በጃኖ ባንድ ቡድን ውስጥ ለአሥር ዓመታት የዘለቀው ድምፃዊ ዲበኩሉ ታፈሰ ‹‹የቱ ጋ ነህ?›› የተሰኘ አልበሙን በገና ዋዜማ ለሕዝብ እንደሚያደርስ አስታውቋል፡፡
አልበሙ 13 ሙዚቃዎችን የያዘና ከዚህ ቀደም በሚታወቅበት የሙዚቃ ሥልት በተጨማሪ በሌሎች የሙዚቃ ዓይነቶችን በአዲሱ አልበሙ እንዳካተተ ታኅሣሥ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. በስካይ ላይት ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግሯል፡፡
የጃኖ ባንድ አቀንቃኞች በየግላቸው የሙዚቃዎችን ለሕዝብ እያደረሱ ሲሆን፣ ዲበከሉም በአልበም ደረጃ የመጀመርያ የሆነውን ሥራ ይዞ መጥቷል፡፡
ወጣቱ አቀንቃኝ በአልበሙ ስያሜ መሠረት ሥራዎቹ የት ላይ እንደደረሰ ለማሳየት መሆኑን ጠቁሟል፡፡
‹‹እኔ የቱ ጋ ነኝ? የሚለውን በሙዚቃዬ ለመመለስ እየሠራሁ እገኛለሁ፤›› ያለው ድምፃዊ ዲበኩሉ፣ ሌሎችም ሙዚቃውን መነሻ በማድረግ የቱ ጋ እንደሆኑ ራሳቸውን እንዲያዩበት ዕድል ይሰጣቸዋል ብሏል፡፡
ሙዚቃዎቹ ስለ አገርና ስለ ፍቅር የሚዳስሱ መሆናቸውን አዲስ የሙዚቃ ሥልት በአልበሙ ውስጥ መካተቱን አስረድቷል፡፡
በጃኖ ባንድ ቆይተው የተለመደው ሮክ፣ ኢትዮጵያዊ ሙዚቃዎች እንደሚታወቀው በአዲሱ ሥራው ዳግም አርኤድ ቢ ሶል ሥልቶችንና ሌሎችም የተካተቱበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከአልበሙ ሙዚቃዎች ውስጥ ሁለቱን በምስል ማውጣቱን፣ በቅርቡ ለሕዝብ የደረሰው ‹‹የልቤ ዜማ›› የተሰኘው ሙዚቃም ይገኝበታል ብሏል፡፡
በግጥም ድርሰት ይልማ ገብረ አብ የተሳተፈበት ሲሆን፣ ድምፃዊውም የተወሰኑ ዜማዎችን እንደደረሰ ተናግሯል፡፡
በኬኔቲክ መልቲ ሚዲያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የቀረበውን አልበም፣ ወጣት የሙዚቃ አቀናባሪዎች መሳተፋቸውም ተገልጿል፡፡ አልበሙ ታኅሣሥ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል፡፡