወሓት ሥልጣን ላይ ሲወጣ ባወጣው በሽግግር መንግሥቱ አዋጅ ቁጥር 7/1984 መሠረት፣ ማንኛውም የግዛት አከላለል በኢትዮጵያ ከ1966 ዓ.ም. በፊት በነበረው እንዲፀና አውጆ ነበር፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረት ጎንደር፣ ወሎና ትግራይ ወዘተ ክፍለ አገር እየተባለ እንዲቀጥል ነው የተደነገገው፡፡ ሕወሓት ግን ሌሎች አካባቢዎችን ለቆ ሲወጣ ወልቃይትን ወደ ጎንደር ሳይመልስ ወደ ትግራይ አጠቃሎት ነበር፡፡ ከተከዜ ምላሽ በጎንደር ግዛት ሥር ተጠቃለው የቆዩ መሬቶችን ወደ ትግራይ አጠቃለላቸው፡፡ በጉልበት የያዛቸውን አካባቢዎች ሕግ ጥሶ የራሱ አደረጋቸው፡፡ ራሱ ያወጣውን ሕግ ጥሶም ወደ ትግራይ ክልል አካለለ፡፡ ሕገ መንግሥቱም ሆነ የፌዴሬሽን  ምክር ቤት ይህ ሁሉ ከተፈጸመ በኋላ የመጡ ናቸው፡፡ በወልቃይት ትግል የተጀመረው ከ1972 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ ሕወሓት ወደ ወልቃይት መግባት የለበትም ብሎ የአካባቢው ሕዝብ ከመጀመርያው ሲዋጋ ነው የኖረው፡፡ ከፋኝ በሚል አደረጃጀት፣ አርበኞች ግንባር፣ ልሳነ ግፉአን እያለ እስካሁን ሲታገል የመጣው ከ1972 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ ሕወሓቶች ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ የሚቃወማቸው እንዳይኖር ዘር የማፅዳት ሥራ ሠርተዋል፡፡ የነቃ የሚባለውን ከሀንም፣ ሼህም፣ ወጣትም፣ ገበሬም ሆነ መምህር ሊቃወም ይችላል የሚባለውን የኅብረተሰብ ክፍል በተለያዩ መንገዶች አጥፍተውታል፡፡ ሴቱንና መሬቱን ብቻ ነው የምንፈልገው በሚለው ብሂላቸው ሊታገለን ይችላል ያሉትን በሙሉ አፅድተዋል፡፡

በቅርቡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያሳተመው የታሪክ ጥናት፣ እንዲሁም ወደፊት የሚወጡት ምርመራዎች የሕወሓቶችን ወንጀል ያጋልጣሉ ተብሎ ይታመናል፡፡ ይህ ሁሉ ጭፍጨፋ የተፈጸመው ደግሞ የወልቃይት ሕዝብ ገና ከትጥቅ ትግሉ ጊዜ ጀምሮ አማራ ነኝ ብሎ ወረራቸውን በመቃወሙ ነው፡፡ እንደ ዳኘው ወልደ ሥላሴ (አምባሳደር)፣ እንዲሁም እንደ ፍትአዝጊ አሰጉ ዓይነት ሰዎች ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ግልጽ ደብዳቤ እስከ መጻፍ ሄደዋል፡፡ ወልቃይት የጎንደር አካል ነው፣ ወደ ትግራይ እንዳታካልሉት ብለው ገና በሽግግር መንግሥቱ ጊዜ ጽፈዋል፡፡   የሚታገላቸው መኖሩንና የሕዝቡ ጥያቄ እንደማይቆም ሲገነዘቡ ግን ማጥፋት ጀመሩ፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የትግራይ ተወላጅ አምጥተው በወልቃይት አስፍረዋል፡፡ የወልቃይትን ተወላጅ ደግሞ በተለያዩ መንገዶች እንዲሰደድ ወይም እንዲጠፋ ነው ያደረጉት፡፡ በተለያየ ሥቃይ ተማሮ ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እንዲበተንና ወደ ሱዳን ጭምር እንዲሰደድ ሕዝቡን አድርገውታል፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ተነስተን ችግሩ በሪፈረንደም (ሕዝበ ውሳኔ) ይፈታ ካልን ጉዳዩ የመርህ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ አንድ ሌባ ሰርቆህ ከሰረቀህ ሌባ ጋር ንብረትህን ተካፈል እንደ መባል ነው፡፡ ሪፈረንደም ውስጥ የሚገባው ለመወሰን ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ሲያጋጥም ነው፡፡ አማራም ሆነ ትግሬ ነኝ ብሎ የሚመጣው ተመጣጣኝ ቢሆንና ለመወሰን ግራ ቢያጋባ፣ ሕዝቡ ራሱ በሪፈረንደም ይወስን ሊባል ይችላል፡፡ ወልቃይት ላይ ግን ከመጀመርያው ጀምሮ አማራ የነበረውን ሕዝብ ለማጥፋትና ወይም በትግራይ ማንነት እንዲዋጥ ለማድረግ እጅግ ብዙ ርቀት ነው የተሄደው፡፡

በዚህ የተነሳ ሪፈረንደም ይደረግ ማለት መርህን አፋልሶ ከሰረቀህ ጋር ተካፈል እንደማለት ብቻ ሳይሆን፣ ለመወሰን የሚያሻማ ጉዳይ በሌለበትና አንዱን ወገን የሚጠቅም ውሳኔ ነው የሚሆነው፡፡ ሦስተኛው ችግር ደግሞ ጉዳዩ የማንነት ጥያቄ መሆኑ ነው፡፡ ማንነት በምርጫ አይገኝም፡፡ ወለጋ ውስጥ ያለ ሰው ኦሮሞ የተባለው ኦሮሞ ለመሆን ምርጫ ተሰጥቶት አይደለም፡፡ ማርቆስ ላይ አማራ አማራ ነህ የተባለውም ሆነ፣ መቀሌ ላይ ትግሬ ትግሬ የሆነው ሁን ተብሎ አይደለም፡፡ የኢሮብ ሕዝብ ኢሮብ የሆነውም ሆነ ሌላው ማኅበረሰብ ማንነቱን ያገኘው በሕዝበ ውሳኔ ወይም በምርጫ አይደለም፡፡ ማንነት የራሱ መሥፈርቶች አሉት፡፡ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ፣ ወግ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ነው የአንድ ማኅበረሰብ ማንነት የሚበየነው፡፡ የወልቃይት ሕዝብ በእነዚህ የማንነት መሥፈርቶች አማራ ነኝ ብሎ ሲታገል ኖሯል፡፡ በሕወሓት አፈና ውስጥ እያለ ራሱ ማንነቴ አማራ ነው ብሎ ፊርማ አሰባስቦ ኮሎኔል ደመቀን መሪ አድርጎ በይፋ ጠይቋል፡፡ ዛሬም ይህ ሕዝብ አማራ ነኝ እያለ ነው፡፡ ራሱን አማራ ነኝ ባለው በዚህ ሕዝብ ላይ ሪፈረንደም ማድረግ መፍትሔ አይሆንም፡፡ ሪፈረንደም በራሱ ይዞት የሚመጣው ችግርም ጉዳዩን ያወሳስበዋል፡፡ ስለዚህ ዘላቂ መፍትሔ አይሆንም፡፡

ሁለተኛው የድርድር መንገድም ቢሆን ማን ከማን ጋር ነው የሚደራደረው? እንዲሁም ምንን መሠረት ያደረገ ድርድር የሚለው ግልጽ አይደለም፡፡ ሰላማዊ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ስለመመሥረት፣ እንዲሁም በጋራ ስለመኖር መደራደር ይቻላል፡፡ ሕወሓት የዘራውን ጥላቻ ለማስወገድ መነጋገር ይቻላል፡፡ የወልቃይት ሕዝብ የተፈጸመበት ብዙ ግፍ አለ፡፡ ሕዝቡ ወደ ቂም በቀል እንዳይሄድ ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር በሰላም እንዲኖር ከማሰብ መነጋገር መልካም ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ማንነትን በተመለከተ የሚደራደረው አካል ሊኖር አይችልም፡፡ የወልቃይት ሕዝብ ማንነት ለድርድር አይቀርብም፡፡ ከዚህ በፊት አልተደራደረም ወደፊትም አይደራደርም፡፡ ሕወሓት በወልቃይት ሕዝብ ላይ የፈጸመውም ሆነ በአማራ ሕዝብ ላይ የፈጸመው ወንጀል፣ በትግራይ ሕዝብ ስም ሲፈጽመው የቆየ ወንጀል ነው፡፡ የትግራይ የፖለቲካ ልሂቅ በተለይም ሕወሓት፣ በትግራይ ሕዝብ ስም ላደረሰው በደል ደግሞ ይቅርታ መጠየቅና መካስ ነው ያለበት፡፡ ሕወሓትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ነው ተብሎ በመሪዎቹም ተነግሮናል፣ በተለያዩ አካላትም ተነግሮናል፡፡ በአማራ በተለይም በወልቃይት ሕዝብ ላይ ለተፈጸመው ወንጀል ሕወሓት ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል፡፡ ይህ ወደ ሰላማዊ ኑሮ ሕዝቡን ለመመለስ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡ ማንነትን ወይም የወልቃይትን ሕዝብ ዕጣ ፈንታ በሚመለከት ግን  ከዚህ በፊትም ሆነ ወደፊት ድርድር  አይኖርም፡፡

ሦስተኛው መንገድ የፖለቲካ ውሳኔ ነው፡፡ አሁን ላይ የወልቃይት መሬት ወደ አማራ እጅ ተመልሷል፡፡ ሕዝቡም አማራነቱን አውጆ እየኖረ ነው፡፡ ሕዝቡ የታገለለትን ዓላማ እየኖረ ነው፡፡ አሁን ከመንግሥት የሚፈልገው ሕጋዊ ዕውቅና ማግኘት ብቻ ነው፡፡ መንግሥት ኃላፊነት ስላለበትና የአገሪቱ የበላይ አስተዳዳሪ ስለሆነ ሕዝቡ ይህን ዕውቅና ይፈልጋል፡፡ ከዕውቅናው ጋር በጀት፣ አስተዳደር፣ ፀጥታ፣ መሠረተ ልማት የተለያዩ ከመንግሥት ጋር የተገናኙ አገልግሎቶች ስለሚመጡ ዕውቅናውን ማግኘት ጠቃሚ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በፓርላማ እንደተናገሩትና ሬድዋን (አምባሳደር) በቅርቡ እንደደገሙት ሁሉ፣ ወልቃይት በጉልበትና በወረራ የተወሰደ መሬት ነው፡፡ ይህንን በሕግ ዕውቅና በመስጠት ወልቃይትን ወደ ነበረበት መመለስ የሚያስችል የፖለቲካ ውሳኔ መውሰድ አስፈላጊ ነው፡፡ ወልቃይት ሕግ ተጥሶ በሕወሓት የተወሰደ በመሆኑ ከወረራው በፊት ወደ ነበረበት መመለስ አለበት፡፡ ሕግ ይጠበቅ ከተባለ የተጣሰውን የፖለቲካ ውሳኔ በመወሰን ከ1983 ዓ.ም. በፊት ወደ ነበረበት ቦታ ወልቃይትን መመለስ ያስፈልጋል፡፡ የወልቃይትን አስተዳደር ወደ ነበረበት ጎንደር መልሰናል፣ የወልቃይት ሕዝብን የአማራ ማንነትም ዕውቅና ሰጥተናል ብሎ መወሰን ነው የሚጠይቀው፡፡ ይህ ከተደረገ በኋላ የምንጠይቀው ደግሞ ልዩ መርማሪ አካል ተቋቁሞ በዚያ አካባቢ የተፈጸሙ ወንጀሎች መመርመር አለባቸው፡፡ ወንጀል ፈጻሚዎች ተጠያቂ መሆን አለባቸው፡፡ ሕዝባችን መካስ አለበት፡፡ በመላው ዓለም ተገዶ የተበተነው ሕዝብ ደግሞ ወደ ርስቱ መመለስ አለበት፡፡ ራሱን እንደ ማኅበረሰብ ሊያቆም የሚችልበት ድጋፍ ያስፈልገዋል፡፡ ስለዚህ በእኛ እምነት ይህን የተከተለ እስከሆነ የፖለቲካ ውሳኔ መፍትሔ ሊሆን ይችላል እንላለን፡፡

ሪፖርተር፡- ወልቃይት ወደ ትግራይ ክልል ቢካለል ምንድነው ችግሩ?

አቶ ዓብዩ፡- ወልቃይት ለ27 ዓመታት በትግራይ ተካሎ ቆይቷል፡፡ ሕወሓት ሰዎችን አሠፈርኩ ቢልም፣ እኔ ግን ለወረራ አምጥቷቸዋል ነው የምለው፡፡ ሕወሓት የራሱን ሰዎች በማምጣት በነባሩ የወልቃይት ሕዝብ ላይ የባህል ማጥፋት (ካልቸራል ጄኖሳይድ) ተፈጽሞበታል፡፡ ሕዝቡ ርስቱን ብቻ ሳይሆን ማንነቱን እንዲያጣ ተደርጓል፡፡ አባቶቹና አያቶቹ በኖሩበት ቦታ መኖር እንዳይችል ተደርጓል፡፡ በፈቃዱ ተጠይቆ የሆነ አይደለም፡፡ ሕዝቡ ሳይፈልግ ተገዶ ነው ሌላ ማንነት የተጫነበት፡፡ የሚቃወም በሙሉ ሲገደልና ሲሳደድ ነው የኖረው፡፡ ይህ ሁሉ በሕወሓት ሥር ወልቃይት በነበረ ጊዜ ተፈጽሟል፡፡ ዛሬ ደግሞ ወደ ትግራይ ቢካለል ምንም ችግር የለውም ካልን፣ ሕወሓት የሚያደርሰው በቀል ቀላል አይሆንም፡፡ የወልቃይት ሕዝብ ከዚህ በኋላ በትግራይ ሥር ልተዳደር የሚልበት ምንም ዕድል የለም፡፡ ሕዝቡ አማራነትን ትተህ ትግሬ ሆነህ ኑር መባልንም የሚቀበል አይመስለኝም፡፡ ይህ የሁለቱን ሕዝቦች ወደፊት በጋራ የመኖር ዕድልንም የሚያበላሽ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ወልቃይት በአማራ ክልል መካለሉን ትክክል የሚያደርጉ የታሪክ፣ የባህል፣ የሕግ ወይም የፖለቲካ መነሻ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

አቶ ዓብዩ፡- ሕወሓት በጉልበት እስኪጠቀልለው ድረስ ኢትዮጵያ እንደ አገረ መንግሥት ቆመች ከተባለ ጊዜ ጀምሮ፣ ወልቃይት በትግራይ ሥር ተዳድሮ አያውቅም፡፡ ሕዝቡም ቢሆን ራሱን ትግሬ ነኝ ብሎ ማንነቱን ሲገልጽ አይታወቅም፡፡ የአቻምየለህ ታምሩን ‹‹የወልቃይት ጉዳይ›› መጽሐፍ እንዲሁም የፍታዬ አሰጉን ‹‹ቲርስ ኦፍ ወልቃይት›› መጽሐፍም መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከቅርብ እስከ ሩቅ በወልቃይት ላይ የተጻፉ መጻሕፍት መዛግብትን ብናገላብጥ የትግራይ ነው የሚያስብል ማስረጃ ማግኘት ይከብዳል፡፡ ወልቃይት የትግራይ ሆኖ እንደማያውቅ የሚመሰክሩ ብዙ የታሪክ ድርሳናት አሉ፡፡ ተከዜ ትልቅ ወንዝ ነው፡፡ ድልድዩ ከመሠራቱ በፊት በነበሩ የታሪክ ወቅቶች ወንዙ በሞላ ጊዜ ለስድስት ወራት መሻገር እንደማይቻል በታሪክ ሲነገር የኖረ ጉዳይ ነው፡፡ የትግራይ ተወላጆች ይህ ወንዝ ሲጎድል ጠብቀው ተሻግረው ከአማራ ወንድሞቻቸው ጋር ይሠሩ፣ ይነግዱና ቤተሰብ መሥርተው በጋራ ይኖሩ እንደነበር ብዙ የታሪክ መረጃዎች ማቅረብ ይቻላል፡፡ ይህ የተፈጥሮ ድንበር የሆነ ትልቅ ወንዝ የሁለቱን ማኅበረሰቦች መስተጋብር ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን ችለው ሲኖሩ የነበረበትን የአስተዳደር፣ የአኗኗርና የማንነት እሴትም ሲበይን የኖረ ነው፡፡ ተከዜን ተሻግሮ ወልቃይት አማራ ነው፡፡ ተከዜን ተሻግሮ ደግሞ ትግራይ ነው፡፡ ሁለቱን ማኅበረሰቦች የሚያዋስነው ይህ ወንዝ ነው፡፡

ሁለተኛው ከፖለቲካ አንፃር ወልቃይት በጉልበት የተወሰደ ነው፡፡ በያኔው አከላለል የጎንደር ግዛት ነበር፡፡ ጎንደር ደግሞ በአሁኑ አከላለል የአማራ ክልል አካል በመሆኑ ወልቃይትም ወደዚሁ መካለል አለበት፡፡ የሕግ አመክንዮችን ካየን ደግሞ በወልቃይት ብዙ ግፍና ጭፍጨፋ ሲፈጸም ነው የኖረው፡፡ በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍንና ዘላቂ ሆኖ እንዲቀጥል የሚፈለግ ከሆነ፣ እንዲሁም ሕዝቦቿ ወደፊት በሰላምና በጉርብትና እንዲኖሩ ከተፈለገ በወልቃይት ለተፈጸሙ ወንጀሎች ፍትሕ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ የወልቃይት ጥያቄ አለመመለሱና በኃይል ተዳፍኖ ብዙ ሰቆቃ ሲፈጸም መቆየቱ፣ አገሪቱን አሁን ወደ የምትገኝበት ቀውስ እንድትገባ ምክንያት መሆኑ መረሳት የለበትም፡፡ ዓለም ሁሉ እንደሚያውቀው ወልቃይትን ሕወሓት የሚፈልገውና በወረራ ይዞ በትግራይ ሥር ያካለለው፣ ትግራይን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ባለው ዓላማ ነው፡፡ ትግራይን ከመገንጠል በተጨማሪ ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች መግቢያ በር መስጠትም ነው ፍላጎቱ፡፡ ሕወሓት ወልቃይትን ቢይዝ በሱዳን በኩል የውጭ ጠላቶችን ለማስገባት እንደማያመነታ፣ በሦስተኛው ዙር ጦርነት ወቅት ታይቷል፡፡ ከፍተኛ የሕወሓት ኃይል በሱዳን ድንበር በኩል ከውጭ ጠላቶች ጋር ሆኖ ኢትዮጵያን ሲወጋ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ግብፅም ሆነ ሌላ ኢትዮጵያን የማተራመስ አጀንዳ ያላቸው ኃይሎች ሕወሓት ወልቃይትን ቢይዝ ምቹ ሁኔታ ነው የሚፈጠርላቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ወልቃይት በጌምድር፣ ስሜን በሚባሉ የግዛት ስያሜዎች ሲጠራ የኖረ መሆኑ በታሪክ ይነሳል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት የወልቃይት ሕዝብ ኮልተፍ ያለ አማርኛና ኮልተፍ ያለ ትግርኛ የሚናገር ራሱን የቻለ ማንነት ያለው ሕዝብ ነው ብለው ነበር፡፡ ወልቃይት አማራም ትግሬም ሳይሆን የራሱ ማንነት ያለው ማኅበረሰብ ነው የሚለውን ትቀበሉታላችሁ?

አቶ ዓብዩ፡- ከመሠረቱ የብሔር ማንነት ከመምጣቱና መሬት ለብሔር ማንነቶች ከመታደሉ ወይም ከኢሕአዴግ በፊት በነበረው የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ፣ ራስን ከአካባቢ ጋር አቆራኝቶ መግለጽ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የተለመደ ነበር፡፡ የጠገዴ ሰው ለምሳሌ እኔ ጠገድቼ ነኝ ይላል፡፡ አንዱን የጎጃም ሰው ብንጠይቀው ማርቆስ ወይ አዴት ነኝ ሊል ይችላል፣ አለፍ ሲልም ጎጃሜ ነኝ ይላል፡፡ የሸዋም ሰው ሸዋ ነኝ ይላል፡፡ ምንጃሩ ምንጃሬ ነኝ ይላል፡፡ ሰዎች ራሳቸውን የሚገልጹት ከተወለዱበት አካባቢ ጋር ራሳቸውን በማያያዝ ነበር፡፡ ወልቃይትም ወልቃይት፣ ጎንደርም ጎንደር፣ አርማጭሆም አርማጭሆ ነኝ ማለታቸው የተለመደ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ቦታ ወይም አካባቢ የብሔር ማንነት መገለጫ ከመሆኑ በፊት ሰው ራሱን በአካባቢ መግለጹ የተለመደ ነበር፡፡ ይህም ቢሆን ግን ማንነቱን በሚጠራው አካባቢ እየተናገረ ነው ሊባል አይችልም፡፡ በአንድ አካባቢ እኮ በኢትዮጵያ ብዙ ዓይነት ማንነት ያላቸው ማኅበረሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በነገራችን ላይ የወልቃይት ሕዝብ በአብዛኛው ታሪኩ ወደ ኤርትራ ሲነግድና ወደ ኤርትራ ሲጓዝ ነው የሚታወቀው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወልቃይት ከፊል ትግርኛ የሚነገርበት ነው ቢሉም፣ የወልቃይት ትግርኛ ለዛ ግን ከትግራይ ጋር ብቻ ሳይሆን ከኤርትራ ትግርኛ ዘዬ ጋርም የሚቀራረብ ነው፡፡ ምንሀጀር በወልቃይት በኩል ቅርብ ስለሆነና ከኤርትራ ጋር የሚያገናኝ ሰፊ ድንበር ስላለው፣ የወልቃይት ሕዝብ በንግድም በግንኙነትም ለኤርትራ የቀረበ ነው፡፡ በወልቃይት የኤርትራም የትግራይም ትግርኛ ዘዬዎች ተደበላልቀው ነው የሚነገሩት፡፡

በሌላ በኩል ለ30 ዓመታት አማርኛ አትናገር ተብሎ በሕግና በኃይል የተጫነበት ማኅበረሰብ የሚችለውን አማርኛው ሆነ ትግርኛ በራሱ ዘዬ ቢናገር አይፈረድበትም፡፡ የተኮላተፈ ትግርኛ፣ የተወላገደ አማርኛ ወይም የተጣመመ ቋንቋ ትናገራለህ ብሎ መናገር ሕዝቡ በተፈጸመበት ግፍ ቁስል ላይ እንጨት እንደመስደድ ሲሆን፣ ሕዝቡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አዝኗል፡፡ ከሕወሓት ጋር የታገሉና ብዙ መስዋዕትነት የከፈሉ ትግርኛ የሚናገሩ አማራ ነው ማንነቴ የሚሉ የወልቃይት ልጆች አሉ፡፡ ወልቃይት አማራም ትግሬም አይደለም የሚለው ተረክ ከየት እንደሚመነጭ እኛ ይገባናል፡፡ ራሱ ሕወሓት ሕዝቡ ላይ የተለየ ማንነት መጫን እንዳቃተው ሲረዳ፣ ግማሽ መንገድ አምጥቼዋለሁና አማራም ትግሬም አይደለም የሚል ማንነት ልፍጠርለት የሚል ታክቲክ እንዳለው እናውቃለን፡፡ ለወልቃይት ራሱን የቻለ አዲስ ማንነት በመስጠት ራስ ገዝ አስተዳደር እንፍጠር የሚል ሁለተኛ ዕቅድ እንዳላቸው አሳምረን እናውቃለን፡፡ እ.ኤ.አ. በ2005 የቀድሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ አዲሱ ለገሰ ራሳቸው አሜሪካ ኦሀዩ ግዛት ኮሎምበስ ድረስ መጥተው ይህን ዕቅድ ነግረውናል፡፡ ብዙ የወልቃይት ተወላጆች በሚኖሩባት ኮሎምበስ በዚያ ወቅት የመጡት አቶ አዲሱ አለቃቸው መለስ ራስ ገዝ የሆነ የወልቃይት አስተዳደር ለመስጠት ፈቃደኛ መሆናቸውን ነግረውናል፡፡ እኛ ግን አማራ ነንና አንፈልግም ነው ያልነው፡፡ እኛ አማራ ነን፣ አገራችንም ጎንደር ነውና ወደ አማራ ክልል መልሱን እንጂ፣ ከዚህ ውጪ አንቀበልም ብሎ ነው የወልቃይት ዳያስፖራ የመለሰላቸው፡፡ ሕወሓት ወልቃይትን ትግሬ ማድረግ ባልችልም ከአማራነት አውጥቼ ግማሽ መንገድ አምጥቼዋለሁ በሚል ሒሳብ፣ አዲስ ወልቃይቴ የሚል ማንነት ሰጥቼ ቀስ በቀስ የራሴ አደርገዋለሁ ብሎ የዘየደው ብልጠት መሆኑ ትግሉ ላይ ብዙ የቆየን ይገባናል፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ አስፍረናል ብለው ስለሚያስቡ በሒደት ማንነቱን ቀይሮ ወልቃይት የትግራይ ይሆናል በሚል የጠነሰሱት ዘዴ ነው፡፡ የወልቃይት ሕዝብ ወልቃይት ነኝ ሲል አማራነቱን ትቶ ሳይሆን ራሱን ከአካባቢው ጋር አገናኝቶ ሁሉም እንደሚገልጸው ዓይነት ነው፡፡ የወልቃይት ሕዝብ ወልቃይት ነኝ ሲል አማራነቱን ትቶ ወይም ራሱን የቻለ በአማራና በትግሬ መካከል ያለ ወልቃይቴ የሚል አዲስ ማንነት ኖሮት አይደለም፡፡  

ሪፖርተር፡- በአማራ ክልልም ሆነ በፌዴራል መንግሥት ላይ ጥያቄ ታነሳላችሁ፡፡ የወልቃይትን ጉዳይ በተመለከተ ሁለቱ አካላት በሚከተሉት አቋም ላይ የምታነሱት ቅሬታ ምንድነው?

አቶ ዓብዩ፡- የአማራ ክልል የሚመሠገኑና አመርቂ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ ወልቃይት በሕወሓት ሲወሰድም ሆነ ሲካለል የሠራው ሥራ ባይኖርም፣ በተለይ የብአዴን ሁለተኛና ሦስተኛ ትውልድ ከተተካ ወዲህ ጥሩ ሥራ ሠርቷል፡፡ ለውጡ ሊመጣ አካባቢ የነበረው ኃይል የሚቻለውን ድጋፍ አድርጓል፡፡ ከዚያ በተጨማሪም ሕወሓት ለወረራና አገር ለማፍረስ ለጦርነት በተዘጋጀ ጊዜ፣ የአማራ ክልል በቂ ዝግጅት በማድረግ ወልቃይትን ከወረራ ነፃ አውጥቷል፡፡ ይህ ክልሉ የሠራው ትልቅ ታሪካዊ ሥራ ነው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ በጦርነቱ የገጠመውን ፈተናና ያለበትን ችግር ተቋቁሞ ወልቃይትን ለማስተዳደርም ሆነ የባሰ ችግር እንዳይፈጠር ለማድረግ ያደረገው ጥረት ትልቅ ነው፡፡ በወልቃይት ሰላም እንዲሰፍንና ሕዝቡ መኖር እንዲችል ለማድረግ ያደረገው ጥረት ቀላል አይደለም፡፡ ይህም ሆኖ ግን የአማራ ክልል የወልቃይትን ጉዳይ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የፌዴራል መንግሥቱን መሞገት በሚገባው ልክ ሞግቷል ብለን አናምንም፡፡ የወልቃይትን ጉዳይ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ወይም በሕገ መንግሥት መፍታት የሚባለው መንገድ እንደማያስኬድ ሁሉም ያውቀዋል፡፡ ይህን እያወቁ ግን ጉዳዩ በፖለቲካ ውሳኔ እንዲፈታ በቂ ግፊት ሲያደርጉ አይታይም፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ሕወሓት በወልቃይት የፈጸማቸው ወንጀሎች እንዲጣሩና ተገቢውን ቅጣት አጥፊዎች እንዲያገኙ ለማድረግ በሚገባው ልክ አልሄዱበትም፡፡ እስካሁን አጣሪ ቡድን አልተቋቋመም፣ ምርመራም ሆነ የፍርድ ሒደት ለማስጀመር በቂ ጥረት አይታይም፡፡ ይህ የአማራ ክልል ትልቁ ድክመት ነው፡፡ ሦስተኛው ሕዝባችን በከፍተኛ ደረጃ ተፈናቅሏል፡፡ ለረዥም ጊዜ ከርስቱ ተባሮ አገሩን ለቆ ተሰዷል፡፡ ንብረቱ ተዘርፎ በብዙ ሥቃይና መከራ ውስጥ አልፏል፡፡ ይህን ሕዝብ ወደ መኖሪያው መልሶ ማቋቋም፣ እንዲሁም እንደ ማኅበረሰብ በእግሩ እንዲቆም ለማድረግ በቂ ሥራ አልተሠራም፡፡ ያወጣናቸው ሰነዶች አሉ፡፡ የወልቃይት ልሳነ ግፉአን ተቋም ያዘጋጃቸው ሰነዶች አሉ፡፡ እነዚህን ሰነዶች መሠረት አድርጎ የፍትሕ ጥያቄያችንን ለማስመለስ ወደፊት ክልሉ ይሠራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የፌዴራል መንግሥቱም ዘግይቶም ቢሆን የወልቃይት ጉዳይ የአገር እስትንፋስ ጉዳይ መሆኑን የተረዳ ይመስለናል፡፡ ሕወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስም ሆነ የፌዴራል መንግሥቱን ለመቆጣጠር የከፈታቸው ጦርነቶች፣ በወልቃይት በኩል ክፍተት ካገኘ በቀላሉ ሊሳኩለት እንደሚችሉ መንግሥት ተረድቶታል፡፡ በተለይ በሁለተኛውና በሦስተኛው ዙር ጦርነቶች ወልቃይት ላይ ኃይሉን አጠናክሮ ሕወሓትን ለመመከት መንግሥት ሲሠራ ነበር፡፡ በሱዳን በኩል የመጣ በታንክ የታገዘ ጦርን ፌዴራል መንግሥቱ ተዘጋጅቶ በመጠበቅ እንዳይሳካ አድርጓል፡፡ ነገር ግን ከበጀትና መሠረተ ልማት ጋር በተያያዘ የወልቃይት ያልተመለሰ ብዙ ጥያቄ አለ፡፡ በሌላ በኩል ቀላል የሆነውን የወልቃይት ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ይህን ያህል ማንዛዛትና ማወሳሰብ አላስፈላጊ አይደለም፡፡ የተፈጸመው ግፍና ወንጀል በግልጽ እየታወቀ፣ እንዲሁም ሕወሓት በጉልበት እንደወረረና ለምን ዓላማም እንደወረረው እየታወቀ በቀላል የፖለቲካ ውሳኔ ሊፈታ የሚችል ጉዳይን፣ ይህን ያህል ለምን ማንዛዛት እንደተፈለገ አልገባንም፡፡ የወልቃይት ጉዳይ በመንዛዛቱና በመወሳሰቡ የጠላት መሰባሰቢያ አጀንዳ እንዲሆን በር ከፍቷል፡፡ ከትግራይ ክልል የሚነሱ ወራሪዎች፣ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችና በኢትዮጵያ ላይ ፍላጎት ያላቸው የውጭ ኃይሎች ግንባር እንዲፈጥሩ ምክንያት እየሆኑ ነው፡፡ የወልቃይት ጉዳይ ሕወሓት ከአራት ኪሎ እንዲባረርና በኢትዮጵያ ለውጥ እንዲመጣ ምክንት ከሆኑ ቀዳሚ ጉዳዮች አንዱ መሆኑ እየታወቀ፣ ለመመለስ ግን ብዙ መጓተቱ ሌሎች ኃይሎች ጣልቃ ገብተው እንዲፈተፍቱ እያደረገ ነው፡፡  

በእርግጥ ከነፃነት የሚበልጥ ነገር የለም፡፡ የወልቃይት ሕዝብ ዛሬ ነፃነቱን አግኝቷል፡፡ ነገር ግን ይህንኑ ነፃነት እየተመገበ በተስፋ ከመኖር በቀር በጀትም ሆነ መንግሥታዊ አገልግሎት ባለፉት ዓመታት አላገኘም፡፡ ይህ ነገር ግን መቀጠል የለበትም እንላለን፡፡ ሕዝቡ ለሌላው ሕዝብ የሚደረገው ሁሉ ሊደረግለት ይገባል፡፡ ሌላው መንግሥት በጣም የሚጋጩ መልዕክቶችን ያስተላልፋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት እርስ በርሱ የተምታታና የሚቃረን መልዕክት በተለያዩ መድረኮች ይናገራሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ መድረክ ላይ የወልቃይት፣ የጠገዴ፣ የአርማጭሆና የጎንደር መሬት የአማራ ነው ይላሉ፡፡ በሌላ መድረክ ላይ ደግሞ የተወላገደ አማርኛና ትግርኛ የሚናገር የራሱ ማንነት ነው በማለት ሕወሓት ዕቅድ ሁለት ብሎ ከዓመታት በፊት ያስቀመጠውን ጉዳይ ያነሳሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወልቃይት የአማራ ነው ይህን የሚያረጋግጥ መረጃም ቤተ መንግሥት ውስጥ ስላለን፣ እሱን ለዓለም ክፍት አድርገን እናሳያለን ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ይህ እርስ በእርሱ የሚጋጭ ሐሳብ ደግሞ ለሕዝባችን ፈጽሞ አልበጀም፡፡ መከፋትና ቅሬታ እንዲሰማው የሚያደርግ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም በወልቃይት ጉዳይ የተዛባ አረዳድ እንዲኖረው የሚያደርግ ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ የወልቃይት ጉዳይን በተመለከተ አፈታቱ ላይ የሚያቀርባቸው አማራጮችም እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ ናቸው፡፡ አንዴ በድርድር፣ ሌላ ጊዜ በፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ በሕዝበ ውሳኔና በፖለቲካ ውሳኔ እያለ ያልተናበቡ፣ ወጥነት፣ ግልጽነትም ሆነ ማብራሪያ የሌላቸው መላምቶች ይሰጣል፡፡ ይህ ነገር ለተለያየ ትንተናና ብዥታ የሚዳርግ ብቻ ሳይሆን፣ ችግሩን ለመፍታትም የበለጠ ውስብስብነትን የሚፈጥር ነው እንላለን፡፡ ይህ ነገር እውነተኛው ታሪክ ላይ ቆሞ ባለው እውነታ መፍትሔ መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የወልቃይት ጉዳይ አገሪቱ ባላት አቅም በሰላም መፍታት ካልተቻለ የመጨረሻው ዕቅድ ምንድነው? በአኅጉራዊ ወይም በዓለም አቀፋዊ ዳኝነቶች ችግሩን ለመፍታት ጥረት ታደርጋላችሁ የሚባል ነገር አለ?

አቶ ዓብዩ፡- እኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን ጥያቄ ለመፍታት አቅም አለው ብለን እናምናለን፡፡ አቅም ሳይሆን ፍላጎት ነው ያጣው ብለን እናምናለን፡፡ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ፍላጎቱ ካለው የሚጠበቅበት በቀላሉ ዕውቅና መስጠት ብቻ ነው፡፡ የሕዝቡን የማንነት ጥያቄን የድንበር ማድረግ አያስፈልግም፡፡ የወልቃይትን ሕዝብ የማንነት ጥያቄ አንዴ ከመለሰ የፍትሕና አስተዳደር ጥያቄዎች አብረው የሚመጡ ናቸው፡፡ ወደ አኅጉርም ሆነ ዓለም አቀፍ ግልግል ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን ወስዶ ለመፍታት ጥረት ማድረጉ ጊዜው አይደለም ብለን እናምናለን፡፡ በአገር ውስጥ ተቋማትና ዳኝነቶች ይፈታል ብለን እናምናለን፡፡ ወደ ውጭ መሄድ ካስፈለገ ጊዜው ሲደርስ ድርጅታችን ወደዚያው ለመግባት ይችላል፡፡ ጉዳዩ ከመንግሥትና ከኢትዮጵያ ሕግ በላይ ነው ብለን ግን አናምንም፡፡  የወልቃይት ጉዳይ ሄዶ ሄዶ የመጨረሻው ግብ የአማራ ነው፡፡ ወልቃይት የአማራ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያም እስትንፋስ ነው፡፡ ሦስት አገሮች ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ኤርትራ የሚዋሰኑበት ቀጣና ነው፡፡ የኢትዮጵያ የንግድ፣ የሰላምና የጂኦ ፖለቲካ ማዕከል መሆን ይችላል፡፡ ወልቃይት የትግራይ፣ የአማራ፣ ሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ብቻ ሳይሆኑ የኤርትራም ሆነ የሱዳን ሕዝቦች በሰላም የሚኖሩበት ማዕከል ይሆናል ብለን እናስባለን፡፡ ወደ እዚህ በአፋጣኝ ለመግባት ደግሞ የማንነት ጥያቄውን መመለስ ቀዳሚው ጉዳይ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተተገበረው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ነው ለማለት ያስቸግራል›› አቶ አሰግድ ገብረመድህን፣ የፋይናንስ ባለሙያና አማካሪ

የዓለም ኢኮኖሚ በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የእያንዳንዱን አገር በር አንኳኩቷል፡፡ መንግሥታት ይህንን ችግር ለማርገብ የተለያዩ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ...

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ...