የኢትዮጵያ ደረጃዎችን እንዲያፀድቅ ሥልጣን የተሰጠው ብሔራዊ የደረጃዎች ምክር ቤት፣ በአምስት የተለያዩ ዘርፎች የሚገኙ 32 አስገዳጅ ደረጃዎችን አፀደቀ፡፡
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ካዘጋጀቸው 1,035 የምርትና የአገልግሎት ደረጃዎች ውስጥ፣ 32ቱን በአስገዳጅ ሁኔታ እንዲፀድቁ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ ከተለያዩ አካላት በተወጣጡ ብሔራዊ የደረጃ ዝግጅት ቴክኒክ ኮሚቴ ጋር በመሆን ያዘጋጀውን ደረጃዎች የሚያፀድቀው ምክር ቤቱ ታኅሳስ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው 35ኛ መደበኛ ስብሰባው 1,035 ደረጃዎችን ማፅደቁን ያስታወቀው፣ ትናንት ታኅሳስ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡
ምክር ቤቱ በሰባት ዘርፎች ካፀደቃቸው ደረጃዎች መካከል 200 አዲስ፣ 203 የተከለሱ ሲሆን፣ 634 ነባር ደረጃዎች እንዲቀጥሉ መደረጉን የኢንስቲትዩቱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ይስማ ጅሩ ገልጸዋል፡፡
በአራት የተለያዩ ዘርፎች ማለትም በኮንስትራክሽን፣ በግብርና፣ በአካባቢና ጤና እንዲሁም በኤሌክትሮ ሜካኒካል፣ ዘርፍ ያሉ 32 ደረጃዎች በአስገዳጅነት የፀደቁ ሲሆን በጨርቃ ጨርቅና ቆዳ፣ በኬሚካል እንዲሁም በመሠረታዊና አጠቃላይ ደረጃዎች ደግሞ አስገዳጅ ያልሆኑ ዘርፎች መሆናቸውን ኢንስቲትዩት በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ኢንስቲትዩት አዲስ የኢትዮጵያ ደረጃዎች እንዲዘጋጁ በማድረግ የሚመለከታቸው የቴክኒክ ኮሚቴዎች በጋራ የተስማሙባቸውን የመጨረሻ ረቂቅ ሰነዶች ዝርዝር፣ ለብሔራዊ ደረጃዎች ምክር ቤት በማቅረብ እንዲፀድቁ መደረጉን አቶ ይስማ ገልጸዋል፡፡
እነዚህ የፀደቁ ደረጃዎች ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት ከፀደቁና ሥራ ላይ ከዋሉ ደረጃዎች በተጨማሪ የዝግጅት ሒደታቸው ፕሮጀክት ዕቅድ ዝግጅት ተገምግሞ ከጥራት፣ ከሰውና ከእንሰሳት ደኅንነት፣ ከአካባቢ ጥበቃና ንግድን ከማቀላጠፍ አኳያ አስተዋጽኦ ያላቸው መሆናቸውን የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሠረት በቀለ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ደረጃዎቹ የምርቶችን ጥራት ከማሻሻልና ከማረጋገጥ አኳያ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዕድገትና የተወዳዳሪነት አቅም ለማሳደግ የሚረዳ መሆኑንም መሠረት (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ደረጃዎችን ማውጣት ለምርምርና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ለመፍጠር፣ የኅብረተሰቡ ጤናና ደኅንነት እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃና ሸማቾችን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚረዳ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ አስረድተዋል፡፡
አምራቾችና አስመጪዎች ደረጃዎቹ መኖራቸውን በማወቅ መጠቀም እንደሚገባቸው፣ የምርቶቻቸውን ጥራት በማሻሻል ጥራታቸውን ያሟሉ ሸቀጦች ወደ አገር በማስገባት፣ እንዲሁም ወደ ውጭ በመላክ ለኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡
የደረጃዎች ኢንስቲትዩት በሁሉም ዘርፍ ያወጣቸውን ደረጃዎች የሚመለከታቸው አካላት እንደ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ የግብርና ሚኒስትርና የኮንስትራክሽን ባለሥልጣን የመሳሰሉ መሥሪያ ቤቶች ተከታትለው ማስፈጽምና መቆጣጠር እንደሚገባቸው በመግለጫው ተወስቷል፡፡
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት የደረጃዎቹን ዶክመንት ለኅብረተሰቡ ተደራሽ የሚያደርግ፣ እንዲሁም የሥልጠናና የቴክኒክ ድጋፍ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ነው፡፡
ኢንስቲትዩቱ የኢትዮጵያን ደረጃዎች እንዲያዘጋጅ ሥልጣን የተሰጠው ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ የደረጃ አዘገጃጀት ሥርዓትን በኢትዮጵያ የደረጃዎች ዝግጅት ሒደትን በመከተል ደረጃዎችን ያዘጋጃል፡፡
በኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ከአሥር ሺሕ በላይ ደረጃዎች ወጥተው መፅደቃቸውም ይታወቃል፡፡
ኢንስቲትዩቱ በ33ኛውና በ34ኛው የብሔራዊ ምክር ቤቱ ጉባዔ በአምስት ዘርፎች ማለትም በምግብና እርሻ፣ በአካባቢና ጤና፣ በኬሚካልና ኬሚካል ውጤቶች፣ በኤሌክትሮ ሜካኒካል እንዲሁም በኮንስትራክሽንና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ዘርፎች የተዘጋጁ 400 ብሔራዊ ደረጃዎች ማፅደቁ ይታወሳል፡፡