የምግብ አቅርቦቶች ከታክስ ነፃ እንዲሆኑ የሚደነግግ ረቂቅ ሕግ ተዘጋጅቷል
መንግሥት ከድጎማ ይልቅ መሠረታዊ የዜጎች ፍጆታ በሆኑ ምግቦች ላይ የሚጣለውን የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) እንዲያስቀር ፐርፐዝ ብላክን ጨምሮ ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት መንግሥትን ጠየቁ፡፡
ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴና ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ጥያቄው በአካል መቅረቡ የታወቀ ሲሆን፣ የጉዳዩ ዋነኛ ባለቤት የሆነው የገንዘብ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ተገቢውን ምልክታ እንዲያደርግ ጥያቄ ለማቅረብ በሚቀጥለው ሳምንት ቀጠሮ መያዙን የፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍስኃ እሸቱ (ዶ/ር) ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
ለዋጋ ግሽበት አንዱና ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገ ያለው ጉዳይ በተለይም በምግብ ውጤቶች ላይ የሚጣለው የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ፍስኃ (ዶ/ር)፣ ዝቅተኛ ገቢ ያለው ኅብረተሰብ ክፍል በሚመገበው ምግብ ላይ 15 በመቶ ታክስ መጨመር ትልቅ ተፅዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል፡፡
ከወር በፊት ጥያቄው ለሚመለከታቸው አካላት መቅረቡ የተገለጸ ሲሆን፣ የገንዘብ ሚኒስትሩን ለማግኘት ጥረቶች እንደተደረጉና ምናልባትም በሚቀጥለው ሳምንት ዕድሉ የሚሳካ ከሆነ ጥያቄውን በግምባር ለማቅረብ እየሠሩ መሆኑን ፍስኃ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ጥያቄውን ‹‹በአዋጅ ሳይሆን በመመርያ ደረጃ መመለስ የሚቻል ነው›› የሚሉት የፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ይሁንታ ካገኘ መስተካከል የሚችል መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አነስተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚጠቀሟቸው በተለይም የአትክልትና ፍራፍሬ ውጤቶች (ሽንኩርት፣ ቲማቲምና ሌሎችም)፣ ከታክስ ነፃ ናቸው ከሚባሉት እንቁላልና ሥጋ በበለጠ ተዘውታሪ በመሆናቸው፣ መንግሥት ከእነዚህ ምርቶች የሚሰበሰበው ቫት እንዲቀር መጠየቁ ተብራርቷል፡፡
እንደ ፐርፐዝ ብላክ ዓይነት ድርጅቶች ከላይ የተጠቀሱትን የምርት ውጤቶች ቫት በማከል ለሸማቹ እንደሚያቀርቡ፣ ይህም ምርቶችን በጣም በረከሰ ዋጋ እንዳያቀርቡ አንዱ እንቅፋት መሆኑን ፍስኃ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የዋጋ ንረት መባባስ የጀመረው የተጨማሪ እሴት ታክስ አሠራር ከመጣ ወዲህ መሆኑን ጥናት ያስረዳል ያሉት ፍስኃ (ዶ/ር)፣ መንግሥት ለሚያከናውናቸው ሥራዎች ገንዘብ እንደሚያስፈልገው ሳይረሳ፣ ነገር ግን በሁሉም የምግብ ፍጆታዎች ላይ ሳይሆን ኅብረተሰቡ በመሠረታዊነት የሚጠቀምባቸውን ምርቶች ከቫት ነፃ ማድረግ እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ከወር በፊት ፐርፐዝ ብላክ ያሰናዳው ትልቅ የውይይት መድረክ እንደነበር ያስታወሱት ፍስኃ (ዶ/ር)፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ተወካዮችን ጨምሮ የኢኮኖሚክስ አሶሴሽንና የሕግ ባለሙያዎች ተገኝተው በጥናታዊ ጽሑፍ የታገዘ ገለጻና ውይይት እንደተደረገ ገልጸዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ ዓመታት በፊት ያወጣውን የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ማዘጋጀቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ረቂቅ አዋጁ መንግሥት ከቫት ታክስ የሚሰበስብበትን መሠረት የሚያሰፋ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በሥራ ላይ ያለው አዋጅ በ1994 ዓ.ም. ከወጣ በኋላ በ2001 ዓ.ም. እና በ2011 ዓ.ም. ለሁለት ጊዜያት መጠነኛ ማሻሻያዎች ተደርጎበት የቀጠለ ሲሆን፣ አዲስ እየወጣ ያለው የተጨማሪ እሴት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ሲፀድቅ የበፊቱን ይሽራል ተብሏል፡፡
በረቂቅ አዋጁ በሰንጠረዥ ሁለት አንቀጽ ስምንት ከታክስ ነፃ የሆኑ አቅርቦቶች መዘርዝር ሥር የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመርያ ዝርዝራቸው የሚወሰን የምግብ አቅርቦቶች እንደሚኖሩ የተደነገገ ሲሆን፣ የትኞቹ ናቸው በሚለው ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ አለመስፈሩ ታውቋል፡፡