Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናሕወሓትን ትጥቅ የማስፈታት ሒደት ሲጠናቀቅ የሽብርተኝነት ፍረጃው ተነስቶ ክስ እንደሚቋረጥ ተነገረ

ሕወሓትን ትጥቅ የማስፈታት ሒደት ሲጠናቀቅ የሽብርተኝነት ፍረጃው ተነስቶ ክስ እንደሚቋረጥ ተነገረ

ቀን:

በደቡብ አፍሪካ በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሠረት የሕወሓት ታጣቂዎችን ሙሉ በሙሉ ትጥቅ የማስፈታት ሒደቱ ጫፍ ሲደርስ፣ በሕወሓት ላይ የተጣለው የሽብርኝነት ፍረጃ እንደሚነሳ፣ እንዲሁም በሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ላይ የተከፈተው የወንጀል ክስም እንደሚቋረጥ ተገለጸ።

ከሕወሓት ጋር የተደረሰውን የሰላም ስምምነት አስመልክቶ ባለፈው ሳምንት ለተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች ገለጻ ያደረጉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳዮች አማካሪ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር)፣ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ለማዝለቅ በቀጣይ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል አንዱ፣ በሕወሓት ላይ የተጣለውን የሽብርተኝነት ፍረጃ ማንሳትና ክስ ማቋረጥ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ሬድዋን (አምባሳደር) ይህንኑ መረጃ ዓርብ ታኅሳስ 21 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከሕወሓት ጋር የተደረሰውን የሰላም ስምምነትና አፈጻጸሙን በተመለከተ ገለጻ ባደረጉበት ወቅት መናገራቸውን፣ የምክር ቤቱ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል።

- Advertisement -

ባለፈው ዓርብ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በተደረገው ገለጻ ላይ ከሬድዋን (አምባሳደር) በተጨማሪ፣ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎና የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ተገኝተው እንደነበር ምንጮች ጠቁመዋል።

ሬድዋን (አምባሳደር) ለተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮች ገለጻ ባደረጉበት ወቅት፣ ‹‹የትጥቅ መፍታት ሒደቱ ጫፍ ሲደርስ ለፖለቲካ ሒደቱ በር መክፈት ስለሚያስፈልግ፣ ፓርላማው የሽብር ፍረጃውን ሊያነሳ ይችላል። የተመሠረተ የወንጀል ክስ ሒደትም እንዲቋረጥ የሚደረግበት ሁኔታ ይኖራል፤›› ብለው ነበር።

ይህ የሚደረገው ሰላም ለማምጣት ሲባል እንደሆነ የተናገሩት ሬድዋን (አምባሳደር)፣ ሽብርተኛ ተብሎ ከተፈረጀና የወንጀል ክስ ከተመሠረተበት አካል ጋር ቁጭ ብሎ መነጋገር ስለማይቻል፣ ክስ መቋረጥና የሽብርተኝነት ፍረጃው መነሳት እንዳለበት ገልጸዋል።

‹‹ሰላም ለማምጣት አንዳንድ መራራ አካሄዶች ይኖራሉ። ይህም ሰላምን ለማምጣት የሚከፈል ዋጋ ነው፤›› ብለዋል።

ወደ ፖለቲካ ውይይት ሲገባ ትኩረት ከሚደረግባቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ የሽግግር መንግሥት እንዴት ይቋቋማልና ምርጫ መቼ ይካሄዳል የሚሉት እንደሆኑም ገልጸዋል።

ሕወሓት በአሁኑ ወቅት ከባድ የጦር መሣሪያዎቹን ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ያስረከበ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የመከላከያ ሠራዊቱ አንድ ሻለቃ ጦር ከባድ መሣሪያውን ተረክቦ በጥበቃ ላይ እንደሚገኝ የመከላከያ ሠራዊቱ አመራሮች ከሰሞኑ ለሚዲያዎች መግለጻቸው ይታወቃል።

ከዚህ በተጨማሪም የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ሰላም ለማስከበርና የፌዴራል ተቋማትን ለመጠበቅ መሰማራታቸውም ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅትም የፌዴራል ፖሊስ ከመቀሌ ከተማ በተጨማሪ፣ በአዲግራትና በተከዜ አካባቢዎች፣ እንዲሁም ከማይጨው እስከ መቀሌ ባሉ ከተሞች እንደተሰማራ ታውቋል። 

ሬድዋን (አምባሳደር) ለተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮች ገለጻ ባደረጉበት ወቅት፣ የፀጥታን ማረጋገጥ ሥራ ከሕወሓት ጋር በጋራ የሚሠራ መሆኑን የጠቆሙ ሲሆን፣ ለዚህም ከሕወሓት በኩል ለፀጥታ ሥራ የተመረጡና የሠለጠኑ ኃይሎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ አስረድተው ነበር።

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...