Monday, February 6, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኢ-መደበኛ ንግድ የተሰማሩ ሰዎችን ለመምራት የሚያስችል ደንብ እየተዘጋጀ መሆኑ ታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሥሪያ ቦታና ሱቆች ተሰጥቷቸው በኢ-መደበኛነት የሚሠሩ ንግዶችን በሕግ ለመምራት የሚያስችል ደንብና ማስፈጸሚያ መመርያ እየተዘጋጀ መሆኑ ታወቀ፡፡

የከተማው የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮን ጨምሮ በዋናነት በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በኩል የተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ፣ ከዚህ በፊት ለተለያዩ ተቋማት ተሰጥቶ ሲገፋፋ የነበረውን የኢ-መደበኛ ንግድ ሥርዓት ቁጥጥር በቅንጅት ለማከናወን የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ የሚፀድቀው ረቂቅ ደንብ ኢ-መደበኛ ነጋዴዎች እንዴት ይተዳደሩ፣ ምን ይሁኑ የሚለውን በሚመለከተው አካል ቁጥጥር እንዲደረግበት በግልጽ ከማስቀመጡ በተጨማሪ፣ በተለምዶ ተለጣፊ ሱቆችን በመቆጣጠር ረገድ ያለውን ኃላፊነት በግልጽ ለማስተዳደር የሚያስችል ሥርዓት የሚዘረጋበት መሆኑን፣ ሪፖርተር ከሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ያገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

ተለጣፊ የሚባሉት ሱቆች በትክክል ለተቋቋሙለት ዓላማ ውለዋል የሚለውን ከመቆጣጠር ጋር ተያይዞ በርካታ ችግሮች እንደነበሩ ተጠቁሞ፣ ሱቆቹ በማን ቁጥጥር ሥር እንደሆኑ እንደማይታወቅና የሚዘጋጀው ደንብ እነዚህን አካላት ወደ አንድ ማዕከል እንዲመጡ የሚያደርግ መሆኑ ታውቋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ በአዋጅ ቁጥር 74/2014 የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ በሚል የተቋቋመ ሲሆን፣ ቢሮው በሥሩ ካሉት ዘርፎች ውስጥ የመሥሪያ ቦታዎችን የማልማት የማስተላለፍና የማስተዳደር ሥራ የተሰጠው አንዱ ዳይሬክቶሬት፣ የተገነቡ የመሥሪያ ቦታዎችን በመረከብ በመመርያው መሠረት በማስተላለፍና በማስተዳደር ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የመሥሪያ ቦታዎችን የማልማት የማስተላለፍና የማስተዳደር እንደተሰጠው ሁሉ፣ በሌላ በኩል በመሥሪያ ቦታዎቹ የሚደረጉ የንግድ ሥርዓቶችን ደግሞ በከተማው የንግድ ቢሮ እንደሚተዳደሩ የሚዘጋጀው ደንብ  የለየ መሆኑ ታውቋል፡፡

በቀጣይ የተለጣፊ ሱቅ፣ መደብር፣ ሊዝ ሼድና ኢ-መደበኛ የሆኑ መሥሪያ ቦታዎችንም በቢሮ ሥር ለማስተዳደር ኃላፊነት የሚውለው ደንብ ረቂቅ የተጠናቀቀ በመሆኑ፣ ዝርዝር መመርያዎች ተዘጋጅተው ከግማሽ ዓመቱ የሥራ አፈጻጸም በኋላ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ለረዥም ጊዜ ከሕግ ማዕቀፍ ውጭ ሲተዳደሩ የነበሩ ሥራዎች ወይም ንግዶች ወደ ሕጋዊ መስመር ይግቡ ሲባል የሚፈጠር ውዥንብር ሊኖር ስለሚችል፣ ወደፊት ደንቡ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት በየደረጃው የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ይደረግበታል ተብሏል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች አስተዳደሩ ያስተላለፋቸው መሥሪያ ቦታዎች በጊዜ ሒደት ተጠቃሚዎች ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላ ሲሸጋገሩ እየተተካኩ ሊሠራባቸው ሲገባ፣ ለረዥም ጊዜ በተመሳሳይ አካላት ሥር ሆነው መቆየታቸው ትክክል አለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ነበር፡፡

እንደ አዲስ አበባ የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ መረጃ በአሥራ አንዱም ክፍላተ ከተሞች 41,963 ተለጣፊ ሱቆች፣ መደብሮች፣ ሊዝ ሼዶችና ኢ-መደበኛ የመሥሪያ ቦታዎች ሲኖሩ፣ ከእነዚህም ኢመደበኛ 25,565፣ ተለጣፊ ሱቅ 11,850፣ መደብር 2,833፣ ሊዝ ሼድ 1,715 ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች