Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅውሻ መኪና ላይ የሚጮኸው ለምንድን ነው?

ውሻ መኪና ላይ የሚጮኸው ለምንድን ነው?

ቀን:

በድሮ ጊዜ ከከተማ ርቃ በምትገኝ መንደር ውስጥ አንድ ውሻ አንድ ፍየልና አንድ አህያ አብረው ይኖሩ ነበር። እነህ ሦስቱ ስለከተማ ሲወራ በመስማታቸው ጠፍተው ሊሔዱ ተመካከሩና ገንዘብ አጠራቀሙ። በቂ ገንዘብ እንዳጠራቀሙም ወደ መንደር ዳር ወጥተው ወደ ከተማ የሚሔድ መኪና መጠበቅ ጀመሩ። ትንሽ እንደቆዩም አንድ የሕዝብ መኪና አስቆሙና የሚሄዱበትን ተናግረው ገቡ። የመኪናው ረዳትም፣ ሒሳቡ ሁለት ብር ካምሳ እንደሆነ ነገራቸው፡፡ ፍየል በመሐረብ ከቋጠረችው አወጣችና ሁለት ብርና ሃምሳ ሳንቲም ከፈለች። አህያም እንደ ፍየል ሁለት ብርና ሃምሳ ሳንቲም ከፈለ። ውሻ ግን ዝርዝር ብር ስላልያዘ አምስት ብር ድፍን ከፈለና መልሱን እየጠበቀ ሣለ በመሐል አሽለበውና አንቀላፋ።

 ረዳቱ፣ የውሻን መልስ ሁለት ብር እና ሃምሳ ሳንቲም ይዞ መጣና፣ ‹‹ጓደኛሽ ውሻ ሲነቃ ስጨልኝ›› ብሎ ለፍየል ሰጣት። በዚህ ጊዜ ከጥግ የተቀመጠው አህያ በመኪናው መስታዎት በኩል ወሬ እያየ ስለነበር ፍየል የውሻን መልስ ስትቀበል አላያትም። በመጨረሻም ውሻ፣ ፍየልና አህያ ካሰበብት ከተማ ደረሱ ‹‹ወራጅ፣ ወራጅ›› ብለው መኪናዋን አስቆሙ።

መኪናዋ ቆማ ረዳቱ በሩን እንደከፈተም ፍየልና አህያ ቀድመው፣ ውሻ ደግሞ ተከትሎ ወረዱ። ውሻ እንደወረደ መልሱ ትዝ አለውና ረዳቱ እንዲሰጠው ጠየቀው። ከዚያም ረዳቱ፣ ‹‹ሰጥቼሃለሁ ውሻ ደግሞ፣ አልሰጠኸኝም እየተባባሉ መጨቃጨቅ ጀመሩ። በዚህ ጊዜ የውሻን መልስ የተቀበለችው ፍየል ከሥፍራው ጠፍታ ነበር።
አህያ ግን ነገሩ ስላልገባው ከመንገዱ ዳር እንደቆመ ነበር። ውሻና ረዳቱ ትንሽ ከተጨቃጨቁ በኋላ መኪናው ተንቀላቀሰ። ረዳቱም ዘሎ ከመኪናው ገባ። መኪናዋም መንገዷን ቀጠለች። ውሻ ግን፣ ‹‹መልሴን! መልሴን!›› እያለ በመጮህ እስኪደክመው ድረስ መኪናዋን አባሮ ተመለሰ። ከዚያን ጊዜ በኋላ መኪና በመንገድ ባለፈ ቁጥር ውሻው እየተከተለው ይጮሃል። ይህን የሚያደርገውም መልሱን ለመቀበል ሲል ነው።

 ፍየል ግን መኪና በመንገድ ሲያልፍ ባየች ቁጥር ትሸሻለች። ይህን የምታደርገውም አጭብርብራ የተቀበለችውን የሁለት ብር ከሃምሳ ሳንቲም መልስ እንዳይቀበሏት ነው።

አህያ እንደ ውሻ የቀረባት መልስ የለም። እንደ ፍየልም ያጭበረበረችው ገንዘብ የለም። ስለዚህም በመንገድ ዳርም ይሁን በመንገድ መሐል ቆማ ሳለች መኪና ቢመጣባት ምንም ንቅንቅ አትልም። ‹‹ጉዳዬ ነው›› ብላ ትቆማለች። በአጠቃላይም ፍየል ከመኪና የምትሸሸው፣ ውሻ መኪና የሚያባርረው፣ አህያ ደግሞ መኪና የማትፈራው በዚህ ምክንያት ነው ይባላል።

–  አብነት ስሜ ‹‹ሳይኪና ኪዩፒድ››

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...