በምዕራባውያን የዘመን አቆጣጠር መሠረት አሮጌው ዓመት 2022፣ ትናንት ዲሴምበር 31 አብቅቶ፣ ዛሬ አዲሱ ዓመት 2023 ጃንዋሪ 1 አሐዱ ተብሎ ተጀምሯል። ዓለሙ ሁሉ በጋራ የሚገናኝበት ይህ ቀመር ጎርጎርዮሳዊ በመባል ይታወቃል። በኢትዮጵያም ከራሷ ቀመር ጋር መሳ ለመሳ የሚያገለግለው ካሌንደሩ “እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር” (እ.ኤ.አ.) እየተባለ ይጠራል።
አገሮች አዲስ ዓመታቸውን እንደየ ባህል ትውፊታቸው በማክበር እየተቀበሉት ነው።
በድዮስጶራ ያሉ ኢትዮጵያውያንም ርዕሰ ዓውደ ዓመቱንም በማክበር ላይ ይገኛሉ። በተለያዩ የአውሮፓና የአሜሪካ ከተሞች እየተዘዋወረ ባህልና ኪነጥበብ አቀናጅቶ ትርዒት የሚያቀርበው ታዋቂው ‘ሰርከስ አቢሲንያ ቱሉ’ ዛሬ ባዲሱ ዓመት መባቻ ትርዒቱን በአሜሪካ ያቀርባል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የውጪውን ዓለም ሚዲያ ትኩረት የሳበው ሰርከስ አቢሲኒያ ‘ቱሉ’ የሚለውን ስም የወሰደው ከመጀመሪያዋ ጥቁር አፍሪካዊት የኦሊምፒክ 10ሺ ሜትር ሩጫ ወርቃዊት አሸናፊዋ ደራርቱ ቱሉ ነው።
ሰርከስ የተለያዩ የመዝናኛ ትርዒቶች የሚቀርብበት አክሮባትን፣ ድርጊቶችን፣ ሙዚቀኞችን፣ ዳንሰኞችን፣ በጠባብ ገመድ የሚራመዱበት ምትሃታዊ ትርዒትን የያዘ የጥበብ ገበታ መሆኑ ይወሳል፡፡ በሰርከስ አማካይነት ታሪክ፣ ባህል፣ ትውፊት፣ ሙዚቃና ሌሎች የጥበብ ዘርፎችም በተከታታይነት እንደሚቀርቡበት ይገለጻል፡፡
ከዚህ አኳያ ሰርከስ አቢሲንያ ባዘጋጀው ትርዒቱ ውስጥ ከተካተቱት ተረኮች ዋናው የኦሊምፒክ ሻምፒዮኗ ደራርቱ ቱሉ ሕያው ታሪክ ነው፡፡
ሊንድሲ ዊንሺፕ በዘጋርዲያን ድረ ገጽ ላይ እንደጻፈችው፣ የሰርከስ አቢሲኒያ አዲሱ ትርኢት ታላቋን ኢትዮጵያዊት የረዥም ርቀት ሯጭ ደራርቱ ቱሉን የሚያከብር ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1992 በ10,000ሜ. የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያን በማስመዝገብ የመጀመሪያዋ ጥቁር አፍሪካዊት ሆናለች ። ያ ጊዜ ለአፍሪካ ስፖርት ትልቅ ክስተት ነበር፡፡ ደራርቱ ቱሉ እና ደቡብ አፍሪካዊቷ ሯጭ ኢላና ሜየር በበላይነት ሲፎካከሩ ቱሉ በመጨረሻው ደረጃ ቀድማለች።
የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት የመጀመሪያዋ ጥቁር አፍሪካዊት በሆነችው በደራርቱ ቱሉ እውነተኛ ታሪክ በመመሥረት ለሰርከሱ ፕሮዳክሽኑን ያዘጋጁት መሐሪ “ቢቢ” ተስፋማርያምና ቢንያም “ቢቹ” ሽመልስ ናቸው፡፡
የሰርከሱ አባል የሆነው ቢቹ ውድድሩን በልዩነት ይገልጸዋል፡፡ ‹‹በጣም ስሜታዊ ነበር። ደራርቱ ለአገሯ ምን ያህል ፍቅር እንደነበራት አስታውሳለሁ። በኋላ ላይ እያነባች ነበር፤ ይህ አጋጣሚ ከእኛ ጋር ለረጅም ጊዜ ከህሊናችን ሊጠፋ አልቻለም፡፡››
ቢቢ ተስፋ ማርያም “ሁሉም ነገር የሚቻል መሆኑን እንድትገነዘብ አድርጎሃል” ይላል፡፡ በቢቹ ተስፋ ማርያም አገላለጽ ትርኢቱ በመንደሯ ውስጥ ከብት እየጠበቀች ስላደገች ደራርቱ ቱሉ ታሪክ ይናገራል፡፡ በትርዒቱ ላይ ደራርቱን ሆና የምትጫወተው ቤተልሔም ደጀኔ ‹‹የደራርቱ ቱሉን ጥንካሬ፣ ቁርጠኝነት እና ድፍረት ማሳየት እፈልጋለሁ›› ትላለች።
በታሪኩ ውስጥ የተሸመኑት የሰርከሱ ልዩ ልዩ ትርዒቶች ሆፕ ዳይቪንግ፣ ከእጅ ወደ እጅ አክሮባት፣ ሮለር-ስኬቲንግ እና የእሳት ጨዋታ ናቸው።
ቢቹ ‹‹ባህላችንን ይዘን ሰርከስ መሥራት እንፈልጋለን፤›› ይላል፡፡ ‹‹ሐሳባችንን እንድንገልጽ፣ ራሳችንን እንድንሆን እንጂ፣ ከምዕራባውያን አገሮች መኮረጅ መቅዳት አንፈልግም፡፡››
‹‹ኢትዮጵያ በጣም የበለፀገ ባህል አላት፡፡ ሁሉም ዓይነት አልባሳት፣ ጭፈራ፣ ሙዚቃ›› የሚለው ቢቢ ነው፡፡ ‹‹አዎ ያንን መጠቀም ፈልገን ነበር፤ ነገር ግን ለድርጊቱ ቅድሚያ መስጠት እንፈልጋለን። ሰዎች አለባበስንና ዳንኪራን ለማየት የሚሄዱባቸው ብዙ የአፍሪካ ትርኢቶች አሉ፡፡ ሰዎች ግን እነዚህ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ተዋናዮች መሆናቸውን ሰዎች እንዲያደንቁልን እንፈልጋለን። ይህን ሁሉ ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ።››
ስለ ኢትዮጵያ ሰርከስ ልዩ የሆነ ምን እናያለን? ብላ ዘጋቢዋ ለጠየቀችው ቢቹ ሲመልስላት ‹‹እኛ በፈገግታ የተሞላን ሰዎች ነን፤›› ካላት በኋላ ቀጠለ።
‹‹ሁሉም ሰው በመድረክ ላይ በመገኘቱ፣ ራሱን ለማሳየት ዕድሉን በማግኘቱና ያቺ የሚሰማህን ነፃነት በማግኘቱ በእውነት ደስተኛ ነው።›› ዝግጅታቸው ኢትዮጵያዊ ቢሆንም፣ ቢቹ ስለ ሰርከስ በሐቅ የሚወደው ነገር አድማሳዊነቱን፣ ሁሉን አቀፍነቱን ነው።
‹‹ምንም ሳትናገር ራስህን መግለጽ ትችላለህ›› ይላል። ‹‹ያለ ቃል ታሪክ መናገር ትችላለህ። ዓለም አቀፋዊ ቋንቋ ነው። ይህም በጣም ኃይል ነው፡፡››