በኅዳር ወር መግቢያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ይፋ አድርገው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜም ሙስና የአገርን አንጡራ ሀብት በልቶ ባዶ የሚያስቀር ነው ብለው ነበር፡፡ ‹‹በፍቅረ ነዋይ የታወሩ ደላሎችና ባለሀብቶች ከዋልጌ ባለሥልጣናት ጋር ሲገጥሙ፣ እንዲሁም ከእነዚህ የሌብነት ፊታውራሪዎች ጀርባ ብዙ ዜጎች ሲሠለፉ ሙስና የተባለው ነቀዝ አገርን እንደ ወረርሽኝ ያጠቃታል፤›› በማለትም ተናግረው ነበር፡፡
በአንድ ወር ልዩነት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) አስደንጋጭ ንግግር ሲናገሩ ተሰማ፡፡ ታኅሳስ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. የወላይታ ሶዶ የዳቦ ፋብሪካ ለማስመረቅ የተገኙት ዓብይ (ዶ/ር) እጅግ ከፍተኛ መነጋገሪያን የፈጠረ ጉዳይ ነበር ስለሙስና ያነሱት፡፡ ‹‹ትናንትና ተሳስታችሁ፣ በስህተት ሰርቃችሁ ሀብት ያከማቻችሁ ሰዎች ካላችሁ መፍትሔው ቀላል ነው፡፡ ብዙ ዳቦ ፋብሪካ ስለምንፈልግ፣ ብዙ ትምህርት ቤት ስለምንፈልግ፣ ፋብሪካዎቹን ከሠራችሁ ሰላም ይመጣል፤›› በማለት መናገራቸው በብዙዎች ዘንድ ግርምት የፈጠረ ነበር፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት፣ ‹‹ስረቁ ግን ስትሰርቁ እንዳትያዙ፤›› ብለው መናገራቸውን በማስታወስ፣ በርካቶች የዓብይ (ዶ/ር) ንግግርንም ሌብነትን ከማበረታታት ጋር አገናኝተውታል፡፡ ዝርዝር ዘገባውን በዚህ ሊንክ ያገኙታል ፡፡