Monday, February 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየገና ገበያ

የገና ገበያ

ቀን:

ለበዓል ግብይት ብቻ ሳይሆን ለወትሮውም ገበያ ከሚደራባቸው የአዲስ አበባ ንግድ ሥፍራዎች አንዱ የየካው ሾላ ገበያ ነው፡፡ ሆኖም ታኅሣሥ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሥፍራው ስንደርስ ከወትሮው ቀዝቅዞ ነበር፡፡ በዓሉ የተወሰኑ ቀናት ቢቀሩትም ከሌሎች ጊዜያት በተለየ ሁኔታ ጭር ብሏል፡፡

የገበያ ማዕከሉ የተወሰነ ክፍል ታኅሣሥ 23 ለ24 አጥቢያ በደረሰበት ድንገተኛ የእሳት አደጋ ምክንያት በእጀጉ ተቀዛቅዟል፡፡ ከሌሊቱ 10፡00 ሰዓት ገደማ የተነሳው የእሳት አደጋ፣ 84 ሱቆች ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡

የተቃጠለው የገበያው ክፍል ከምግብ ዓይነቶች በተለይ ቅቤ፣ ቆጮ፣ ቡላ፣ ቅመማ ቅመምና ሌሎችም የሚሸጡበት በመሆኑም፣ ቅቤና ሌሎች የበዓል ግብዓቶችን ለመሸመት የመጡ ሰዎች ሲመለሱ አይተናል፡፡ በዕለቱ አደጋ የደረሰባቸው ሱቆችና ከአካባቢ ያሉ አገልግሎት ባይሰጡም፣ ሌሎች የግብይት ሥፍራዎች ለገበያ ክፍት ነበሩ፡፡

ዶሮ ተራ፣ ቅመማ ቅመም ተራ፣ በርበሬ ተራና የሸቀጣ ሸቀጥ መደብሮች ለሸማቾች ክፍት ስለነበሩ አንዳንዶቹን ለማነጋገር ችለናል፡፡    

በዘንድሮ የገና በዓል ዋዜማ በርካታ ግብዓቶች ገበያው ላይ አይተናል፡፡ በ2014 ዓ.ም. ክረምት ውስጥ እስከ 50 ብር ደርሶ የነበረው ቀይ ሽንኩርት፣ ከጥቅምት 2015 ዓ.ም. ወዲህ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ በዚህ ሰሞን ደግሞ ቀይ ሽንኩርት ከ15 ብር ጀምሮ እስከ 22 ብር ድረስ በተለያዩ የገበያ ቦታዎች እየተሸጠ ይገኛል፡፡

በሾላ ገበያ እንደ ሽንኩርቱ ጥራትና የመጣበት ቦታ ዋጋው ዝቅና ከፍ ብሏል፡፡ ከሻሸመኔና ከመቂ አካባቢ የገባ ሽንኩርት ከ23 ብር እስከ 25 ብር በኪሎ እየተሸጠ ይገኛል፡፡ በዚሁ ገበያ የዶሮ ዋጋ ከአምና አንፃር ቅናሽ ያሳየ ሲሆን፣ የወላይታ ዶሮ 700፣ ሐበሻ ዶሮ 600፣ ድቅል ዶሮ 550 ብር እንዲሁም የፈረንጅ ዶሮ 350 ብር ይጠራል፡፡

የሐበሻ ሽንኩርት እንደ ሱቆቹ የዋጋ ልዩነት ያለው ሲሆን፣ ከ100 እስከ 120 ብር ድረስ በኪሎ እየተሸጠ ይገኛል፡፡ የዘይት ዋጋ ሾላን ጨምሮ በሌሎች ገበያዎች ብዙም ልዩነት የለውም፡፡ ፎር ኦልና ሌሎችም የምግብ ዘይቶች ከ1,000 ብር በታች ለሽያጭ ቀርበዋል፡፡  

ከኅዳር እስከ ታኅሳስ ማብቂያ የዛላ በርበሬ ወቅት በመሆኑ፣ በርበሬን ለማዘጋጀት ከሚውሉ ግብዓቶች አንዱ የሆነው ነጭ ሽንኩርት በኪሎ 150 ብር ደርሶ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ትንሽ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ከአገረ ማርያምና ከምንጃር የሚመጣው ነጭ ሽንኩርት በኪሎ ከ120 እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ቅመማ ቅመም ተራ ከተደረደሩ የወጥ ማጣፈጫዎች አንዱ ኮረሪማ ግን ብዙም ቅናሽ አላሳየም፡፡ ከደቡብ ክልል ጋም ጎፋ ዞን የሚመጣው ኮረሪማ በኪሎ 250 ብር ነው፡፡

በሾላ ገበያ በርበሬ በመነገድ ስምንት ዓመታት ያስቆጠሩት ወ/ሮ አስናቀች ወርቁ እንደተናገሩት፣ የአላባና የፀዳሌ በርበሬ የሾላ ገበያ ድምቀቶች ናቸው፡፡ ከ270 እስከ 280 ብር ድረስ በኪሎ እየተሸጡ ይገኛሉ፡፡

ለበዓል ድምቀት ከሚሰጡ የምግብ ዓይነቶች አንዱ ዕንቁላል ነው፡፡ በተለይም ዶሮ ወጥ ከተሠራ በኋላ ዕንቁላል መጨመር በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ እንዲያውም ዶሮ ወጥ ያለ ዕንቁላል የማይታሰብ ተደርጎ በመወሰዱ ይመስል፣ በበዓል ወቅት ዋጋቸው ከፍ ከሚሉ ግብዓቶች አንዱ ሆኗል፡፡

በሾላ ገበያ የሐበሻ ዕንቁላል አሥራ አንድ ብር ሲሆን፣ የፈረንጅ ከዘጠኝ ብር ጀምሮ ይሸጣል፡፡ ነገር ግን በተለያዩ የገበያ ቦታዎች ከዚህ በቀነሰ እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ከዊንስ ሱፐር ማርኬት አንድ ዕንቁላል በስምንት ብር እየተሸጠ ነው፡፡ በተለያዩ የሸማች ሱቆችም አንዱ በ8 ብር ከ50 ሳንቲም እየተሸጠ ነው፡፡ በሌላ በኩል በሁሉም ክፍላተ ከተሞች ጊዜያዊ የገበያ ማዕከሎች ዕንቁላልና ሌሎች ምርቶችን አቅርበዋል፡፡

በዘንድሮ የገና በዓል ዋዜማ አዲሱ ገበያ በሚገኘው ሾላ ገበያ ዶሮና ዕንቁላል ለገበያ ቀርቧል፡፡ ምርቶቹ በዋናነት ከሱሉልታና ከሌሎቹ አቅራቢያ አካባቢዎች የሚመጡ መሆናቸውን ነጋዴዎቹ ነግረውናል፡፡ የሐበሻ ዕንቁላል 10 ብር እየተሸጠ ሲሆን፣ የፈረጅን ደግሞ በ8 ብር 50 ሳንቲም ለገበያ ቀርቧል፡፡

በአካባቢውና በሌሎችም ሥፍራዎች የበዓል ቀን ባለመድረሱ የበግና የፍየል አቅርቦት ባይጀመርም፣ የዶሮና የዕንቁላል ገበያው ደርቶ እንደነበር በቦታው ተገኝተን አይተናል፡፡

በዚሁ ገበያ መካከለኛ ዶሮ 650፣ ትልቅ 700፣ አነስተኛ የተባሉ ዶሮዎች 500 ብር እየተሸጡ ሲሆን፣ የፈረንጅ ዶሮ የሚባሉት ደግሞ ከ250 ብርና ጀምሮ ለሽያጭ ቀርበዋል፡፡

ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ከሚገኙ የገበያ ሥፍራዎች አንዱ መሪ ገበያ ነው፡፡ መሪ ገበያ ለአያት፣ ለሲኤምሲና ለሰሚት አካባቢ በአቅራቢያቸው የሚገኝ የገበያ አማራጭ ነው፡፡

ሰኞ ታኅሣሥ 24 ቀን ባደረግነው የገበያ ቅኝት ደማቅና ግርግር የበዛበት እንደነበር ለመታዘብ ችለናል፡፡

የገበያ ሁኔታውም ወይም ድባቡ የተሻለ የሚባል ሲሆን፣ የግብዓቶችም ዋጋ ብዙም ጭማሪ ያልታየበት ነው፡፡

ሽንኩርት በኪሎ ከ23 ብር ጀምሮ፣ ነጭ ሽንኩርት 170 ብር፣ ትልቅ የሚባለው ዶሮ 750 ብር መሆኑን ከነጋዴዎች ሰምተናል፡፡ የቅቤ ገበያው ደግሞ ለጋ የሚባለው በኪሎ 600 ብር፣ መካከለኛ 700 እና የበሰለ የሚባለው በ550 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ተመልክተናል፡፡

መንግሥት በተለያዩ ክፍላተ ከተሞች ያቋቋማቸው የእሑድ ገበያዎች የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ቅዳሜና እሑድን ጨምሮ በተከታታይ የሥራ ቀናት ምርቶቻቸውን ይዘው ቀርበዋል፡፡

በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አማካይነት የተከፈቱት 127 የገበያ ሥፍራዎች እስከ በዓሉ ዋዜማ ድረስ ለአገልግሎት ክፍት ናቸው፡፡ በእነዚህ ገበያዎች ከሚቀርቡ ግብዓቶች ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ዕንቁላል፣ የንፅህና መጠበቂያዎችና በአጠቃላይም አትክልትና ፍራፍሬዎች ይገኙበታል፡፡

ንግድ ቢሮው ባቋቋማቸው 127 ገበያዎች ከቀረቡት ምርቶች መካከል ሽንኩርት ሜክሲኮ፣ ጉርድ ሾላ፣ መገናኛና አያት አደባባይ በተዘረጉ ገበያዎች በኪሎ ከ20 ብር ጀምሮ እየተሸጠ ይገኛል፡፡

በመገናኛ መገበያያ ቦታ ያገኘናቸው እናት ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የእሑድ ገበያ ለብዙዎች ዕፎይታን ፈጥሯል፡፡ ምክንያቱም የሚቀርቡት ምርቶች ዋጋቸው ቅናሽ ነው፡፡ ነጭ ሽንኩርት በኪሎ ከ120 ብር ጀምሮ፣ አንዱ የፈረንጅ ዕንቁላል ስምንት ብር፣ ቲማቲም በኪሎ 15 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡

ሌሎችም አትክልትና ፍራፍሬዎች በዚሁ ገበያ የቀረቡ ሲሆን፣ ከነባር ገበያዎች አንፃር በዋጋ ቅናሽ እንዳላቸው ሪፖርተር ተመልክቷል፡፡ በገበያዎቹ ያገኘናቸው አንዳንድ ሸማቾች በዋጋው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ ሌሎችም ምርቶች ቢቀርቡ የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...