Tuesday, February 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ነዳጅ አዳዮች በትርፍ ህዳግ ማስተካከያ ትግበራ መዘግየት እንደተማረሩ ገለጹ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የተወሰኑ ማደያዎች ከጥር ወር ጀምሮ ሥራ ለመቀጠል እንቸገራለን አሉ
  • ትርፋቸውን እስከ አምስት በመቶ ለማሳደግ ከወሰነ አንድ ዓመት አልፎታል

በአገሪቱ የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች በመንግሥት ተመድቦላቸው ያለው የትርፍ ህዳግ እንደሚሻሻልላቸው በተደጋጋሚ ቃል ቢገባላቸውም ተግባራዊነቱ በመዘግየቱ እንደተማረሩ ገለጹ፡፡ በመንግሥት በኩልም ለመጨረሻ ጊዜ በአንድ ወር ውስጥ እንደሚስተካከልላቸው ከሳምንታት በፊት ቃል ተገብቶላቸው፣ የዚህን ቃል ተግባራዊነት እስከ ታኅሳስ ወር መጨረሻ ድረስ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ለረዥም ዓመታት ሲሠሩበት የነበረው በአንድ ሊትር 23 ሳንቲም ትርፍ፣ አሁን ለኪሣራ እየዳረጋቸው መሆኑን ለመንግሥት አካላት በተለያዩ ጊዜ ያሳወቁ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሆኖም ግን የማደያዎቹ ባለቤቶች ‹‹ትዕግሥታቸው አልቆ ጫፍ ላይ›› እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማኅበር አመራር አባላት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ታኅሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ የነዳጅ ውጤቶች የዋጋ ግንባታና የትርፍ ህዳግ አሠራር፣ እንዲሁም የነዳጅ ውጤቶች መሸጫ ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማ አፈጻጸምን የሚያካትት ሁለት ውሳኔዎችን እንዲሁም በነዳጅ ላይ የተሰማሩ የንግድ አካላት ስለሚያገኙት የትርፍ አሠራር ውሳኔ ተላልፎ ነበር፡፡

የትርፍ ህዳግን አሠራር አሻሽሎ ከዓመት በፊት የወጣው ውሳኔ እንደሚያሳየው፣ የነዳጅ አዳዮች ትርፍ ከጠቅላላ ወጪያቸው ከ0.5 በመቶ እስከ አምስት በመቶ እንዲያገኙ የሚያስችሉ አማራጮች እንዲቀርቡና እንዲወሰን የሚደነግግ ሲሆን፣ ከፀደቀበት ዕለት ጀምሮም ተፈጻሚ እንዲሆን ይላል፡፡ ሆኖም ግን ማደያዎቹ ይህ ውሳኔ ከመጽደቁ በፊትም በሚሠሩበት በ23 ሳንቲም ትርፍ እየሠሩ እንዳለና በመቶኛም ከ0.39 እንደማይበልጥ የማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ ሔኖክ መኮንን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

መንግሥትም ይህ የትርፍ ህዳግ እንደሚያንስ እንደሚያውቅና ከሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ጀምሮ ይጨመርልናል በሚል ተስፋ እየጠበቁ እንደሚገኙ፣ ነገር ግን ተግባራዊነቱ እጅጉን እንደዘገየ አቶ ሔኖክ ተናግረዋል፡፡ የሥራ ዘርፉ በዚህ አሠራር በመቀጠሉ አዳዲስ ኢንቨስተሮችም መዋዕለ ነዋያቸውን በዚህ ላይ እያሰፈሩ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹የሥራ ማስኬጃ ወጪ ጫናው በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ከአንድ መኪና ነዳጅ ለማራገፍ እስከ ሦስት ሚሊዮን ያስፈልጋል፣ ነገር ግን ከዚህ የሚገኘው ትርፉ ያልተጣራ አሥር ሺሕ ብር ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የተወሰኑ አዳዮች ለሥራ ማስኬጃ የሚያገኙትን ገንዘብ ከትርፍ በበለጠ ወለድ እየተበደሩ እንደሚሠሩ የተገለጸ ሲሆን፣ የነዳጅ ግዥ ከብድር ውጪ እጅ በእጅ እንደሚገዙ ይታወቃል፡፡

ማኅበሩ ከመንግሥት ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ የገለጹት አቶ ሔኖክ፣ በአንድ ወር ውስጥ እንደሚጨመርላቸውም ከሦስት ሳምንታት በፊት ተገልጾላቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ ከአባሎቻቸው ጋር የተነጋገሩ መሆኑንና አብዛኛው አባሎቻቸውም ይህ ውሳኔ በቅርቡ ተግባራዊ የማይሆን ከሆነ በሥራቸው ለመቀጠል አቅም እንደማይኖራቸው ገልጸው ነበር፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን የሥራ ኃላፊ እንደገለጹት፣ ባለሥልጣኑ ጥናት አከናውኖ ጨርሶ ለአዳዮች ሊጨመር የሚገባውን የትርፍ ህዳግ ተመን አዘጋጅቶ ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ማስተላለፉን ተናግርዋል፡፡ ሊጨመር ስለታሰበው የትርፍ መጠን ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ያልቻሉት የሥራ ኃላፊ ሲናገሩ፣ ባለሥልጣኑ በበኩሉ ከአዳዮች ማኅበር ጋርም ሲነጋገር መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ሪፖርተር ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የውሳኔው ተግባራዊነት ያለበትን ደረጃ ለማጣራት ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ የቀረ ሲሆን፣ የባለሥልጣኑ የሥራ ኃላፊ እንደተናገሩት በሚቀጥለው አንድ ወይም ሁለት ሳምንታት አዲስ የትርፍ ህዳግ በሚኒስቴሩ እንደሚወጣ እምነታቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ማኅበሩ በባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባስገባው ደብዳቤ፣ የትርፍ ህዳጉ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት እንዲስተካከልላቸውና ቢያንስ በአንድ ሊትር ነዳጅ እስከ አንድ ብር ከ20 ሳንቲም እንዲያዝላቸው፣ በዚህም የነዳጅ ማደያ ሥራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

ከዚህ በማስቀጠልም የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ጭማሪ ለማድረግ እንዲረዳው ጥናት እንደጀመረና ማኅበሩ ለዚህም ጥናት የሚሆን አባሎቹ መረጃ በመስጠት እንዲተባበሩት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ጠይቆ ነበር፡፡ የማኅበሩ አባሎችም በዚህ ተስፋ አድርገው የነበረ ቢሆንም እስካሁን ምንም ለውጥ አለመምጣቱን አመራሮቹ ይናገራሉ፡፡

የማኅበሩ ቦርድ አመራር አባል የሆኑት አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ ለሪፖርተር ሲገልጹ፣ ይህ የትርፉ ህዳግ ማነስ አዳዲስ ወደ ቢዝነሱ የሚገቡ ሰዎችን ማራቅ ብቻም ሳይሆን ተፅዕኖው ለሕገወጥ ንግድ ያለው አስተዋጽኦም ከፍተኛ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ሕገወጥ ሥራ ላይ ላለመሰማራት የሚፈልጉና ከሥራው ያልወጡ አዳዮች ግን እጅጉን እየተቸገሩና የመንግሥትን ውሳኔ በመጠባበቅ መማረራቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡

‹‹አሁን ትዕግሥታችን አልቆ የመጨረሻ ጫፍ ላይ ነው ያለው፤›› ብለው የተናገሩት አቶ ኤፍሬም፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በየዓመቱ እንዲከለስ ብሎ ያወጣውን ውሳኔ ዓመቱን ሙሉ አንዴም እንኳን ተግባራዊ አለመደረጉ ትልቅ የማስፈጸም ችግር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የማኅበሩ አመራሮች በሰሞኑ ባደጉት ተደጋጋሚ ምክክርም አብዛኛው የማኅበሩ አባላት የታኅሳስ ወር ሲያልቅ የሚደረገውን ጭማሪ እየተጠባበቁ እንደሆነና ከጥር ወር ጀምሮ ክለሳ የማይደረግ ከሆነም በሥራ ለመቀጠል እንደሚቸገሩ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች