Tuesday, February 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባህረኞችን በውጭ የመርከብ ድርጅቶች የሚያስቀጥር ኤጀንሲ ሊቋቋም ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ተጨማሪ ማሠልጠኛ ተቋማትን የማቋቋም ዕቅድ ተይዟል

በኢትዮጵያ የባህረኝነት ሥልጠና ወስደው በውጭ አገሮች የመርከብ ድርጅቶች ተቀጥረው መሥራት የሚፈልጉ ባለሙያዎችን ሥራ ለማስቀጠር የሚሠራ፣ በአገሪቱ የመጀመርያ የሆነ የመርከበኞች የቅጥር ኤጀንሲ (Government Manning Agency) ለማቋቋም ዕቅድ መያዙ ታወቀ፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ከምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ጋር በጋራ በመሆን ይፋ ያደረጉት፣ የኢትዮጵያ አምስት ዓመታት ብሔራዊ ‹‹ብሉ ኢኮኖሚ›› ስትራቴጂ እንደሚጠቁመው፣ ስትራቴጂው ለውጥ ለማምጣት ከወጠናቸው ዘርፎች ውስጥ አንደኛው የማሪታይም ዘርፍ ነው፡፡ በዚህም ውስጥ የባህረኞች ልማት ዋነኛው ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ያልነበረውን የባህረኞች ሥራ አስቀጣሪ ኤጀንሲ ማቋቋም እንደ ‹‹ግዴታ›› ይዟል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ሥልጠና የወሰዱና አስፈላጊውን መሥፈርት ያሟሉ ባህረኞች በውጭ አገሮች ሥራ እያገኙ ያሉት በሚገኙ ኤጀንሲዎች (Manning Agencies) አማካይነት ሲሆን፣ ይህ አሠራር የወደፊት ውጤታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል ሲል ስትራቴጂው ያስረዳል፡፡ ለዚህም አስፈላጊውን የሕግ ማዕቀፍ የማውጣትና ተቋማትን የማቋቋም ሥራዎች መከናወን እንዳለባቸው ይጠቅሳል፡፡

ለባህረኞች የገበያ ትስስርን መፍጠር በሚመለከትም፣ በርካታ የመርከብ ባለቤት ድርጅቶች ባሉባቸው አገሮች የሚመደቡ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች፣ ግንኙነት ፈጥረው ገበያ ማምጣት እንዳለባቸው፣ በቢሯቸውም የማሪታይም አታሼ በማቋቋም መሥራት እንዳለባቸው ዕቅዱ አሥፍሯል፡፡ የተለያዩ ማስታወቂያ መሰል ሥራዎችን በማከናወን ኢትዮጵያ ወደ ገበያ ሰብራ የመግባት ዕቅድ እንዳላት ተጠቅሷል፡፡

ከዚህ ዕቅድ በፊትም በኢትዮጵያ የመርከበኞች ሥራ አስቀጣሪ ኤጀንሲን ለማቋቋም ጥረቶች ተጀምረው እንደነበረ፣ በተጨማሪም በየትኛው ተቋም ኃላፊነት ይቋቋም በሚለው ለክርክር እንደነበረ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ የሺ ፈቃደ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የበፊቱ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ወደ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከመቀየሩ በፊት፣ ስለባህረኞች የውጭ ቅጥር ሊኖሩ የሚገባቸውን የሕግ ማዕቀፎች እንዲያዘጋጅ ኃላፊነት ተሰጥቶት እንደነበረ የጠቀሱት ወ/ሮ የሺ፣ ባለሥልጣኑ በበኩሉ እስካሁን ያገኘው የተዘጋጀ ሕጋዊ ማዕቀፍ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ የባለሥልጣኑ ኃላፊነትም ከማስቀጠር ውጪ ያሉ ባህረኞችን የሚመለከቱ ሥራዎች ላይ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡  

‹‹የባለሥልጣኑ ኃላፊነት በባህረኞች ፈቃድ አሰጣጥ፣ ከሥልጠና ጋር በተያያዘ ብቃታቸውን ማረጋገጥ፣ ከመርከብ ምዝገባ ጋር በተያያዘና በባህር ላይ የጉዞ ደኅንነትን በተመለከተ ነው፡፡ ሥልጠናው ሲጠናቀቅና የባህረኞች ደብተራቸውን (Seamen’s Book) ሲይዙ ነው የአስቀጣሪው ድርጅት ኃላፊነት የሚሆነው፤›› ሲሉ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አሰግድ ጌታቸው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መመርያን ጨምሮ ሕጋዊ ማዕቀፎችን እያዘጋጀ መሆኑን ነው፡፡

በማሪታይም ዘርፍ የባህረኞችን ልማት የማስፋፋት ዕቅድ ሌላኛው ዋነኛ አካል የሆነው፣ በስትራቴጂ ሰነዱም የተጠቀሰው የባህረኞች ማሠልጠኛ ተቋማትን ማስፋትና በተጨማሪም አዳዲስ ማቋቋም ነው፡፡ በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ሁለት የባህረኞች ማሠልጠኛ ተቋማት የሚገኙ ሲሆን፣ እነሱም በመንግሥት የሚተዳደረው የባቦጋያ ማሪታይምና ሎጂስቲክስ አካዴሚና ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር አብሮ የሚሠራው የኢትዮጵያ የባህረኞች ማሠልጠኛ ተቋም አክሲዮን ማኅበር ናቸው፡፡

ይህ ‹‹የብሉ ኢኮኖሚ› ስትራቴጂ›› ዕቅድ እንደሚጠቁመው፣ በሜካኒካልና ኤሌክትሪካል ምህንድስና የተመረቁ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን በስድስት ወራት ሥልጠና፣ በሌሎች አዳዲስ በሚቋቋሙ ማሠልጠኛዎችም ጭምር በስፋት ማሠልጠን ነው፡፡ በተጨማሪም እንደ ሜኢርስክ (Maersk) ዓይነት በዓለም ላይ ያሉ ትልልቅ የመርከብ ድርጅቶች ኢትዮጵያ መጥተው፣ ከመንግሥት ጋር ባህረኞችን በጋራ አሠልጥነው ወስደው እንዲቀጥሩ ግብዣ እንደሚደረግ ሰነዱ ይገልጻል፡፡

የባለሥልጣኑ ሕዝብ ግንኙንት ኃላፊ ወ/ሮ የሺ ስለማሠልጠኛ ተቋማት ማስፋፋት ሲገልጹ፣ በቅርቡም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥልጠናውን ለመስጠት እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ እንደሆነና ሌሎችም በውኃ አካባቢ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ለማስፋፋት ዕቅድ አለ፡፡ ‹‹ሙሉ ለሙሉ በዚህ ዓመት ይጀመራል ማለት ባያስችልም ቢያንስ ንግግር ተካሂዷል፡፡ በምን ያህል ፍጥነት እንደሚሄድ ባይታወቅም፣ በአሥር ዓመቱ ዕቅድና በዚህ ስትራቴጂ ላይ ግን እንደ ዕቅድ ተቀምጧል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ባህር ዳር የሚገኘውን የማሠልጠኛ ተቋም ያቋቋመው የውጭ አገር ድርጅት ሲሆን፣ አሁን ግን የአገር ውስጥ ድርጅቶችም ቢሆኑ ፍላጎት ካላቸው ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ በመሥራት ሊያቋቁሙ እንደሚችሉ ወ/ሮ የሺ አስረድተዋል፡፡ ‹‹በእርግጥም ትልቅ ኢንቨስትመንት የሚፈልግ ሥራ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች