ከአሠልጣኝ ተመስገን ዳና ጋር በውሉ መሠረት መለያየታቸውን ገልጿል
የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ክለቡ አስተባበለ፡፡
በሳምንቱ መጨረሻ የክለቡ ሥራ አመራር ቦርድ በክለቡ ወቅታዊ ጉዳይ ለመምከር ስብሰባ መቀመጡ የተነገረ ሲሆን፣ ሥራ አስኪያጁ አቶ ገዛኸን ወልዴ የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸው ሲነገር ቢቆይም፣ የክለቡ ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ መረጃው ‹‹ሐሰት›› መሆኑን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
የክለቡ ሥራ አመራር ቦርድ ሥልጣን መጠናቀቁን ተከትሎ የተለያዩ አመራሮች የመልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸው ቢነገርም፣ መረጃው ሐሰት መሆኑንና ክለቡ አዲስ ነገር ሲኖር በይፋ እንደሚያሳወቅ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በተያያዘ ምንም አዲስ የተፈጠረ ነገር እንደሌለ ፕሬዚዳንቱ ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ መልቀቂያ ማስገባታቸው፣ ነገር ግን ትንሽ ቆዩ መባላቸው ቢገለጽም፣ መረጃው ሐሰት መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡
የክለቡ ሥራ አመራር ዘመን ከአራት ዓመት መሻገሩና በጊዜው ጠቅላላ ጉባዔ ተጠርቶ፣ የሥልጣን ዘመናቸው ባለፉ አመራሮች ምርጫ ማድረግ የሚሉ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር ከተመረጠ ስድስት ወር እንዳለፈው የተነገረለት የክለቡ አዲሱ የደጋፊ ማኅበር አመራሮች ደጋፊውን በአስፈላጊው መንገድ ሊያንቀሳቅሱ አለመቻላቸው ተጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ከመጀመሩ አስቀድሞ ክለቡን የያዙት አሠልጣኝ ተመስገን ዳናን ማሰናበቱ ይታወሳል፡፡
ከሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ለሁለት ዓመት የሚቆይ ውል ከአሠልጣኝ ተመስገን ጋር ውል ያሰረው ኢትዮጵያ ቡና፣ ኅዳር 30 ቀን በይፋ መለያየቱ ተሰምቷል፡፡ አሠልጣኝ ተመስገን ክለቡን ውጤታማ ለማድረግ በዝውውር መስኮቱ አዳዲስ ተጫዋቾች ማስፈረም ቢችሉም ያስመዘገቡት ውጤት ግን በተቃራኒው ለስንብቱ ምክንያት መሆኑ ይነገራል፡፡
አሠልጣኙ እስኪሰናበቱ ድረስ ክለቡ ካደረጋቸው አሥር ጨዋታዎች ውስጥ በአራቱ አሸንፎ፣ በአራቱ ተሸንፎ በሁለቱ አቻ በመውጣት በሊጉ 14 ነጥብ ብቻ በመያዝ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ መቀመጡ ይታወሳል፡፡ በዚህም መሠረት ክለቡ አሠልጣኙን ቢያሰናብትም፣ በአንፃሩ አሠልጣኙ ክለቡ ያቀረበውን የስምምነት ይዘት ላይ ጥያቄ በማንሳት የስንብት ደብዳቤውን እንዳልተቀሉት ገልጸዋል፡፡
እንደ አሠልጣኙ አስተያየት ከሆነ፣ በውሉ መቋረጥ ቅር እንዳልተሰኙ፣ ነገር ግን በውሉ መሠረት የነበረው ክፍያና ጥቅማ ጥቅም እንዳልተጠበቀላቸው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስዱት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ከስምምነቱ ጋር በተያያዘ ለሪፖርተር አስተያየታቸው የሰጡት የክለቡ ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ፈቃደ፣ ‹‹በውላችን መሠረት ከአሠልጣኙ ጋር ተለያይተናል፡፡ አሠልጣኙም ጉዳዩን ፍርድ ቤት ይወስደዋል ብዬ አላስብም፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
ስንበት የተባለው ውሳኔ እንደ ክለብ በደብዳቤ ወይም ይፋዊ በሆኑ መልኩ እንዳልሆነ የሚጠቅሱት አሠልጣኝ ተመስገን፣ ስምምነቱ ጥቅማ ጥቅሜን ያስጠበቀ ባለመሆኑ፣ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰዳቸውንና ክትትል እያደረጉ እንደሚገኙ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡
ጉዳዩ በፍርድ ቤት መያዙን ተከትሎ ተጨማሪ አስተያየት ለሚዲያ ከመስጠት የተቆጠቡት አሠልጣኝ ተመስገን፣ የክሱን ሒደቱ በጠበቃው በኩል እየተከታተሉ መሆኑ ገልጸዋል፡፡