Tuesday, February 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበአካል ጉዳተኞች ላይ ስለሚደርሱ የመብት ጥሰቶች የቀረበ ቅሬታ!

በአካል ጉዳተኞች ላይ ስለሚደርሱ የመብት ጥሰቶች የቀረበ ቅሬታ!

ቀን:

በገመቹ ሐጎስ

አካል ጉዳተኝነትን በተመለከተ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ከባህል፣ ከሃይማኖት፣ ከሕክምና፣ እንዲሁም ከመብትና ከመሳሰሉት ዕይታዎች አንፃር ጉራማይሌ የሆኑ አረዳዶችና አመለካከቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም አሁን በአካል ጉዳተኞች በኩል ትግል እየተደረገባቸው ስለሚገኙት የእኩል ተሳትፎ ጥያቄዎች ዙሪያ፣ ሁሉም ሰው የተስተካከለ አመለካከት ይኖረዋል ተብሎ አይገመትም፡፡ በአካል ጉዳተኝነት ላይ ብቻም አይደለም፣ በሌሎችም አንኳር ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ለመግባባት ብዙ ይቀረናል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት የአካል ጉዳተኝነት ጉዳይ በተለይም ከሰብዓዊ መብት ጋር ተያይዞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ የጉዳዩ ፅንሰ ሐሳብም ሆነ የአተገባበር ሒደት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 2006 በወጣው ‹‹ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ጥበቃ ስምምነት›› (0UNCRPD) ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡

በዚህ ስምምነት መሠረት አካል ጉዳተኝነት ማለት የረጅም ወይም የአጭር ጊዜ የአካል፣ የአዕምሮ፣ የማሰብ፣ የማየት፣ የመስማትና የሌሎች የአካልና የስሜት ሕዋሳት መጎዳትን ተከትሎ በሚያጋጥም የተዛባ አመለካከት ወይም አካባቢያዊ መሰናክሎች ምክንያት፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ እኩል እንቅስቃሴና ሙሉ ተሳትፎ ማድረግን የሚገድብ ችግር ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ስለአካል ጉዳተኞች ሲታሰብ በዋናነት መተኮር ያለበት እኩል እንቅስቃሴና ሙሉ ተሳትፎ ማድረግን በሚገድቡ ‹‹የአመለካከት፣ ተቋማዊና አካባቢያዊ ችግርች›› ላይ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

ይህን ስምምነት የፈረሙ አገሮች በሙሉ የአካል ጉዳተኞችን መብት እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ፣ ወይም በሌላ አገላለጽ “መሰናክልን” እንዲያስወግዱ ሕጋዊ ግዴታና ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያም የዚህ ኮንቬንሽን ፈራሚ በመሆኗ፣ ስምምነቱ በ2002 ዓ.ም. በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ ተደርጓል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 (4) መሠረትም የአገሪቱ አንድ የሕግ አካል እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በዚህ መሠረትም አፈጻጸሙ በየዓመቱ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት እየተደረገ ነው፡፡

ሕጋዊ ዕውቅና ያገኘው የአካል ጉዳተኝነት ትርጉም፣ ጽንሰ ሐሳብና መርሁ በዚሁ የስምምነት ሰነድ ላይ በግል ተቀምጦ እያለ ግን አንዳንድ “ባለሙያዎች” ሳይንስ ነው በሚል ጠባብ ግላዊ ምልከታ በመነሳት በተለያዩ መድረኮች በሚያቀርቡት ጽሑፍና በሕግም ሆነ በሞራል ተቀባይነት የሌለው ማብራሪያ ሲሰጡ ይታያል፡፡ ይህ አሉታዊ ልማድ አካል ጉዳተኞችን የበለጠ ለአድልኦና መገለል የሚያጋልጥ ከመሆኑም ባሻገር የመብት ጥሰት እንደሆነ በግልጽ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ ምክንያት በቅርቡ የጤና ሚኒስቴር በሁሉም የፌዴራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ለሚገኙ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን የሥራ ኃላፊዎች በአዳማ ከተማ በአዘጋጀው ዓውደ ጥናት ላይ፣ በጽሑፍ አቅራቢነት የተጋበዙ አንድ የጤና ባለሙያ አካል ጉዳተኝነትን በተመለከተ ለተሳታፊዎች ሲገልጹበት የነበረው የተዛባ ዕይታ ስላሳሰበኝ ነው፡፡

ዓውደ ጥናቱ የተካሄደው ከታኅሳስ 4 እስከ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚያካሂደው የኩፍና የኮቪድ-19 በሽታ መከላከያ ክትባት የተቀናጀ ዘመቻ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን የሥራ ኃላፊዎች ግንዛቤ ጨብጠው፣ ለዘመቻው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ነው፡፡ ከእነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች በተጓዳኝ ግን ተቀናጅተው ሊተገበሩ የሚገባቸው የሥርዓ ምግብ፣ የፊስቱላ ተጠቂዎች፣ የአካል ጉዳተኛ ሕፃናት ጉዳዮችና ተያያዥ ገለጻዎችም በመድረኩ ቀርበው ነበር፡፡

በዚሁ የውይይት መደረክ “Club Foot Case Identification” የሚል ርዕስ የያዘውን ጹሑፍ ያቀረቡት ባለሙያ ለረጅም ጊዜ በፊዚዮ ቴራፒስትነት በአካል ጉዳተኞች ላይ በመሥራት ላይ እንደሚገኙ፣ በትምህርታቸውም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን፣ እንዲሁም በአሁን ጊዜ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን እየሠሩ ያሉት አሁንም በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የገለጻው አቅራቢ መልዕክት በጥቅሉ ሲታይ ከወሊድ በፊትም ሆነ በኋላ እግራቸው ላይ ችግር ያጋጠማቸውን ሕፃናት በእንግሊዝኛው አጠራር “Club Foot”፣ ወይም በእሳቸው አጠራር “ቆልማማ እግር” የሆኑ ሕፃናት ወደ ሕክምና መስጫ ማዕከላት በመሄድ የሕክምና ዕርዳታ ያግኙ የሚል ነው፡፡ ይህ የተቀደሰ ሐሳብ ነው፡፡ ባለሙያውም  በሠለጠኑበት ሙያ አካል ጉዳተኛ ሕፃናትን ለመርዳት እያደረጉት ስላለው አስተዋጽኦ በእውነቱ ከምሥጋና በስተቀር የሚነቀፉበት አንዳች ነገር አይኖርም፡፡

አንኳር ችግሩ ያለው ግን ወዲህ ነው፡፡ የጤና ባለሙያው በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ስለአካል ጉዳተኝነት ያላቸው አመለካከት እጅግ የተዛባና ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡ እኚህ ባለሙያው ካቀረቡት ገለጻ መካከል ለዚህ ማሳያ የሚሆኑትም፣ ‹‹አካል ጉዳተኛ ሆነው የተወለዱ ሕፃናት በሕክምና ሳይንስ እንደ ሞቱ ነው የሚቆጠሩት፤›› የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ ይህንም ሲያብራሩ፣ ‹‹የሰው ልጅ በዚህ ምድር የሚወለደው ሊያመርት ነው፣ አካል ጉዳተኛ ሆነው የተወለዱ ሕፃናት ግን ማምረት ስለማይችሉ ያው እንደ ሞቱ ነው የሚቆጠሩት፤›› ብለዋል፡፡

ማንም ቅን ልቦና ያለው ሰው እንደሚፈርደው ዕውን ይህ አመለካከት አሁን ለደረስንበት ዘመን የሚመጥን ነው? የፌዴራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የኮሙዩኒኬሽን የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት መድረክ ላይ ግለሰቡ ምን ያህል የአካል ጉዳተኞችን ተፈጥሯዊ ክብርና ግለሰብዓዊ ልዕልና በሚፃረር ሁኔታ ያልተገባ አስተምህሮ እያቀረቡ እንደሚገኙ መረዳት አያዳግትም፡፡ መልዕክቱ አካል ጉዳተኞች ምንም ነገር የማይሠሩና የማኅበረሰብ ሸክም በመሆናቸው፣ ያው ከሰውነት በታች እንደሆኑ በአስተሳሰብ አምነው እንዲቀበሉ የሚሰብክ የዘቀጠ ምልከታ ነው፡፡

እርግጥ ነው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ አካል ጉዳተኞች እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የታወቀ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በየዕለቱ የሚያጋጥማቸውን መሰናክል በብርቱ ትዕግሥትና ጥረት በማለፍ በትምህርታቸው፣ በሥራቸውና በማኅበራዊ ሕይወታቸው ለሌሎችም አርዓያ የሚሆኑ በርካታ አካል ጉዳተኞች በአገራችን እንዳሉም አሌ የሚባል አይደለም፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ላይ በጥበባዊ ፈጠራ፣ በፖለቲካዊ አመራር፣ በሃይማኖታዊ ፍልስፍና፣ ወዘተ. ለምድራችን ትልልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አካል ጉዳተኞችን በመዘርዘር አንባቢያንን አላሰለችም፡፡ ነገር ግን በወቅቱ አንድ ተሳታፊ ይህንን ጽሑፍ አቅራቢ በተቃወሙበት ወቅት ሲጠቅሷቸው ከሰማሁት፣ ታላቋን አሜሪካ በጭንቅ ወቅት መርተው ቀና ስላደረጓት 32ኛው አካል ጉዳተኛ ፕሬዚዳንት ስኬት ጠቆም አድርጌ ልለፍ፡፡

ፕሬዚዳንት ዴላኖ ፍራንክሊን ሩዝቬልት እ.ኤ.አ. በ1921 በፖሊዮ ቫይረስ ሳቢያ በደረሰባቸው የአካል ጉዳት ያለ ሁዊልቸርና የሰው ድጋፍ ፈጽሞ መንቀሳቀስ አይችሉም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከ12 ዓመታት በኋላ በ51 ዓመታቸው ማለትም እ.ኤ.አ. በ1933 አሜሪካ በከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት (Great Depression) ውስጥ በነበረችበት ወቅት፣ ፕሬዚዳንት ሆነው ከመመረጥ አካል ጉዳተኝነታቸው አላገዳቸውም ነበር፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ከአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች መካከል ከሩዝቬልት በስተቀር ለሦስት ተከታታይ ጊዜያት (1933-1945) ተመርጦ አሜሪካን ለረጅም ጊዜ የመራ ፕሬዚዳንት እስካሁን በታሪክ የለም፡፡ የጤና ባለሙያው ሳይንስ ነው እያሉ ግራ ከማጋባት ውጪ ይህን መሰል ታሪኮችን ስለመስማታቸው እጠራጠራለሁ፡፡

እንዳሻቸው የሚናገሩት ግለሰቡ በዚህ መቼ አበቁና፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ቁጥር ወደ 19 ሚሊዮን ይደርሳሉ እየተባለ ነው አሉ፡፡ ከዚህ ጋር አያይዘው፣ ‹‹የአካል ጉዳተኞች ቁጥር መብዛት በተዘዋዋሪ የአንድን አገር ኢኮኖሚ (GDP) አመላካች ነው፤›› የሚል ኢኮኖሚያዊ ትንታኔም አቅርበዋል፡፡

መረጃዎች በቅጡ ተደራጅቶ ከሚገኝባት አሜሪካ አሁንም ሳንወጣ በቅርቡ ሲዲሲ ይፋ ባደረገው መረጃ፣ በዚያች አገር ውስጥ 51 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በከባድ የአካል ጉዳት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ይህ እንግዲህ ከጠቅላላው የጣሊያን ሕዝብ ቁጥር ጋር የሚስተካከል ነው፡፡ በጦርነትና በተሽከርካሪ አደጋ ምክንያት በየቀኑ የሚደርሰውን የአካል ጉዳት እንዳለ ሆኖ፣ በተለይ በአደጉ አገሮች ከማሽን ጋር የተያያዙ ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ በሄዱ ቁጥር የአካል ጉዳት የተለመደ ክስተት ነው፡፡ የጽሑፉ አቅራቢው እንደሚሉት ከሆነ፣ ይህ ሁሉ የአካል ጉዳተኛ ቁጥር ባለባት አሜሪካ ታዲያ ኢኮኖሚው እንዴት አልወደቀም፡፡ ለማምረትስ ዋናው የፈጠራ ማዕከል አዕምሮ እንደሆነ እንደምን ሳቱት፡፡

ከሁሉ በላይ ግን ጭራሽ አስቤውም ሆነ ሰምቸው የማላውቀው ነገር አንድ ሰው አካል ጉዳተኛ ከሆነ በሥቃይ ውስጥ ስለሚኖር እነዚህ ዓመታት “ከዕድሜው ላይ ተቀናሽ” እንደሚደረጉ የሕክምና ቲዮሪዎች ያሳያሉ በማለት፣ በጥልቅ ሙያዊ ስሜት ተውጠው ለዓውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች የሰጡት ማብራሪያ ነው፡፡

በመሠረቱ አካል ጉዳተኝነት ባለሙያውን የመሳሰሉ ሰዎች በያዙት ‹‹አሉታዊ አመለካከትና የአካባቢያዊ ተደራሽ አለመሆን፤›› ድምር ውጤት የሚደርስ ጉዳት እንጂ፣ በሰዎች ውስጥ የሚኖር በሽታ ወይም አካላዊ ሥቃይ አይደለም፡፡ በመሆኑም ወደ ሕክምና ተቋማት ሲኬድ የአካል ድጋፍ እንጂ ክስተቱን በአንዴ ማስወገድ እንደማይቻል መረዳት ይገባል፡፡ የአካል ጉዳተኞች ትልቁ ፈተና አካላዊ ሕመም አይደለም፡፡ ከአመለካከት ጋር ተያይዞ የሚደርስባቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ ወይም ባህላዊ መድልኦ ነው፡፡ ይህንን አካል ጉዳተኛ ወገኖች ራሳቸው ቢናገሩት ይሻላል፡፡ ደግሞስ በሕክምና ስህተት ስንቱ ሰው እጅና እግሩን አጥቶ እንደተቀመጠ እንዴት ማገናዘብ ተሳናቸው?

‹‹ተመልከቱ ይህን ምሥል በእንግሊዝኛው አጠራር “Club Foot” ይባላል:: በአማርኛ ‘ቆልማማ እግር’ ወይስ “የዞረ እግር” እንበለው? የዞረ እግር ለማለት ደግሞ ወዴት አቅጣጫ ሲዞር ነው ዞረ የሚባለው? በአንድ መድረክ ላይ ‘ደጋን’ የሚል ሐሳብም ተነስቶ ነበር… እስኪ እናንተ የኮሙዩኒኬሽን ሰዎች ጥሩ መጠርያ ስጡት፣ እኛ በሕክምና ያለን ሰዎች በአማርኛ ምን ብለን እንደምንጠራው ተቸግረናል፡፡ እንደምታዩት አንዲት እናት የዚህ ዓይነት ልጅ ብትወልድ ልትስመው አትፈልግ… ለመሳም አይመችም…›› ብለዋል፡፡

ከላይ በጥቅስ ውስጥ የቀረበውን ንግግር በዓውደ ጥናቱ ላይ በፓወር ፖይንት ዲስፕሌይ ወደ አደረጉት ምሥል በእጃቸው እያመለከቱ የጤና ባለሙያው ቃል በቃል የተናገሩት ነበር፡፡ አቅራቢው ይህን ካሉ ከደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ወደ ሕክምና ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት የሄዱ የተጎሳቆሉ አካል ጉዳተኞችን የሚያሳይ ቪዲዮና ድምፅ (ብዙዎቹ ሴቶች ናቸው) እየደጋገሙ ለተሳታፊዎች ያሳያሉ፡፡

በእውነቱ ባለሙያው የአካል ጉዳቱን በትክክለኛው አማርኛ ለመግለጽ ያን ያህል ከተጨነቁ፣ በአካል ጉዳተኞች ላይ አትኩረው ከሚሠሩ ተቋማት ወይም ደግሞ ከሚመለከተው የአካል ጉዳተኛ ማኅበር ጋር ተመካክረው የሚቀራረበውን አዎንታዊ ቃል በተጠቀሙ ነበር፡፡ ይህን ማድረግ እንኳ ባይችሉ ከትክክለኛው ምንጭ የተገኘ ከሆነ “Club Foot” ያሉትን የእንግሊዝኛ ቃል ብቻ ተጠቅመው ማለፍ ሲገባቸው፣ ከሙያዊ ሥነ ምግባር ውጪ በግድየለሽነት “ቆልማማ”፣ “የዞረ” እና “ደጋን” የመሳሰሉ አሉታዊ ትርጉም ያላቸውን ቃላት መናገራቸው ሳያንስ፣ ተሳታፊዎችን ስያሜ አውጡለት ማለት ኃላፊነት በጎደለው መንገድ አካል ጉዳተኝነትን መዘባበቻ ከማድረግ ውጪ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም፡፡ ሲያሠራጩት የነበረው የቪዲዮና የድምፅ መረጃም ቢሆን፣ ከእውነተኛው የሰብዓዊነት ተግባር ውጪ ገንዘብ ለመሰብሰቢያ ተግባር አጋጣሚውን እንደ ቢዝነስ አድርገው ከያዙ አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅቶች የተገኘ ይሁን፣ አሊያም ደግሞ ዓላማውን በትክክል ተረድተው ልጆቹ በፈቃዳቸው ስለመቀረፃቸው የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ከሚሰጡት የጤና አገልግሎት ጋር በተገናኘ ተቀርፆ የተያዘ መረጃም ከሆነ የታካሚን መረጃ በአደባባይ ማሠራጨት የሙያ ሥነ ምግባራቸው የሚፈቅድ አይመስለኝም፡፡ ለማስተማሪያነት የግድ ትክክለኛ ቪዲዮና ፎቶ መሆን የለበትም፡፡ ዕድሜ ለኢንተርኔት ሌሎች አማራጮች ሞልተዋል፡፡

ላይ ላዩን የሚመለከት ሰው፣ ‹‹የጤና ባለሙያው በዓውደ ጥናቱ ላይ ተገኝተው የአካል ጉዳት ያለባቸው ሕፃናት ወደ ሕክምና ማዕከል ሄደው እንዲታከሙ እንርዳቸው ማለታቸው ክፋቱ ምኑ ላይ ነው?›› ሊል ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ እምነት ከሰብዕና፣ ከማንነት፣ ከሃይማኖት፣ ከመብትና እነዚህን ከመሳሰሉ ጉዳዮች ጋር የተገናኙ ርዕሰ ጉዳዮችን መድረክ ላይ ይዘን ስንቀርብ በከፍተኛ ጥንቃቄና የኃላፊነት መንፈስ ካልሆነ በስተቀር፣ ይዘቱ የቱንም ያህል መልካም ቢሆን ውጤታማ እንደማንሆን ልብ ሊባል ይገባል፡፡

በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ እንሠራለን የሚሉ ተቋማት ራሳቸው የኋላቀር አመለካከት ሰለባ ሆነው ሲገኙ እንግዲህ ምን ማለት ይቻላል? በተለይም ደግሞ ሁሉም የሕክምና ባለሙያዎች ስለአካል ጉዳተኝነትን ያላች አረዳድ እንደ ሰውየው ተመሳሳይ ከሆነ፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ ከሚንፀባረቀው ኋላቀር አመለካከት በከፋ ሁኔታ ችግሩ ያለው “በፕሮፌሽናሎች” ውስጥ ነው ብሎ መደምደም ላይ ያደርሳል፡፡

ጽሑፌን ሳጠቃልል የጤናም ሆነ ሌሎች ተቋማት ተግባራቸውን በሚያስፈጽሙበት ወቅት፣ አካል ጉዳተኝነትን በተመለከተ የወጡ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፎችን በማገናዘብ፣ የአካል ጉዳተኞችን የእኩል ተሳትፎ ጥያቄዎች በወጉ እንዲመለሱና በተዛባ አመለካከት ምክንያት በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚደርሱ የመብት ጥሰቶችን መንግሥት በገባው ቃል መሠረት በአግባቡ እንዲያስከብር በአፅንኦት በመጠየቅ ነው፡፡ ለዛሬ አበቃሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው gemuchuhagos@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቤተክህነት ባቀረበችው የይግባኝ አቤቱታ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለዕሮብ ተቀጠረ

የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሀገወጥ ነው በተባለው አዲሱ ሲኖዶስና...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...