ክፍል ፩
በተሾመ ብርሃኑ ከማል
‹‹ጀበርቲ›› የተባለው የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የሶማሊያ፣ የየመንና የሰሜን ኬንያ ሙስሊሞች የጋራ መጠሪያና ሰፊ ሙስሊም ኅብረተሰብ የያዘ ሲሆን ስለቃሉ አመጣጥም የተለያዩ መገለጫዎች አሉት። በዚህ ርዕስ እንደሚብራራው ሁሉ በርካታ አውሮፓውያን ትኩረት ሰጥተው በየምዕራፎቻቸው አውስተውታል። ለምን? የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በአብዛኛው ለኢትዮጵያ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያበረክት የነበረው ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ኅብረተሰብን ለመግለጽ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስላለው ነው።
ምንም እንኳን የዚህ ጽሑፍ መሠረታዊ ዓላማ፣ ስለኢትዮጵያውያን ጀበርቲዎች መግለጽ ቢሆንም ታሪክ ራሱ እየጎተተ የሚያስገባቸው ኤርትራውያንና የሶማሊያ ሪፐብሊክ ጀበርቲዎችም መጠቃለላቸው አልቀረም። ጸሐፊው ላውጣቸው ቢልም እንደቀደምት አጥኚዎቹ ሁሉ የሚቻል ሆኖ አላገኘውም። ስለሆነም የሦስቱ አገሮች ሉዓላዊነት እንደተጠበቀ ሆኖ በጀበርቲ ጠንካራ ሰንሰለት መተሳሰራቸው ግን ይቀርባል። አዎን የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የሶማሊያ ሪፐብሊክ ሙስሊም ኅብረተሰብ የተሰናሰለ ነው። የማንነታቸው መገለጫ ነው። አፍንጫና ዓይን ናቸው።
ሆኖም፣ በዚህ አርዕስተ ጉዳይ የምንዳስሰው መሠረታዊ ሐሳብ አፈ ታሪክንም የሚያካትት በመሆኑ ያንን ለማጥራትና ወደ ትክክለኛው ግንዛቤ ለመድረስ የሚደረገውን ትንታኔ በትዕግሥትና በጥንቃቄ መከታተል እንደሚያስፈልግ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በቅድሚያ ለማስታወስ ይፈልጋል። በእርግጥም፣ ጀበርቲን በሚመለከት የሚቀርበው ሐሳብ በመጀመሪያ ሲያዩት ትክክል እንኳን ባይመስል እውነቱ ከሚቀዳበት ምንጭ የተገኘ ስለሆነ፣ እውነቱ ነጥሮ እንዲወጣ የቀረበ መሆኑንን አውቆ መስመር በመስመር ማንበብን ይጠይቃል። በተለይም የወደፊት ተመራማሪዎች ይህ ሥራ ምንም ያህል ጥረት ቢደረግበትና አዲስ የሚፈነጥቀው ሐሳብ ቢኖርም እንኳን ጸሐፊው ያላየው፣ ነገር ግን እነሱ የሚያዩት ክፍተት ስለሚኖር በንቃት መከታተል እንደሚያስፈልግም በቅድሚያ ለማስታወስ ይወዳል፡፡
እዚህ ላይ፣ በአንድ በኩል የሶማሊያ መስሊም ኅብረተሰብ ማንነት የሚጀምረው ዓብዲራሕማን ቢን ኢስማኤል አል ጀበርቲ እንደሆነ የሚጠቁሙ ሲኖሩ በሌላ በኩል ደግሞ ሸኹን ተቀብለው ያሰተናገዷቸው ሶማሊ ሙስሊሞች እንደነበሩ አንዳንድ መረጃዎች አሉ። ስለሆነም በዚህ ጽሑፍ በአብዛኛው የሚወሳው ስለጀበርቲ እንጂ ኢስላም በሶማሊ አለመሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል።
ጸሐፊው ይህን ያህል መንደርደሪያ ከሰጠ በኋላ በመጀመሪያ ስለ ሶማሊ ጀበርቲ፣ ቀጥሎ ስለተቀረው ኢትዮጵያና ኤርትራ ጀበርቲ ካቀረበ በኋላ ስለጀበርቲና ጀበርቲነት የማጠቃለያ ሐሳብ ይሰጣል።
ሶማሊ ጀበርቲ
ዓብዲራሕማን ቢን ኢስማኤል አል ጀበርቲ የሶማሌ ዳሮድ ጎሳ የጋራ አባት ሲሆኑ እርሳቸውም የበኑ ሐሽም የትውልድ ሐረግ ያላቸው ናቸው። ከዚህ የዘር ሐረግም የዓቂል ኢብን አቢጣሊብ ማለትም የነብዩ ሙሐመድ (ሱዓወ) አጎት ይወለዳሉ። ስለዚህም ዓብዲራሕማን ቢን ኢስማኤል አል ጀበርቲ የነብዩ ሙሐመድ (ሱዓወ) ዘመድ መሆናቸው ነው። እርግጥ ነው፣ ዓብዲራሕማን ቢን ኢስማኤል አል-ጀበርቲ መች እንደተወለዱ አይታወቅም። ዳሩ ግን ብዙዎቹ እንደሚገምቱት በዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ሳይሆን አይቀርም። የሃይማኖት አባቶች ታሪኩን ቀደም ብለው ከተጻፉ የእስልምና መጻሕፍት ጠቅሰው እንደሚጠቁሙት፣ ነብዩ ሙሐመድ (ሱዓወ) ከሞቱ በኋላ ብዙ የዓረቢያ ሰዎች ወደ ሶማሊያ ሰሜናዊ ክፍል እየመጡ ይቀመጡ ነበር። ኢብን ሐቃል አል-ሙቀደሲ እና ኢብን ሰዒድ የተባሉ ዕውቅ ጸሐፍትም የዓረብ ተወላጆች በበርበራ፣ በዘይላ፣ በጀበርታና በምጽዋ ውስጥ ይኖሩ እንደነበረ በጽሑፎቻቸው አስፍረዋል። አል-መስዑዲ የተባለው ጸሐፊም «ዓቂሊዩን» በሚል ርዕስ ባዘጋጀው መጽሐፍ በጀበርታና በዘይላ የሚታወቁ የዓረቢያ ተወላጆች ይኖሩ እንደነበረ ገልጧል። በዚህ ጸሐፊ መረጃ መሠረት በተለይም ኢስማዒል ኢብን ኢብራሒም አል-ጀበርታ የሚባል ሱፊ ሸኽ እንደነበሩ ጠቅሶ የኒህም ሸኽ ልጅ ዓብዲረሕማን እንደሚባሉና እኒህም ሰው የሶማሌ ባላባት (የጎሳ መሪ) ልጅ አግብተው እንደነበር፣ እንዲሁም ከዚች ሴት አምስት ወንዶች ልጆችን እንደወለዱ አውስተዋል። በአል-መስዑዲ ትንታኔ መሠረትም አብዲራሕማን ቢን ኢስማዔል፣ ቢን ኢብራሂም፣ ቢን አብዲራሕማን ቢን ሙሐመድ፣ ቢን ዓብዲ፣ ቢን ሐምባል፣ ቢን ማህዲ፣ ቢን አሕመድ፣ ቢን ዓብዱሌ፣ ቢን አቡጣሊብ፣ ቢን ዓብዱል ሙጠሊብ፣ ቢን ሐሺም፣ ቢን ቁሳይ ሲል ገልጧል።
የዳሩድ አባት ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ዓብዲራሕማን ቢን ኢስማዒል አል-ጀበርቲ ሲሆኑ የዚህ ሰው ጎሳ አባላትም በሶማሊያ፣ በኢትዮጵያ፣ በየመንና በኬንያ እንደሚገኙ ይታወቃል። ዳሩድ የሚለው ቃል ከሁለት የሶማልኛ ቃላት የተገኘ ሲሆን ዳር «ግቢ» ዑድ ደግሞ «በግንብ ወይም በእንጨት ወይም በአጥር የታጠረ ሥፍራ›› ማለት ነው። ይህም በዘራቸው ምርጥ የሆኑና የተከበሩ ጎሳዎች መሆናቸውን ለመግለጥ የተጠቀሙበት ይመስላል። እነዚህ ሰዎች ዓረብኛና ሶማሊኛ የሚናገሩ ሲሆን እምነታቸውም ሱኒ እስልምና ነው። ጎሳቸውም ባኑ ሐሺም፣ መኸሪ፣ ሀዊዬ፣ ኢስሐቅ፣ በሚልና በሌሎች ይከፋፈላል።
ሶማሌዎች ዋናዎቹ የዳሩድ ተወላጆች በሰሜን፣ በደቡብና በሞቃዲሾ እንደሚገኙ ቢገልጡም ከእነሱ የሚወርዱ ዝርያዎች በኢትዮጵያ፣ በኬንያና በየመን እንደሚኖሩ አይክዱም።
ሙሐመድ ኢብን ዓቂል የተባለው ጸሐፊ እንደሚገልጠውም፣ ዓብዲራሕማን ኢስማዒል አል-ጀበርቲ የቃዲሪያ ሥርዓት ከሚከተሉ ሱፊ ሸኽ እንደሚወለዱና ከአባታቸው ጋር በመጣላታቸው ምክንያት የዓረቢያን የባህር ወሽመጥ ተከትለው ወደ ሰሜን ሶማሊያ በ10ኛው ወይም በ11ኛው ክፍለ ዘመን እንደመጡና የሶማሌ ጎሳ መሪ ልጅ አግብተው እንደተቀመጡ ይገልጣል። የኒህ ሰው ቀብር (ዶሪሕ) በሰሜን ሶማሌ «ሐደፍቲሞ» ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ ሲገኝ የአካባቢው ሙስሊሞች ወደ መቃብሩ በመሄድ ጸሎት ያደርሳሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ ከሸኽ ኢስሐቅ ቢን አሕመድ አል ዓለዊ የሚወለዱ ሌላው የበኑ ሐሺም ዝርያ በተመሳሳይ ጊዜ መምጣታቸው ይነገራል። የዳሩድ ኢስማዒልን ትውልድ የሚቆጥሩ ሰዎች እንደሚያስቀምጡትም ዳሩድ ኢስማዒል አምስት ወንድ ልጆች አሏቸው። እነሱም አሕመድ ቢን ዓብዲራሕማን፣ ሙሐመድ ቢን ዓብዲራሕማን፣ ሑሴይን ኢብን ዓብዲራሕማን፣ ዩሱፍ ቢን ዓብዲራሕማንና ሳ ቢን ዓብዱራሕማን ናቸው።
በሌላ በኩል ደግሞ ስፔንሰር ትሪሚንግሃም ጂ ሬቮይ የተባለ ፈረንሣዊ አጥኚና አሳሽን ጠቅሶ ጀበርቲ ቢን ኢስማዒል ወደ ሶማሌ ሊመጣ የቻለው በኬፕጋርዳፉሪ አጠገብ በምትገኝ ሥፍራ የመርከብ መጋጨት አደጋ ደርሶበት እንደሆነና እዚያም እንደደረሰ የተደበቀ ወርቅ ተገለጸለት። ባለ ብዙ ሀብት በመሆኑም የንጉሥ ዱር ዘመድ የሆነችውን ዱባራ የተባለች ሴት አገባ። እርሷም ወንድ ልጅ ወለደችለትና ሐርቲ (ዳሮድ) ተባለ። እርሱም ዱልባሐንታ፣ ደቺቺ፣ መጀርቲን፣ ወረሰንገሊ የተባሉ የልጅ ልጆችን (የጎሳ መሪዎችን) አስገኘ። ይህ በዚህ እንዳለ በ15ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሸሪፍ ኢስሐቅ ቢን አሕመድ ከ44 ቅዱሳን (አው አባድርም ከ44 ቅዱሳን ጋር ወደ ሐረር እንደመጡ ልብ ይሏል) ጋር በመሆን ከሐድረሞት (የመን ተነሱና ወደ ሶማሊ መጡና መኻን (ለንፋስ የተጋለጠ ወደብ) መቀመጥ ጀመሩ። እዚያም የመግዴሌ ጎሳ አባላትን በማግባት የባህር መግዴሌ ጎሳን መሠረቱ። ከአንዲት ሐበሻ ሴትም ባ ሐብር ሐቡሸድ ወለዱና የዚህን ሰው ጎሳ ዕውን አደረጉ።
የዳሩድ ዝርያዎች አውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች መጥተው የፖለቲካ ሥርዓቱን እስከ ቀየሩት ድረስ የአካባቢው መሪዎች እነሱ ነበሩ። በ16ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያን የገዙት ኢማም አሕመድ ኢብራሂምም ከፍተኛ ድጋፍ ያገኙት ከገሪ፣ መሬሐን፣ በሬ፣ ሐርቲ፣ በርቲሬ ከተባሉ ጎሳዎች እንደነበር ይታወቃል። እነዚህ የጎሳ አባላት በተለይም በሽምብራ ኩሬ ለተገኘው ድል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበራቸው። ከሽምብራ ኩሬ ድል በኋላም በሺዎች የሚቆጠሩ ሶማሌዎች እጅግ ከተከበሩ ዓሊሞቻቸውና ኢማሞቻቸው ጋር በኢትዮጵያና በኤርትራ ተሠራጭተው ኖረዋል። ከሕዝቡ ጋር ተጋብተውም ዘራቸውን እስከ በኑ ሐሺም ድረስ የሚቆጥሩ ትውልዶች ትተው አልፈዋል።
ይህም ሆኖ ከኢማም አሕመድ በኋላ በምድረ ሐበሻ ጠንካራ መንግሥት ለማቋቋም ከ300 ዓመት በላይ ስለወሰደ፣ በርካታ የታሪክ መረጃዎች ከመጥፋታቸውም በላይ ሰዎችም ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ ተገደዋል። ግዴታውን ያልተቀበሉም አካባቢያቸውን ለቀው ተሰደዋል። የተቀሩትም አገዛዙን አሜን ብለው በመቀበል ተንቀውና ተዋርደው ኖረዋል። ስለሆነም፣ በተቀረው የኢትዮጵያ ግዛትና በኤርትራ የምናገኘው መረጃ የተበጣጠሰ በመሆኑ ጠንካራ ሆኖ አናገኘውም። ጠንካራ ባለመሆኑም በተለያዩ ጊዜያትና አጋጣሚዎች ወደ አገራችን የመጡ ምዕራባውያን ጸሐፊዎች በአጭር ጊዜ ቆይታቸው ወይም እዚያው አገራቸው ሆነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ባጠናቀሩት መረጃ የተበጣጠሰ ክር የመሰለ ሐሳብ ይፈነጥቁልናል። ሆኖም እኛ ባለቤቶቹ ኢትዮጵያውያን አንድ ጠንካራና የማይለወጠም፣ የማይናወጥም መረጃችን ከኢማም አሕመድ ኢብራሂም ጋር በሺዎች የሚቆጠሩ የጀበርቲ ዝርያዎች የሆኑ ሶማሌዎች፣ ዓፋሮች፣ ሐረሪዎች፣ አርጎባዎችና ወርጅዎች መጥተው በመላው ኢትዮጵያና በኤርትራ መኖራቸው ነው።
ጀበርቲዎች በሰሜን ኢትዮጵያና በኤርትራ
በሰሜን ኢትዮጵያ ያሉ ሙስሊሞች ቀዳሚዎቹ ጀበርቲዎች ሲሆኑ ተከታዮቹ ደግሞ ዓዲ ከቢረ ወይም አደ ከብሬ እየተባሉ ይታወቃሉ። አንዳንዶቹ ጀበርቲን ትግርኛ ተናጋሪ ሙስሊሞች በማለት ይጠሯቸዋል። አንዳንዱም ጀበርቲዎች፣ አማሮች፣ አገዎችና ትግራዮች መሆናቸውን ወደፊት የምናገኛቸውን አስረጂዎች ይጠቅሳሉ። አንዳንድ የታሪክ ጸሐፊዎች፣ ትግርኛ ተናጋሪ ጀበርቲዎች በአንድ በኩል የአክሱም ሥልጣኔን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የኢስላም ሥልጣኔ የነበራቸው ሕዝቦች እንደሆኑ አድርገው ይወስዷቸዋል። ለምሳሌ ሙሐመድ ኑር ሰዒድ ዋኘው የተባሉ ወጣት ተመራማሪ እንደጻፉትና ዶ/ር ያሲን ሙሐመድ አበራ የተባሉ ምሁር አስተያየታቸውን የሰጡበት ጽሑፍ እንደሚያቀርበው፣ ጀበርቲዎች በደቡብ ኤርትራ በተለይም በሰራየ አውራጃ ዓናገር፣ መራጉሰ፣ ማይ ጻዕዳ፣ በሚባሉ ቀበሌዎች፣ ዓዲ ዑግሪ፣ ዓዲ ዃላ፣ በከረን፣ ደቀ መሐረ፣ ዓዲ ቀይሕና ጊንዳዕ በተባሉ ከተሞች የሚገኙ ሙሰሊሞች ጀበርቲዎች ተብለው እንደሚጠሩና እነርሱም በትግራይ ውስጥ በሽሬ፣ በአዲያቦ ከሚገኙ ሙስሊሞች ጋር ዝምድና እንዳላቸው በሰፊው ያብራራሉ።
አጥኚው ከዚህም በተጨማሪ የእነዚህ ዝርያዎች አዲስ አበባ ውስጥ በተለይም ኮልፌ ተብሎ በሚታወቀው ሥፍራ መኖራቸውንም ይጠቁማሉ። ዶ/ር ያሲን ሙሐመድ ኑር በገጠር የሚኖሩ ጀበርቲዎች በግብርና የሚተዳደሩ ሲሆን፣ በከተማ የሚኖሩት ደግሞ በንግድ፣ በልብስ ስፌት፣ በሽመናና በመሳሰሉት የእጅ ሙያዎች ሕይወታቸውን እንደሚመሩ ያስረዳሉ።
ጀበርቲዎች ለኤርትራ ነጻነት ከታገሉት ግንባር ቀደምት ማኅበረሰቦች ሲሆኑ ምክንያታቸውም ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት የክርስቲያን መንግሥት ስለሆነ በዚህ መንግሥት አንተዳደርም›› የሚል እንደነበር የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ‹‹የሰላም ፍኖት ለኢትዮጵያና ኤርትራ ሕዝብ አንድነት››፣ ‹‹ኮናባ›› እና ‹‹ዓይን አብራዎቹ›› ኢስላማዊ ሥልጣኔ በኢትዮጵያ በሚሉ አርዕስት ለኅትመት ባበቃቸው መጻሕፍቱ አስፍሯል። ያሲን ሙሐመድኑርም (ዶ/ር) በተጠቀሰው ሥራቸው ውስጥ፣ ዓብዱራሕማን ጀበርቲ የተባሉ የታወቁ የእስልምና እምነት ሊቅና የታሪክ ጸሐፊ በግብፅ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኙ ምሁር እንደነበሩ ጠቅሰው፣ ለብዙ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ስደተኞች ጥገኝነት እንዲያገኙ ያደረጉ እንደነበሩ ገልጸዋል። ዶ/ር ያሲን ሙሐመድኑር ንጉሥ አሕመድ አልነጃሽን (ንጉሥ አራማህ ዳግማዊ) ጀበርቲ ያደረጉበት መንገድ ግን ታሪካዊ መሠረት ስለሌለው ትቶታል። እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ግብፅ የነበሩት ዓብዱራህማ ጀበርቲ ዳግማዊ እንጂ ቀዳማዊው እንዳልሆኑ ነው።
አርቢ ሰርጀንት የተባሉ ተመራማሪ እ.ኤ.አ. በ1966ቱ ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ጉባዔ መድበለ ጥናት (ፕረውሲዲንግ) ላይ እንዳቀረቡት የኢፋት ግዛት በዓረቦች ዘንድ ጀበርታ ተብሎ እንደሚጠራ ጠቅሰዋል፡፡ የመኒዎች ከቤይሉል ጀምሮ እስከ ዜላዕ ባሉት ግዛቶች አል-ዜላዒ የሚባሉና ከ9ኛው ክፍለ ዘመን እስከ 15ኛው ክፍለ ጊዜ በነበረው ዘመን ኢል-ጀበርቲ የሚባሉ ወገኖቻቸው በታዒዝ እንደነበሩ ሲገልጹ፣ ግብጻዊው የሕይወት ታሪክ ጸሐፊው አል-ሸኽዊ ከ9ኛው እስከ 15ኛው ክፍለ ዘመን የጀበርታ ሸኾች በመካ እንደነበሩ በጥናታቸው አስፍረዋል። ግብፅ ውስጥ የናፖሊዮንን ወረራ አስመልክተው የጻፉት የታሪክ ምሁርም የዘይላዑ ጀበርቲ ዝርያ እንደሆኑ ይናገራሉ። ሪዋቅ አል-ጀበርት የተሰኘ የእንግዶች ማረፊያም በአዝሃር ዩኒቨርሲቲ አሠርተዋል።
ኤድዋርድ ኡሎንዶርፍ (ከ1920-2011) ስለኢትዮጵያ ታሪክና ቋንቋ በስፋት ካጠኑት አውሮፓውያን አንዱ ሲሆኑ እርሳቸውም በየመን፣ በሶማሊያ፣ በኤርትራ ስለሚገኙ ጀበርቲዎች ያደረጉትን ጥናት ለኅትመት አብቅተዋል። በጥናታቸውም የየመኖቹ ሚሜ ጀበርቲ፣ የሶማሊዎቹ ኢስማዒሊ ጀበርቲ፣ የኤርትራና የትግራዮቹ ነጃሺ ጀበርቲ ተብለው እንደሚጠሩም አመልክተዋል። ስለሰሜኑ ኅብረተሰብ ጀበርቲ ስብጥር ሲገልጹም አማርኛ፣ አገውኛና ትግርኛ ተናጋሪዎች እንደሆኑ ያወሳሉ።
በዚህ መጽሐፍ አዘጋጅ ግምት አማርኛ ተናጋሪዎቹ የጎንደር ሰዎች ሊሆኑ ሲችሉ፣ አገውኛ ተናጋሪዎቹ ኤርትራ ውስጥ የሚገኙ ብሌኖች ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም ሰቆጣና አካባቢዋም በኢማም አሕመድ ጊዜና በኋላ በርካታ ሙስሊሞች ይኖሩባት እንደነበር ስለሚታወቅ ታሪክን መረጃ አድርገው አቅርበውት ይሆናል።
ጸሐፊው እንደሚያውቀው ደሀና ወረዳ በብዙ ቀበሌዎች ሙስሊሞች ኖረዋል፣ የቀብር ቦታም አለ፡፡ አርጎባ፣ ሲልዳና ሌሎችም የበርካታ ሙስሊሞች መንደሮች ነበሩ።
ጻታ፣ ጻግብጂ ሙስሊሞች የኖሩ እንደነበር ይነገራል፡፡ አስከተማ ጋዝጊብላ ወረዳ እስላሞ የሚባል ሠፈር አለ። በመረቅደዳ የጥንት የሙስሊሞች የቀብር ቦታ ይገኛል፡፡ በብርብር መንገድ ‹‹አውሣኢዶ›› በተባለ ሥፍራ እንዲሁም አቅም ዮሐንስ፣ በላይ ንጭሩ፣ ፋያ ማሪያም እስላም ኻትማ፣ ውቅር እና ወለህ አካባቢ ነበሩ።
በሸደሆ፣ በመቄት በነገላ፣ በእብናት፣ በበለሳ የነበሩ ሙስሊሞች ከሰቆጣ ሙስሊሞች ጋር የቅርብ ዝምድና ያላቸው ናቸው። ሆነም ቀረ ግን እነዚህ ማኅበረሰቦች የተለያየ ቋንቋ መናገራቸው ጀበርቲ ከመሆን ማለትም በአንድ የሸሪዓ ሕግ ከመመራት እንዳላገዳቸው ኤድዋርድ ኡሎንዶርፍ ይጠቅሳል።
ስፔንሰር ትሪሚንግሀም ‹‹ኢስላም ኢን ኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ በ1952 ባሳተመው መጽሐፉ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ብሔርና ዘር ሳይጠቅስ ሁሉንም ጀበርቲዎች የሚላቸው ሲሆን እርሱን የሚጠቅሰው ፕሮፌሰር ፍሬድሪክ ጄ ሲሙንስም ስለሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ባቀረበው ጥናቱ ‹‹ጀበርቲ የሚለውን ቃል የምጠቀመው ትሪሚንግሃም በተጠቀመበት መንገድ ነው›› በማለት ይገልጣል። ምንም እንኳን ፕሮፌሰሩ ያደረገው ጥናት ጠቃሚነቱ የጎላ ቢሆንም ጀበርቲ የሚለውን ቃልና ትርጉም ከትሪሚንግሃም እስከወሰደ ድረስ እዚህ ላይ በተለየ ሁኔታ የሚጠቀስበት ምክንያት የለም።
ጀምስ ኩዊሪን፣ የፊስክ ዩኒቨርሲቲ (ናሽቪል፣ ቴኒሰን፣ አሜሪካ የሚገኝ) ፕሮፌሰር፣ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ 13ኛው ጉባዔ ባቀረበው ጥናታዊ ሥራው እንዳሰፈረው በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ አገዎች፣ አማሮችና ትግራዮች መኖራቸውን ጠቅሶ እነርሱም በእምነታቸው ክርስቲያኖች፣ አይሁዶችና ሙስሊሞች መሆናቸውን፣ ሙስሊሞቹም ጀበርቲዎች እንደሆኑና ጀበርቲዎችም አንድም አማርኛ ወይም ትግርኛ ተናጋሪዎች እንደሆኑ ያስረዳል።
ጀምስ ኩዊሪን እንደሌሎቹ የታሪክ አጥኚዎች ሁሉ ጀበርቲ የሚላቸው ሙስሊሞች የንግዱን ክፍለ ኢኮኖሚ ከባህር ጠረፍ እስከ ምዕራብ የአገሪቱ ጥግ በበላይነት እንደሚመራ ያብራራል። ጀበርቲዎች ወደ ውጭ ከሚልኳቸው የአገር ምርቶች ውስጥም ቡና፣ ዝባድ፣ ማር፣ ሰምና ወርቅ እንደሚገኙበት እንደ ሐር ልብሶች፣ ምንጣፎች፣ ብርጭቆ (መስታወት) ነክ ምርቶች፣ ወደ አገር ውስጥ ያስገቡ እንደነበረ ይጠቁማል። ጀምስ ኩዊሪን ‹‹ምንም እንኳን የእስልምናና የአይሁድ እምነት ተከታዮች ዓረብ ሳይሆኑ ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያውያን ቢሆኑም መብታቸው በአዋጅ ተገፎ ነበር። በዚህም መሠረት ጀበርቲዎቹ የሚፈለጉት ለግብር ሲሆን የሚተዳደሩት ግን በራሳቸው ሸሪዓ ሕግ መሠረት ነበር። ከሁሉም ነገሥታት በበለጠ ቀዳማዊ ዮሐንስ (1667-1682) እና አራተኛው ዮሐንስ ጀበርቲዎችን ጨቁነዋል። ሃይማኖታቸውንም ወደ ክርስትና እንዲቀይሩ አስገድደዋል። የጎንደር ጀበርቲዎች በአፄዎቹ ይደርስባቸው ከነበረው ግፍ የተገላገሉት በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመን ነው፤›› የሚል ጥናት አቅርቧል። ትሪሚንግሃም በተጠቀሰው መጽሐፉ ከኢትዮጵያዊት ሴት የሚወለድ የዑስማን ኢብን ዐፋንን ልጅ በኢትዮጵያ ውስጥ እስልምናን እንዳስፋፋ ይጠቅስና ሸኽ አደም አል-ቂናኒ የሚባሉ የጀበርቲ ዝርያ ዶሪሐቸው በዓቢይ ዐዲ (ትግራይ) እና ዓዲ ኢታይ (ኤርትራ) ውስጥ እንደሚገኝ ይገልጻል። በዐዲ አርቃይ (ስሜን) በተለይ በሮክ ወሃ በሚባል ሥፍራ፣ በቤጌምድር፣ በደብረታቦር፣ በእስላምጌ፣ በደረስጌ፣ ደበርጌ፣ በዳንግላ፣ በአዲስ ዓለም፣ በሰቆጣ ይገኛሉ።
(ይቀጥላል)
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው bktesheat@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡