Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በአዲስ አበባ የተንሰራፋው የመሬት ዘረፋ ይታሰብበት!

በአዲስ አበባ ከተማ፣ ‹‹በኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ከሁለት ሺሕ ሔክታር መሬት በላይ ተዘጋጅቷል›› በሚል ርዕስ የተሰናዳ አንድ ዜና ቀልቤን ስቦት ደጋግሜ አነበብኩት፡፡ ዜናው ዝርዝር ነገሮች ባይኖሩትም፣ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ኢንቨስትመንት መስኮት ላይ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የሚውል ሁለት ሺሕ ሔክታር መሬት ዝግጁ ማድረጉን፣ የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽኑ ማስታወቁን የሚገልጽ ነው፡፡ 

ለባለሀብቶች ተዘጋጀ የተባለው መሬት ስፋት ከአዲስ አበባ ከተማ አላት ተብሎ ከሚታሰበው የቆዳ ስፋት አንፃር ሲመዘን በጣም ሰፊ የሚባል ነው፡፡ ሁለት ሺሕ ሔክታር መሬት በአንድ ጊዜ ለባለሀብቶች ይቀርባል ተብሎ የተገለጸበትን ጊዜ ስለማስታውስ መረጃው ግርታ መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ቢሆንም ኮርፖሬሽኑ የተገለጸውን ያህል መሬት ስለማዘጋጀቱ በይፋ አስታውቋል፡፡

መሬት ‹‹ጥብስ›› በሆነበት ከተማ ይህንን ያህል ለልማት ዝግጁ የሆነ መሬት ተዘጋጅቷል መባሉ በራሱ በመልካም ሊታይ ይችል ይሆናል፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶች እንዳይስፋፉ ትልቅ እንቅፋት ሆኖ ለዘመናት የዘለቀው የመሬት አቅርቦት ካለመኖሩ ጋር የተያያዘ ነውና እንዲህ ያለው ዜና እንደ መልካም አጋጣሚ ቢወሰድ አግባብ ይሆናል፡፡  የመኖሪያ ቤት እጥረት የዜጎች ትልቅ ችግር ሆኖ ለመቀጠሉ፣ አንዱና ዋነኛው ምክንያት ይኼው የማልሚያ ቦታ ዕጦት መሆኑንም ስለምገነዘብ ዕርምጃው በዚህ ረገድ ያለውንም ችግር ሊያቃልል የሚችል በመሆኑ እሰየው ሊባል ይችላል፡፡ ቢያንስ በጋራ የመኖሪያ ቤት ሠርቶ ለመኖር የሚያስችል ተስፋ ሰጪ ነው፡፡

እስካሁን የከተማ አስተዳደሩ ለአልሚዎችም ሆነ ለተለያዩ የግንባታ ሥራዎች ሊውሉ የሚችሉ ቦታዎች ተገቢ በሚባል ዋጋ ማቅረብ ያለመቻሉ ለአገር ጠቃሚ የሚባሉ ኢንቨስትመንቶች በሐሳብ ቀርተዋል፡፡ ስለዚህ መሬት የዚህች አገር፣ በተለይም የመዲናችን ኢኮኖሚያዊ ችግር ሆኖ ባለበት ሰዓት ሁለት ሺሕ ሔክታር ቦታ ብዙ ሊያሠራ ይችላል፡፡ የመሬትን ጉዳይ በሌላው ገጽታ ስንመለከተው ደግሞ ሕገወጦች ሚሊየነር የሆኑበትና ደላሎች ከኋላ ኪሳቸው መዥረጥ አድርገው ይህንን ያህል ካሬ ሜትር አለኝ ብለው እንዳሻቸው የሚቸበችቡት፣ ሕግና ሥርዓትን ይዘው መሥራት ለሚሹ ግን አልቀመስ ብሎ የቆየ ነው፡፡ 

በዚህም ምክንያት ነው መሬት የኢትዮጵያ ዋነኛ የሌብነት መገለጫ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ ከመሬትና ተያያዥ ሥራዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ተቋማት ሹመኞች ኪሳቸውን ያሳበጡበት ነገር ካለ መሬት በዋናነት ተጠቃሽ ነው፡፡ ስለዚህ በአንዴ ‹‹ሁለት ሺሕ ሔክታር መሬት ለባለሀብት ተዘጋጀ›› ሲባል እንዲህ ያሉ ነገሮችን ሁሉ እናስባለን፡፡

በከተማዋ የሚፈጸም የመሬት ወረራና አሁን ደግሞ ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ሳይኖራቸው እየተገነቡ ያሉ፣ እንዲሁም የተጠናቀቁ ግንባታዎችን ካሰብን የመሬት ጉዳይ ቆጥረን የማንጨርሰው ብዙ የሙስና ታሪክ አለው፡፡ ስንቱ ጎጆ የሚቀልስበት አይደለም ተከራይቶ ሊኖርበት የሚችልበት ቤት እያጣ፣ መሬት እያገላበጡ የሚቸበችቡ የዘመኑ ባለጡንቻዎች በነገሡበት በዚህ ወቅት ሁለት ሺሕ ሔክታር መሬት ለአልሚዎች ሊሰጥ ነው መባሉን ስንሰማ፣ ‹‹ስንቱ ሊከብርበት ይሆን?›› ብለን ብንጠይቅ ትክክል ነው። ምክንያቱም በየጊዜው የከተማዋ መሬት ተወረረ፣ ተዘረፈ እየተባለ ወራሪዎቹም ሆኑ አስወራሪዎቹ ምንም ሳይነካቸው እያስተዋልን በመሆኑ፣ ዛሬ ሁለት ሺሕ ሔክታር መሬት ተሰነዳ ሲባል ሥጋት ቢሰማን ወይም የመሬት ደላሎችና መሰሎቻቸው ለዘረፋ የተመቻቸ ሁኔታ ተፈጠረላቸው ብለን ብናስብ ያለፍንበት በመሆኑ እውነት አለን።

ለአርሶ አደር ልጆች፣ ለተፈናቃይ ቤተሰቦችና በመሳሰሉ ምክንያቶች ለሚመለከተውም ለማይመለከተውም ከዚህ ቀደም የታደለውን መሬት ካሰላን ደግሞ ከዚህ ተዘጋጀ ከተባለው መሬት በእነዚህ ጊዜ ወለድ ምክንያቶች ስንቶች ሊከብሩ ይሆን? ነገር ለማሳጠር ያህል የመሬት ጉዳይ ብዙ የሚያነጋግር፣ ብዙ ውንብድና የሚፈጠርበት ነው፣ ፖለቲካም ነው፡፡ ለኢንቨስመንትም ሆነ ለሌሎች ግንባታዎች መሬት እንዴት እንደሚገኝ እንኳን የጠራ መረጃ የሌለበት ወቅት ላይ ነንና ከሰሞኑ ሁለት ሺሕ  ሔክታር መሬት ለባለሀብት ተዘጋጀ ሲባል መደነቅና መጠራጠር ቢኖር በምክንያት ነው ብሎ መቀበል ያስፈልጋል፡፡  

ቀደም ብሎ እንደጠቀስኩት ኮርፖሬሽኑ ይህንን ያህል መሬት በትክክል ለሚያለሙ ባለሀብቶች አቀርባሁ ማለቱ እንደ መረጃ እንደ መልካም ሆኖ፣ እንዴት የሚለውን ጥያቄ የምናነሳው የቀድሞ ስህተቶች እንዳይደገሙ በማሰብ ጭምር ነው፡፡  

መረጃው መሬት እንዴት ለባለሀብቶች እንደሚተላለፍና በምን ዓይነት መሥፈርት ባለሀብቶች እንደሚስተናገዱ አይገልጽም፡፡ ኮርፖሬሽኑ መሬቱን በሊዝ አጫርቶ ይሽጥ፣ አይሽጥ የተገለጸ ነገር የለም፡፡ መረጃው ድፍንፍን ብሎ የተቀመጠ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እንደተባለው በትክክል ሊያለሙ ለሚችሉ ባለሀብቶች የሚሰጥ ከሆነ አሰጣጡ በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡ 

በመሬት አሰጣጡ ዙሪያ እስከ ዛሬ የሰማናቸው እጅግ የበዙ ውንብድናዎች እንዳይደገሙ ከተፈለገ፣ በተዘጋጀው መሬት በአግባቡ ለሚመለከተው የሚተላለፍ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ያስፈልጋል፡፡ አሠራሩ ግን ግልጽ ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ባለሀብቶቹ የተረከቡትን ቦታ በአግባቡ መገንባት አለመገንባታቸውን ማረጋገጥ ተገቢ ይሆናል፡፡ አንድ ባለሀብት ቦታውን በምን ያህል ዋጋ ተረከበ፣ ወይም በምን ያህል የጨረታ መነሻ ዋጋ ተወዳድሮ ገዛ የሚለው የሚመልስ አዲስ አሠራር ያሻናል፡፡

ለልማት ተብሎ የተወሰደ መሬት አጥሮ አየር በአየር የሚቸበችበውንና ትክክለኛውን አልሚ መለየትም የኮርፖሬሽኑ ሥራ መሆን ይገባዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የመሬት ጉዳይ እስከዛሬ ሲሠራበት በነበረው አሠራር እንዲቀጥል የሚፈቅድ ከሆነ ግን ለደላሎችና ለብልሹ ሹማምንት ሠርግና ምላሽ ሆነ ማለት ነው፡፡ 

ስለዚህ እውነት እንደተባለው ይህ መሬት ለባለሀብቶች የሚተላለፍ ከሆነ፣ በመጀመርያ ኮርፖሬሽኑ በቂ መረጃ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ መረጃው በሕዝብ ማስታወቂያ ጭምር የተደገፈ መሆን አለበት፡፡

በነገራችን ላይ እስከዛሬ በሊዝ የተላለፉ መሬቶች በትክክል ወቅቱን ጠብቆ የሊዝ ዋጋቸው እየተከፈለ መሆን አለመሆኑን መፈተሽ ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ፍተሻ የሚገኘው መረጃ ሁለት ሺሕ ሔክታር መሬት እንዴት መተላለፍ እንደሚኖርበት ትምህርት ሊሰጥ ይችላል፡፡ ይህንን ማድረግ መሬትን በአግባቡ የመጠቀም ልምድንና ሕገወጥነትን ለመከላከል ያግዛል፡፡ ከመሬት ወረራና ዝርፊያ ጋር ተያይዘው ያሉ ችግሮችን እንዳይቀጥሉም ይረዳልና መሬት ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን ከሌብነት ተጠብቆ ለትክክለኛ አልሚው ለማስተላለፍ ጥብቅ ሕጋዊ አሠራር ሊኖረን ይገባል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት