የፌደራል ፍርድ ቤቶች የፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬት አሠራሮችና የሥራ ክፍተቶችን ያሻሽላል ተብሎ የሚታሰብ መመርያ፣ በዳይሬክቶሬቱ ተረቆ የባለድርሻ አካላት ውይይት እየተካደዱበት ነው፡፡
ረቂቅ መመርያው የፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬቱ ያለበትን ‹‹በጥናት የተረጋገገጠ የሥራ ክፍተት›› ይሸፍናል በሚል ዕሳቤና፣ የሥራ ክፍሉ ከአንድ በላይ ለሆኑ ፍርድ ቤቶች በማገልገሉ ሊያስነሳ የሚችለውን ‹‹የተጠሪነትን ውስብስብነት›› ሊያግዝ እንደሚችል ተጠቅሷል፡፡
ዳይሬክቶሬቱ ከጀስቲስ ፎር ኦል ፒኤፍ ኢትዮጵያ (Justice for All – PF Ethiopia) ጋር በመተባበር እየተዘጋጀ ያለው ይህ መመርያ፣ ለዳኞች፣ የተለያዩ የፍርድ ቤቶች አመራሮችና ፍርድ አስፈጻሚ ባለሙያዎች ጋ ቀርቦ በውይይት ላይ ያለ ሲሆን፣ ለማዘጋጀት እንደ ዋነኛ ምክንያት የተጠቀሰውም ከአሥር ዓመታት በፊት ወጥቶ የነበረውን መመርያ የተሻለ አሠራር በሚያሠራ ለመቀየር የታሰበ መሆኑን ረቂቅ መመርያው ይገልጻል፡፡
የአፈጻጸሙ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የተሰጣቸውን ሥልጣንና ተጠያቂነት በ2005 ዓ.ም. የወጣው መመርያ እንደሚያመለክትም ተገልጿል፡፡ ስለ መመርያው ለውይይት የቀረበው ሰነድ እንደሚገልጸው፣ የዳይሬክቶሬቱ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተግባርና ሥልጣን ‹‹በግልጽ የሚያመላክት ደንብና መመርያ ባለመኖሩ›› ከእዚህ በፊትም የነበረው መመርያ እነዚህን ክፍተቶች ባለሟሟላቱ መቀየር እንዳስፈለገ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የዳይሬክቶሬቱ ሠራተኞች ገልጸዋል፡፡
ሠራተኞቹ አክለው ሲያስረዱም፣ አሁን ያለው መመርያ በአብላጫ በሥራ ክፍሉ ውስጥ በተግባር የሚሠሩትን ሥራዎች ግንዛቤ ውስጥ ሊየስገባ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ሠራተኞቹ ለአፈጻጸሙ ሥራዎች መመርያው አንደኛው ማነቆ ነበር ሲሉም የገለጹ ሲሆን፣ እንደ አዲስ የተዘጋጀውን ሰነድም በመመርያ ወይም በማኑዋል ስም ለማውጣት በሚለው ላይ ገና ከውሳኔ አለመደረሱን ተናግረዋል፡፡
በፍርድ አፈጻጸም ዳይሬክቶሬቱ የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት በሚል አሥራ አንድ ተግባራትን የደረደረው አዲሱ ረቂቅ መመርያ እንደሚያሳየው፣ ከሐራጅ ሽያጭ ጋር የተያያዙ ክንውኖችን፣ ግራና ቀኝን ማደራደርን፣ ግብር ማጣራትና መሰል ተግባራትን በንብረቶች ላይ ማካሄድ፣ የክፍያ ሰነድ ማዘጋጀትና እንደ አገልግሎት ዓይነት ክፍያዎችን መሰብሰብ፣ የፍርድ አፈጻጸም መዝገቦችን ማደራጀት፣ እንዲሁም መሰል ተግባራን ማከናወን ይገኙበታል፡፡
ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቱና ምክረ ሐሳብ መቀበሉ እንደተጠናቀቀ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቢሮ ፀድቆ ተፈጻሚ እንደሚሆን በመመርያው ተጠቅሷል፡፡
በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕግ ጥናት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አሮን ደጎል ለሪፖርተር ሲገልጹ፣ እሳቸው በፍርድ አፈጻጸም ላይ የተለየ አቋም እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ አሮን ሐሳብ የፍርድ አፈጻጸምና የተከላካይ ጠበቆች ቢሮ አደረጃጀት በዳይሬክቶሬትም ሆነ በጽሕፈት ቤት ሳይሆን በአዋጅ እንደ አዲስ ተቋቁመው ሙሉ በሙሉ ከፍርድ ቤት ሥር ተጠሪ መሆን እንዳለባቸው ነው፡፡ ከዚያም ራሱን እንደቻለ ተቋም ሆነው ለጠቅላይ ፍርድ ቤት መጠራት እንደሚችሉም አክለው ገልጸዋል፡፡
‹‹አሁን ባለው ሁኔታ እየጠጋገኑ ማስኬድ ጩኸቱን አያበርደውም›› ሲሉም አክለው ተናግረዋል፡፡